Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow ፖስታ ድርጅት ከ140ሺ ብር...
ፖስታ ድርጅት ከ140ሺ ብር... Print E-mail
Wednesday, 23 April 2008
ፖስታ ድርጅት ከ140ሺ ብር በላይ በሠራተኛው ተዘረፈ

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የገንዘብ ክፍያ ሰራተኛ የሆኑ ግለሰብ፤ ከ140ሺ ብር በላይ ዘርፈው ተሰወሩ፡፡ ግለሰቡ በፖሊስ እየተፈለጉ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ውስጥ የገንዘብ ከፋይ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ገዛኸኝ በተጭበረበረ ሰነድ ወጪ ያደረጉትን 144ሺህ 460 ብር ይዘው መሰወራቸውን ምንጮቻችን አስታውቀዋል፡፡ ግለሰቡ በድርጅቱ ውስጥ በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ ከአራት አመት በላይ በቋሚ የሥራ መደብ ላይ መሥራታቸውን፣ ከታህሳስ 2000 ዓ.ም ጀምሮ በገንዘብ ከፋይነት ከተመደቡ በኋላ አስራ ስድስት የተጭበረበሩ ሰነዶችን በማዘጋጀት ዝርፊያውን ፈጽመዋል ተብሏል፡፡ ከጋምቤላ ፖስታ አገልግሎት የተላኩ የሀዋላ ገንዘብ ክፍያ በማስመሰል ስርቆቱን መፈፀማቸው ታውቋል፡፡

የድርጅቱ የፋይናንሺያል ቢዝነስ የሥራ ሂደት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢያዝንልኝ አስረስ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "አቶ ቴዎድሮስ የሀዋላ ገንዘብ ተቀባይም ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ምዝበራውን ፈጽመው ተሰውረዋል" ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

በአቶ ቢያዝንልኝ ገለፃ መሰረት ግለሰቡ ከታህሳስ ወር ጀምሮ በገንዘብ ከፋይነት እየሰሩ መቆየታቸውንና በዚህም ገንዘብ የመክፈልና የመቀበል ኃላፊነት የነበራቸው ሲሆን ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው የተጭበረበረ ሰነድ በማዘጋጀት ገንዘቡን ወጪ አደርገዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ በየቀኑ 50ሺህ ብር ወጪ አድርገው ሀዋላ ተልኮላቸዋል ላሉዋቸው ሰዎች ክፍያ ይፈጽሙ ነበር፡፡

"የገንዘቡን ማውጫ ሰነድ ቁጥሩን እየቀያየሩ፤ ወጪ የተደረገበትን ሰነድ ፎቶ ኮፒ እያደረጉ፤ ራሳቸው እየፈረሙ ወጪ ሲያደርጉ ቆይተዋል" ብለዋል አቶ ቢያዝንልኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ ገንዘብ ሲመዘብሩ የቆዩት አቶ ቴዎድሮስ የ15 ቀናት የእረፍት ጊዜ ተሰጥቷቸው ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡ ግለሰቡ መጥፋታቸውን ያወቀው ድርጅቱ፤ በድርጅቱ በኦዲተር አማካይነት የግለሰቡን የሂሳብ ሰነድ ለመዝጋት ባደረገው ሙከራ በተጭበረበረ ሰነድ ገንዘብ ወጪ መደረጉ ታውቋል፡፡

በዚህም ምክንያት ድርጅቱ ያለፈው ሰኞ ለፖሊስ በማመልከት ፖሊስ በግለሰቡ ላይ ክትትል ማድረግ መጀመሩ ከአቶ ቢያዝንልኝ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

 "ድርጅቱ ከሦስት ወራት በላይ ጊዜ የግለሰቡን ሰነድ ሳይመረምር ለምን ቆየ?" በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ አቶ ቢያዝንልኝ፤ ከ19 የክልል ፖስታ ቤቶች እንዲሁም ከ400 በላይ ቋሚ በፖስታ ቤት የሚላኩ የገንዘብ ተቀባይ ሰነዶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለምርመራ ጊዜ የሚፈጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከጋምቤላ ፖስታ ቤት የሚመጡ ሰነዶች በተለይ ከሦስት ወራት በላይ የሚቆዩበት ሁኔታ መኖሩን አብራርተዋል፡፡ በዚህም ግለሰቡ ለስርቆቱ ከጋምቤላ ፖስታ ቤት የተላኩ ሰነዶችን መጠቀማቸውን አቶ ቢያዝንልኝ አብራርተዋል፡፡

አንዳንድ የድርጅቱ ሠራተኞች  የአሰራር ስርዓት (ቢፒአር) ማሻሻያ መሰረት አንድ ሰው ገንዘብ ከፋይና ገንዘብ ተቀባይ እንዲሆን መደረጉ ለምዝበራ ክፍተት መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡   

በተሾመ ንቁ
 
< Prev   Next >