| ልጆች በአርጩሜ (በዱላ) አትምቱ ማለት... |
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
ልጆች በአርጩሜ (በዱላ) አትምቱ ማለት እንደፈለጉ ይሁኑ ማለት አይደለም ወይዘሮ የሺሀረግ ዳምጤ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕፃናት፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ኮሚሽነር ናቸው፡፡ የሕፃናት ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ አነጋግረናቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በአገራችን በሕፃናት መብት አጠባበቅ ዙሪያ የሚታዩት ችግሮች ምንድ ናቸው? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- በሕፃናት መብት አጠባበቅ ዙሪያ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የጉልበት ብዝበዛ፣ ሕፃናትን በሕገወጥ መንገድ ማዘዋወር (ቻይልድ ትራፊኪንግ..፣ በሕፃናት ላይ የሚፈፀም አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ ወላጅ አልባና በከፍተኛ ችግር የሚኖሩ ሕፃናት መብዛት፣ በእስር ቤት ከእናቶቻቸው ጋር የሚገኙ ሕፃናት ቁጥር እየተበራከቱ መሄድ፣ የመብቶች ግንዛቤ በኅብረተሰቡ፣ በወላጆችና በራሳቸው በሕፃናቱ አለመጎልበት ወዘተ. ናቸው፡፡ የማኅበረሰቡ የወደፊት ተስፋዎች የሆኑት ሕፃናት በዕድሜያቸው ለጋነት ምክንያት አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ ስለሌላቸው ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የተካተቱ የበርካታ መብቶች ባለቤት ቢሆኑም ሰብዓዊ መብታቸው በስፋት ከማይከበርላቸው የኅብረተሰብ ክችሎች ውስጥ ሕፃናት በሁለተኛ ደረጃ የሚፈረጁ ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- ጥናቶቹ በምን መልኩ ነው የተከናወኑት? የቱን ያህልስ ተግባራዊ ሆነዋል? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- ጥናቶቹ የተከናወኑትና ውጤቶቻቸውም ተግባራዊ በመሆን ላይ ያሉት ሁሉንም ክልሎች ባከተቱና በናሙና በተመረጡ የትግራይና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ በቅርቡም በአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ከጥናቶቹም በመነሳት ሕፃናቱ በትምህርት ቤት የሰብዓዊ መብት አጠባበቅን እንዲማሩ፣ ጽንሰ ሃሳቡን ይዘው እንዲያድጉ፣ እንዲያውቁ፣ የባህሪና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ነው ተቀርፆ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ያለው፡፡ የፕሮግራሙም ስም ..ትምህርት ቤቶችን ሰብዓዊ መብት የሚከበርባቸውና የሚስፋፋባቸው ማዕከላት ማድረግ.. የሚል ነው፡፡ ይህም በትምህርት ቤቶች ሰብዓዊ መብትን ተግባራዊ በማድረጉና በማስፋፋቱ ላይ ሕፃናት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ያስችላቸዋል፡፡ በሕፃናትና በመምህራን መካከል በሚኖሩት ግንኙነቶች መቻቻልን፣ ግጭቶችን በሰላም የመፍታትና አብሮ የመኖር ጽንሰ ሃሳቦችን በማጎልበት ረገድም ሕፃናት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ በተግባርም ያሳያሉ፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት የአመለካከት ለውጥ ማምጣት የግድ ይላል፡፡ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትም ዕውቀት ተገኝቶ በተግባር መታየት አለበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲመቻቹና ሲዋሃዱ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚታዩ የመብት ጥሰቶችን ሕፃናት ራሳቸው እንዲከላከሉ፣ እንዲከራከሩና እንዲጠይቁ ያስችላቸዋል፡፡ የኮሚሽኑ ራዕይ ኅብረተሰቡ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጠብቅና የሚያከብር እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የማይሸከም እንዲሆን የማድረግ ነው፡፡ ይህም ተግባራዊ የሚሆነው ሕፃናትን መለወጥ ሲቻል ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ሕፃናትን እንዴት መለወጥ ይቻላል? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- ሕፃናት የሚመላለሱት ከወላጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ከዚያም ወደ ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት የቀሰሙትን ጽንሰ ሃሳብ ወደ ኅብረተሰቡና ወደ ወላጆች የማስተላለፍ አጋጣሚ በጣም የሰፋ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በሕፃናቱ አእምሮ ላይ የሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሃሳብ እንዲሰርጽ በማድረግ መለወጥ ያስችላል፡፡ በትምህርት ቤቶች ሰብዓዊ መብት እንዲስፋፋና እንዲከበር ማድረግ የሚቻለው በሁለት መንገዶች ነው፡፡ አንደኛው በመደበኛው ሥርዓተ ትምህርት ጽንሰ ሃሳቦቹ በሚገባ ተካትተው ህፃናቱ በክፍል ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንዲማሩና ሁለተኛው ደግሞ ከክፍል ውጭ በሚከናወኑ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች አማካይነት እንዲከታተሉ በማድረግ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙ በመካሄድ ላይ ያለው በየትኞቹ ትምህርት ቤቶች ነው? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- ፕሮግራሙ እየተካሄደ ያለው በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በተመረጡ 20 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የተመረጡት ሃሳቡን ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች የማስፋፋት አቅም ያላቸው ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ የተመረጡ ትምህርት ቤቶች ወደፊት እንደ ማዕከል ይሆኑንና ለሌሎች ልምድ መቅሰሚያ ይሆናሉ፡፡ ትምህርት ቤቶችም ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ከሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሃሳብ ጋር የተጣጣመ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሥልጠናውም ከየትምህርት ቤቱ የተውጣጡ ሕፃናት፣ መምህራንና ርዕሳነ መምህራን፣ ወላጆችና ተወካዮቻቸው ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ አንድ ሕፃን ሲያድግ የሰብዓዊ መብትንም እያወቀ ማደግ ይኖርበታል፡፡ ሰው፣ ሰው በመሆኑ ብቻ ምን አይነት መብት አለው የሚለውንም መረዳት ይገባዋል፡፡ አንድ ሰው መብቱን ሲጠቀም የሌላውንም መብት የማክበር ግዴታ አለበት የሚለውንም ጽንሰ ሃሳብ በውስጡ ሊሰርጽ ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- በየትምህርት ቤቶች በሕፃናት ላይ የሚፈፀም አካላዊና ስነ ልቦናዊ ቅጣት እንዲቆም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በየጊዜው መመሪያ ቢያወጣም ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- አካላዊና ስነ ልቦናዊ ቅጣትን ለማስቆም መመሪያ ማውረዱ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን መመሪያ በማውረድ ብቻ የሚፈፀም ነገር የለም፡፡ መብቶች በጣም እንዲከበሩና እንዲጠበቁ ማድረግ የሚቻለው የሰውን አመለካከት በመቀየር ነው፡፡ በአመለካከት ለውጥ ላይ ባለመሰራቱ የተነሳ ወደ ኮሚሽኑ የሚቀርቡ በርካታ ማመልከቻዎች አሉ፡፡ በድብደባ የሞቱ ሕፃናት እንዳሉም በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ሕፃናትን አትምቱ፣ አትቆጡ፣ እንደፈለጉ ይሁኑ በመባላቸው ልቅ እየሆኑ መጥተዋል የሚል ሮሮ ይሰማል? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- ልጆችን በአርጩሜ (በበትር) አትምቱ ማለት እንደፈለጉ ይሁኑ ማለት አይደለም፡፡ በአርጩሜ ሳይመቱ የትምህርት ቤቱን ዲሲፕሊን የሚያከብሩበት የተለያዩ ሥነስርዓቶች ሊቀረጹ (ሊኖሩ) ይገባል፡፡ በአርጩሜ አይመቱ፣ ሞራላቸውንና አእምሯቸውን የሚነካ ነገር አይደረግባቸው ማለት ልጆቹን አትከታተሏቸው አትምቷቸው፣ አትቅረጿቸው ማለት አይደለም፡፡ ካልተደበደቡ ደግሞ እንደተፈለገው አይሆኑም የሚለው አስተሳሰብ አይሰራም፡፡ ልጆች ሕፃናት ናቸው፡፡ ስለሆነም የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ትክክል ይመስላቸዋል፡፡ በዚህም ወላጆች ቀናውን መንገድ ሊመሯቸው ይገባል፡፡ ይህም የሚሆነው በዱላ፣ በስድብና ሞራልን በሚነካ ተግባር መሆን የለበትም፡፡ ሪፖርተር፡- በሁለቱም ክልሎች በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ሰብዓዊ መብትን የማስፋፋትና ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ? በኃላፊነት ተረክቦ የሚያከናውነው ማን ነው? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- ኃላፊነቱን ተረክበው የሚያከናውኑት የየክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶቹም ሰፊ ድርሻ አላቸው፡፡ ፕሮግራሙ ሲቀረጽ መጀመሪያ ታስቦ የነበረው ኮሚሽኑ የተወሰነ ትምህርት ቤቶችን መርጦ ፕሮግራሙን ተግባራዊ እንዲያደርግና ክትትሉንም ራሱ እንዲያከናውን ለማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሮግራሙ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ አካል ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ይህም በትምህርት ፖሊሲውም ላይ ተቀርጿል፡፡ አገሪቷ ተቀብላ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይም ተካትቷል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ሰብዓዊ መብቶች የሚስፋፉባቸውና የሚከበርባቸው ማዕከላት የማድረግና የመከታተል ሥራ የትምህርት ቢሮ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ኮሚሽኑ ግን አጋር ሆኖ ያሉትን ክፍተቶች በጥናት እንዲታዩ ያደርጋል፡፡ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎችን ያቀርባል፡፡ የቴክኒክ ድጋፍም ይሰጣል፡፡ ሪፖርተር፡- በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ከተማ ያለውን የሕፃናት ፓርላማ አቅም ለማሳደግ ኮሚሽኑ ምን አደረገ? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- የኮንሶ ሕፃናት ፓርላማን ሁኔታ የሚከታተለው የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ነው፡፡ ፓርላማው ሊቋቋም የቻለው ከፊንላንድ ሕፃናት አድን ጋር በመቀናጀት ነው፡፡ በሌላም ክልል ይህ አይነቱ ፓርላማ የተጀመረ ይመስለኛል፡፡ ይህም አካሄድ ሕፃናት ተሰሚነታቸውንና ተሳትፏቸውን ለማበርከት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ጋር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ፓርላማ ሲባል ውክልና መኖር እንዳለበት ነው፡፡ ለሕፃናቱ የፓርላማን ሞዴል ነው እንዲያዩት እየተደረገ ያለው፡፡ ሕፃናትን በፓርላማም ሆነ በፎረም የማሳተፍ ተግባር እንደተጠበቀ ሆኖ ከክፍል ትምህርት ውጪም የሰብዓዊ መብት ትምህርት እንዲጎለብትና እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ በትምህርት ቤቶች የሰብዓዊ መብቶችን የሚያስፋፋና የሚያጎለብት፣ እንዲሁም ጥሰቶችን የሚከላከል ፎረም ወይም ፓርላማ ሲመሰረት ከየክፍሉ ተወካዮች መኖር አለባቸው፡፡ አንድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 20 ክፍሎች ቢኖሩት ከእያንዳንዱ ክፍል ቢያንስ ሁለት ተወካዮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ይህም አካሄድ ልጆቹ እኩል ውክልና እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ እነዚህም ተወካዮች መምህራን በማይኖሩበት ጊዜ ወይም መምህሩ እስከሚመጣ ድረስ የሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሃሳቦችን አንስተው አብረዋቸው ከሚማሩ የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር ሊወያዩበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ..ማንኛውም ሰው የሕይወትና የአካል ደህንነት ሊኖረው ይገባል.. በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ላይ ብቻ ሕፃናቱ ቢወያዩ እንኳን ትልቅ ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎ ሕፃናት በተለያየ ምክንያት እርስ በርሳቸው ይጣላሉ ወይም ወንዶች ሕፃናት ሴት ሕፃናትን አናስኬድም፤ አናሳልፍም በማለት ሊተናኮሏቸው ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከቀሰሙት ጽንሰ ሃሳብ በመነሳት የሚያከናውኑት ተግባር ሁሉ እኩይ መሆኑን በመረዳት ከድርጊታቸው ወዲያውኑ ይቆጠባሉ፡፡ ራሳቸውንንም እንዲፈትሹና እንዲጠይቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ከሰብዓዊ መብት ሰነዶች አንዳንድ ጽንሰ ሃሳብ እየተመዘዘ ጠዋት ጠዋት ሁልጊዜ ሰልፍ ላይ ለሕፃናቱ ቢነገራቸው የማይናቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፡፡ አንድ ሕፃን ተነስቶ ሌላውን ለመተናኮል ቢሞክር እንኳን ሙከራ የተቃጣበት ሕፃን ..ማንም ሰው በሠላም የመኖር መብት አለው.. የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በመናገር ሙከራውን ሊያስቆም ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- የግል መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ እያደረጉ ነው፡፡ ከሕፃናት የመማር መብት አኳያ ይህ ትክክል ነው? ወ/ሮ የሺሀረግ፡- የመንግስት መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የግል መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በእንግሊዝኛ/በፈረንሳይኛ ያስተምራሉ፡፡ ይህም ከሕፃናት መብት አኳያ ሲታይ አንድ ሕፃን እውቀትን ማግኘት እንዳለበት ያመለከታል፡፡ በትምህርት ቤት የሚሰጡ ትምህርቶችም የሕፃናቱን ስብዕናንና ተሰጥኦ እንዲሁም የአእምሮና የአካል ችሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ ለማዳበር የሚያስችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ መሠረቱ ቋንቋው ሳይሆን ምን ያህል ዕውቀት አግኝቷል የሚለው ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው እንግሊዝኛ/ፈረንሳይኛ ከተናገሩ ሁሉንም ዕውቀት ያወቁና በሁሉም ነገር ውጤታማ የሆኑ ይመስላቸዋል፡፡ በተሟላ ስብዕና ያደጉና የተሻሉ ሆኑ ያገኟቸው አድርገው ነው የሚወስዱት፡፡ ሕፃናት የቤት ቋንቋቸው ሌላ ነው፡፡ የሚማሩበት ቋንቋ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ በመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤታቸው ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢናገሩ ተቀባይነትን አያገኙም፡፡ መግለጽ የሚገባቸውን ነገር አይገልፁም፡፡ አንድ ሕፃን የበለጠ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው መግለጽና ማወቅ የሚገባውን በትክክል ገልፆና ጠይቆ መረዳት ሲችል ነው፡፡ በቋንቋ መገናኘት በማይቻልበት ጊዜ ያስቸግራል፡፡ የፈጠራ ችሎታንም አፍኖ ያስቀራል፡፡ ወ/ሮ የሺሀረግ፡- ብዙዎቹ የግል መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤቶች የእንግሊዝኛ ችሎታ እንደ አንድ መስፈርት አድርገው እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ሕፃናቱ እንግሊዝኛን አውቀው ካላደጉ ውጤታማ አይሆኑም የሚለው ስጋት በሁሉም ወላጆች ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከመዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድረስ ትምህርቱ የሚሰጠው በራሳቸው ቋንቋ ሲሆን በአገራችን ግን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የእንግሊዝኛ ቋንቋው ትክክል ነው ወይ የሚለውም መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለዚሁ ሁሉ መፍትሄ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ተወስዶ መማር፣ የቀሩትን የትምህርት ዓይነቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መስጠት ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |