| በቴዲ የዋስትና ጉዳይ ዛሬ ፍ/ቤት ውሳኔ ይሰጣል |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
![]() ቴዎድሮስ ካሳሁን ሚያዚያ 13 ቀን 2000 ዓ.ም፡፡ ልደታ ከፍተኛ ደረጃ 8ኛ ወንጀል ችሎት ከወትሮው በተለየ መልኩ በሰዎች ተጨናንቋል፡፡ በዕለቱ በትራፊክ አደጋ በቸልተኝነት የሰው ህይወት አጥፍተሀል በሚል ክስ የተመሰረተበት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ ጉዳይ ፍርድ ቤቱ የሚያይበት ዕለት ነበር፡፡ ቤት የጥበቃ ሰራተኞች እየተፈተሸ ይገባ የነበረው ባለጉዳይ በዚህ ዕለት ግን በሦስት ረድፍ ተሰልፎ በፌዴራል ፖሊሶችም ጭምር እየተፈተሸ ገባ፡፡ የፍርድ ቤቱ ግቢ ባልተለመደ ሁኔታ ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ አድናቂዎች እንዲሁም በጋዜጠኞችና በፌዴራል አባላት ተሞላ፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች ሁልጊዜ ይደረግ እንደነበረው ቀደም ብለው ለመግባት ወደ ችሎቱ በራፍ (8ኛ ወንጀል ችሎት) ሲጠጉ ባልተለመደ መልኩ በፍርድ ቤቱ ግቢ በተመደቡ የፌዴራል ፖሊሶች እንዳይገቡ ተከልክለዋል፡፡ በዕለቱ ከጧቱ ሁለት ተኩል ሆኖ ወደ ፍርድ ቤቱ ባለጉዳይ ከመግባቱ በፊት ቀድሞ የደረሰው አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን /ቴዲ አፍሮ/ ከመጣበት የእስረኛ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ወርዶ ወደ ችሎቱ (8ኛ ወንጀል ችሎት) ሲያመራ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል የመጣው በሺዎች የሚቆጠር ደጋፊ በፉጨት፣ በጭብጨባ “ቴዲ፣ ቴዲ” በማለት የማበረታቻ ድጋፋቸውን አሰምተዋል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን በፍርድ ቤት ቅጥር ጊቢ ለተገኙና ድጋፋቸውን ለሰጡ አደናቂዎቹ እጁን በማውለብለብና ከአንገቱ ዝቅ በማለት አፀፋውን መልሶ ወደ ችሎቱ በመግባት ተከሳሾች በሚቀመጡበት ሳጥን ውስጥ ለብቻው ተቀመጠ፡፡ ተከሳሹ ሲገባ ተከታትለው የገቡት አንዳንድ ጋዜጠኞች በችሎት ተከታታዮች መቀመጫ ስፍራ ቢይዙም፣ ከማረሚያ ቤት የመጡ የፖሊሶች ሃላፊ “ጋዜጠኛ ገብቶ ከሆነ ባስቸኳይ ይውጣ፣ አንድ ጋዜጠኛ ገብቶ ቢገኝ".” በማለት መታወቂያ በመጠየቃቸው ጋዜጠኞቹ ፈርተው ችሎቱን ለቅቀው ወጥተዋል፡፡ በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ከተገኙት አድናቂዎች ቴዎድሮስ ወደ ችሎቱ ሲገባ የተሰማውን ፉጨትና ጩኸት የሰሙ መንገደኞች የአካባቢው ነዋሪዎችና በፍርድ ሁለተኛና ሦስተኛ ፎቅ ላይ የሚሠሩ ሰራተኞች በመስኮት፣ በአጥርና በመንገድ ዳርና ዳር ተሰባስበው ታይተዋል፡፡ ዳኞች ከጧቱ ሦስት ሰዓት ተኩል በኋላ ሲሰየሙ፣ ጋዜጠኞች እንዲገቡ ቢፈቅዱም ፖሊስ ለይቶ ለማስገባት “ጋዜጠኞች የሆናችሁ ብቻ” ሲል ግር ብሎ በመጠጋቱ፣ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ችሎቶች ሥራቸውን በሚገባ እንዳይሠሩ እየተደረገ ነው በማለት መልሰው እንዳይገቡ ከልክለዋል፡፡ በዕለቱ ቴዎድሮስ ካሣሁን /ቴዲ አፍሮ/ ላይ አቃቤ ሕግ በመሰረተው በቸልተኝነት ማሽከርከር የሰው መግደል ወንጀል ውስጥ “ድርጊቱን የፈፀመው መንጃ ፈቃድ ሳይዝ ነው” የሚለውን ክስ፣ የተከሳሽ ጠበቃ ባቀረቡት ክርክር፣ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ ከአንድ ሰው በላይ ሞቷል፤ ወይም መጠጥ ጠጥቷል፤ በሚል ያቀረበው ስለሌለ የመንጃ ፈቃድ አለመያዝ ደንብ መተላለፍ መሆኑን የሚገልፀውን አንቀፅ አስደግፎ ስላላቀረበ፡፡ የትራፊክ ደንብ ቁጥር በመጥቀስ የመንጃ ፈቃድ ሳይዝ አሽከርክሮ በቸልተኝነት ሰው ገድሏል የሚል ስላልጠቀሰ፣ ክሱ መሰረዝ ወይም መሻሻል እንዳለበት መቃወሚያ በማቅረቡ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 13 ቀን 2000 ተቀጥሮ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡትን ተቃውሞ ተቀብሎ “ዐቃቤ ህግ ደንብ ተላልፏል” ከሚል ውጭ ደንብ ያልጠቀሰ መሆኑን ተናግሮ ክሱን እንዲያሻሽል ትዕዛዝ መስጠቱን በችሎት ውስጥ የተገኙ ዕማኞች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡ የተከሳሹ ጠበቃ በቴዲ አፍሮ ላይ ዐቃቤ ሕግ የመሰረተውን ሁለተኛ ክስ ተጠቃሎ በአንድ ይሁንልን በማለት የተቃወሙትን፣ “ፍርድ ቤቱ በቸልተኝነት ሰው መግደል አንድ የወንጀል ሀሳብ የተጎዳን ሰው አለመርዳት ደግሞ ሌላ የወንጀል ሀሳብ በመሆኑ አንድ ላይ ሊጠቃለሉ አይችሉም” በማለት መቃወሚያውን ውድቅ አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት ዐቃቤ ሕግ አሻሽሎ በሚያቀርበው ላይ ተመስርቶ በሚደረግ ክርክር የአርቲስት የዋስትና ሁኔታ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ መቀጠሩ ታውቋል ተገል"ል፡፡ የአርቲስት ቴዲ አፍሮ የዕለቱ የፍርድ ቤት ውሎ ከተጠናቀቀ በኋላ አርቲስቱ በዳኞች መግቢያ (የኋላ በር) እንዲወጣ ተደርጎ ወደ መጣበት ተሽከርካሪ ሊገባ ውጤቱን ሲጠባበቅ የነበረው አድናቂ፣ በጩኸት “ቴዲ፣ ቴዲ” እያለ በጭብጨባና በፉጨት አድናቂው ድጋፉን ገል"ል፡፡ በዕለቱ ተመድበው የነበሩ በርካታ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ድጋፉ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን ሲከላከሉ ታይተዋል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን ከአንድ ዓመት በፊት አንድ የጎዳና ተዳዳሪ ገጭቶ በማምለጥ፣ ያለመንጃ ፈቃድ በማሽከርከርና ተጎጂን ባለ ክስ ተመስርቶበት የዛሬ ሳምንት (ሚያዚያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም) ፍርድ ቤት መቅረቡ ይታወሳል፡፡ በታምሩ ጽጌ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |