Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ኦፌዴን በመሰነጣጠቅ ሌላው ተረኛ ይሆን?
ኦፌዴን በመሰነጣጠቅ ሌላው ተረኛ ይሆን? Print E-mail
Wednesday, 23 April 2008
ኦፌዴን ባለፈው ሣምንት ከምርጫ አቋርጦ መውጣቱን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጠበት ወቅት ጀምሮ ፈተና ገጥሞታል፡፡ አንዳንድ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ውሳኔውን ተቃውመውታል፡፡

ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት (ማክሰኞ) ከምርጫ አቋርጦ መውጣቱን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ተቃውሞአቸውን ያሰሙ በድርጅቱ ስም ከምዕራብ ወለጋ ዞን የኒጆ ወረዳ ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትና ቀደም ሲል በፓርላማ የኦፌዴን ተጠሪ የነበሩት አቶ መስፍን ነመራ ናቸው፡፡ የእሳቸው ተቃውሞ ድርጅቱ የወሰደው ከምርጫ ራሱን የማግለል እርምጃ በመጀመሪያ ጊዜውን የጠበቀ አለመሆኑ ነው፡፡ እንደ አቶ መስፍን አባባል ከሆነ ድርጅቱ አጠቃላይ ሁኔታውን ገምግሞ መውጣት ካለበትም ቀደም ብሎ መሆን ነበረበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ድርጅቱ የወሰደው እርምጃ አባላቱን ሳያማክርና ሳያሳውቅ በመሆኑ አሰራሩን የጠበቀ አካሄድ አለመሆኑ ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡

“ጊዜ አመራረጡ ትክክል አይደለም ወይ  መውጣት ነበረበት፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የፓርላማ አባላትም ማማከር ነበረበት” ብለዋል አቶ መስፍን፡፡ እሳቸው እንደሚሉት እርምጃው የተወሰደው በራሳቸው ወጪ ለወረዳ ምርጫ እየተንቀሳቀሱ በነበረበት ሁኔታ መሆኑ አሳዝኖዋቸዋል፡፡

በሚያዚያ አምስት በተካሄደው ምርጫ እሳቸው በተንቀሳቀሱበት አካባቢ (ኒጆ ከተማ) ለከተማ ምክር ቤት እስከ ሶስት የሚደርሱ የድርጅቱ ተወዳዳሪዎች ማሸነፋቸው መረጃ እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ ኦፌዴን በምርጫው የተወዳደረው ለማሸነፍ አስቦ ሳይሆን የኦፌዴን አባላት የሉም ወጥተዋል እየተባለ የሚነዛውን የገዢውን ፓርቲ መሰረተ ቢስ ወሬ ውሸት መሆኑን ለማሳየትና የተወሰኑ ወንበሮችንም ለማግኘት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ሆኖ ውሳኔ መስጠት የሚችል ቢሆንም ይሄ የፓርቲውን አጠቃላይ ህልውና የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ አባላት ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ቀድመው መመካከርና መወያየት እንደነበረባቸው ጠቁመው የእርምጃውን ድንገታዊነት ተችተዋል፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ የ”ስህተቱ” ዋና ተጠያቂ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ መስፍን፣ ከዚህ በፊትም ከሌሎች አመራሮችና አባላት ጋር ሳይመካከሩ ብዙ ጊዜ “ፓርቲያችን እንደዚህ ብሎ ያምናል” በማለት የግላቸውን  የፓርቲው አድርገው ሲወስዱ መቆየታቸውን ይወቅሳሉ፡፡ ጉዳዩን በምሳሌ ሲያብራሩም በአንድ ወቅት “ፓርቲያችን ዓሰብ የኢትዮጵያ አካል ነው ብሎ ያምናል”  መናገራቸው ለእኛ የድርጅቱ አባላትና የምክር ቤት ተመራጮች አዲስ ነበር ብለዋል፡፡ እንዲሁም ኤች አር 2003ን በተመለከተ በረቂቁ ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው የሚጎዳ ወይስ የኦሮሞና የተቀረው የኢትዮጵያን ድሃ የህብረተሰብ ክፍልም ይጎዳል የሚል ጥያቄ ተነስቶ እንዲወያዩበት ቢጠየቁም ጥያቄውን ወደ ጎን ትተው በራሳቸው የግል ውሳኔ "እንደግፈዋለን" ማለታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

እንዲሁም አቶ መስፍን ድርጅታቸው ከተመሰረተ ሶስት ዓመት የሆነው ቢሆንም ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ በአንዳንድ አገራዊ ጉዳዮች ላይም ሆነ በድርጅቱ አካሄድ ውይይት አለመደረጉን በመጥቀስ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በተለይ የድርጅቱ አመራሮች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመረጡ በተደጋጋሚ  ቢሆንም ለጥያቄያቸው አወንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

“ፓርቲው አልተከፋፈለም” የሚሉት አቶ መስፍን አሁንም ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ አዲስ አመራር ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመረጥ የእሳቸውና  ፍላጎት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ በፊትም ያፈነገጡ ሃሳቦች ሲያራምድ ቆይተዋል” በሚል በአቶ ቡልቻ ወቀሳ የተሰነዘረባቸው አቶ መስፍን፣ “መቼ ተገናኝተን ተወያይተን ነው ማን ምን ዓይነት አቋም እንደሚያራምድ የታወቀው?” በማለት መልሰው ወቅሰዋል፡፡

 ፓርቲው ከምርጫ ማግለሉን አስመለክተው በአካባቢው በነበሩበት ወቅት ወከባውና አሉባልታ ማስወራት ከፍተኛ እንደነበረ ይቀበሉ እንጂ ገዢው ፓርቲ ሆን ብሎ ያረገው ነው የሚል  እንደሌላቸውና የግለሰቦቹ (ካድሬዎቹ) ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኦፌዴን ራሱን ከምርጫ ማግለል አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣

“መውጣት ትክክል አይደለም እያልኩኝ ሳይሆን፣ አንዴ ከተገባበት፣ ግማሽ መንገድ ተሂዶ አሁን የተወጣው  አይደለም” ብለዋል አቶ መስፍን፡፡

በቅርቡ ኦፌዴን ከምርጫ ራሱን ለማግለል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገኝተው እርምጃውን የተቃወሙት አቶ መስፍን፣  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የተሰነዘረባቸው ”ወደ ስብሰባ የጠራህም የለም ተነስተህ ውጣ” የሚል ምላሽም አምባገነንነትን ያሳያል ብለዋል፡፡

አቶ መስፍን የተቃዋሚዎች ምርጫን ጥለው የመውጣት አስፈላጊነትና ጉዳት አስመልክተው ሲናገሩ “ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች ለማፈራረስና ለማዳከም የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ችግሩን በመቋቋም ተቃዋሚዎች ወደ ራሳቸው ውስጥ  አለባቸው” በማለት የፓርቲዎች ከምርጫ መሸሽ በሂደቱ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እንዳለ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ  የፓርቲው አባልና ዕጩ ተወዳዳሪ አቶ ተክሉ ተረፈ ውድድር ላይ እያለን ሊቀመንበሩ ድንገት ተነስተው “አግልለናል” ማለታቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊትም በፓርቲው የውስጥ አሰራር ችግር መኖሩን የጠቁሙት አቶ ተክሉ፣ በተለይ በፋይናንስ አጠቃቀምና በአንዳንድ አገራዊ ጉዳዮች የፓርቲው አባላት ያልተቀበሉትን አቋም ሲይዙ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ የኢፈዲሪ ህገ መንግሥት አንቀፅ 39ን “ኦፌዴን አይቀበለውም” የሚል አቋም የፓርቲው አባላት አቋም እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

አቶ ቡልቻ ፓርቲያቸው ከምርጫ ራሱን ለማግለል የተገደደው ከገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና አስፈፃሚዎች የተፈፀመበት ወከባ ተባብሶ በመቀጠሉ መሆኑን ቢናገሩም፣ አቶ ተክሉ በተሳተፉበት አካባቢ  ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡ ሰዎች እንዳንድ ችግሮች የገጠሙዋቸው ከመሆኑ ውጭ በሂደቱ ለመቀጠል የሚያዳግት ሁኔታ እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል፡፡ ታዛቢዎችም አስቀምጠው ማማረጣቸውንና የሚጋነን ችግር እንዳልገጠማቸው የሚገልፁት አቶ ተክሉ፣ ፓርቲው ከምርጫ ማግለሉን ተቃውመዋል፡፡ የወጣበት ጊዜም ትክክል አለመሆኑን ጠቁመው ውሳኔ መተላለፍ ካለበትም የሚመለከታቸው ዕጩዎች መክረውበት መሆን እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡

ይህንን የፓርቲው ከምርጫ መውጣት በመቃወማቸው የስልክ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነና ከአመራሮቹ ጋር ያላቸው ግንኙነት መቋረጡንም አቶ ተክሉ ግልፅ አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል በፓርላማ ውስጥ ያሉት አንዳንድ ለጊዜው ስማቸው እንዳይታወቅ የሚፈልጉ የኦፌዴን አባላት ከሌሎች ዕጩ ተመራጮች ጋር በጋራ ቃለ ጉባኤ መያዛቸውን፣ ለወደፊቱም ምን ማድረግ እንዳለባቸው እያጠኑ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ፓርቲው ይህንን እርምጃ ለመውሰድ በሥራ አስፈፃሚዎች ያስወሰነ በመሆኑ የፓርቲው አባላት ለውሳኔው ተገዢ መሆን የለባችሁም ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ አቶ ተክሉ፣ “ይሄ የፓርቲው ዓብይ ጉዳይ በመሆኑ፣ እኛን ጨምሮ የፓርቲው አባላት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በቀጥታ የሚነካ ጉዳይ በመሆኑ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሊወያይበት ይገባ ነበር” ብለዋል፡፡

የሥራ አስፈፃሚውም ሆነ የሊቀመንበሩ እርምጃ የተሳሳተ በመሆኑ እንደማይቀበሉት አረጋግጠዋል፡፡ ሥራ አስፈፃሚዎችም በተደጋጋሚ የሚያንፀባረቁት አቋም የሊቀመንበሩ ውሳኔ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለዕጩ  የአቋም ልዩነት  የሰጡን የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ያልሆኑትን የማማከር ግዴታ እንደሌለባቸው ገልፀዋል፡፡

ለዕጩ ተወዳዳሪዎችና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቀድማችሁ ይህንን ነገር ማማከር አልነበረባችሁም ወይ? የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው “በእርግጥ ጉዳዩን መስማት አለባቸው እናምናለን፡፡ በይሁን እንጂ አቶ መስፍንን በጊዜው ልናገኘው አልቻልንም” ብለዋል፡፡

አቶ ተክሉን በተመለከተም በቴሌቪዥን ሲናገሩ ብቻ መስማታቸውን ጠቁመው የግለሰቡ እንቅስቃሴ ፓርቲውን የሚጎዳ በመሆኑ ከአባልነት እንደአስወጡዋቸው ተናግረዋል፡፡ በኦፌዴን ስም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከእነሱ ጋር ተቧድኗል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ገልፀዋል፡፡

ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱን ተጠይቀው እስከ አሁን ስላልተመቻቸው አለማካሄዳቸውን አምነው በቅርቡ ለማካሄድ እየተንቀሳቀሱ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ አያይዘውም “እስከአሁን  ጉባኤ ጠርተን የምናካሂድበት ጊዜ አልነበረንም” ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ ባለፈው የካቲት 5 እና 12 የተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ በተፎካካሪነት (በተቃዋሚነት) ከቀረቡ ፓርቲዎች አንዱ ቢሆንም በመጀመሪያው ምርጫ ከተሳተፈ በኋላ ከቀሪው ራሱን ማግለሉ ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የፓርቲው እርምጃ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “ህገ ወጥ” በማለት ተቃውሞታል፡፡

በሌላ በኩል በተወካዮች ምክር ቤት የሚገኙ አንዳንድ የፓርቲው አባላትና ፓርቲውን ወክለው በምርጫው በዕጩ ተወዳዳሪነት እየተንቀሳቀሱ የቆዩ አባላት የፓርቲውን እርምጃ ተቃውመዋል፡፡ ጉዳዩ በፓርቲው ህልውና ላይ ሊያሳድረው የሚችል ተፅዕኖ ካለም ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

በየማነ ናግሽ
 
< Prev   Next >