| አፍሪካን የሚያዋህዷት ህዝቦቿ ወይስ መሪዎቿ? |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
|
ሁሌም እንደሚባለው አፍሪካ በተፈጥሮአዊ አቀማመጧ ከነበረችበት ሁኔታ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ተለዋውጣለች፡፡ አንድ ላይ የነበሩት ተለያይተዋል፡፡ ተለይተው የነበሩት በጉልበት አንድ ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ግማሹ ህዝብ ለአንድነት ሌላኛው ሕዝብ ለመገንጠል በሚያደርጉት ትግል የተነሳ ሰላምና መረጋጋት በአህጉሪቱ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ለመሪዎቹ ደግሞ ግጭት በመፍጠር ሥልጣንን የሙጥኝ እንዲሉበት መሳሪያ ሆኗል፡፡ እነኚህ ውስጣቸው ሰላም የሌላቸው ከ50 በላይ የሆኑ ሃገራት በአዲሱ አፍሪካ ህብረት በጥንቱ አፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካኝነት ውህደት ለመፍጠር ሲሞክሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ውህደቱ እንዴት ይፈፀማል? ማን ይፈፅመዋል? እነማንን ያሳትፋል? በፖለቲካው ወይስ በኢኮኖሚው ይጀመር? በመሪዎቹ የበላይ ተመልካችነት ወይስ በብዙሀኑ ህዝብ ተሳትፎ? የሌሎች አህጉሮችንና አካባቢያዋ ውህደትን በመውሰድ ወይስ አፍሪካዊ በሆነ መንገድ? አፍሪካዊ የሆነ መንገድስ የቱ ነው? . . . ብዙ ጥያቄዎች . . . ጥቂት መልሶች ለዚያውም የማያረኩ፡፡ ዶ/ር አዳምስ ኦሉ ኬንያ በሚገኘው ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ሕዝብ አስተዳደር አስተማሪ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በቅርቡ ባሳተመው "The Bulletin of Fridays of the Commission" መፅሄት ላይ ከላይ በተነሳው ጉዳይ ላይ ያለ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡ ዶክተሩ አፍሪካ በመሪዎቿ ነው የምትዋሃደው የሚል አቋም የጀመሩት ዝነኛው የጋና የነፃነት መሪ ክዋሜ ንኩሩማ እንደነበሩ ያወሳሉ፡፡ የጊኒው አህመድ ሴኩ ቱሬ እና የማሊው ሞዲቦ ኪዬታ ከዚሁ ጎራ የተቀላቀሉ ነበሩ፡፡ ሌሎች ግን በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ የባህል ልውውጥ በብዙሀኑ ሕዝብ ተሳትፎ በቅድሚያ ካልዳበረ ትክክለኛ ውህደት አይመጣም ብለው ያስቡ ነበር፡፡ ይህ በታንዛኒያው መሪ ምዋሊሙ ጁልዬስ ኔሬሬ ፈር ቀዳጅነት የተመሠረተ ሃሳብ በናይጄሪያው ተፈዋ በለዋ፣ በላይቤሪያው ዊሊያም ቱብማን፣ በሴኔጋሉ ሊዮፓልድ ሴንጎር እና በአይቮሪኮስቱ ሁኘዋት ቢዮግኒ ይደገፍ ነበር፡፡ ኔሬሬ ከአፍሪካ ውህደት በፊት የአካባቢ ውህደቶች በቅድሚያ ሊረጋገጡ ይገባል የሚል አቋም ነበራቸው፡፡ ይህም ከህዝቡ ተሳትፎ ጠንካራ ውህደት ይገኛል ከሚል እሳቤ ነው፡፡ ከዘመነኞቹ መሪዎች የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች የደቡብ አፍሪካው ታቦ ምቤኪና የናይጄሪያው ኡማሩ ያርአዱአ ናቸው፡፡ የንክሩማን ሃሳብ የሚጋሩት ደግሞ የሊቢያው ሙአማር ጋዳፊ፣ የሴኔጋሉ አብዱላዬ ዋዴና የማሊው አልፋ ኮናሬ ናቸው፡፡ ዶክተር አዳምስ ሁለቱም እሳቤዎች ከላይ ሲታዩ የአፍሪካን ሕብረት ስለመፍጠር ያልሙ እንጂ ውስጣቸው ችግር እንዳለበት ያምናሉ፡፡ "መሪዎቹ ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ሕዝቦቹም ያለ ጥሩ መሪ ውህደቱን መፈፀም ስለማይችሉ ከሁለቱም የተዳቀለ ኮንፌዴሬሽን ለአፍሪካ ውህደት የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ ይላሉ፡፡ እንደ አውሮፓ ሕብረት ፖለቲካዊ ውህደት አልያም እንደሰሜን አሜሪካ ነፃ ገበያ ማህበር ነፃ ገበያ ተኮር ውህደት ዋነኛ ዓላማው የተወሰነ ግብን ለመምታት በጋራ ውሳኔ ማሳለፍና ወደ ተግባር መዝለቅ ነው፡፡ ዋነኛ መለያውም እቃን፣ አገልግሎትን፣ ካፒታልንና ሰዎችን ያለ ገደብና አድልኦ መለዋወጥ ነው፡፡ የውህደቱን ሒደትና ውጤት እንዲሁም ተፅእኖ ሙያተኞች፣ ህብረቱ፣ ሐገራቱ፣ ፌዴሬሽኑ አልያም ኮንፌደሬሽኑ በበላይነት እንዲመራው የሚያቀነቅኑ ፅንሰ ሃሳቦች አሉ፡፡ አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ከላይ የተገለፁ እሳቤዎች በውህደቱ ዓላማ፣ ቅርፅ፣ ተቋምና ስልት ላይ እንጂ ሕብረቱን ለመመስረት ለምን እንደተፈለገ የሚገልፁት ነገር እንደሌለ ይገልፃሉ፡፡ መቀራረብ፣ ጥቅም ደህንነትና ጉልበት ውሕደቱ ለምን እንደሚፈለግ የሚገለፅባቸው ነጥቦች እንደሆኑም ይገልፃሉ፡፡ ውህደቱ ለአንዳንድ ሐገራት የምርጫ ለሌሎች ደግሞ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ የጥቅም ጉዳይ ከሁሉም ምክንያቶች የበለጠ ድጋፍ አለው፡፡ በተለይ አህጉር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቶች የሚያመጡትን ጥቅምና ጉዳት በህብረት ለመታገል ውህደቱ ዋነኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ኮሚሽን፣ የደቡብ አፍሪካ ልማት ኮሚሽን፣ ኢኮዋስ፣ ኢጋድ እና ኮሜሳ ከባቢያዊ የንግድ ውህደት የሚገለፀውም በዚሁ የጥቅም ተመራጭነት ነው፡፡ ጥቅምን ያስቀደመ ውህደት ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባውን የፖለቲካ ሃሳብ በኢኮኖሚ ሃሳብ ስለሚሸፍን ድክመት አለበት የሚሉት ዶክተር አዳምስ ናቸው፡፡ ዶክተሩ ጥቅም እንደ ውህደት ምክንያትና እንደ ውህደቱ ውጤት ልዩነቱ እንዳልተጤነ ይገልፃሉ፡፡ የአውሮፓ ሕብረት በደህንነትና ሰላም ፍለጋ ተቋቁሞ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ማምጣቱንም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ ዶ/ር አዳምስ የአፍሪካ ውህደት መጀመር ያለበትም የአፍሪካን ደህንነት በማረጋገጥ ነው፡፡ አፍሪካ ህብረት ከባቢያዊ የጦር ኃይል ማቋቋሙም ወደዚሁ አቅጣጫ ለመጓዝ ፍንጭ የሰጠ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ አፍሪካን በጉልበት አንድ ለማድረግ የሚያስፈልገው የኢኮኖሚና ወታደራዊ ኃይል ያለው አፍሪካዊ ሀገር በቀላሉ ማግኘት ይክበድ እንጂ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ አቅሙ እንዳላቸው ዶክተሩ ይከራከራሉ፡፡ የሊቢያን ቅጥ ያጣ አስተዳደር ደቡብ አፍሪካ በግልፅ መተቸቷም ለፀሐፊም ግምቱን አጠናክሮላቸዋል፡፡ ፀሐፊው በመሪዎቿ የተዋሃደችውን አሜሪካን በአንድ ጎን በምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን አነሳሽነት ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ የተዋሃደችውን አውሮፓን በሌላ ወገን በመውሰድ ሂደቱን፣ ጥንካሬና ድክመቱን እንዲሁም ውጤቱን በጥልቀት ተንትነዋል፡፡ ዶ/ር አዳምስ እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በአፍሪካ አህጉር ብዙ ደጋፊ ያለው በመሪዎች ደረጃ የሚደረገው የውህደት ጥረት ነው ይላሉ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረት ቀስ በቀስ ያደረገው ሽግግር እንዲሁም የሌጎስ የተግባር እቅድ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚዩኒቲ እና አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ እድገት ምስረታ የተከናወነው በመሪዎች ጥረት ብቻ መሆኑን ለምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚዩኒቲን የመሰረቱት መሪዎች ህብረቱ በ34 ዓመት ጊዜ ውስጥ በ6 ዋና ዋና ደረጃዎች እስከ 2025 ድረስ ከለዘብተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ቁርኝት ወደ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውህደት እንዲመጣ አቅደዋል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ደረጃዎች ከባቢያዊ የኢኮኖሚ ትብብር በመመስረት ወደ ነፃ የንግድና የጉምሩክ ቀጠና ሕብረትነት እንዲለውጡ የማድረግ መሪ እቅድ ይዘዋል፡፡ የቀሩት ሦስት ደረጃዎች ከባቢያዊ የኢኮኖሚ ትብብሩ ወደ አህጉራዊ ጉምሩክ ህብረትና የአፍሪካ የጋራ ገበያ ወደ መፍጠር እንዲሸጋገር አህጉራዊ የኢኮኖሚና የገንዘብ ተቋማት መፍጠር፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ ውህደት ለማረጋገጥ የፓን አፍሪካን ፓርላማ እውን ማድረግ የሚሉ መሪ የተግባር እቅዶችን ይዘዋል፡፡ የኔፓድ መመስረት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሙኒቲን እንዳጠፋው ዶክተሩ ይገልፃሉ፡፡ ኔፓድ በ2000/01 እ.ኤ.አ ለአፍሪካ ማገገም የሚሊኒየሙ አጋርነት ኘሮግራም አፍሪካ ታቦምቤኪ፣ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ ከናይጄሪያ እንደሁም አብዲልአዚዝ ቡተፍሊካ ከአልጀሪያ በተዋቀሩትና አፍሪካ ያለባትን የእዳ ቀውስ እንዴት መቋቋም አለባት የሚለውን ጉዳይ እንዲመረምሩ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የቤት ሥራ ከተሰጣቸው በኋላ እንደሆነ ዶክተር አዳምስ ያብራራሉ፡፡ ምቤኪ "የአፍሪካ ህዳሴ"ን ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የማህበራዊ ኑሮና የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልጋል የሚል አቋም እንደነበራቸውም ያስታውሳሉ፡፡ የቀድሞው የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች በሴኔጋሉ ኘሬዚዳንት አብዱላዬ ዋዴ በመመራት ለኔፓድ አማራጭ የሆነ ኦሜጋ የተሰኘ ኘሮግራም እ.ኤ.አ በ2001 ነደፉ፡፡ ይህም ኔፓድን የቀድሞው የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች እቅድ አድርጎ በመውሰድ ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው ዓመት ኔፓድና ኦሜጋ ወደ አዲስ የአፍሪካ ተነሳሽነት (NAI) ተቀላቀሉ፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ በጥቅምት 2ዐዐ1 አቡጃ ናይጄሪያ ላይ የተገናኙት የአፍሪካ መሪዎች በድጋሚ ኔፓድን እንደ አዲስ አዋቀሩት፡፡ ለኘሮግራሙም የቡድን ስምንት አገራት ቡራኬአቸውን ሰጡት፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ኮሚዩኒቲ የጉምሩክ ህብረትን የፈጠረ ሲሆን ወደ ጋራ ገበያና የፖለቲካ ህብረት የሚያደርገው ጉዞ ግን ችግር እየገጠመው ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ የልማት ኮሚዩኒቲ፣ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚክ ኮሚዩኒቲ (SADC)፣ የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ ድርጅት (COMESA)፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚክ ኮምዩኒቲ (ECCAS)፣ የአረብ መግረብ ህብረት፣ የሳህሎ ሳሃራን ሃገራት ኮሚዩኒቲ እና ለልማት የመንግሥታት ሥልጣን (IGAD) በእስከአሁኑ ጉዟቸው በንግድ እድገት በኩል በርካታ ችግሮችን እያስተናገዱ ነው፡፡ ይህም በሕዝቡ ተሳትፎ እየተደረገ ያለው የውህደት ጥረት ድክመት እንዳለበት ያሳያል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ፖለቲካዊ ውህደት እንዲፈፅም የሰብአዊ መብት ተሟጋቹና ገጣሚው ማርከስ ጋርቬይ ፅንሰ ሃሳቡን የጣለው ሲሆን ክዋሜ ንኩሩማህ በበርካታ መፅሀፎቹና በሃሳቦቹ ነፍስ ዘርቶበት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1999 በኋላ ደግሞ የሊቢያው ሙአማር ጋዳፊ የሃሳቡ አቀንቃኝ ሁነዋል፡፡ ሆኖም እስከ አሁን እንዴት የፖለቲካ ውህደቱ ይፈፀማል? ለሚለው ጥያቄ ጋዳፊም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው አጥጋቢ መልስ አልሰጡም፡፡ ዶክተር አዳምስ ኦሉ የሃሳብ ክርክሩ እስካሁን የኮንፌደራልን ፅንሰ ሃሳብ ግምት ውስጥ አለመካተቱን ጠቅሰው ይከራከራሉ፡፡ ኮንፌደሬሽኖቹ ለደህንነትና ለመከላከያ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ሃገራቱም ሉአላዊነታቸውን አስጠብቀው በፈለጉበት ሰዓት ከኮንፌዴሬሽኑ የመውጣት መብት አላቸው፡፡ የተወካዮች ስብስብ በውጭ ጉዳይና በመከላከያ ረገድ የተሟላ ሥልጣን አለው፡፡ በተጨማሪም ኤምባሲዎችን የመቀበልና የማሰናበት፣ ውል የመዋዋል፣ ጦርነት የማወጅ፣ ንግድን የመቆጣጠር፣ ገንዘብ የማተም . . . ወዘተ ስልጣን አለው፡፡ ፀሐፊው የስዊዘርላንድ፣ ሆላንድ፣ ጀርመንና አሜሪካ ኮንፌሬሽኖችን ልምድ አካፍለው አንዳቸውም ልልነቱን ተጠቅመው እንዳልፈረሱ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ኮንፌደሬሽን ለመበታተን የተጋለጠ ነው በማለት ለአፍሪካ አህጉር እንደማይሆን የሚከራከሩትን ይተቻሉ፡፡ ለምን አሉታዊ ምስል እንዳለውም እንደማይገባቸው ይገልፃሉ፡፡ የአፍሪካ ሃገሮች የንግድ መሰናክሎችን ለማጥፋት፣ የጋራ ፖሊሲዎችን ለመቅረፅ እና የጋራ ተቋማትን ለመገንባት የሚወላውሉት ለሉአላዊነታቸው የተጋነነ ግምት ስለሚሰጡ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አዳምስ ይህ ስጋት ካልተቀረፈ የድጋፍ፣ የትብብርና የውህደት ምኞት ብቻ ይሆናል ይላሉ፡፡ የፖለቲካ አመራሩ ያለመጠናከርና ለውጥ ያለማምጣት ኔፓድን ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት እንደሆነበትም ፀሐፊው ይገልፃሉ፡፡ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ከ53 የአፍሪካ ሃገራት መካከል የፖለቲካ ስልጣኑን ለአፍሪካ ህብረት አሳልፎ የሰጠ አንድም ሀገር እንደሌላ ያወሳሉ፡፡ የአፍሪካ ፓርላማም ምክር ከመስጠት በዘለለ ተፈፃሚ የሚሆኑ ህጎችን አያወጣም፡፡ ኮሚሽኑም ቢሆን የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚነት የላቸውም፡፡ አፍሪካ ከልብ መዋሃድ የምትፈልግ ከሆነ ሃገራቱ ከሥልጣናቸው ጥቂቱን በስምምነት ለኮሚሽኑ አልያም ለፓርላማው አሳልፈው ሊሰጡ ግድ ይላቸዋል የሚሉት ዶ/ር አዳምስ የአውሮፓና የአሜሪካ ውህደት ከዚህ መጀመሩንም ያስታውሳሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መርሖዎችና የጋራ ተቋማት ግንባታ ላይ የሚደረግ ስምምነት ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ፀሐፊው የአፍሪካ ሕብረት አባላት ፈቃድና ፍላጎት አላቸው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ በአውሮፓ ልምድ ኮሚሽኑ፣ ፓርላማውና ፍርድ ቤቱ ሲቋቋም መስማማት ስለነበር ነገሮች በአጭር ጊዜ አልቀዋል፡፡ በአፍሪካ ልምድ ግን እስከ አሁን ህጎችና ተቋማት አመሰራረትና አሰራር ላይ ስምምነት አልተደረሰም፡፡ የአፍሪካ ፓርላማና ፍርድ ቤት ምክር በመስጠት እንዲወሰኑ የተደረገው የአፍሪካ ሃገራት ስራ አስፈፃሚዎች ስልጣናችን አይሸረፍም በማለታቸው ነው፡፡ አውሮፓና አሜሪካን ደህንነትና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዳዋሃዳቸው ሁሉ አፍሪካን ይህ ያላነሳሳት ኔፓድ የተመሰረተበትን ዋነኛ ግብ ባለመምታቱ እንደሆነ ዶ/ር አዳምስ ያምናሉ፡፡ በአፍሪካ የሚደረጉ ምርጫዎች በግጭት፣ ማጭበርበርና ማሰቃየት የሚታጀቡት የአፍሪካ ህብረት የሚያስፈፅም አካል ባለመኖሩ ነው ይከራከራሉ፡፡ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች እንደፈለጉት ሰብአዊ መብት ጥሰት ቢፈፅሙም የሚናገራቸው አካል የለም፡፡ ይህ ግን ከቻርተሩና ከኔፓድ አላማ ጋር በግልፅ ይፃረራል ይላሉ ዶክተሩ፡፡ አውሮፓና አሜሪካን በውህደት ያጀቡት አባላት ብዙም ያልተራራቁ ሲሆኑ የአፍሪካ ሃገራት ግን በማህበራዊ ህይወትም ሆነ በኢኮኖሚ ሥርዓቱ የተራራቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ብዙሃኑን ያሳተፈ የማቀራረብ ሥራ መሰራት አለበት በማለት ፀሐፊው ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡ በሃገራቱ ያሉት ተቋማት መሠረታቸውን ያልጣሉ ደካማና ያልተረጋጉ በመሆናቸው ለአህጉራዊ ተቋማት ግንባታ ሚናቸው አናሳ መሆኑንም ዶክተር አዳምስ ገልፀዋል፡፡ የአፍሪካ ሕብረቱን አላማ ቀስ በቀስ ለማሟላት የተቋቋሙት ከባቢያዊ የኢኮኖሚ ማህበራት ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያላቸው ግንኙነት ደካማ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡ በሃገርም ሆነ በአካባቢ ደረጃ ብዙሃኑ ሕዝብ ለአፍሪካ ሕብረት ውህደት መጠናቀቅ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች አለመመቻቸታቸውን ይተቻሉ፡፡ ሃገራቱ በውጭ እርዳታ ለጋሾች ከመጠን በላይ መተማመናቸውም ለውህደቱ ትኩረት እንዳይሰጡ እንዳደረገ ይገልፃሉ፡፡ የሚወጡ ፖሊሲዎችንም ለማስፈፀም የሚወሰዱ እርምጃዎች አናሳ ናቸው፡፡ በማጠቃለያቸው አፍሪካ ኮንፌዴሬሽንን መሞከር አለባት የሚሉት ዶ/ር አዳምስ ጉዳዩ የሕዝቦቿ ሳይሆን የመሪዎቿ ነው ብለዋል፡፡ በሰለሞን ጐሹ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |