| ለአሜሪካ ገበያ ከተላከው አልባሳትና... |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
|
ለአሜሪካ ገበያ ከተላከው አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ የተገኘው ገቢ ቀነሰ
ለአሜሪካ በ2007 ገበያ ከቀረበው የኢትዮጵያ አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ ምርት ሽያጭ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ18 በመቶ ቀነሰ፡፡ ከአሜሪካ ኮሜርስ ዲፓርትመንት ድረገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ሽያጭ በ2006 ስድስት ሚሊዮን፣ በ2007 4.9 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ለአሜሪካ ገበያ የቀረቡት የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ምርቶች ዋጋ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ የቀነሰ ሲሆን ከውጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ በአሁኑ ሰዓት ካለው በ25 በመቶ መቀነሱን መረጃው አመልክቷል፡፡ በ2005 ለገበያ ከቀረቡት የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች 1.7 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን በተመሳሳይ ምርቶች ሽያጭ በ2007 421 ሺህ ዶላር ተገኝቷል፡፡ ኢትዮጵያም ሆነ የአጎዋ እድል (አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት"ን ተጠቃሚ የሆኑ 38 ከሠሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ቢገልፁም ከእድሉ የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት አናሳ መሆኑ ተገል"ል፡፡ በኢትዮጵያ በቅርቡ በሚከፈቱት የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች ሥራ ሲጀምሩ አገሪቱ ከዘርፍ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለመጨመር እንደሚያስችላት ተጠቁሟል፡፡ አሜሪካ የተላከው የሚኒራልና የብረታ ብረት ወጪ ንግድ መቀነሱም መረጃው ያስረዳል፡፡ በ2007 ኢትዮጵያ በሜኒራልና በብረታ ብረት ወጪ ንግድ 24 ሺህ ዶላር ያገኘች ሲሆን ከተመሳሳይ ምርት ወጪ ንግድ በ2005 48 ሺህ ዶላር ተገኝቶ ነበር፡፡ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው የሜኒራልና የብረታ ብረት ሽያጭ በ2005 ከነበረው 250ሺህ ዶላር በ2007 ወደ 819 ሺህ ዶላር ማደጉን መረጃው ያመለክታል፡፡ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ትልቅ የገበያ ድርሻ ባለው የግብርና ምርቶች ገበያ አሜሪካ የ10 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ (Surplus) ገቢ ስታገኝ በ2007፣ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ 77 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የግብርና ምርቶችን ለአሜሪካ ገበያ ያቀረበች ሲሆን 93 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ተመሳሳይ ምርት ወደ አገር ውስጥ መግባቱንም መረጃው ያስረዳል፡፡ የትራንስፖርት መሳሪያ በሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ ሁለተኛ ድርሻ ሲኖረው አሜሪካ በገበያው ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች፡፡ በ2007 ኢትዮጵያ ለትራንስፖርት በ29 ሚሊዮን ዶላር ግዢ ያከናወነች ሲሆን በተመሳሳይ አመት ወደ አሜሪካ ገበያ 9000 ዶላር የሚያወጣ የትራንስፖርት መሳሪያ መላኩ ተገል"ል፡፡ በ2007 በሁለቱ አገሮች መካከል የ271 ሚሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን አሜሪካ የ60 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ (Surplus) ገቢ አግኝታለች፡፡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ባደረገችው ጠቅላላ የንግድ ልውውጥ 105 ሚሊዮን ዶላር ያገኘች ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ10 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በተመሳሳይ አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከላከችው ምርት 166 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቷ መረጃው ያመለክታል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በነበረው የንግድ ልውውጥ አሜሪካ የተሻለ ተጠቃሚ እንደነበረች መረጃው ጠቁሞ፣ በ2005 አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው ምርት 513 ሚሊዮን ዶላር ሲያወጣ ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የላከችው 70 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር አትቷል፡፡ ከታሪፍና ኮታ ወደ አሜሪካ ገበያ ምርቶችን እንዲያስገቡ እድል ከተሰጣቸው የአፍሪካ አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች አንፃር ያላት ተጠቃሚነት አናሳ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በአጎዋ እድል ተጠቃሚ የሆኑት የአፍሪካ አገራት በ2007 ወደ አሜሪካ በድምሩ 64.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት የላኩ ሲሆን በተመሳሳይ ዓመት አሜሪካ 13 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርትን ወደ አገሮቹ ልካለች፡፡ የአጎዋ የገበያ እድል ከጥቅምት 2000 እስከ መስከረም 2008 የሚቆይ የነበረ ቢሆንም እድሉ እስከ 2015 ድረስ ተራዝሟል፡፡ ከአጎዋና ጄነራል ሲስተም ኦፍ ፕሪፈረንስ ወደ አሜሪካ ገበያ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተነሳው ቀረጥ ታሪፍ በሚከፈልባቸው 7000 በጄነራል ሲስተም ኦፍ ፕሪፈረንስ የተካተቱን 1800 ምርቶችን ያካተተ ሲሆን አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ወይን፣ ዕቃዎችና መለዋወጫዎች የግብርና ምርቶች፣ ኬሚካሎች፣ ቆርቆሮና ሌሎችን ያካተተ ነው፡፡ በጋዜጣው ሪፖርተር |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |