Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ኢትዮጵያ አሣን ለቱሪዝም በማዋል...
ኢትዮጵያ አሣን ለቱሪዝም በማዋል... Print E-mail
Wednesday, 23 April 2008
Image
አቶ ረድኤት ሃብተሥላሴ
ኢትዮጵያ አሣን ለቱሪዝም በማዋል ተጠቃሚ አልሆነችም

ሁለት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የአሣ ዝርያዎች ለመጥፋት ተቃርበዋል


ኢትዮጵያ ያላትን የአሣ ሃብት ለቱሪዝም አገልግሎት በማዋል ልታገኝ የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ አለማግኘቷ ተገለፀ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙ የሁለት አሣ ዝርያዎች ለመጥፋት መቃረባቸው ተጠቆመ፡፡

በብሔራዊ አሣና የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ተመራማሪ አቶ ረድኤት ሃብተሥላሴ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር በርካታ የአሣ ዝርያዎች ቢኖርዋትም ይህንን ሃብት ከምግብነት ውጪ ለቱሪዝም አገልግሎት ማዋል አልቻለችም፡፡

ሌሎች አገሮች በአሣ ቱሪዝም (ስፖርት ፊሽንግ) የሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ የቱሪዝም አገልግሎት የሚከፈለው ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያም አሣን ለቱሪዝም መስህብነት በመጠቀም የቱሪዝም ገቢዋን ማሳደግ የምትችል መሆንዋን አመልክተዋል፡፡

በዓለም ላይ አሣን ለቱሪዝም አገልግሎት እንዲውል ያደረጉ አገሮች ከፍተኛ ገቢ እያገኙበት ነው፡፡ ኬንያ የዚህ ተጠቃሚ ነች፡፡ ለስፖርት ፊሽንግ ወይም አሣን ማጥመድ ለመዝናኛ አገልግሎት በማዋል ሥራ ተሰማርተው የገቢ ምንጭ አድርገው የሚጠቀሙ አገሮችም ለዚህ አገልግሎት የሚከልሉት ቦታ ትንሽ ቢሆንም የአገልግሎቱ  ከፍተኛ በመሆኑ ጥሩ ጥቅም ያገኙበታል፡፡

ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎትም የራሳቸው የሆነ ሕግ እንዳላቸው ያመለከቱት አቶ ረድኤት ለስፖርት ፊሽንግ ተብሎ በተከለለ ቦታ አንድ ቱሪስት ምን ያህል ማጥመድ እንዳለበት፣ ምን ያህል ሰዓት መጠቀም እንደሚችል፣ ሊያጠምዳቸው የሚገቡ የአሣ ዝርያዎች ምን ዓይነት እንደሆኑና ለዚህም አገልግሎት ምን ያህል ክፍያ እንደሚጠየቅበት በዝርዝር የሚያስረዳ ሕግ ስላለ ቱሪስቱ በሕጉ መሠረት ማጥመድ ይችላል፡፡

በአገራችን ግን ለዚህ አገልግሎት የሚሆን ህግ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ አሣዎቻችንን ለዚህ አገልግሎት እየተጠቀምንባቸው አይደለም ያሉት አቶ ረድኤት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትታወቅበት ትላልቅ ፓርኮች ወንዝ የሚያቋርጥባቸውና ለስፖርት ፊሽ እጅግ አመቺ በመሆናቸው ልንጠቀምባቸው እንችል ነበር፡፡ ይህንን ባለማድረጋችን ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሪ ልናጣ ችለናል ይላሉ፡፡

ነጭ ሣር፣ የባሌ ተራሮች፣ ኦሞ፣ አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በምሣሌነት የጠቀሱት አቶ ረድኤት ወደእነዚህ አካባቢዎች  ቱሪስቶች ተጨማሪ ክፍያ ከፍለው  ፊሽንግን ሊጠቀሙ ይችሉ ነበር፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ ስፖርት ፊሽንግን የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተወሰነ ደረጃ የሚጠቀምበት ቢሆንም ይህንን አገልግሎት እንደሚሰጥ  ሁኔታ አልተገለፀም፡፡ አገልግሎቱ በደንብ ቢተዋወቅ ለዚህ ብለው የሚመጡ ቱሪስቶች በርካታ ይሆኑ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ 183 የሚደርሱ የአሣ ዝርያዎች እንዳሉ የተረጋገጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 30 የሚሆኑት ኢንደሚክ (በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ) ናቸው፡፡ እነዚህን በማሳየት ራሱ ትልቅ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡

የቱሪዝም መስህብና አስደናቂ ባህሪ እንዳላቸው የጠቆሙት ተመራማሪው በኦሞ ወንዝ ውስጥ የሚገኝ ማሌፕትሩረስ ኤሌክትሪክስ የሚባል አሣ ከሌሎች አሣዎች በተለየ በአንድ ጊዜ 350 ቮልት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ባህሪ አለው፡፡ ይህ አሣ አሣዎችን የኤሌክትሪክ ሃይል በመርጨት ካደነዘዘ ወይም ከገደለ በኋላ ይመገባቸዋል፡፡

በጣና ሃይቅ ውስጥ ያሉ አሣዎች ደግሞ ጥርስ ሳይኖራቸው ሌሎች አሣዎችን ይመገባሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ለየት ያሉ ባህሪያትን ለመመልከት ወይም ለማጥመድ ከሚመጡ ቱሪስቶች ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡

አሣን ለቱሪዝም መስህብነት ለመጠቀም የሚያስችል ሕግ አለመኖር አንዱ ችግር መሆኑን ያስቀመጡት ተመራማሪው በ1995 ዓ.ም ስለአሣ ሃብት የወጣው ሕግ ተጨማሪ መመሪያዎችና ማስፈፀሚያዎች እንዲወጡለት ባለመደረጉ ይህንን ለመተግበር አለመቻሉና የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትም በጥምረት አለመሥራት በሃብቱ ላለመጠቀም እንደምክንያት ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩልም ኢንደሚክ መሆናቸው የተረጋገጡ ሁለት የአሣ ዝርያዎች በመጥፋት ላይ መሆናቸውን እኒሁ ተመራማሪ ገልፀዋል፡፡ እነዚህ አሣዎችም ባርቢስ ኢትዮፒከስ እና በጣና ሐይቅ ያለ አንድ የአሣ ዝርያዎች ናቸው፡፡ ባርበስ ኢትዮጲክስ የሚባል የአሣ ዝርያ የሚኖረው በመቂ ወንዝ በዝዋይ ሐይቅ ብቻ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ዝርያው እየተመናመነና ለመጥፋት እየተቃረበ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

አቶ ረድኤት እንዳሉት የሁለቱ የአሣ ዝርያዎች ለአደጋ መጋለጥ ምክንያቱ አግባብ ያልሆነ የአሣ ማስገር፣ በአካባቢው ያሉ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች፣ የውሃ ብክለት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በተለይ የባርበስ ኢትዮ ፒኪስ ለአደጋ መጋለጥ ዋነኛ  በዝዋይ ሐይቅና በመቂ ወንዝ ላይ እየተካሄደ ያለው የመስኖ ልማት ነው፡፡ እንደተመራማሪው ገለፃ በእነዚህ የውሃ አካላት አካባቢ በአሁኑ ጊዜ ከ400 በላይ የውሃ ፓምፖች በየዕለቱ ውሃ በመሳብ ለመስኖ አገልግሎት ይውላሉ፡፡ ከፓምፕ ውጪ የሚያለሙ አልሚዎች የመቂ ወንዝን ጠልፈው እየተጠቀሙ መሆኑ አደጋውን አፋጥኖታል፡፡   

የውሃ አካላቱ ከአቅማቸው በላይ ውሃ ስለሚወሰድባቸው እየተጐዱ ነው፡፡ በተለይ የመቂ ወንዝ ከዚህ ቀደም ክረምትና በጋ ይፈስ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን የውሃው መጠንና ፍሰት ቀንሶ ወደ መድረቅ ደረጃ መድረሱን አቶ ረድኤት ጠቁመዋል፡፡

የእነዚህ ዝርያዎች መጥፋት የአካባቢ ጥበቃን የሚጐዳና በዓለም አቀፍ ደረጃ በብቸኝነት የሚታወቁና በዓለም የተፈጥሮ ሃብትነት የሚታወቁ የአሣ ዝርያዎች እንዲጠፉ የሚያደርግ በመሆኑ የምርምር ማዕከሉ እነዚህን በመጥፋት ላይ ያሉ የአሣ ዝርያዎችን በማዕከሉ ለማራባት ቢሞክርም ወራጅ ውሃ የሚያስፈልግ በመሆኑ ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ዝርያዎቹን ለማዳን በዓለም አቀፍ ደረጃ መስራት የሚያስፈልግ  በእነዚህ ዝርያዎች ዙሪያ ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያዎች "ሬድ ሊስት" በሚባለው ዓለማቀፋዊ መዝገብ ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ሬድሊስት በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎችን በመመዝገብ ዓለም አቀፍ እገዛ ማስገኘት የሚያስችል በመሆኑ ምዝገባው እንዲሳካ በማድረግ ሊገኝ በሚችለው ገንዘብ ዝርያዎቹ እንዲበራከቱ ይደረጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ዝርያዎቹ በአጭር ጊዜ የሚጠፉ መሆኑን ተመራማሪው አመልክተዋል፡፡

አሣ በተፈጥሮው የሚራባውና እንቁላሉን የሚጥለው በውሃ አካላቱ ዳርቻ ላይ በመሆኑና ለመስኖ የሚጠቀሙ ሰዎች ይህንን የአሣ እንቁላል መራቢያ ቦታ ስለሚጐዱት ዝርያው ለማራባት እንዳይቻል አድርጐታል፡፡ በመቂ አካባቢ ደግሞ ከፍተኛ አሸዋ የሚመረትበት በመሆኑ ይህንን ምርት ለመሰብሰብ ሲባል የአሣዎቹ እንቁላሎች እንዲጠፉ እየተደረገ ነው፡፡

በጣና ሐይቅ ያሉ ዝርያዎች መመናመን ደግሞ በተለየ መልኩ የሚታይ ነው ያሉት ተመራማሪው ዝርያዎች እንቁላላቸውን የሚጥሉት ከሐይቁ ወጥተው ወደ ሐይቁ በሚገቡ ወንዞች ዳርቻ በመሆኑና የመራቢያ ጊዜያቸውም (ብዙውን ጊዜ ነሐሴ ወር ላይ ነው) ወደ ወንዞቹ እያመሩ የአካባቢው አስጋሪዎች ስለሚያጠምዷቸው ዘር ሳይተኩ እንዲጠፉ እየተደረጉ ነው፡፡   

ይህንን ችግር የክልሉ ግብርና ቢሮ እንዲያውቀው ተደርጎ ችግሩን ተገንዝቦ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም አሁንም ያልተገባ የማስገር ሥራ እየተሠራ በመሆኑ እነዚህ ዝርያዎቹ አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡

በዳዊት ታዬ
 
< Prev   Next >