| አንድ ኩንታል ሲሚንቶ 300 ብር ገባ |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
|
ከአንድ ዓመት በላይ ተረጋግቶ የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ ተመልሶ ማሻቀብ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ ሦስት መቶ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የሲሚንቶ መሸጫ መደብሮች ይይዙት የነበረው የሲሚንቶ መጠንም ቀንሷል፡፡
በአንዳንድ ሲሚንቶ መሸጫ መደብሮች ሰሞኑን ባደረግነው ቅኝት በአብዛኛው በሽያጭ ላይ ያለው ሲሚንቶ በአገር ውስጥ የሚመረት ቢሆንም በተለይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዋጋው ከ280 እስከ 300 ብር ሊደርስ ችሏል፡፡ አብዛኛዎቹ የሲሚንቶ መደብሮች ቀደም ብለው ይይዟቸው የነበሩት ከውጭ የሚገቡ የሲሚንቶ ምርቶች እንደጨረሱና የአገር ውስጥ ሲሚንቶ በበቂ መጠን እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡ የሲሚንቶ ነጋዴዎቹ እንዳሉት ለሲሚንቶ ዋጋ መጨመር ምክንያቱ ከውጭ ይገቡ የነበሩ የሲሚንቶ ምርቶች እንዳይገቡ በመደረጋቸው ነው፡፡ ሲሚንቶ ከውጭ እንዳይገባ በመንግሥት መከልከሉ እንደተነገረ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ አንዱ ኩንታል እስከ 190 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ አሁን ግን በአንድ ጊዜ ከአንድ መቶ ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ከአንድ አመት ተኩል በፊት ወደነበረው የሲሚንቶ ዋጋ እየተመለሰ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ብዙ ነጋዴዎች በአገር ውስጥ የሚመረተውን ሲሚንቶ በቀጥታ ከፋብሪካ ማግኘት የሚያዳግታቸው በመሆኑ ለሲሚንቶ መወደድ ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ሣሪስ አካባቢ በአንድ ሲሚንቶ መሸጫ መደብር ያገኘነው የሽያጭ ሠራተኛ እንደነገረን ከሆነ ደግሞ ከውጭ የሚገባው ሲሚንቶ ከመከልከሉ በፊት የፈለጉትን ያህል ሲሚንቶ ስለነበር አንዱን ኩንታል እስከ 150 ብር ይሸጡ ነበር፡፡ አሁን ግን ከፋብሪካው በ140 ብር የሚሸጠው ሲሚንቶ ነጋዴው እጅ ሲደርስ ከሁለት መቶ ብር በላይ ሆኗል፡፡ ይህ ሰሞኑን የተከሰተው ዋጋ ከእጥረት ጋር ተያይዞ ዋጋው ሊወጣ መቻሉን እንጂ የሲሚንቶ ነጋዴዎች የፈጠሩት ችግር እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስጋት የሆነው የዋጋው መወደድ ብቻ ሳይሆን እጥረቱም ጭምር ነው ያሉት እኚሁ የሽያጭ ሠራተኛ በፊት ሱቁ ሙሉ አሁን በእጃቸው ላይ ያለው የሲሚንቶ መጠን ከሁለትና ከሦስት ቀናት በላይ የሚቆይ እንዳልሆነም ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት በማምረት ላይ የሚገኙት የሙገር፣ የመሶቦና ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካዎች አመታዊ የምርት መጠናቸው 1.6 ሚሊዮን ቶን ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያለው የሲሚንቶ ፍላጎት የሚያሟላ ነው፡፡ ከሲሚንቶ እጥረት ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ 24 የሚሆኑ ኩባንያዎች የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 13 የሚሆኑት አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወደ ማምረት ሥራ በመግባት ላይ ናቸው፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ ግርማ ብሩ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም እነዚህ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሥራ ሲጀምሩ የተፈጠረው እጥረት እንደሚቀንስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በዳዊት ታዬ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |