| የፋሲካ ገበያ ቅኝት በከፊል |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
መጪውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ባደረግነው የገበያ ቅኝት ለበዓሉ ከሚሸመቱ እቃዎች ሁሉ የቅቤ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱንና የዘንድሮው የአውደ ዓመት ገበያ ቀዝቃዛ እንደነበር ለመረዳት ችለናል፡፡ሰኞና ማክሰኞ በተለያዩ የአዲስ አበባ ገበያ ሥፍራዎች ተዘዋውረን እንዳየነው አንድ ኪሎ ቅቤ እስከ ዘጠና ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ሦስት ሊትር ዘይት 62 ብር የገባ ሲሆን ይህ ዋጋ ከሦስት ወራት 44 ብር ነበር፡፡ ሸኖ ለጋ ያሉ የታሸጉ የአትክልት ቅቤ ዋጋቸው ወደ 32 ብር አሸቅቧል፡፡ ባለፈው ሳምንት 50 እና 60 ብር ይሸጥ የነበረው ቅቤ በዚህ ሣምንት ከ85 እስከ 90 ብር የመድረሱ ምክንያት የአቅርቦት እጥረት እንደሆነ በሳሪስ በቂርቆስና በሾላ ገበያ ያነጋገርናቸው የቅቤ ነጋዴዎች ገልፀውልናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ድርቅ ስላለ የአቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ መገደዳቸውን በሳሪስ ገበያ የቅቤ ነጋዴ ወ/ሮ ታደለች ነግረውናል፡፡ የቅቤ ዋጋ መጨመር ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ገጠር የተጠራቀመ በቂ ቅቤ ባለመኖሩ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ የአንድ ኪሎ ግራም የሸኖ ቅቤ ዋጋ 85 ብር ሲሆን ካለው ፍላጎት አንፃር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የቅቤ ነጋዴ አቶ እንደነገረን፣ በሳል 65፣ መካከለኛ የጎጃም ለጋ 75 የሸኖ ቅቤ 85 ብር ገብቷል፡፡ ዋጋ ሳይጨመር ገዝቶ የመያዝና በችርቻሮ የመሸጥ ሂደት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ቅቤ ለመግዛት በአካባቢው ሲዘዋወሩ ያገኘናቸው ወ/ሮ እማዋይሽ የቅቤ ዋጋ 90 ብር ሆነ ሲሏቸው እግረ መንገዳቸውን ለማጣራት መምጣታቸውንና ከልጃቸው በሚያገኙት እገዛ እንደሚኖሩና ባለፈው ዓመት በላከላቸው ገንዘብ እንደ አቅማቸው ዶሮና ቅቤ መግዛታቸውን አስታውሰው ዘንድሮ ግን የሚቻል እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡ በዚሁ የሳሪስ ገበያ ዶሮ ሲገዙ አግኝተን ያነጋገርናቸው ወይዘሮ “ቅቤ ለእኔ የቅንጦት በመሆኑ አልገዛም” ብለውናል፡፡ ቅቤ ሲገዙ ያገኘናቸው ወ/ሮ ገነት ደግሞ በሰፈራቸው በጣም ተጋኖ ቅቤ 100 ብር ገባ ተብሎ እየተወራ በ85 ብር መግዛታቸውን ነግረውናል፡፡ ሌላ የተመለከትነው የዶሮ ገበያ ሲሆን ዶሮ ሲሸጡ ያገኘናቸው አቶ ተስፋዬ ሐሳስ የዶሮ ዋጋ ከ30 ስከ 45 ብር እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ ሰው ደፍሮ መግዛት አልፈለገም በዓል እስኪደርስ ዶሮዎቹ ላይቆዩ ይችላሉ በሚል ሥጋት ብዙ ገበያ እንደሌለ ነግረውናል፡፡ ባለፈው ሳምንት ዶሮ እስከ 25 እና 30 ብር ሲሸጥ እንደነበር አሁን ግን ለበዓሉ ዋጋ የሚጨምርበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመውናል፡፡ በበዓል ጊዜ ሁሉም ለንግድ ወደ ገበሬው ስለሚሄድ ካለው ፍላጎት አንፃር ዋጋ እንደሚጨምር የነገረን የዶሮ ነጋዴ መላኩ ረታ ነው፡፡ ባለፉት ሳምንታት አንድ ኪሎ ሽንኩር እስከ 1 ብር የሚሸጥበት ሁኔታ ተቀይሮ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ 2.25 ገብቷል፡፡ ይህን አስመልክተን ያነጋገርናቸው ነጋዴ ወ/ሮ ባየች አማረ የሽንኩርት ዋጋ ላይ ጭማሪ ማሳየቱን፣ እስከ በዓሉ ከዚህ የበለጠ ሊጨምር እንደሚችል አስረድተውናል፡፡ ዋጋው በየእለቱ የሚቀያየርበት እንዳለ የገለፁልን ሌላኛው ነጋዴ የሽንኩርትና የቲማቲም ዋጋ በየእለቱ በገባው ምርት የሚወሰን ሲሆን ነጋዴዎች ከገጠር ብዙ ምርት ካገኙ ዋጋ እንደሚቀንስና ዋጋው ምክንያት በማድረግ ብቻ ሳይሆን በአቅርቦቱ መጠን የተወሰነ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ በሾላ ገበያ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች እንዳሉት የበግ፣ የፍየልና የቅቤ ዋጋ ሲጨምር የዶሮ ዋጋ ግን ጥሩ ነው፡፡ በበግና ፍየል ተራ ያነጋገርነው ወጣት ተከስተ እንደገለፀው ቅጥቅጥ በግ እስከ 1"600 መቶ ብር፣ ትንሽ ከ200-250 የሚሸጥ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከነበረው የቅጥቅጥ በግ ዋጋ የዘንድሮው ከ200-300 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ተናግሯል፡፡ የፍየል ሙክት (ቅጥቅጥ) እስከ 1000 ሺህ ብር፣ አነስተኛ (ወጠጤ) ከ500 - 600 ይሸጣል፡፡ በሾላ ገበያ ለረጅም ዓመታት በበግና ፍየል አሻሻጭነት የሚሰራው ተከስተ እንደተናገረው በጎቹና ፍየሎቹ ከሚመጡበት ቦታ አንፃር ዋጋቸው መጨመሩ እና የትራንስፖርትና የማሳደሪያ ወጪ መጨመር የዋጋ ለውጥ ማስከተሉን ተናግሯል፡፡ በጎቹ የአርሲ፣ የወሎ (ደሴ"፣ የሐረርና የወላይታ ተብለው የሚሸጡ ሲሆን በቁመናና በስጋ ይዘት የወላይታው ተላፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፡፡ እኛ በተዘዋወርንባቸው ቀናት በበርበሬና ቅመማቅመም ላይ የዋጋ ለውጥ አልታየም፡፡ አንድ ኪሎ በርበሬ 42 ብር ይሸጣል፡፡ በቤዛዊት ሥዩምና በአዜብ መሐሪ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |