| ሊበላ? |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
|
ጋብሮቮዬው ሶፊያ ከተማ ባቡር ጣቢያ ሲደርስ መሽቶ ነበርና ጋሪ ጠርቶ “ከክቡናር ሠፈር አድርሰኝ” ብሎ ይሳፈራል፡፡
“ይኸ ከርፋፋ ጋሪ ሲሳፈር ዋጋ እንኳን አይነጋገርም? ቆይ እንክት አድርጌ እበላው የለ?” እያለ ወደ ታዘዘበት ሥፍራ ሸመጠጠ ባለ ጋሪው፡፡ ከክቡናር አካባቢ ሲቃረቡ ጋብሮቮዬው “ጉድ ሆንኩ ጃል! አንዴ አቁምልኝ” ሲል ጮኸ፡፡ ከጋሪው ክብሪት ፍለጋ ኪሶቹን እየዳበሰ “በሰው ስስቅ በኔው ይድረስ? ወቸ ጉድ" የወርቅ ጊኒዬ (ዐሥር ብር የወርቅ ሳንቲም) ተንከባላ መቀመጫው ሥር ገብታለች፡፡ አንዴ ታገሠኝ ልፈልጋት” አለ፡፡ ይኸኔ ጋሪ ነጂው ፈረሱን ሾጥ አድርጎ ሸመጠጠ፡፡ ጋብሮቮዬውም ብቻውን እየሳቀ አቅጣጫውን ለውጦ ሄደ፡፡ (ዐረፈ ዓይኔ ሐጐስ፣ ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር (ትርጉም)፣ 1979) ዶሮ በ1979 ዓመቱን ሙሉ እንቁላል የጣለች ዶሮ አሜሪካ ውስጥ ነበረች፡፡ ይህችው በሚሶሪ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚተዳደረው የግብርና ኮሌጅ ዕርባታ ውስጥ የነበረችው ዶሮ በተጠቀሰው ዓመት 371 እንቁላሎች ጥላለች፡፡ ዶሮይቱ በዚያው ዓመት ለአንድ ቀን ሳታስተጓጉል መጣል ብቻ ሳይሆን በስድስቱ ቀናት ውስጥ ሁለት ሁለት ዕንቁላል ጥላለች፡፡ የእንግሊዟ ዶሮም በ1957 በ365 ቀናት ውስጥ 353 እንቁላል ጥላለች፡፡ ይህችኛዋ በዓመቱ ውስጥ እንቁላል ያልጣለችባቸው ቀናት 12 ብቻ ነበሩ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በአንድ እንቁላል ውስጥ ሁለት አስኳል ሊያጋጥማችሁ ይችላል፡፡ እንቁላሉ ጤናማ አይደለም ብላችሁ ሳትፈሩ እንክት አድርጋችሁ ብሉት፡፡ የአስኳሉ ቁጥር ከዚያም በላይ ቢሆን መደንገጥ አያስፈልግም፡፡ ዘጠኝ አስኳል ያላቸው እንቁላሎች በኒውዮርክና ኪርጊዝያ በተባለችው የሶቭዬት ክፍለ ሀገር ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ ሁለት ኰፈን ያለው እንቁላልም አልፎ አልፎ ያጋጥማል፡፡ (ሻለቃ አባይነህ አበራ፣ ጭላሃ ወግ (ትርጉም)፣ 1981) አውሮፕላን በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ አቪዬሽን የተጀመረው ንጉሥ ተፈሪ ከገዟቸው ሦስት ፈረንሳይ ስሪት ፓቴዝ አይሮፕላኖች አንደኛዋን ፈረንሳዊው ሙሴ አንድሬ ማዮ ከጅቡቲ በማብረር ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ሥጋ ሜዳ አውሮፕላን ማረፊያ ከቀኑ 7፡10 ደቂቃ ላይ ባሳረፈበት ወቅት ነው፡፡ አይሮፕላኗም ንሥረ ተፈሪ ተብላ ተሰየመች፡፡ ጅቡቲ ቀርተው የነበሩትን ሁለቱን ፓቴዝ አይሮፕላኖች አንዷን ካፒቴን ማዮ፤ ሁለተኛዋን ደግሞ ጀርመናዊው ካውንት ሼዝበርግ እየበረሩ መስከረም 12 ቀን 1922 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አመጧቸው፡፡ እነዚህም አውሮፕላኖች ከመጡ በኋላ የተሰጣቸው ስያሜ የሁለተኛዋ ፓቴዝ አውሮፕላን ንሥረ አስፋ ወሰን የሦስተኛዋ ፓቴዝ አውሮፕላን ደግሞ ንሥረ መኮንን ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ሕዝቡ አዲሱን የቴክኖሎጂ ውጤት እንዲህ በማለት ተቀበለው “አውሮፕላን መጣ ሰማይ ለሰማይ የተበደለውን ደሃውን ሊያይ” የኢትዮጵያ አየር መንገድ መስከረም 1 ቀን 1939 ዓ.ም ባለቤትነቱ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ በመሆን ቲ.ደብልዩ.ኢ ከተባለው የአሜሪካ አየር መንገድ ኩባንያ ጋር ውል በመፈራረም ጠቅላላ አስተዳደሩን ቲ.ደብልዩ.ኤ እንዲመራው በ1,000,000 የአሜሪካ ዶላር (በወቅቱ በ2,500,000 ብር) ካፒታል ተመሠረተ፡፡ በወቅቱም የመጀመሪያው አየር መንገድ የበላይ ቦርድ ፕሬዚዳንት ፊታውራሪ ታደሰ ሀብተ ሚካኤል ሲሆኑ፣ የመጀመሪያው የአየር መንገዱ አስተዳዳሪ ደግሞ አሜሪካዊው ካፒቴን ሆሎዌይ ይባላሉ፡፡ አየር መንገዳችን መጋቢት 30 ቀን 1939 ዓ.ም በይፋ ሥራውን የጀመረ ሲሆን አየር መንገዱ ሥራውን የጀመረባቸው አውሮፕላኖች ዲሲ 3 የተባሉት ሲሆኑ በቁጥርም 6 ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ የበረራ ሥራውን በዲሲ 3 የጀመረው በአገር ውስጥ በረራ ሲሆን በረራው ከአዲስ አበባ በመነሳት የተደረገባቸው ከተሞች ጎንደር፣ ደብረማርቆስ፣ ድሬዳዋ፣ ጅማና ጎሬ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ አንዳንድ ጣቢያዎች ላይ ሠራተኛ እስከሚቀጠር ተሳፋሪው የሚከፍለው ለፓይለቶቹ ነበር፡፡ ከአየር ኃይል ወደ አየር መንገድ ግንቦት 15 ቀን 1943 ዓ.ም የተዘዋወሩት የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን ፓይለት መኮንኖች ዓለማየሁ አበበ፣ ጋዲሳ ጉማ፣ አሰፋ አየለና ግርማ በዳኔ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የአየር መንገድ ጄት አብራሪ የሆኑት ካፒቴን አለማየሁ አበበ ናቸው፡፡ ጊዜውም ታህሳስ 1949 ዓ.ም ነው፡፡ እኚህ ሰው ከአፍሪካም የመጀመሪያ የንግድ ጄት አብራሪ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ (ቴዎድሮስ በየነ፣ ኅብረ ኢትዮጵያ፣ 1999) የሚንሳፈፍ ቤት በኔዘርላንድስ ያለው የመሬት ስፋትና በየዕለቱ የሚጨምረው የሕዝብ ብዛት ሊመጣጠን ባለመቻሉ የሀገሪቱ አርክቴክቶች ቤት የመሥሪያ ቦታ ይሆናሉ የሚሏቸውን ማናቸውንም አማራጮች እየተጠቀሙ ነው፡፡ የሀገሪቱ ዜጎችም አርክቴክቶቹ በሚነድፉላቸው ዲዛይን መሠረት በሐይቅና በውቅያኖስ ጠረፎች፣ በወንዞች ዳርቻ፣ ከባሕር ጠለል በታች በመሳሰሉት ቦታዎች ሁሉ ቤት ይሠራሉ፡፡ በቅርቡ በኢንጂነር ፍሪትስ ሹውት የተሠራው ቤት ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት የአሠራር ዘዴዎች ለየት ያለና በውሃ ላይ የሚንሳፈፍ ነው፡፡ የቤቱ መሠረት የተሠራው ክፍት ከሆነ ኮንክሪት ሲሆን ይህም በባህር ውስጥ የሚፈጠረውን ሞገድ ተቋቁሞ እንደመርከብ እንዲንሳፈፍ ይረዳዋል፡፡ ቤቱ በቀላሉ በንፋስ ወይም በባህር ሞገድ እንዳይወሰድ ከባህር ዳርቻ ወይም እዚያው ባሕር ውስጥ በትላልቅ የብረት ሰንሰለቶች ወይም ኬብሎች አማካኝነት ከሚተከል ነገር ጋር እንዲታሠር ተደርጓል፡፡ ይህንኑ ቤት ለማሞቅና የባሕሩን ውሃ ለመጠጥነት ለማጣራት ኢንጂነሩ ከንፋስና ከባሕር ሞገድ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡ ቤቱ ኢኮቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በቱሪስቶችና በሀገሪቱ ዜጎች ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ (ሥነ ምግባር፣ መጋቢት 2000) ጨዋታ ገዴ አሞራ እርሷ ያልገደለችውን ሥጋ አትበላም፡፡ መልካምም ሰው ያለገንዘቡ አይነካም፡፡ ረሃብ ውሎውና አዳሩ ከማነው ሥራ ከማይወድ ከኩሩ ሰው ጋር ነው፣ ጥጋብ ውሎውና አዳሩ ከማነው ከሠራተኛና ከቸር ሰው ጋር ነው፡፡ ሰይጣንስ አዳሩና ውሎው ከማን ጋር ነው ከልበ ጠማማና ከዕቡይ ሰው ጋር ነው፡፡ ካለውና ከሞተው ሰው ማን ይበልጣል፣ ስግብግብ ሰው ለመብል የሚጣደፍ ሆዱ አምላኩ ነውና ታላቅ ጉርሻ ጎርሶ አንቆት ወይም ሆዱን ነፍቶት ቁንጣን ይገድለዋል፡፡ (ዘነብ ኢትዮጵያዊ፣ መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ መንፈሳዊ፣ 1957) አቢሲኒያ ባንክ በ1905 ዳግማዊ ምኒልክ ከግብፅ ብሔራዊ ባንክ ጋር ባደረጉት ውል መሠረት የአቢሲኒያ ባንክ ተቋቋመ፡፡ ባንኩ በወቅቱ ዋና የንግድ ማዕከላት በነበሩት በድሬዳዋ፣ በደሴ፣ በጋምቤላ፣ በጎሬና በሐረር ቅርንጫፎች ነበሩት፡፡ የወረቀት ገንዘብ ታተመ በ1931 በግብፅ ብሔራዊ ባንክ ባለቤትነት ስር የነበረው ባንክ ፈርሶ በምትኩ የኢትዮጵያ ባንክ (Bank of Ethiopia) ተቋቋመ፡፡ ይህ ባንክ የወረቀት ገንዘብ አትሞ ነበር፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝና በስፋት አገልግሎት ላይ እንዲው"ል ማድረግ አልቻለም፡፡ (ተፈራ ደግፌ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች መጽሔት) ገራገር ቻይናዊው በበረዶ ውስጥ በመቆየት ሪከርድ ሰበረ የ43 ዓመቱ ቻይናዊ ዋንግጂንቱ ደቂቃ በበረዶ ገንዳ በመቆየት የተያዘውን ሪከርድ መስበሩን የሌጋል ኢቭኒንግ ፖስት አስታወቀ፡፡ አንድ ሰዓት ከ13 ደቂቃ በመቆየት በሮችማን ዊም ተይዞ የነበረውን የቀድሞ ሪከርድ ያሻሻለው ዋንግ ከ90 ደቂቃ ቆይታ በኋላ ለመቆም ዕርዳታ ቢያስፈልገውም ለተመልካቾቹ ሰላምታ ለመስጠት ግን ችሏል፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ቅዝቃዜን ይቋቋማል ያለችው የዋንግ ልጅ በቀዝቃዛ የክረምት ወቅት እንኳ አጫጭር ቁምጣዎችን እንደሚለብስ ገልፃለች፡፡ ታዳጊው የጭነት መኪና በማስነሳት ሑከት ፈጠረ የስምንት ዓመት ታዳጊ ባንስሻየር ውስጥ የቆመ የጭነት መኪናን በማስነሳትና በመንዳት ሁከት ፈጥሮ እንደነበር ዘሰን ዘግቧል፡፡ ታዳጊው የጭነት መኪናውን ሊያንቀሳቅስ የቻለው መኪናውን በመኪና ማቆሚያ ክልል ውስጥ ቁልፉ እላዩ ላይ ተንጠልጥሎ በመመልከቱ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በሰጡት ጥቆማ ታዳጊው በፖሊስ ሊያዝ መቻሉንና አንድ የስምንት ዓመት ታዳጊ መኪና በማንቀሳቀስ አካባቢ ይረብሻል ብሎ መገመት ከባድ መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣን ኒጌል ኢቫንስ ተናግረዋል፡፡ የናይት ክለብ መርቀው የከፈቱት ቄስ ተወቀሱ ስቱዲዮ 74 በመባል የሚጠራውን ናይት ክለብ በመመረቅ የከፈቱ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቄስ ወቀሳ ደረሰባቸው፡፡ በቺበያቢንስክ ከተማ ውስጥ የተከፈተውን ስቱዲዮ 74 መርቀው የከፈቱት ቄስ ኒስባይ ክለቡ የባሌት ዳንስ መማሪያ ነው ተብሎ በባለቤቶቹ ስለተነገራቸው እንጂ ናይት ክለብ መሆኑን እንዳላወቁ ገልፀዋል፡፡ የስቱዲዮ 74 ቃል አቀባይ አና አስማኖቫ በበኩላቸው ክለቡ ከተከፈተ ጀምሮ የሚመጡ ተስተናጋጆች የተለያየ የሚያስደስት ቦታ መሆኑን በተደጋጋሚ እንደሚገልፁ በመጠቆም የቄሱ ምረቃ ሳይጠቅም እንዳልቀረ ተናግረዋል፡፡ የዓለም ትንሹ ስዕል አንድሪው ኒኮላስ የተባለ የሀምፕ ሻየር አርቲስት በዓለም የመጨረሻውን ትንሽ የሞናሊዛ ስዕል መሳሉ ታወቀ፡፡ በዚህ አርቲስት የተሳለው የሞናሊዛ ስዕል መጠን ከቴምብር አንድ አራተኛ እንኳን ያንሳል፡፡ ስዕሉ አስራ አንድ ሚሊ ሜትር ርዝመትና ሰባት ሚሊ ሜትር ስፋት እንዳለው ታውቋል፡፡ “ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ትናንሽ ስዕሎችን ሥሠራ ቆይቻለሁ፡፡ ይህ የሞናሊዛ ስዕል ግን አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር” ብሏል አንድሪው ኒኮላስ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |