| የሕዝብን ምርጫ ካላካተትክ ዘፈን... |
|
| Wednesday, 09 January 2008 | |
|
የሕዝብን ምርጫ ካላካተትክ ዘፈን ለራስህ ብቻ ይሆናል ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው፡፡ ..ጋዜጠኛው.. በሚለው ነጠላ ዜማው የሙዚቃ ህይወትን ተቀላቀለ፡፡ ..የጐረቤት ልጅ..ና ..ኰከብ አይን.. የተሰኙ ዜማዎችን ያካተተ የመጀመሪያ አልበሙን ከለቀቀ በኋላ በ1995 እና በ1997 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የኮራ ውድድር በእጩነት ቀርቧል፡፡ በአዲሱ ሥራው ዙሪያ አነጋግረነዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ለአልበምህ ርዕስ ..ቅዳሜ..ን ለምን መረጥክ? ቴዎድሮስ፡- ቅዳሜ ጥሩ የእረፍት ቀናችን ነች፡፡ የከተማ ልጆችም ብቻ ሳይሆን ገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎችም ቢሆኑ ቅዳሜን ከእሑድ በላይ የሚዝናኑበት ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለከተሜዎች ቅዳሜ ልዩ ነች፡፡ በውጭው ዓለም ደግሞ እጅግ በጣም የተከበረች ቅዳሜ ነች፡፡ ከአርብ ምሽት ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ያለው ጊዜ በጣም የሚወደድ ነው፡፡ ያ ስሜት በእኔ ውስጥም አለ፡፡ ቅዳሜን በጣም እወዳታለሁ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ቅዳሜ ጧት የምትወጣውን ፀሐይ ከሌሎች ቀናት የበለጠ እወዳታለሁ፡፡ ቅዳሜ ለእኔ ብሩህ ናት፡፡ ተማሪ ሆነህ ወደ ት/ቤት የማትሄድበት ቀን ነው፡፡ በሥራ አለም ውስጥ ከሆንክም ከሥራ ወደ እረፍት የምትሄድበት ቀን ነው፡፡ እሑድም የእረፍት ቀን ቢሆንም የምታስበው ወደ ሥራ መሄድህን በመሆኑ ስሜቱ ያን ያክል አይደለም፡፡ ለዘፈኔ ርዕስ የመሆኑ ምክንያት ይኸው ነው፡፡ ቅዳሜን እንደኔና ጓደኞቼ የሚወዱ ሁሉ ለምን እንደኛ እኩል ስሜት አይኖራቸውም በሚል መነሻ ነው ስለቅዳሜ ተፅፎ ዜማ የተሠራውና የአልበሙ ርዕስ እንዲሆንም የተመረጠው፡፡ ሪፖርተር፡- ቅዳሜ ዕለቱ ብቻ ሳይሆን የተዘፈነላት እንስትም አለች፡፡ የፍቅር ዘፈን ነው ማለት አንችልም? ቴዎድሮስ፡- ብዙም የተጋነነ አይደለም፡፡ ለቀኗ እንጅ ለሴት (ለፍቅር) አይደለም የተዘፈነው በአብዛኛው፡፡ ማንም ጥንድ ቅዳሜ በመጣ ቁጥር የሚዝናናው ብቻውን አይደለም፡፡ ከፍቅረኛው ጋር ብዙ ይዝናናል፡፡ ባለ ጥንዱ ቅዳሜን ሲያስብ በውስጡ የሚያስባትን አብሮ እንዲያዜምላት ታስቦ የተገጠመ ግጥም ነው እንጂ ለፍቅር ተብሎ የተዘፈነላት የለችም፡፡ ሪፖርተር፡- በካሴትህ ለፍቅሯ የዘፈንክላት እንስት የለችም? ቴዎድሮስ፡- እንዴታ አለች እንጂ.. ..እድለኛው ልጅ.. የሚለውን ብንወስድ የራሴና የባለቤቴ ታሪክ ነው፡፡ ..የእኔ ፍቅርም.. ለእሷ ነው፡፡ በተለይ ..እድለኛው ልጅ.. የሚለው የእኔና የእሷ የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በካሴት ሥራህ ላይ የነማን አስተዋፅኦና እጅ አለበት? ቴዎድሮስ፡- አበጋዝ ክብረ ወርቅ ስድስት ዘፈኖችን፣ ኤልያስ መልካ አምስቱን፣ ዳግማዊ አሊ ሶስቱን ኪሩቤል ደግሞ አንድ አቀናብረዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ግጥምና ዜማ ግን አብዛኛው የአንተ ሥራ ነው? ቴዎድሮስ፡- አዎ በዜማና ግጥም ከ80 በመቶ በላይ እኔ ነኝ የሠራሁት፡፡ በቀሪዎቹ ላይ ነው ሌሎች የተሳተፉት፡፡ ..ቅዳሜ..ን ግጥሙን እኔ ነኝ የፃፍኩት፡፡ ዜማውን ኤልያስ በማሻሻል አግዞኛል፡፡ ..እንዳጣሁሽ.. የሚለውን ዘፈን ግጥሙን የፃፈችው ስመኝ ግዛው ነች፡፡ ዜማውን እኔ ነኝ የሠራሁት፡፡ ..ወርቁን ዜማ.. ግጥሙንም ዜማውንም የሠራው ኤልያስ መልካ ነው፡፡ ..እህቴ.. የሚለውን ፍቃዱ ገረመው ግጥሙን ፃፈው ዜማውን እኔ ሠራሁት፡፡ ..ናባርሲሲ.. የሚለውን ኦሮምኛ ደግሞ የፃፈው አድናን መሃመድ ነው፡፡ ኢቦኒና ቤቲ በፊውቸሪንግ ተሳትፈዋል፡፡ በተረፈ የእኔ ሥራዎች ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- በዜማና ግጥም የበርካታ አርቲስቶች ተሳትፎ የሌለው ለምንድን ነው? ቴዎድሮስ፡- አልተሳካም እንጂ ለተለያዩ የዜማና ግጥም ደራሲዎች፡፡ ብዙ ግብዣ አቅርቤያለሁ፡፡ በወቅቱ ምላሽ ካገኘሁበትም ቢሆን የምፈልገውንና የሚያረካኝን ያህል አላገኘሁም፡፡ ለነገሩ ከውስጥህ ከራስህ ፈልቆ የምትሠራውን የመሰለ የለም፡፡ እኔ ከስር ከስሩ ሄድኩበት፡፡ እንደ ቴዲ አፍሮ ሁሉንም መሥራት ቢቻል ጥሩ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ሥራ አንተ ብቻ ለመሥራት ምን ያህል ጊዜ ወሰደብህ? ቴዎድሮስ፡- በጣም ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ አልበም ካወጣሁ አራት ዓመት ተኩል አልፎኛል፡፡ ይህን ሥራ ከጀመርነው ወደ ሶስት ዓመት ተኩል ሆኖናል፡፡ ስቱዲዮ እንኳን ከተገባ ከሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ተሰርተው ያለቁት ወደ ሃያ አራት የሚጠጉ ሥራዎችን አዘጋጀን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተሻሉ ያልናቸውን አሥራ አምስት መርጠን ነው አልበሙን የሠራነው፡፡ ሥራው እጅግ አድክሞናል፣ ብዙ ጊዜና ገንዘብም ወስዶብናል፡፡ እውነቱን ለመናገር አልበም ማዘጋጀት አድካሚና ከባድ መሆኑን የተገነዘብከት በሁለተኛው ሥራዬ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ከመጀመሪያው ሥራህ ይህ በምን ይለያል? ቴዎድሮስ፡- የመጀመሪያው አልበሜ ከቤቴ እንደመጣሁ ስለሙዚቃው ዓለም፣ ስለሙዚቃ ገበያው፣ ስለሕዝቡ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ በአሁኑ ግን የሕዝቡን ስሜት ከማዳመጥ አኳያ የተሻለ ነገር ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያው አልበሜ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ የራሴን ስሜት ነበር ያወረድኩት፡፡ አሁን ግን የሙዚቃ አድማጩን ስሜት የሚያሟላና ..ማርኬተብል.. ሊሆን እንዲችል አስቤ ነው የሠራሁት፡፡ እንደገና ደግሞ በጣም ቀዝቀዝ ያለ፣ በጣም ፈጠን ያለ፣ በየዓይነቱ ለሁሉም ዓይነት አድማጮች የሚሆኑ ተካተውበታል፡፡ ከመጀመሪያው ለየት የሚልበት በመጀመሪያ አልበሜ የተሰጠኝን አስተያየት በመስማት ..የተለያዩ ዘፈኖችን.. ለማሟላት መሞከሬ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ገበያ ተኮር እንዲሆን ማሰብህ ፈጣን ዘፈኖችን እንድታበዛ ተፅዕኖ አድርጓል የሚሉ ወገኖች አሉ፤ ቴዎድሮስ፡- ሕዝቡ የሚፈልገውን ማካተት አለብህ፡፡ ሙዚቃ መተከዣ ብቻ አይደለም መዝናኛም ነው፡፡ የምታዝናናው ሕዝብ ደግሞ የሚፈልገውን ማግኘት አለበት፡፡ ብዙ ፈጣን ዘፈኖች አሉ ማለት አልችልም፡፡ የችክቸካና የእስክስታ ዘፈኖች ሁሌም ፈጣን ናቸው፡፡ በጣም ለስላሳ ዘፈኖች አሉ፡፡ ..ወዳጄ..ና ..የእኔ ፍቅር.. የሚሉት በጣም ለስላሳ ናቸው፡፡ ሌላው እንዲያጫውትና እንዲያንቀሳቅስ ታስቦ የተሠራ ነው ግን ሁሉም አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- የሕዝቡን ስሜት ላለማጣትና ገበያ ለማግኘት ማሰብህ በሥራው ላይ ተፅዕኖ የለውም? ቴዎድሮስ፡- ጥሩ ያደርገዋል፡፡ የሕዝብን ምርጫ ካላካተትክ ዘፈን ለራስህ ብቻ ይሆናል፡፡ የተለያየ የኅብረተሰብ ክፍልን ማሰብ አለብህ፡፡ በመጀመሪያው አልበሜ ይህ አልነበረም የራሴ ስሜት ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን አርሜዋለሁ፡፡ የሕዝቡን ስሜት ለማዳመጥ ሞክሬያለሁ፡፡ የምትዘፍነው ሰውን ለማዝናናት ነው፡፡ ስሜቱን ጠንቅቀህ ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ በውጪው ዓለም በጣም የተለመደ ነው፡፡ እነሱ እንዲያውም ጥናት አድርገው ነው የሚሠሩት፡፡ በእኛም ይሄ ሊለመድ ይገባል፡፡ መጨፈር ለሚፈልገው የሚያስጨፍር፣ ለስላሳ ለሚፈልገው ለስላሳ ዘፈኖች ሊኖሩ ያስፈልጋል፡፡ የእኔ የምትላቸውም ሊኖሩ ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- ገበያ ተኰር ሥራ አልሠራህም? ቴዎድሮስ፡- ..ማርኬት ኦሬንትድ.. ነው የሚባለውን ሥራ አገር ሲፈልገው ትሰማለህ፡፡ እንደዚያ ዓይነት ዘፈን ደግሞ ከአንድ ወር በኋላ መልሰህ አትሰማውም፡፡ ..ገበያ..ን የፈለገ ዘፈን በአብዛኛው እንደዚህ ነው የሚሆነው፡፡ የእኔ ዘፈን ግን አሁን እንደምናየው በጣም ጮሆ አይረብሽም፡፡ ..ማርኬት ኦሬንትድ.. አይደለም ማለት ነው፡፡ ቀስ እያለ እንደ መድሃኒት ደም ውስጥ እንዲገባ ነው የተዘጋጀው፡፡ ቀስ እያልክ የምትሰማውን ዘፈን በአጭር ጊዜ አትጥለውም ሁልጊዜ አብሮህ ይኖራል፡፡ የእኔ አልበም እንዲህ እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡ ..ቅዳሜ.. ሞቅ ስላለች አንዳንድ ሰዎች እንደዚያ ዓይነት ስሜት አድሮባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ አልበሙን በደንብ ያዳመጠ ሰው ግን ይረዳዋል፡፡ ሪፖርተር፡- በፍቅር ላይ ብዙ አተኩረሃል፤ ቴዎድሮስ፡- ጠንካራ ሃሳቦች የተነሱት በዚህ አልበም ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ..ሳልነግስ አልሞትም.. የሚለውን ማየት እንችላለን፡፡ ..እህቴ..፣ ..ይለወጣል ታሪኬ.. እና ..ወዳጄ.. በፍቅር አያተኩሩም፡፡ ከመጀመሪያው በርከት ያሉ ሌሎች ሃሳቦች በዚህ ተካተዋል፡፡ ቴዎድሮስ፡- እንደ ..ጋዜጠኛው..፣ ..ሳልነግስ አልሞትም.. የሚለው ዘፈን ሃይል አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ማለት ዙፋን እጨብጣለሁ ማለት ሳይሆን ኑሮን አሸንፈን ድህነትን አስወግደን በራሳችን በቤታችን የህይወታችን ጌጥ እንሆናለን ለማለት ነው፡፡ ወጣቱን ለማበረታታትና የእድገቴ ጌታ እኔ ነኝ እንዲል በአቅሙ በጉልበቱ ሰርቶ መሆን የሚፈልገውን እንዲሆንና ከተኛበት የሚያነቃ ዘፈን ነው፡፡ የስልጣን ኰርቻና ዙፋን ላይ መቆናጠጥ ብቻ ሳይሆን ራስን አሸንፎ በተደላደለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችል እውቀት መያዝን የሚጠቁም ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ..ይለወጣል ታሪኬ.. ብለሃል፤ ቴዎድሮስ፡- በአዲሱ ሚሌኒየም እንድንለወጥ ነው የፃፍኩት፡፡ አዲስ ዘመን በመሆኑ ለሚሌኒየሙ የሚሆን ዘፈን መዝፈን እንዳለብኝ አስብ ነበር፡፡ ወጣቱ አሳፋሪ የድህነት የኋላ ቀርነት፣ የተመፅዋችነትና በበሽታ የመመታት ታሪኰችን አስወግዶ አዲስ ታሪኩን የሚፅፍበት ክፍለ ዘመን መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ሁላችንም የሚገባንን ልናደርግ ይገባናል የሚል ቅስቀሳ ነው፡፡ በዚህኛው ዘመን የተሻለች ሀገር የተሻለ ኑሮ ሊሆን ይገባል፡፡ ስደት ታሪክ መሆን አለበት፡፡ በአምሳ ዓመት ውስጥ አብዛኛው የተማረና መሥራት የሚችለው ሕዝባችን በሰው አገር ተሰዶ የባዕድ አገር እያለማ ነው፡፡ ይሄ መሰረዝ አለበት፡፡ በዚህ ሚሌኒየም መቀየር አለብን የሚል ህልሜን ነው እዚያ ላይ ያሰፈርኩት፡፡ ቴዎድሮስ፡- የአቀናባሪው ምርጫ ነው፡፡ የእኔም ፍላጐት አለበት፡፡ ..ሪትሙን.. የመረጥኩት እኔ ነኝ፡፡ ቅንብሩ ላይ የብራዚሎችን ሳንባ እንዲሆን የመረጠው አቀናባሪው አበጋዝ ነው፡፡ እስኪ ኦሮምኛን በአዲስ ዓይነት ..ቢት.. እንሞክረው ለምን በተለመደው እንጠቀማለን በሚል ተዘጋጀ፡፡ የኢትዮጵያን የተለያዩ ዓይነት ዘፈኖች በተለያየ ዓይነት ..ሪትም.. መሞከር መልመድ አለብን፡፡ አዲስ ነገር ለማግኘት ሞክረን ከአድማጮች ጥሩ ምላሽ እያገኘንበት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በተለመደው የኦሮምኛ ..ቢት.. አልሞከራችሁትም? ቴዎድሮስ፡- አልሞከርነውም፡፡ ሪፖርተር፡- በዜማህ ሀገርኛ ለመጠቀም ሞክረሃል ግን... ቴዎድሮስ፡- አዎ አንች ሆዬ ብቻ ነው የሌለኝ እንጂ ትዝታን ጨምሮ ሌሎቹ አሉ፡፡ ሪፖርተር፡- ግን ዜማዎችን ተጠቅመህ ሀገርኛ የሙዚቃ መሣሪያዎችን አልተጠቀምክም፤ ቴዎድሮስ፡- ዘመናዊ ዘፈን በመሆኑ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች አልተጠቀምንም፡፡ ሪፖርተር፡- በዘመናዊ ዘፈኖች ውስጥ እንደ ማሲንቆና ክራር ያሉ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች እየገቡ እያዳመጥን አይደለም እንዴ? ቴዎድሮስ፡- የሙዚቃ መሣሪያዎቹን የመረጡት አቀናባሪዎቹ ናቸው፡፡ የእነሱ ምርጫ ነው፡፡ ዘፈኑም ይጋብዝሃል፡፡ አንዳንዴ የሰራኸው ዜማ በራሱ ማሲንቆ ወይም ክራር በገና ወይም ከበሮ የሚፈልገውን ይነግርሃል፡፡ በእኛ ሥራ ውስጥ ግን እነዚህን መሣሪያዎች ሊጠራ የቻለ ዜማ ባለመኖሩ ይመስለኛል ያልተጠቀምነው፡፡ ሪፖርተር፡- ለካሴትህ ምን ያህል ተከፈለህ? ቴዎድሮስ፡- ይህን መናገር አልፈልግም፡፡ ሪፖርተር፡- ለምን? ቴዎድሮስ፡- ሰው ሙዚቃውን መስማት (ማዳመጥ) ትቶ ይህን ያህል ያወጣል አያወጣም እያለ ሲሟገት ዘፈኑ እያለቀ ተቸገርን፡፡ ዘፈኑ ሲጀምርና ሰው ሙግት ሲጀምር እኩል ይሆንና ሙግቱ ሳያባራ ዘፈኑ ያልቃል፡፡ አርቲስቱ ለፍቶ ለፍቶ ሳይሰማና ሳይደመጥ እየቀረ ችግር መጥቷል፡፡ ስለገንዘብና ስለ ስንት ተሸጠ ባናወራ ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሰው ሙዚቃውን አዳምጦ ጥሩ ሥራ ተሠራ፣ ጥሩ አልተዘፈነም ብሎ ቢተች የተሻለ ነው፡፡ የሳንቲም ወሬ ዘፈኖች እንዳይሰሙ እያደረገ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |