Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow “ሕንፃዎች የሚበላሹት ሕንፃው ተጀምሮ...
“ሕንፃዎች የሚበላሹት ሕንፃው ተጀምሮ... Print E-mail
Wednesday, 23 April 2008
“ሕንፃዎች የሚበላሹት ሕንፃው ተጀምሮ እስኪጨረስ አርክቴክቱ በውስጡ ባለመኖሩ ነው”
አቶ ዘለቀ በላይ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር የተመሰረተው ኪነ ሕንፃን ለማሳደግ ሙያዊ መድረክ ለማመቻቸት፣ ስልጠናዎችን ለማበረታታትና ለመደገፍ፣ ጥናት ለማድረግ፣ ባህላዊ ህንፃዎችን ጠብቆ ለማቆየትና ለማሻሻል፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ዘርፉን ለማሳደግ አጠቃላይ የኪነ ሕንፃን ግንዛቤ ለማሳደግና የባለሙያውን የሙያ እድገት ለማስጠበቅ ነው፡፡ አቶ ዘለቀ በላይ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
    
አቶ ዘለቀ፡
- የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ሁለት ደረጃ አለው፡፡ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ሲመሰረት የኢትዮጵያ አርክቴክቶችና ሲቪል መሃንዲሶች አንድ ላይ ሆነው ነበር፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ አርክቴክቶችና ሲቪል ማሃንዲሶች ማህበር ነበር የሚባለው፡፡ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንደነበር ነው የምናስበው፡፡ ምክንያቱም አመሰራረቱ ላይ ትልቅ ሚና የነበራቸው አርክቴክቶቹ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ማይክል ቴዎድሮስም አርክቴክት ነበሩ፡፡ በኤክስኪዩቲቭ ደረጃም ብዙ አርክቴክቶች ሲሰሩ ነበር፡፡ በወቅቱ አርክቴክቶችና ሲቪል መሃንዲሶች ብዛታቸው አነስተኛ ስለሆነ በጋራ መመስረትን ነበር የመረጡት፡፡ ከ17 ዓመት በፊት ግን አርክቴክቶች ማህበሩን ለብቻቸው አቋቋሙ፡፡

ሪፖርተር፡- ከ17 ዓመት በፊት የአርክቴክቶች ማህበር ለብቻው ሲመሰረት ከመጀመሪያው የአላማ ልዩነት አድርጓል?

አቶ ዘለቀ፡-
ብዙ የአላማ ልዩነት ይኖራል አልልም፡፡ አርክቴክቸር ምንድነው? እሱን የሚሰሩት አርክቴክቶች እነማን ናቸው? የሚለው ላይ አተኩረን መስራት ነው የምንፈልገው፡፡ አርክቴክቸር የህንፃ ዘርፍ ነው፡፡ አርክቴክቶች የሚማሩትም ይህንኑ አርክቴክቸር (ኪነ ህንፃ) ብቻ ነው፡፡ በዲግሪ ለአምስት አመት በሚሰጥ ኮርስ በኪነ ህንፃ ይሰለጥናሉ፡፡ የማህበሩ አላማ አርክቴክቸር የሚባል ትምህርትን አርክቴክት የሚባል ሙያውን የሚተገብር ባለሙያ መኖሩን፣ ሰዎች በጅምላ መሃንዲስ ማለት እንደሌለባቸው ለማሳወቅ ነው፡፡ ሰዎች ቤት ለማሰራት ሲፈልጉ የሚያውቁት መሃንዲስ የሚለውን ቃል ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሙያ ትኩረት ሰጥተው ለብቻ የሚሰለጥኑ የተለዩ ባለሙያዎች ወይም አርክቴክቶች አሉ፡፡ ይህ አገልግሎት መኖሩን ለህብረተሰቡ ማሳየትና ህብረተሰቡም ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሙያው ሃላፊነት ነውና ይህንን ማሳወቅ አንዱ ስራችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቢዩልዲንግ (ግንባታ) የሚያጠኑት ከአርክቴክቶች በተለየ መልኩ ነው?

አቶ ዘለቀ፡
- በቢዩልዲንግ ዘርፍ የሰለጠኑት የሚሰማሩት ግንባታውን ለማከናወን ነው፡፡ አርክቴክት ንድፍን ይሰራል፡፡ ንድፍን ሕንፃ ለማድረግ የተለያዩ ባለሙያዎችን ያሳትፋል፡፡ እንደባለሙያ ሌሎቹን አሳትፎ ለህንፃው ቅርፅ የሚሰጠው አርክቴክቱ ነው፡፡ ሲቪል፣ ሳኒተሪ (ፍሳሽ) ኤሌክትሪክን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንጂነሮች አርክቴክቱ ለሚነድፈው ንድፍ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ እነዚህ አንድን ህንፃ እውን ለማድረግ የሚሰሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን የሚያስተባብረውና የህንፃው ራዕይ  ደግሞ አርክቴክቱ ነው፡፡ አንድ ሰው ቤት ሊያሰራ ሲፈልግም በህንፃው ውስጥ ሊካተት የሚፈልገውን ሥራ መግለጽ ያለበት ለአርክቴክቱ ነው፡፡ አርክቴክቱ የባለቤቱን ሃሳብ፣ የሚሰራበትን አካባቢ፣ የህብረተሰቡን አኗኗርና ተያያዥ ጉዳዮችን አገናዝቦ የባለቤቱን ፍላጎት ወደ ህንፃ ይቀይረዋል፡፡ አርክቴክቱ በሌሎች ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ስለሚያስፈልጉት ያማክራቸዋል፣ አገልግሎታቸውንም ይጠቀማል፡፡

ሪፖርተር፡- ሲቪል፣ ኤሌክትሪካልና ለህንፃ ዘርፍ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች አብረው ከአርክቴክቱ ጋር የሚሰሩ ቢሆንም አንድ ህንፃ ሲበላሽ ሁሌም ተወቃሹ አርክቴክቱ ነው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ከሆነ ለምን አርክቴክቱ ብቻ ይወቀሳል?

አቶ ዘለቀ፡
- መወቀስ ያለበት አርክቴክቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ንድፍ የአርክቴክቱ ሃሳብ ነው፡፡ አርክቴክቱ ትምህርቱን በሚያጠናበት ጊዜም ሆነ በስራ ላይ ሲሆን ስለእያንዳንዱ ህንፃ ጥልቅ ሃሳብና በቂ እውቀት ኖሮት ነው፡፡ ኤሌክትሪክ፣ ፍሳሽና የመሣሠሉት ሁሉ ለህንፃው ምን አይነት ሚና እንዳላቸው ያውቃል፡፡ በመሆኑም በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች የሚሰጡትን አገልግሎት አርክቴክቱ በሚፈልገው መንገድ ህንፃውን በማያበላሽ መልኩ ለህንፃው አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎችን አገልግሎት በማስቀመጥ የመጠቀም ሃላፊነት የአርክቴክቱ ነው፡፡ አርክቴክቱ የሌሎች ባለሙያዎና አገልግሎት በህንፃው ላይ ያለውን ተፅዕኖ ተረድቶ ንድፉን የማስተካከል ወይም ፍሳሽም ሆነ የኤሌክትሪክ አካሄዱ ለንድፉ አመቺ እንዲሆን ማድረግ ሃላፊነቱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ህንፃዎች ብዙ ጊዜ የሚበላሹት ለምንድን ነው?

አቶ ዘለቀ፡
- ህንፃዎች የሚበላሹት በብዙ ምክንያት ነው፡፡ ዋናው መንስዔ ግን አርክቴክቱ በህንፃው ሕይወት ውስጥ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ አለመኖሩ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ስህተቶች ይፈጠራሉ፡፡ የህንፃ ባለቤቶች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የህንፃውን ግንባታ በተለያየ መንገድ ወደራሳቸው ፍላጎት ወስደው በፈለጉት መንገድ ከሰሩ በኋላ የሰራልን እገሌ የተባለ አርክቴክት ነው፣ ያበላሸው እሱ/እሷ ነው/ናት ወደሚለው ይመጣሉ፡፡ አርክቴክቱ የሰራው ንድፍ በትክክል ስለመቀመጡ በግንባታ ወቅት ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ከተከታተለውና እድሉን ካገኘ የምናያቸው ስህተቶች አይኖሩም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደምናየው የህንፃ አሰሪዎች ንድፉን ከተቀበሉ በኋላ አርክቴክቶችን አይፈልጉም፡፡ አንድ ህንፃ ሲሰራ የንድፍ ባለቤት የሆነው አርክቴክት ስራውን እንዲያይም ሆነ በስራው እንዲሳተፍ የሚያደርግ ህግ አለ?

አቶ ዘለቀ፡-
ማህበራችን እየተንቀሳቀሰበት ያለው አርክቴክቱ በነደፈው ሕንፃ ግንባታ ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡ አንደ ባለሙያ ከትምህርት ቤት ወጥቶ የሚሰራው ብዙ ውስብስብ ስርዓቶች ያሉትን የህንፃ ንድፍ ነው፡፡ ሕንፃዎች ትክክለኛውን ባለሙያ አግኝተውን ተሠርተው ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ አልፎም ለአገር መኩሪያ እንዲሆኑ ለማድረግ የአርክቴክቱ ሚና ያስፈልጋል፡፡ የአርክቴክቱን ሚና ለማጉላት በመንግሥት የሚወጡ ሕጎች ያስፈልጋሉ፡፡ ህብረተሰቡ ያውቃል ተብሎ ብቻ ሳይሆን የማያውቃቸውንና የሚጠቅሙት ነገሮች በሕግ ተቀርፀው መግባት አለባቸው፡፡ ማህበሩ የሚያደርገው የህንፃ ሕግ በአገሪቱ ላይ እንዲኖርና ሕጉም አርክቴክቱን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሳይሆን የአርክቴክቱ አገልግሎት አስፈላጊ ስለሆነ ሕብረተሰቡ ከጥፋት እንዲድን ነው፡፡ አንድ ህንፃ ተነድፎ በባለሙያው ክትትል እንዲደረግበት የሚያስገድድ ግልፅ የሆነ  የለም፡፡ አንድ ሕንፃ በባለሙያ እንዲፈቀድ የማድረግ ሕግ ስላለ ለማስፈቀድ ባለሙያውን ይጠቀሙበታል፡፡ ወደ ግንባታ ሲኬድ አስገዳጅ ሕግ ባለመኖሩ ተገቢውን ባለሙያ ያለመጠቀም ሁኔታ አለ፡፡ የግድ ነዋሪው ወይም ተጠቃሚው እስኪያልቅ ሊጠበቅ አይገባም፡፡ አስፈላጊ ስለሆነ በሕግ ሊገደብ ይገባል፡፡ ህብረተሰቡ የህንፃ ተጠቃሚ እንደመሆኑ ቢያንስ በትንሹ እንኳን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎቱን ማግኘት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ደረጃውን የጠበቀ ንድፍ እንዲሰራና የግንባታ ፍቃድ እንዲገኝ የአርክቴክቱ ሚና  ለአርክቴክቱም ቢሆን ስለ ቦታዎች፣ የአየር ሁኔታ፣ አእዋፋት በአጠቃላይም ወደፊት ሊኖሩ ስለሚችሉ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የአካባቢውን ራዕይ ሊቀይሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥልቅ የሆነ መረጃ የለም፣

አቶ ዘለቀ፡-
ለከተማ በሁለት ደረጃ የተቀመጡ ሕጎች አሉ ማለት እንችላለን፡፡
አንደኛው ከተማ አቀፍ ሕግ ወይም ማስተር ፕላን ነው፡፡ ማስተር ፕላን እስከ 10 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ እንዲያገለግል ተደርጎ የሚሰራ ነው፡፡ መንገዶች በየት እንደሚያልፉ፣ ህንፃዎች በምን መልኩና አይነት እንደሚሰሩ፣ የአካባቢ ጥበቃ መረጃ ያሏቸው ፕላኖች አሉ፡፡ አዲስ አበባም ማስተር ፕለን አላት፡፡ ከዚህ በመቀጠል የሚመጣው ሕንፃ ነው፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ መንገዶች ሲሰሩ ቤቶች ሲፈርሱ ብናይም በማስተር ፕላኑ መሰረት የሚሰሩ ናቸው፡፡ አንዳንዴ በማስተር ፕላን ደረጃ የታዩት በዝርዝር ሳይታዩ ቀርተው የሚስተካከሉበት ሁኔታ አለ፡፡ በመሠረቱ ግን ሕጎች አሉ፡፡ ወደ ህንፃ ሲመጣ ትክክለኛው ባለሙያ ትክክለኛውን ስራ እየሰራ ነው ወይ የሚለው ካልሆነ በስተቀር በመሰረቱ ህንፃዎችን አስተካክሎ ለመስራት የሚያስችሉ መረጃዎችም ሆነ እውቀት ያቸው ሰዎች አሉ፡፡

ረፖርተር፡-  የአየር ሁኔታ፣ ነዋሪውና የመሣሠሉት ከህንፃ ግንባታ በፊት መጤን ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዝርዝር መረጃ አለ?

አቶ ዘለቀ፡-
አዎ፡፡ መሰረታዊ የሆኑ አርክቴክት የሚያስፈልገው መረጃ የፀሐይ አቅጣጫ፣ መሬት ላይ ያለ አቀመማመጥና ሌሎችን በተመለከተ መረጃዎች አሉ፡፡ ሕንፃ ለመስራት የሚያስፈልጉ መረጃዎች ብዙ አይደሉም፡፡ የማስተር ፕላኑም አለ፡፡ እነዚህን በአግባቡ የመጠቀም ካልሆነ በስተቀር ይሄን እቃ ስላላገኘሁና መረጃ ስለሌለኝ ነው ጥሩ ህንፃ ያልሰራሁት የሚል አርክቴክት ያለ አይመስለኝም፡፡

ረፖርተር፡- መረጃው ካለ ለምንድነው አሁን ያሉ  የሙቀት መጠናቸው እንኳን በተመጣጠነ መልኩ ያልተሠሩት?

አቶ ዘለቀ፡-
አሁን ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ለምን ቤቶች በተፈለገው ሁኔታ አልተሠሩም? ባለቤቶች ወይም ለሙያው ሩቅ የሆኑ ሰዎች እስኪተችዋቸው ድረስ የተበላሹ ብዙ ቤቶች ለምን እናያለን? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ችግር ትክክለኛውን ሙያ በበቂ ሁኔታ አለመጠቀም ነው፡፡ ሰዎች ብዙ ገንዘብ ለማውጣትና ኢንቨስት ለማድረግ ሲነሱ መጀመሪያ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ትክክለኛባለሙያ ማግኘት ነው፡፡ መሰረታዊው ስህተት በትክክለኛ ባለሙያ አለማሰራት ነው፡፡ ብዙዎች አርክቴክት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አርክቴክቱን በትክክል እየተጠቀሙበት ነው ወይ? በፕላኑ ላይ የተቀመጡ ነገሮች ወደ ተግባር እየተተረጎሙ ነው ወይ የሚለው በጥያቄ የሚቀመጥ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በከፊል ባለቤቶች ላይ ችግር እንዳለ እናያለን፡፡ በአገራችን ባለው አሰራር ብዙ ጊዜ ባለቤቶች ራሳቸው በራሳቸው መስራታቸውን በኩራት የሚገልፁበት አጋጣሚ እናያለን፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ሙያቸው ባልሆነ ዘርፍ ሰርተው ሊኮሩ አይገባም፡፡ የህንፃ ስራ ከባለሙያ ውጭ በመላምት ሙከራ የሚደረግበት አይደለም፡፡ የህንፃ ሂደት ንድፍና የቤት ሥራ ፈቃድ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ወደ ግንባታ ሲኬድ ዝርዝር ጉዳዮችን ከአርክቴክቱ ማግኘት አለባቸው፡፡ በግንባታ ሂደትም ውስጥ በንድፍ ወቅት ሳይታዩ ያመለጡ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ህንፃ በግንባታ ላይ ስለሆነ ህይወቱ በመመስረት ላይ ያለ ስለሆነ በባለቤቱ አዳዲስ ሃሳቦች ይፈጠራሉ፡፡ አዳዲስ ሃሳቦችን ከመጀመሪያው ፅንሰ ሀሳብ ጋር አያይዞ ማስተካከልና የተሻለ ማድረግ የሚችለው አርክቴክቱ ነው፡፡ ሆኖም ህንፃው ተጀምሮ እስኪያልቅ አርክቴክቱ እንዲያረጋግጥ የሚያስችል መመሪያ የለም፡፡ አሰሪዎቹም ጥቅሙን ተረድተው ዝግጁ ስላልሆኑ የሚፈጠር ስህተት ነው፡፡

ረፖርተር፡- ማህበሩ  ለመፍታት ምን ያደርጋል?

አቶ ዘለቀ፡-
ጥረት የምናደርገው በመንግሥት የአሰራር መስመር ውስጥ ለምሳሌ ከሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር አዲስ የመግባቢያ ስምምነት አድርገናል፡፡ እንደ አጀንዳ ወደፊት ከመንግሥት ጋር ማድረግ የምንፈልገው በህንፃ ስራ ውስጥ ሥርዓቱ አስፈላጊ እንደሆነና ሥርዓቱን መንግሥት አምኖበት በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በግል ፕሮጀክቶች ላይም አስገዳጅነት ባለው ሁኔታ በሁሉም ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ የሚውልበትን መንገድ ለማመቻቸት ጥረት ማድረግ ነው፡፡ ሕጎችም ለወደፊት እንደሚወጡ ተስፋ አለን፡፡

ረፖርተር፡- ማህበራችሁ ያቀፈው አርክቴክቶችን ነው፡፡ በህንፃዎች ላይ ችግር እንዳይፈጠር ባለሀብቱንና አባሎቻችሁን የምታገናኙበት መንገድ የለም?

አቶ ዘለቀ፡-
ስለሙያው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር አንደኛው ሥራችን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አርክቴክቱን ከህብረተሰቡ ጋር የሚያገናኝ ድልድይ እንዲኖርና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥርዓቶች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አርክቴክቶች እርስ በርሳቸው የሚተዳደሩበት ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ ይህንን እያደረግን ነው፡፡ በአርክቴክቶች መካከል ውድድር በሚካሄድበት ጊዜ ሥርዓት ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ህጋዊ መሰረት ያለው የውድድር ሥርዓት ከ2 ዓመት በፊት አውጥተናል፡፡ አርክቴክቶች እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት የሥራ ግንኙነት ውስጥ ማድረግ የሚገባቸውን የስነ ምግባርና የሥራ ግንኙነት የሚመሩና የሚገድቡ ህጎችም አሉን፡፡

ረፖርተር፡- ከጓደኝነትና ቅርበት የተነሳ ጥፋት እንኳን ቢኖር ደፍሮ የመናገሩ ባህል የለም፡፡ አርክቴክቶቻችሁ እርስ በርስ የሚተቻቹበት መድረክ አላችሁ?

አቶ ዘለቀ፡-
በወር አንድ ጊዜ ገለፃዎች አሉ፡፡ የተለያዩ በአለማቀፍ ደረጃ የሚሰሩ አርክቴክቶች ወደ አገራችን በሚመጡበት ጊዜ ውይይት አንዲኖር የማድረግ ሂደትም አለ፡፡ ማህበራችን የአለም የአርክቴክቶች ማህበር አባል ነው፡፡ የአለም አርክቴክቶች ማህበር ተከታታይ የሆነ የትምህርት እድገት የሚል ፕሮግራም አለው፡፡ ባለሙያዎች ከተመረቁ በኋላ በየአመቱ ሊጨምሩ የሚገባቸውን እውቀት በተመለከተ በአለማቀፍ ደረጃ እየተሰራበት ነው፡፡ ይህ ዝግጁ ሲሆን ኮርሶቹ በማህበራችን አማካይነት ይገኛሉ፡፡ አርክቴክቶች በሙያቸው ለሚያደርጉት እድገት ስልጠናዎች ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ከአለም አርክቴክቶች ማህበርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርኪቴክቶች ዲፓርትመንት ጋር በመተባበር ትምህርት ቤቶች ላይ "School +" የሚል አለማቀፍ አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡ ከጀርመን፣ ከእስራኤልና ስፔን ዩኒቨርስቲዎች ፕሮፌሰሮችን ተማሪዎች አገራችን መጥተው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተገኙበት ትምህርት ቤቶች ከለት ተለት የማስተማር ሂደት በተጨማሪ ተቋማቱ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚውሉበትንና የከተማ አካል ሆነው የህብረተሰቡን አኗኗር የሚያንፀባርቁበት መንገድ እንዲኖር በአዲስ አበባ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተው የዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት እንደ አንድ ናሙና ወስደው ፕሮጀክት እየሰሩ ነው ያሉት፡፡

ረፖርተር፡- የፕሮጀክቱ አላማ ምንድን ነው?

አቶ ዘለቀ፡-
ትምህርት ቤቶችን እንደ አንድ የከተማ ማዕከል ለማድረግ ነው፡፡ ት/ቤቶች ከመማር ማስተማሩ ሂደት በተጨማሪ ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት የተሻለ አቅም ስላላቸው ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤትን እንደናሙና ወስደው እያጠኑ ነው ያሉት፡፡ ውጤቱም ሰኔ/2000 መጨረሻ ላይ ጣሊያን ቱሪን የአለም አርክቴክቶች ስብሰባ ላይ እንደ አንድ ፕሮጀክት ሆኖ ተማሪዎች የሚያቀርቡት ስራ ይሆናል፡፡ በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ተሳትፏል፡፡

ረፖርተር፡- የአርክቴክቱን ክሂል ለማሳደግ በፐብሊክ ሌክቸር ትሳተፋላችሁ?

አቶ ዘለቀ፡-
በወር አንድ ጊዜ አለ፡፡ ማህበሩም አመታዊ ስብሰባውን ሲያካሂድ ጥናቶች ተሠርተው ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡ አውደ ርዕይም ይኖራል፡፡ የአርክቴክቶች ስራ የሚታይ ነው፡፡ ሆኖም አርክቴክቶች በየቢሮዋቸው ብዙ እየሰሩ ቢሆንም ወደ ሕዝብ ወጥቶ እየታየ አይደለም፡፡ ማህበሩ በሚችለው መንገድ አጋጣሚ ሲያገኝ አውደ ርዕይ ያዘጋጃል፡፡ አባላት ከቤታቸው ወጥተው ስራቸውን እንዲያሳዩ ያበረታታል፡፡ ሕዝቡ በቅጡ ስላላወቃቸውና ስራውን ለሌላ እያሰራ ስለሆነ ያንን እንዲያውቁ እንሰራለን፡፡ አርክቴክቶች እንደ አርቲስትም ስለሆኑ ብዙ ጊዜ አንድ ስራ ይዘው እሱኑ እየሰሩ ሌላ ስራ ፍለጋ ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ጥሩ ሥራዎች በየቤቱ ተቀምጠዋል፡፡ ለወደፊት እነዚህ ሥራዎች በአውደ ርዕይ ብቻ ሳይሆን ማህበራችን የአባላት ሥራዎች መረጃ የሚያገኙበትን ሥርዓት የመስራት ሂደት ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- አርክቴክቶቻችን የራሳቸውን ስራ ትተው የውጪውን የሚገለብጡበት ሁኔታ አለ፤

አቶ ዘለቀ፡-
ሙያው በራሱ ከህብረተሰብ አኗኗርና ከባህል ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ አሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ግንዛቤ ባህላዊ ህንፃዎች ወይም ውስጡ የሚታዩ ምልክቶችን በቀጥታ በመለጠፍ ወይም መስራት ባህላዊውን ጠብቆ እንደማቆየት ነው፡፡
በዚህ ዙሪያ ጥናት መሰራት አለበት፡፡ ፍላጎቱ ያላቸውና ጥናት እያደረጉ የሚገኙ አርክቴክቶችም አሉ፡፡ ስለ ኪነህንፃዎች ያላቸውን ባህሪና ውበት፣ ለአዲሱ ትውልድ ሊያበረክቱ የሚገባቸውን አስተዋፅኦ የሚያጠኑ አሉ፡፡ አርክቴክቱ እነዚህን መጠቀም ሲፈልግ ጥንት የነበረውን በቀጥታ እንዲገለገልባቸው አይደለም፡፡ ሆኖም ኪነ ህንፃ፣ ባህል፣ የአየር ሁኔታንና አኗኗርን የመሳሰሉትን ይጠቀልላል፡፡ አርክቴክቶች ዘመናዊውን የኪነ ህንፃ እቃዎች መጠቀማቸው ችግር የለውም፡፡ መጠቀምም አለባቸው፡፡ በዚህ ዘመን ያሉ እቃዎች በሙሉ የሁላችንም እቃና ንብረት ናቸው፡፡ በጥንት ጊዜ አባቶቻችን በድንጋይ ስለሰሩ እኛ አሁን በድንጋይ መስራት አይኖርብንም፡፡ በጥንት ጊዜ በድንጋይ ሲሰሩ ሙቀት ለመከላከል አስበው ሰርተው ከሆነ አሁን ስንሰራ ሙቀትን መከላከል ካልቻልን ግን ባህላችንን አበላሽተናል ማለት ነው፡፡ ባህል ማደግ ያለበት አዲሱንም ቁሳቁስ በመጠቀም ነው፡፡ አርክቴክቶች አዲሱን ባህል መፍጠርም አለባቸው፡፡ አልፎ አልፎ በውጭው አለም የምናያቸው አስተሳሰቦች እንዳሉ የሚቀመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ሆኖም በአገራችን በቅርብ ልናገኝ የምንችላቸውን እቃዎች ተጠቅመን ጥንታዊ ጠቃሚ አስተሳሰቦችን አካትተን መስራትና ባህላችንን ማሳደግም አለብን፡፡ ባህላዊ ነገሮችን ማጥናትና ጠቃሚ ነገሮችን መውሰድ እንዲሁም አዲሱንም ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን፡፡ ይህን ሳናደርግ ቀርተን ከሆነ ግን መወቀስ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ኪነ ህንፃን አስመልክቶ እየተጠቀምንበት ያለው አሰራር ይህን ያገናዘበ ነው?

አቶ ዘለቀ፡-
ለማለት ያስቸግራል፡፡ ብዙ ስህተቶችን እናያለን፡፡ ስህተቱን ነቅሰን አንዱን ብቻ ብናይ የተጋነነ ስለሚሆን በጥቅሉ ማየት ይገባል፡፡ አርክቴክቶች አሁን ባለው ሁኔታ ጥሩ ለመስራት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ይሄ ስላልተስተካከለልን ነው የተበላሸው ማለት አንችልም፡፡ በሂደት መስተካከል ያለባቸው መስተካከል አለባቸው፡፡ አሁን ላለው ስህተት ሁላችንም ተወቃሽ ነን ማለት እንችላለን፡፡ አርክቴክቱም፣ አሰሪውም በውስጡ ያለው ህብረተሰብም ሃላፊነት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ማህበራችሁ ችግሩን ለመፍታት ምን ያደርጋል?

አቶ ዘለቀ፡-
አርክቴክቶች ያላቸውን እድል በጥንቃቄ ተጠቅመው ለህብረተሰቡ ጥሩ መስራት እንደሚችሉ ማሳየት፣ የማነቃቃትና የውይይት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ ህብረተሰቡም የአርክቴክቶችን ሙያ በአግባቡ እንዲጠቀም ዘርፉ ምንድነው የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ እንዲገነዘብ ማሳወቅ እንዳለብን እናምናለን፡፡ በተወሰነ ደረጃም እያደረግ ነው ነው፡፡ የአሰራር ሥርዓቱ በመንግሥት ሕግ ውስጥ መካተት ስለሚገባው ከመንግሥት ጋር አብረን ሆነን መከላከያዎቹ እንዲኖሩ፣ ህብረተሰቡና ባለሙያው በሥርዓቱ ውስጥ ማለፍ እንዲችሉና አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን እየሰራንበት ነው፡፡
 
< Prev   Next >