Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow የወጣቶቹ የጋራ መድረክ
የወጣቶቹ የጋራ መድረክ Print E-mail
Wednesday, 23 April 2008
Image
ወጣት ናታን ጥላሁን
2006 በአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም ለተወሰኑ አፍሪካውያን ወጣቶች የተሰጠውን የሚዲያ ስልጠና ወስዷል፡፡ በሥልጠናው ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡና እድሜአቸው ከ12-35 የሆኑ ወጣቶች የተካፈሉ ሲሆን ከሥልጠናው በኋላ በተሳታፊዎች መካከል የፅሑፍ ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡
በውድድሩ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን ወክለው ከመጡ ሰላሳ ወጣቶች የተመረጡት አሥራ አምስት ነበሩ፡፡ ከአሥራ አምስቱ ወጣቶች መካከል ኢትዮጵያን ወክለው በውድድሩ የተሳተፉት ወጣት ናታን ጥላሁንና ሊንዳ ዮሐንስ ይገኙበታል፡፡ የተመረጡት አሥራ አምስት ወጣቶች በዚያው ዓመት አፍሪካን ዴቨሎኘመንት ፎረም በተለያዩ ርእሶች ያዘጋጀውን ስብሰባዎች በወሰዱት የሚዲያ ስልጠና መሠረት በተለያየ መልኩ ዘግበዋል፡፡

አፍሪካውያን ወጣቶቹ በአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም እንቅስቃሴ ያገኙትን የሚዲያ ሥልጠናና ያካሄዱዋቸውን ተግባራት በማስመልከት ወጣት ናታን ጥላሁንን አነጋግረነዋል፡፡

በአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም በየዓመቱ በተለያየ ርዕስ በተለይም ወጣቱን በሚመለከቱ ውድድሮች በየዓመቱ ይደረግ እንደነበር የሚናገረው ወጣት ናታን የ2006ቱን የአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም ያዘጋጀውን ስብሰባ እሱና ሌሎች አፍሪካውያን ጓደኞቹን በተለያየ መልኩ ከዘገቡ በኋላ ከአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም ጋር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለአንድ ዓመት ያህል ቀዝቅዞ እንደነበር አልደበቀም፡፡

“ምንም እንኳ ጅማሬው ጠንካራ ሆኖ በወቅቱ ባይቀጥልም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ ወጣቶች የሚገጥማቸው ችግር ተመሳሳይ በመሆኑ አፍሪካውያን ወጣቶች ስለችግሮቻቸው የሚወያዩበትና መፍትሔ የሚፈልጉበትን መንገድ ከማስቀመጥ አንፃር መድረኩ በቂ አቅም ነበረው፡፡ ከሁሉም በላይ መጠናከር ቢችል አፍሪካውያን ወጣቶች የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚነሱበት መድረክ የሚወከሉበትን ሁኔታ ይፈጥራል” ብሏል፡፡ የአፍሪካ መሪዎችም ሆነ ባለሥልጣናት አህጉራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር በሚገኙባቸው መድረኮች እያንዳንዱን አገራት  ባይሆንም እንኳ የተለያዩ የአፍሪካ ክልሎችን በመወከል አፍሪካውያን ወጣቶችን ማሳተፍ የሚያስችል አወቃቀር በአህጉር ደረጃ ሊኖር እንደሚገባ አመልክቷል፡፡

ናታንና ሌሎች አፍሪካውያን ጓደኞቹ በወቅቱ የዘገቡት የአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም ስብሰባ ወጣቶችና አመራር በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ አፍሪካውያን ወጣቶች ዋና ዋና ችግሮችና አፍሪካን ለወጣቶች ምቹ ማድረግ በሚል ርዕስ ውድድሮች ተደርገዋል፡፡ “2006 ላይ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተደረገውን የአፍሪካ ዴቨሎኘመንት ስብሰባ የእለት ተእለት ክንዋኔ መዘገብ ስለነበረብን ማምሸትና ሌሊት መሥራት ነበረብን፡፡ በስብሰባው ላይ ከመካፈላችን ባሻገር ዘገባውን አንድ ላይ መሥራታችን ስለምንኖርበት አካባቢ እርስ በርስ የተለያዩ መረጃዎችን እንድንለዋወጥ ረድቶናል” በማለት ተናግሯል፡፡

ናታን እንደገለፀው የቦብ ማርሊን ልደት በአዲስ አበባ መከበር ተከትሎ በዝግጅቱ ላይ ለመገኘት ከበርካታ የአፍሪካ አገራት የመጡ አርቲስቶች የአፍሪካውያን ወጣቶች ድምፃቸውን በጋራ ማሰማት የሚችሉበትን ፎረም ለመፍጠር ላደረጉት እንቅስቃሴ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ድጋፍ አድርጐ የስፒክ አፍሪካ ኘሮግራም ሊጀመር ችሏል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት አፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረም በተከታታይ ያደርጋቸው ለነበሩ የወጣቶች ውድድር ድጋፍ ያደርግ የነበረ ሲሆን አፍሪካ ዴቨሎኘመንት ፎረምና ስፒክ አፍሪካ የአፍሪካውያን ወጣቶችን የጋራ መድረክ ከመፍጠር አንፃር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ከተለያዩ የአፍሪካ ክልሎች ወጣቶች በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በወጣቶች የሚወከሉበትን መንገድ ለመፍጠር በማሰብ ስፒክ አፍሪካ ኘሮግራምን እንደጀመረ ናታን ያስረዳል፡፡ በዚሁ ኘሮግራም እሱና ክልሎቻቸውን በመወከል በኘሮግራሙ የታቀፉ ወጣቶች በሚኖሩበት አገር በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የሠሯቸው ዘገባዎች መኖራቸውንም ጠቁሟል፡፡

2001 ላይ አፍሪካን ለሕፃናትና ለታዳጊዎች ምቹ ማድረግ በሚል ርዕስ የአፍሪካ ባለሥልጣናት ካይሮ ላይ ተገናኝተው ወጣቶችን በሚመለከት ያስቀመጧቸውን እቅዶች ተፈፃሚነት ለመገምገም በ2ዐዐ7 በድጋሚ ካይሮ ላይ ባደረጉት ስብሰባ በስፒክ አፍሪካ ኘሮግራም አፍሪካውያን ወጣቶችን ለመወከል መገኘቱን ገልፆልናል፡፡ “ይህ ተከታታይ ስብሰባ ቀደም ሲል በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከዚያም በአፍሪካ ህብረት ነው የተካሄደው፡፡ ወጣቶችንና ሕፃናትን በሚመለከት 2ዐዐ5 ላይ በተደረገው የአፍሪካ ባለሥልጣናት ውይይት ላይ ወጣቶች የተወከሉበት ሁኔታ ባይኖርም በተወሰነ መልኩ አፍሪካውያን ወጣቶች የሚወከሉበት ሁኔታ ተመቻችቶ ነበር” ብሏል፡፡

በ2007ቱ የካይሮ ስብሰባ አፍሪካውያን ወጣቶች በጥሩ ሁኔታ የተወከሉበት አሠራር ነበር ለማለት እንደማይቻል የሚናገረው ወጣት ናታን በስብሰባው ላይ ክልሎቻቸውን በመወከል የተገኙት ወጣቶች የተወከሉበት ግልፅ አወቃቀር እንደነበር ይጠራጠራል፡፡ በዚህም ምክንያት እዚያ ስብሰባ ላይ የተገኙት ጥቂት ወጣቶች ቅሬታ ማሰማታቸውንና በየአንዳንዱ የአፍሪካ አገራት የወጣቶች ምክር ቤት (youth parliament) ሊኖር እንደሚገባ ሀሳብ ማቅረባቸውን ገልፆልናል፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ ወጣቶች የተሳተፉበት ግልፅ የሆነ አወቃቀር ባይኖርም እንደጥሩ ጅማሬ ሊታይ ይገባል ይላል፡፡

 በምህረት አስቻለው
 
< Prev   Next >