Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version

Thursday
Nov 20th
Home arrow Sections arrow የእራት እድር
የእራት እድር E-mail
Wednesday, 09 January 2008
መሳለሚያ እህል በረንዳ ቀበሌ 08 ውስጥ ከሚገኝ አንድ መንደር ስንደርስ ከቀኑ ስምንት ሠዓት ሆኖ ነበር፡፡ ወደዚያ መንደር የሄድነው ከረዥም ዓመታት በፊት ..የእራት እድር.. በሚል በተወሰኑ ሰዎች በተቋቋመ ማኀበር እየተረዱ ያሉ አዛውንቶችን ለማነጋገር ነው፡፡ ረዥም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ተጉዘን አንድ ያረጀ ቤት ደረስን፡፡

በሩ ተዘግቷል፡፡ ደጋግመን ካንኳኳን በኋላ እድሜአቸው በሰማኒያዎቹ የሚሆን አዛውንት በሩን ከፍተው ወደ ውስጥ እንድንገባ ጋበዙን፡፡ ቤቱ መስኮት የለውም፣ መብራትም ስለሌለ በጣም ጨልሟል፡፡ ወዲያው ተመልሰው አልጋቸው ላይ ተቀመጡ፡፡ ወይዘሮ ማሚቴ ዳዲ ይባላሉ፡፡ ዘጠኝ ልጆች የነበራቸው ሲሆን አሁን ሁሉም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ይረዳቸው የነበረው የመጨረሻ ልጃቸው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በድንገተኛ ህመም ከሞተ በኋላ ምንም ረዳት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡

ከሁለት ዓመት ወዲህ ግን ..በእራት እድር.. እየተረዱ እንደሆነና በዚህም የእለት ምግባቸውን ማግኘት እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡ ቀደም ሲል ለቤት ኪራይ አምስት ብር ይከፍሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ያለባቸውን ችግር በመረዳት ቀበሌው ክፍያውን ሠርዞላቸዋል፡፡ ማህበሩ ምን ምን ይረዳዎታል? ብለን ስንጠይቃቸው ..በቀን ሦስት ጊዜ ምግብ ያመጡልኛል፡፡ በተወሰነ ጊዜ ሳሙናና ሌሎች ደረቅ ምግቦችን ይሰጡኛል፡፡ ቢሆንም ብዙ ችግሮች አሉብኝ፡፡ መብራት ስለሌለኝ በኩራዝ ነው የምጠቀመው፡፡ ጋዝ ያጣሁ እለት ጨለማ ውስጥ የምቀመጥበት ጊዜ አለ.. በማለት መለሱልን፡፡ እዚያው አካባቢ ወደሚገኙና የእራት እድሩ ወደሚረዱ ሌላ አዛውንት ቤት አመራን፡፡ ወ/ሮ ተዳዳ ተክለወልድ ይባላሉ፡፡ ልጆች የሏቸውም፡፡ አቅማቸው ከመድከሙ በፊት ካቲካላ በማውጣት እየሸጡ ይተዳደሩ እንደነበር በመጠቆም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እድሜአቸው በመግፋቱ አቅም ስላነሳቸውና የጤናቸው ሁኔታም ሠርተው ለማደር ስላልቻሉ መለመን ጀምረው ነበር፡፡ ከዛሬ ሁለት ዓመት ጀምሮ ..የእራት እድር.. የእለት ጉርሳቸውን በመስጠት እየረዳቸው ስለሆነ ልመና ማቆማቸውን ገልፀዋል፡፡

የእራት እድሩ የእለት ምግባቸውን ስለሚረዳቸው ከዚህም በተጨማሪ እንደሳሙና የመሳሰሉትን ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ስለሚረዳቸው መለመን ማቆማቸውን አመልክተዋል፡፡ ..ሠርቼ ራሴን መርዳት ብችል መልካም ነበር፡፡ ቀላል የሆኑ ሥራዎችን ካልሆነ በስተቀር እንደልብ ተንቀሳቅሼ ለመሥራት አልችልም፡፡ ቢሆንም የምመገበው እስካገኘሁ ድረስ ወደ ጐዳና ለልመና ለመውጣት የማያስገድደኝ ነገር የለም..

መጀመሪያ እንዳነጋገርናቸው አዛውንት ሁሉ ወ/ሮ ተዳዳ ቤትም መብራት የለም፡፡ ብርሀን ሲፈልጉ ሻማ እንደሚለኩሱና ቤታቸው አስፋልት ዳር በመሆኑ ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለ የመንገድ መብራት ብርሀንን ለመጠቀም አብዛኛውን ጊዜ ምሽትም ቢሆን በራቸውን እንደማይዘጉ ይናገራሉ፡፡ አብዛኛው ሠው ደፍሮ ለልመና ወደ ጐዳና የሚወጣው በልቶ ለማደር እንደሆነ በመመልከት የተቸገሩ ሠዎችን በተለይም አረጋውያንን የእለት ጉርሳቸውን እንዲያገኙ መርዳት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያምናሉ፡፡

በእራት እድር የሚረዱት አዛውንቶች አሥር ሲሆኑ አዛውንቶቹ በቀበሌ ሠራተኞች ጥቆማ መመረጣቸውን የማኀበሩ ሠብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዘለቀ አስረድተዋል፡፡ የእራት እድሩ ሀያ የሚሆኑ አባላት ያሉት ሲሆን አሥር አረጋዊያንን እየረዳ ይገኛል፡፡ የማኀበሩ አባላት በየወሩ መዋጮ የሚያደርጉ ሲሆን አሁን በአዛውንቶቹ እያደረጉ ያለውን እርዳታ ከሁለት ዓመት በፊት ለመጀመር አሜሪካን አገር የምትገኝና በበጐ አገልግሎት ሥራ ላይ የምትገኝ አባላቸው የላከችላቸው ገንዘብ መነሻ እንደሆናቸው ይናገራሉ፡፡

..አሥሩም አረጋዊያን ምንም ዓይነት ረዳት የሌላቸው ናቸው፡፡ በወር አንድ ሺህ ስድስት መቶ ብር መገኘቱንና ምግብ የሚያበስሉት ለአረጋዊያኑ በየቤታቸው ምግብ የሚያደርሱ አራት ሠዎችን በመቅጠር የእለት ምግባቸው እንዳይጐድልባቸው እያደረግን ነው.. በማለት የተወሰኑ ሠዎች ተሰባስበው በአካባበያቸው የሚገኙና ረዳት የሌላቸውን አዛውንቶች የመርዳት ሁኔታ ቢለመድ ወደ ልመና የሚሄዱ ሠዎችን ቁጥር በመቀነስና የበጐ አገልግሎት በማዳበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

እርስ በርስ ለመረዳዳት ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በመርዳት ማኀበር ማቋቋም አስፈላጊ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ የእራት እድር እንቅስቃሴን ለማስፋትና እየረዷቸው ያሉ አዛውንቶች ሕክምናና ሌሎችም ተጨማሪ እርዳታዎችን እንዲያገኙ እንዲሁም ቀላል የሆኑ ሥራዎችን ሠርተው ራሳቸውን መርዳት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲያስችላቸው ከአምስት ወር በፊት ፈቃድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በውጭ አገር የተወሰነ ወርሃዊ ገንዘብ የሚያገኙ አረጋውያንን የሚረዱ ማእከላት ያሉ ሲሆን በእኛ አገር ካለው እውነታ አንፃር እያንዳንዱ ግለሠብ አነስተኛ ማኀበራትን በመመስረት ረዳት የሌላቸውን አረጋውያንን የመርዳት ባህል ማዳበር እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡ ..እያንዳንዳችን ባለንበት ደረጃ መርዳት የምንችለውን ብንረዳ ለአገራችን እድገት በተወሰነ መልኩ አስተዋፅኦ አደረግን ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ እድሮች የሚያስከፍሉት ወርሀዊ ገንዘብ ላይ በአካባቢያቸው የሚገኙ አቅመ ደካሞች እንዲረዱ አንድ ብር እንኳ ተጨማሪ እንዲሰባሰብ ቢያደርጉ መልካም ይሆናል.. ብለዋል፡፡

በምህረት አስቻለው

 
< Prev   Next >