| ከመብራትና ከስልክ ይልቅ ችግሩ... |
|
|
| Wednesday, 23 April 2008 | |
|
ከመብራትና ከስልክ ይልቅ ችግሩ የ”ግልጽነት” እንዳይሆን!?
እንዲህ ንጉሥ የንጉሥ ቃናጣ ውሃ በመዘውር አየር የሚያወጣ ያደፈው ሊታጠብ የጠማው ሊጠጣ ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ በማለት ነው፡፡ በ1892 የስልክ መስመር መዘርጋት ተጀመረ ኤሌክትሪክም (እንዴት ባለሁኔታና አጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚነገረው የሚገርምና የማይገጥም እንዲሁም የማይተመን ቢሆንም) በተመሳሳይ ሁኔታ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ነው የገባው፡፡ የቧንቧ ውሃን የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይልን እና ስልክ ወይም ቴሌኮሙኒኬሽንን የሚያስተባብራቸው ሁሉም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥትና የዘያን ወቅት ጅምር የሥልጣኔ ጮራን የፈነጠቁት እነሱ ናቸው በመባሉ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅና ከሁሉም ይበልጥ እነዚህ ሦስቱ “እየተባበሩ” አሁንም ድረስ አብረው የሚጠፉ አንድ ላይ “የሚያጠፉ” በአንድነት እልም ድርግም የሚሉ መሆኑ ነው፡፡ በውሃ ምክንያት መብራት ይጠፋል፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ምክንያት ውሃና ቴሌፎን ይጠፋል፡፡ ይህ አሁን አሁን እየከፋና እየሰፋ የመጣው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ሲል ደግሞ አንዱ የገዛ ራሱንና የአገርን ለምሳሌ የመብራትና ኃይል አቅም እገነባለሁ ብሎ የሌላውን አገልግሎት ያቋርጣል፤ ያወድማል፡፡ ሌላው የተቋረጠውን አገልግሎት ሲቀጥል የሌላው ይቋረጣል፡፡ ከዚህ በከፋና በባሰ ሁኔታ ደግሞ ለምሳሌ የተቆረጠ የተጠላለፈ ሽቧቸው አደጋ ማስከተሉ አልቀረም፡፡ አደጋ ከደረሰ በኋላም ተጠያቂና ኃላፊ የለም፡፡ አንድ ቴክኖሎጂ ከተፈጠረበት፣ ካደገበትና ከክፉ ከደጉም ተምሮ የበለፀገ ወግና ሥርዓት ካካበተበት አገርና ባህል ሲመጣ አገር ውስጥ ሰተት ብሎ የሚገባው ሁለመናውን ይዞ አይደለም፡፡ ቴሌፎንና ኤሌክትሪክ ወደ ሀገራችን ሲገቡ እንደማንኛውም የሕዝብ አገልግሎት ሥራ ድርጅት ተቋሞች መሬት ከማስለቀቅ ጀምሮ ልዩ ጥበቃ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ደንብ እንዲወጣላቸው ተደረገ፡፡ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ ይህንን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁንም ዛሬ ድረስ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ እነዚህ ድርጅቶችን ለማቋቋም መጠየቅና መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችን ከተቋሞቹ ምንም ያልቀረ መሆኑን የሚረጋገጥ ጉዳይ አለ፡፡ የተጠቃሚውን፣ የደንበኛውን ወይም የማንኛውም ሰው መብት ከመጠበቅ ከተጠያቂነትና ከኃላፊነት አንጻር አሁንም እጅግ በጣም ብዙ የጐደለ ነገር አለ፡፡ ተቋሞቹ የሚገባቸው የደህንነትና፣ የጥበቃ ጉዳይ ያለውን ያህል ከእነሱም የሚጠበቅ በርካታ ጉዳይ አለ፡፡ በተቋሞቹ እና በተጠቃሚው እንዲሁም ባጠቃላይ እነሱ በሚያደርሱት ጥፋት ወይም በእነሱ ቸልተኝነት ምክንያት በሚደርስ ጉዳት፣ ምክንያት ተጠቂ ሰው መካከል ያለው ግንኙነት ግን የድንጋይ እና ቃል መለጋትና ሙግት ዓይነት ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ በተለይ ከተጠቃሚው ሕዝብ አኳያ "የተበደልን እኛ ካሱ ይሉናል በዳኛ" ሆኗል፡፡ በዚያ ላይ ግልጽነት የለም፡፡ ለዚህ አንዱ ማስረጃ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሚያዚያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ መግለጫው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በቅርቡ ባጋጠመው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት በፈረቃ እየተሰጠ ያለውን የመብራት አገልግሎት ተከትሎ 24 ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የኔትወርክ ማሰራጫና ማከፋፈያ መሣሪያዎች ላይ እያጋጠመ በሚገኘው የኃይል እጥረት ምክንያት መብራት በሚቋረጥባቸው ቀናት መሳሪያዎቹ በበቂ ሁኔታ መሥራት ባለመቻላቸው በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት በከፊል የመቋረጥ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ያጋጠማቸው የኮርፖሬሽኑ መሣሪያዎች በማዞሪያዎችና በደንበኞች መካከል የሚገኙ የኦፕቲካል ፋይበር ኔትወርክ የኬብል ማከፋፈያ ሳጥኖች ONU (optical network Units) ሲሆኑ፣ እነዚህ መሣሪያዎች የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የቴሌኮም አገልግሎት ፍላጐት በዓይነትም ሆነ በጥራት ለደንበኞች ለማድረስ ከፍተኛ አቅም የሚሰጡና ከማዞሪያዎች የሚወጣውን ኔትወርክ ተቀብለው ወደ ደንበኞች የሚያከፋፍሉ መሣሪያዎች ስለመሆናቸው፣ እነዚህ የከተማ ውስጥ የኦፕቲካል ፋይበር ኔትወርክ ማከፋፈያ ሳጥኖች የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ በተጠባባቂነት የሚያገለግል ባትሪ ቢኖራቸውም እንዲህ ዓይነት ባትሪዎች በባህርያቸው አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ በመሆኑና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሚገኘው ሀይል (commercial power) በአሁኑ ጊዜ በተፈጠረው የፈረቃ ፕሮግራም ምክንያት ለ12 ሰዓታት የሚቋረጥ በመሆኑ በተጠቀሱት መሣሪያዎች ላይ ከፍተኛ የሃይል እጥረት (ክፍተት) እያጋጠመ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን በእነዚህ የኦፕቲካል ፋይበር ኔትወርክ ማከፋፈያ ሳጥኖች ላይ እያጋጠመ ያለውን የሃይል እጥረት ለመቅረፍ ፈጽሞ የስልክ አገልግሎት ሊቋረጥባቸው በማይችሉና በተመረጡ ውሱን ቦታዎች ላይ ተንቀሳቃሽ ጄኔሬተር በማዘጋጀት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጾ ይሁን እንጅ በአዲስ አበባ የሚገኙት እነዚህ የኬብል ማከፋፈያ ሳጥኖች እጅግ በጣም በርካታ በመሆናቸው የኤሌክትሪክ ሃይል በሚቋረጥባቸው ሁሉም አካባቢዎች በሙሉ ተንቀሳቃሽ ጄኔሬተር ለማዘጋጀት ስለሚያዳግት በፈረቃ እየተሰጠ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እስኪቀረፍ ድረስ ሊቀጥል ስለሚችል ደንበኞች በሃገር አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውን የኃይል እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ በቴሌኮም አገልግሎት ላይ እየተከሰተ ያለውን ችግር እንዲያውቁት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማስገንዘቢያ ያስተላልፏል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሰጠውን መግለጫ አገላብጦ ማየት የቻለ ከመንግሥት ኢንፎርሜሽን ቅርቦት ግልጽነትና ወዲያው በዚያ አማካኝነት የሚታዘቡትን የግልጽነትና የተጠያቂነት ጉዳይ መመርመር ይቻላል፡፡ የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል የፈረቃ ፕሮግራም ከዚያም ቀደም ስለችግሩ እንደማይታወቅ በሽታ ወይም እንዳልተተነበየ የተፈጥሮ አደጋ የተከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ይፋ መግለጫ ከመስጠቱ በፊት ነው፡፡ የወረፋ የፈረቃ ነገር የመጣውና በይፋ በጋዜጣ የወጣው ከዚያ በኋላ ቆይቶ ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ሲልም በተለይም በአንድ ወቅት የተወሰኑ የአገር ውስጥ ጋዜጦች ሁኔታውን በዜና ገፃቸው እንዳስተጋቡት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ከቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መቋረጥ ጋር መያያዙ ወይም የዚህ ምክንያት መሆኑ ቀስ በቀስ እየታወቀ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ሚያዚያ 10 ቀን የበተነውን ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣው (የቀረበው) ጋዜጣዊ መግለጫው ግርጌ ላይ የተጻፈው ቀን እንደሚያመለክተው ሚያዚያ 7 ቀን 2000 ዓ.ም ነው፡፡ ጉዳዩ ይህን ያህል ለምን ዘገየ የምንለው በሚያዚያ 7 እና 10 መካከል ያለው የሦስት የአራት ቀን ልዩነት ብቻና እሱም ብቻውን ስለሚከነክን አይደለም፡፡ የአገራችን የኤሌክትሪክ የመብራትና የኃይል አቅርቦት ላይ በብዙ ነገሮች መካከል ድንገት ይህን የመሰለ ችግር ሲከሰት እያንዳንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ እያንዳንዱ የግል የኮርፖሬት ሥራ አካሄድ በሰፊውና በአጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ሥራ ማዕቀፍ ውስጥ ችግሩን ከወዲሁ ማሳየት ማሳወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ከኤሌክትሪክ መብራት እና በተለይም ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አኳያ ጉዳዩን ጉዳየ ሊለው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን፣ ወይም "በቴሌፎን አገልግሎት ላይ በከፊል ተከትሎ ወይም ሰምቶ ሳይሆን ቀደሞ ሊያሳውቀን ይገባው ነበር፡፡ በዚህ ረገድና ቴሌን በተመለከተ የሚያሳስቡት ተጨማሪ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን "በኤሌክትሪክ ኃይል የፈረቃም ሆነ ድንገተኛ ወይም ሙሉ በሙሉ ፕሮግራም ምክንያት የሚለው ነገር ሊኖረው ይችላል ወይ? ለምሳሌ አሁን ኮርፖሬሽኑ ወደ ግል ቢዛወር ወይም ሌሎች የግል ተጨማሪ የቴሌኮም ኩባንያዎች ቢቋቋሙ ለእነሱም ብቸኛውና ዋነኛው የመብራትና የኃይል አቅራቢያቸው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ (መብራትና) ኃይል ኩባንያዎች ናቸው ወይ? የአንድ የቴሌኮሙኒኬሽን ሰጭ ኩባንያ ሥራ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል አገልግሎት አይሰጥም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የአንድ ወይም የብዙ ሌሎች የኤሌክትሪክ መብራትና ሃይል አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ሥራ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኩባንያ ሥራ መሥራት አይደለም፡፡ ይህ ግልጽና የታወቀ ህግና ደንብ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን አንድ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያ የግልም ሆነ የመንግሥቱ ዘርፍ ከማቋቋሙ ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት ሊያሟላቸው ከሚገቡት ቅድመ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የራሱና ኢንዱስትሪው የሚሰጠው አገልግሎት አስፈላጊ የሆነው የኃይል መጠባበቂያ (ባክአፕ ፓወር) ሊኖረው የግድ አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የዚህን እውነት የምንረዳው “በግልጽ ከሚታወቀው” የአገር ወይም የሚመለከተው ኢንዱስትሪ ወይም ኩባንያ ከሚገዛበት ሕግና ደንብ አይደለም፡፡ በአገራችን የስልክ መስመር መዘርጋት፣ የቴሌፎን አገልግሎት መስፋፋት የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይልን መስፋፋት እግር ለእግር እየተከተለ የመጣ አይደለም፡፡ “ሀሎ ደብረ ማርቆስ ማዞሪያው ደጀን ነው” ሲባል ደጀንና ምናልባትም ደብረ ማርቆስም ጭምር አልነበራቸውም ይሆናል ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ዛሬም ጭምር ኩራዝ ከነጭሱ ባልቀረበት ቦታ ወይም መብራት በተወሰነ ሰዓት ብቻ ምሽት በሚሰራበት ቦታ ወይም አዲስ አበባም ውስጥ በሻማ ማብራት ውስጥ ስንኖር የቤት ስልክ ያለን ስልኩ የሚያሰማውን የቃጭል ድምፅ የማስተጋባት ኃይል የሚያገኘው ከሌኤክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የንግድና የሽያጭ ኃይል ምንጭ አይደለም፡፡ የቴሌ ነው፡፡ በየክፍለ ሀገሩና በየክልሉ በቅርጻቸው የሚታወቁት የቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የማዞሪያ ህንጻዎች ዲዛይን ሲደረጉና ሲታነፁ አዲስ አበባም ሆነ ሌላ “አዲስ የሰፈራ ጣቢያ” የጀኔሬተራቸውን የባትሪያቸውን ማስቀመጫና መኖር ታሳቢ አድርገው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እንደማንኛውም “ደንበኛ” የሚያገኙት የኮረንቲ ጅረት ቢቋረጥ ጄኔሬተሩ ይቀጥላል፡፡ ጄኔሬተሩ ድንገት እምቢ ቢል ወይም ሌላ መጠባበቂያ ባትሪ አለ ወይም መኖር አለበት፡፡ ቴክኖሎጂው የተፈጠረው ከዚህ ስጋት እና ስጋቱን ለመቋቋም ከተዘየደው ብልሀት ጋር ነው፡፡ ዝርዝሩንና ውስጡን የሚያውቁት ባለሙያዎችና የተወሰኑ “የውስጥ አዋቂዎች” ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ምንም እንኳን ቋንቋውን ወደ ቀለል ያለና የኔቢጤ መሀይሙን ወደሚገባ አማረሽ መተርጐም ያለበት ቢሆንም በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ደንብ ቁጥር 47/90 የተደነገገ ይመስለናል፡፡ ይህም፣ 1ኛ. የፓወር ሲስተም ዲዛይንና ብቃት ከጠቅላላው ሲስተሙ ብቃት ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት፣ 2ኛ. ለማናቸውም የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያ የሚያስፈልገው የዳይሬክት ከረንት ቮልቴጅ 48 ቮልት ሊሆን እንደሚገባ፣ 3ኛ. የፓወር ሲስተም አቅርቦት ሬክቲፋይሮችን የጋራ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችንና የመጠባበቂያ ባትሪ ባንኮችን እንደሚጨምር፣ 4ኛ. ሬኮቲፋየሮች ቢያንስ 50 ፐርሰንት ክምችት አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ 5ኛ. የፓወር አቅርቦት አገልግሎት በሌለበት ቦታ ለቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያ የሚውል በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ፓወር ሲስተም መኖር ያለበት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የአገራችን የቴሌኮሙኒኬሽን ሕግ የመሸጋገሪያ ድንጋጌ (ሕጉ ከሚያዚያ 1991 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ነው) የቴሌኮመኒኬሽን አገልግሎቶች በመስጠት ላይ የሚገኘው ድርጅት (የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ማለት ነው"፤ ይህ ደንብ በሥራ ላይ ከሚውልበት ቀን ጀምሮ በ12 ወራት ውስጥ በዚህ ደንብ መሠረት የሚሰጡ አስፈላጊዎቹን ፈቃዶች ማውጣት እንዳለበት ሆኖም ግን የቴክኖሎጂ ምርጫና ዝርዝር የቴክኒክ ደረጃዎችን በሚመለከት (የፓወር ሲስተም፣ ዲዛይንና ብቃትን ጨምሮ) የተደነገጉት ተፈጻሚ የሚሆኑት ደንቡ (ሕጉ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ) አዲስ ለሚተከሉ የቴለኮመኒኬሽን ኢንስተሌሽኖች ብቻ መሆኑን ይወስናል፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ የቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ላይ ተፈጻሚ ስለሚሆኑት “የቴክኖሎጂ ምርጫና ዝርዝር የቴክኒክ ደረጃዎች” ብዙም ሆነ በዝርዝር መናገር የሚችሉት አሁንም “ቋንቋ”ው የሚገባቸው የውስጥ አዋቂዎች የኢንዱስትሪውም የቴክኖሎጂውም እውቀቱ ያላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን የገለፁልን ነገር ቢኖር የፊክስድ ላይን (የመደበኛ ባለሽና) ቴሌፎኖችን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከእነሱም መካከል የተነገረን የሁሉም ሳይሆን ኬብሉ ፋይበል ኦፕቲክ የሆነውን ብቻ ነው፡፡ ሞባይላቸው ኮፐር/መዳብ የሆኑትን የመቋረጥ ችግርም ሆነ ምስጢር አይነግረንም፡፡ የሞባይል ስልክ የዋየርለስ ስልክ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተያያዘ ችግርስ? ይህንንም መግለጫው አይናገርም፡፡ እዚህ ውስጥ ትልቁ ችግር የኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል እንዲሁም የቴሌ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመቋረጡ ችግር ሳይሆን ሁሉንም ዘርዝሮ ያለመናገሩ ጉዳይ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |