| የአካባቢ ምክር ቤት ጉባኤ በአራት... |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
የአካባቢ ምክር ቤት ጉባኤ በአራት ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳለፈ
ውሀና አየር በካይ ቆሻሻዎችን የሚመለከተው መመሪያ ፀደቀ በጋዜጣው ሪፖርተር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሠ ሰብሳቢነት የመጀመሪያው የአካባቢ ምክር ቤት ጉባዔ ባለፈው ረቡዕ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የተካሄደ ሲሆን ጉባዔው በአራት ያህል አካባቢያዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉ ተጠቆመ፡፡ ምክር ቤቱ እንደና ከተዋቀረ በኋላ ጉባዔውን ሲያካሂድ ይኼ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በአራት ያህል አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ተወያይቶ በሁለቱ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ ሁለቱን ለሌላ ጊዜ ለማየት ወስኗል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሔር በተለይ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደተናገሩት የኢንዱስትሪ ብክለት መከላከያ ደንብ ላይ ጉባዔው ተወያይቶ አንዳንድ ማሻሻያዎች እንዲደረጉበት ሃሳብ በመስጠት ረቂቅ ደንቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡ ከማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እና ከሌሎችም ተቋማት ወደውሀ እና አየር የሚለቀቁ ቆሻሻዎች ደረጃ ለመወሰን የወጣው የአካባቢ ደረጃዎች መመሪያ በዕለቱ ፀድቋል፡፡ ከእንግዲህ ፋብሪካዎችና ሌሎች ተቋማት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ቆሻሻ እንዳይለቁ መመሪያው ያግዳቸዋል ተብሏል፡፡ በዕለቱ በጉባዔው 0.03 ውፍረት ያላቸው የኘላስቲክ ውጤቶች የአካባቢ ብክለት መንስኤ ናቸው በሚል ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ወይም እንዳይመረቱ የሚከለክለውን አዋጅ ለማስፈፀም የወጣው መመሪያ በሌላ ጊዜ ለማየት ወስኗል፡፡ ባለሥልጣኑ ወሳኝ ለሆኑ ጥቅሞች ለምሳሌ ለሕክምና አገልግሎት የተጠቀሰው መጠን ኘላስቲክ ጥቅም ላይ እንዲውል በረቂቅ መመሪያው ውስጥ ተካትቶ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ የደህንነተ-ሕይወት ረቂቅ አዋጅ በዕለቱ በጉባዔው ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ለውይይት በቂ ጊዜ አይኖርም በሚል ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡ የአካባቢ ምክር ቤት ጉባዔ ሰብሳቢ አቶ አዲሱ ለገሰ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ሲሆኑ አባላቱም የክልል ኘሬዚዳንቶች፣ ሚኒስትሮች፣ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተወካዮች፣ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወካይ፣ የኢሠማኮ ተወካይ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካይ፣ አካባቢ ነክ ሥራ ላይ የተሰማሩ አገር በቀል ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ምክር ቤት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ፣ እንደአስፈላጊነቱም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ጉባዔውን እንደሚያካሂድ ዶ/ር ተወልደብርሃን ተናግረዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |