| የፌደራል ፖሊስ 500 ያህል አባላት... |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
የፌደራል ፖሊስ 500 ያህል አባላት ቤት ልቀቁ በመባላቸው ቅር ተሰኙ
በተሾመ ንቁ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ፈጥኖ ደራሽ በመባል የሚታወቀው የማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ 500 ያህል የፌደራል ፖሊስ የልዩ ኃይል አባላት የመኖሪያ ቤት ልቀቁ በሚል ሰበብ የደመወዝ እገዳ እንደተካሄደባቸው አስታወቁ፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የደመወዝ እገዳው እንዳልተካሄደ ነገር ግን መኖሪያ ቤቶቹን መልቀቅ እንዳለባቸው አስታወቀ፡፡ በግቢው ውስጥ የሚገኙትን ቤቶች በመኖሪያ ቤትነት በመጠቀም ለአመታት ሲኖሩበት እንደነበረ የጠቀሱት እነዚሁ የፖሊስ አባላት "ቤቱን ልቀቁ መባላችን አግባብ አይደለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ የካምፑ አስተዳደር ግቢውን በምን ምክንያት መልቀቅ እንዳለባቸው ያላስረዳቸው መሆኑን የገለፁት የፖሊስ አባላቱ፤ "በድንገት በአጭር ጊዜ ውስጥ ልቀቁ" ተብለናል ሲሉ አማርረዋል፡፡ የፖሊስ አባላቱ ከፌደራል ፖሊስ በተሰጣቸው ፈቃድ ለረጅም ጊዜ በካምፑ ውስጥ ቤተሰብ መስርተው እንደሚኖሩ በመግለጽ "በዚህ የኑሮ ውድነት ለረጅም ጊዜ ከኖርንበት ቤታችን ልቀቁ መባላችን ተገቢ አይደለም" ይላሉ፡፡ አባላቱ በማከልም ቤቶቹ ለፖሊስ አባላት መኖሪያነት የተገነቡ መሆኑን በማስታወስ በፖሊስ አባልነታችን ደግሞ በካምፑ ውስጥ የመኖር መብት አለን በማለት ተናግረዋል፡፡ የካምፑ አስተዳደር ግቢውን ካልለቀቃችሁ በማለት ደመወዛቸውን ያገደባቸው መሆኑን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ ደመወዛቸው ከታገደ ሁለተኛ ወራቸውን እንደያዙ የሚናገሩት የፖሊስ አባላቱ "የሰራንበትን ደመወዛችን መታገዱ ያሳዝናል" ሱሉ ወቅሰዋል፡፡ በዚህም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ቤተሰቦቻቸው ጋር ለችግር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክተን ጥያቄ ያቀረብንላቸው አንድ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ከሶስት ዓመት በላይ ግቢውን እንዲለቁ ለአባላቱ በደብዳቤና በቃል መገለፁን አረጋግጠዋል፡፡ አባላቱ ግን እንቢተኛ ሆነው በመቆየታቸው የካምፑ እንዲሁም የኮሚሽኑ አስተዳደር እየተነጋገሩበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ መልኩ በአባላቱ ላይ የደመወዝ እገዳ ስለመካሄዱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እኚሁ ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡ ኃላፊው አያይዘውም ካምፑ ወታደራዊ ማሰልጠኛ እንጂ መኖሪያ ግቢ አለመሆኑንና በካምፑ ውስጥ አሰልጣኞችና ሰልጣኞች ብቻ የሚኖሩበት ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ጡረተኛ እንዲሁም በስራ ላይ የሚገኙ የሰራዊት አባላት በግቢው ውስጥ ከነቤተሰቦቻቸው በመኖራቸው፤ ግቢው ከማሰልጠኛነት አልፎ የመጠለያ ካምፕ መምሰሉን ገልፀዋል፡፡ በዚህም በማሰልጠኛ ካምፑ ሥራ ላይ ተጽዕኖ መፍጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡ በካምፑ ውስጥ የሚስተናገዱ አባላት ከመብዛቱ የተነሳ የካምፑን ደህንነት መቆጣጠር አለመቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ በግቢው ውስጥ የሚኖሩ የሰራዊቱ አባላት መንግሥት ቤት ሊያዘጋጅላቸው እንደማይገባና እንደማንኛውም የመንግሥት ሰራተኛ በግላቸው የቤት ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደሚገባቸው አስታውቀዋል፡፡ በካምፑ ውስጥ ከሚኖሩ ግለሰቦች መካከል ኮንዶሚኒየም ቤት የደረሳቸው፣ የመኖሪያ ቤት የሰሩ እንደሚገኙና በማከራየት ጥቅማ ጥቅም የሚያገኙ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |