| በቴዲ አፍሮ የዋስትና ጥያቄ ላይ... |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
በቴዲ አፍሮ የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ተቀጠረ ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሻለ
በታምሩ ጽጌ በከሳሽ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግና በተከሳሽ በአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ጠበቃ መካከል ሚያዚያ 15 ቀን 2000 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት (ፍትሕ አዳራሽ) የተደረገውን ክርክር ተመልክቶና ከሕግ ጋር አመሳክሮ ብይን ለመስጠት ፍ/ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ሚያዚያ 15 ቀን 2000 ዓ.ም አሻሽሎ ባቀረበው ክስ፣ ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ እና የትራንስፖርት ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 279/1956 አንቀፅ 5/4/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ወንጀል ፈፅሟል በሚል ሁለት ክስ መስርቷል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በአንደኛ ክሱ፣ እንደጠቀሰው "ተከሳሹ ለማሽከርከር የሚያስችል መንጃ ፈቃድ ሊኖረው እንደሚገባ የሚያዘውን ግልፅ የሆነ ደንብ በመተላለፍ መንጃ ፈቃድ ሳይኖረው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ሲሆን በሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-59869 አ/አ ቢ.ኤም.ደብሊው አውቶሞቢሉን እያሽከረከረ ሲጓዝ በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 ልዩ ቦታው ፊት በር በተባለ አካባቢ ሲደርስ መንገዱን ከቀኝ ወደ ግራ በማቋረጥ ላይ የነበረውን ሟች ደጉ ይበልጣል የተባለውን ቅድሚያ በመከልከል ገጭቶ በመግደሉ በፈፀመው በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል ተከሷል" ይላል፡፡ በሁለተኛ ክሱ ደግሞ እንደገለፀው፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 575/2/ሀ/ የተመለከተውን በመተላለፍ፣ ተከሳሹ በአንደኛው ክስ በተጠቀሰው ጊዜና ቦታ፣ የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-59869 አ/አ የሆነ ቢ.ኤም.ደብሊው አውቶሞቢሉን እያሽከረከረ ሲጓዝ ሟች ደጉ ይበልጣልን ከገጨ በኋላ፣ ተገጪው ሕይወቱ በከባድ አደጋ ላይ መሆኑን እያወቀ እርዳታ ሳያደርግለት ጥሎት በመሸሹ በፈፀመው በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት ወንጀል ተከሷል በሚል ዐቃቤ ሕግ እሱን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ አራት የሰውና አምስት የፅሁፍ ማስረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ በፅሁፍ ማስረጃዎቹ ሟች ላይ የደረሰውን አደጋ የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ፣ ሟች የተገጨበት ተሽከርካሪ ሰሌዳ ቁጥር የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ የዳግማዊ ምኒሊክ የአስከሬን ምርመራ ውጤት፣ አደጋው የደረሰበትን ቦታ የሚያሳይ የትራፊክ ፕላንና የአውቶሞቢሉ የቴክኒክ ምርመራ ውጤት አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተሻሻለው የክስ ቻርጅ ለተከሳሽ እንደደረሳቸውና እንዳልደረሳቸው አረጋግጦ፣ በክሱ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ክሱ እንደደረሳቸው አረጋግጠው፣ "አንደኛው ክስ ከማስረጃዎቹ ጋር ተያይዞ ሲታይ፣ የፕላን እንጂ የዓይን እማኝ መኖሩን አያረጋግጥም፡፡ በመንጃ ፈቃዱም ላይ ማስረጃ አልቀረበም፡፡ የፕላን ማስረጃውም ቢሆን ሞቶ የተገኘበትን ቦታ እንጂ፣ ሲገጭና ሲገድል የሚያሳይ የዓይን እማኝን ማስረጃ አያሳይም፡፡ ዐቃቤ ሕግ አራት የሰው ማስረጃዎች አሉኝ የሚላቸው፣ ትራፊክ ፕላን ሲያነሳ በትክክል በቦታው ላይ (ሞቶ የተገኘበትን) ሲያነሳ ማየታቸውን የፈረሙ ከመሆናቸው ውጭ ድርጊቱ ሲፈፀም አይተናል በማለት የሚመሰክሩ የዓይን እማኞች አይደሉም" በማለት ደንበኛቸው በበቂ ዋስትና ተለቀውና በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ተከሳሹ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ ከአምስት ዓመት እስከ 15 ዓመት ድረስ የሚያስቀጣቸው በመሆኑ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ሆኖ በማረሚያ ቤት ሆነው ይከራከሩ ሲል ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሁለቱም በኩል የቀረበውን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ ሁለቱ ወገኖች ያደረጉትን ክርክር ከሕግ አኳያ ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ሚያዚያ 13 ቀን 2000 ዓ.ም ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሚያዚያ 15 ቀን 2000 የተሻሻለውን ክስ ለመስማትና አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁንን ለማየት ደጋፊዎቹ ከጠዋቱ 1፡30 ጀምሮ በፍርድ ቤት በመገኘት በፍርድ ቤቱ አጥር ዙሪያ ተሰልፈው ታይተዋል፡፡ በዕለቱ ከልደታ ማርያም ጀምሮ ግራና ቀኝ እስከ ወይን ጠጅ ፋብሪካ ድረስ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ እንዳይቆም በብዛት የተሰማሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሲከለክሉ ተስተውለዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ የሥራ ሰዓት ሲደርስ በሦስት ረድፍ (በፌዴራል ፖሊስ) እየተፈተሸ የገባው ለተለያየ ጉዳይ የሚገባው የህብረተሰብ ክፍል፣ የ8ኛ ወንጀል ችሎትን በር በመክፈትና ቴዲ አፍሮ ሲገባ ለማየት ሁሉም ቆሞ ቢጠባበቅም ሳይመጣ በዚያው ቀረ፡፡ ሚያዚያ 13 ቀን 2000 በዋለው ችሎት የነበረውን ሕዝብ ብዛት በማሰብ የቴዲ አፍሮ ጉዳይ በርካታ ሰዎችን በሚይዘው ሦስተኛ ወንጀል ችሎት (ፍትሕ አዳራሽ) ተዛውሮ እንዲታይ በመደረጉ ቤተሰቦቹ፣ አድናቂዎቹና ጋዜጠኞች ችሎቱን ተከታትለዋል፡፡ በዕለቱ የተሰሙት ብቸኛ ዳኛ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ችሎቱን ጨርሰው ሲመለሱ፣ አርቲስቱን ፖሊሶች ይዘው ሊወጡ ወደ በር ሲያመሩ ችሎቱን ሲከታተሉ ከነበሩት ውስጥ ጩኸት በማሰማታቸው ቴዲ አፍሮን ወደ ዳኞች ማረፊያ ክፍል ይዘው በመግባት ሕዝቡ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ከፍርድ ቤቱ ውስጥ የተሰማው የፉጨትና የጩኸት ድምፅ፣ ከውጭ የአርቲስቱን የፍርድ ቤት ውጤት ሲጠባበቅ የነበረው ደጋፊ በመቀበል ጩኸትና ፉጨት በመጀመራቸው፣ አድማ በታኝ ፖሊሶች ተሰማርተው ግርግርሩ በቀላሉ ሊረግብ ችሏል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |