|
Saturday, 26 April 2008 |
|
ቦታው ከ10 ሺህ ህዝብ በላይ እንደሚኖርበት በሚነገርለት የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ከፋብሪካው ፊት ለፊት በሚገኝ ሰፋ ያለ ሜዳ ላይ የተከመረውን አሸዋ እየዛቁ በማመላለስ ሥራ ላይ በርከት ያሉ ሰዎች ይረባረባሉ፡፡ ከመካከላቸው ሁለት ሻሽ ያሰሩና ወገባቸውን የታጠቁ ሴቶችም ላባቸውን ጠብ በማድረግ ሲሰሩ ተመለከትኩ፡፡ በፋብሪካው ግቢ ውስጥ በር ላይ በፈታሽነት፣ በሆስፒታሉ ውስጥ ከሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችና የቢሮ ሰራተኛ ከሆኑ ጥቂት ሴቶች በስተቀር በቦታው በተገኘሁበት ወቅት በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው ያስተዋልኳቸው ሴቶች እነኚህ ብቻ ነበሩ፡፡
እጅግ ሰፊና ውስብስብ በሆነው የመተሃራ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ወደ ላይና ወደ ታች እየወጡ እየወረዱ ሥራቸውን ከሚያከናውኑት መካከል ሴት ሰራተኛ አላየሁም፡፡ የሥራ ቱታ ለብሰው የሚሰሩት ሁሉ ወንዶች ናቸው፡፡ ሴቶች የሚሰማሩት በፅዳት ሥራው ላይ ብቻ እንደሆነ ተገለፀልኝ፡፡ አካፋ የጨበጡት ሁለት ሴቶች ግን አካላዊ ጥንካሬ የሚጠይቀውን የጉልበት ሥራ ተያይዘውታል፡፡
በእድሜ ጠና ያሉት እናት ወይዘሮ ፅጌ አስማማው ይባላሉ፡፡ እድሜያቸውን በትክክል አያወቁትም፡፡ ህይወትን ለማሸነፍና ልጆቻቸውን ለማሳደግ በቀን ሥራ የተሰማሩት ከስድስት ወር ወዲህ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ወደ ሥራ ለመግባት የተገደዱትም ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩበት አማራጭ ስላጡ እንደሆነ ገልፀውልኛል፡፡
ተወልደው ያደጉት ወሎ ክፍለ ሃገር መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ ፅጌ መጀመሪያ ወደ መተሃራ ሲያመሩ ያገኙትን ሰርተው ራሳቸውን ለማስተዳደር ነበር፡፡ ሰው ቤት በሰራተኝነት ገብተው ጥቂት ዓመታትን እንደሰሩ በአካባቢያቸው በጉልበት ሥራ የሚተዳደረውን የልጆቻቸውን አባት ተዋውቀው ትዳር መሰረቱ፡፡
ባለቤታቸው በፋብሪካው ውስጥ ሸንኮራ አገዳ እየኮተኮቱና ሌሎች የጉልበት ሥራዎችንም እየሰሩ ያስተዳድራቸው እንደነበር እኒሁ እናት ገልፀውልኛል፡ ባለቤታቸው በነበሩ ወቅት እሳቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከማከናወን ውጭ ምንም አይነት ገቢ የሚያስገኝ ሥራ አይሰሩም ነበር፡፡ ባለቤታቸው ሰርቶ የሚያመጡት ገንዘብ መጥነው በማብቃቃትና ለምግብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በመገዛዛት ቤታቸውን ይመሩ ነበር፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ከስድስት ዓመት በፊት ባለቤታቸው በሞት ሲለዮዋቸው የወለዷቸውን አራት ልጆች የማሳደግ ኃላፊነት እሳቸው ላይ ብቻ ወደቀ፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ጠላ እየጠመቁ መሸጥና በኋላም መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ምግብ እየሰሩ በመሸጥ ኑሮን ተያያዙት፡፡ በጉልበት ሥራውና በማስተናገዱ ልጆቻቸው ያግዟቸው ነበር፡፡ ከዛ ውጭ ግን ምግቡን የሚሰሩትም ሆነ ጠላውን የሚጠምቁት ብቻቸውን ነው፡፡ ሌሊት ተነስተው እንጀራ ሲጋግሩ ወጥ ሲሰሩ ያድራሉ፡፡ ቀን ደንበኞቻቸውን በማስተናገድና እቃ በማጠብ ሲዋከቡ ይውላሉ፡፡ ሥራው ልፋት ቢኖረውም አትራፊ እንደነበርና ልጆቻቸውንም ሳይቸገሩ ማስተዳደር ችለው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለይ የመተሃራ ገበያ በሚቆምበት ቀን ምግቡም ሆነ ጠላው እንደልብ እንደሚሸጥላቸውም ገልፀዋል፡፡
ወ/ሮ ፀጋ እንደሚሉት ጠላ እየሸጡ ይተዳደሩበት የነበረውና ልጆቻቸውንም ያሳደጉበት ..ኩይሳ ቤት.. ነበር፡፡ የሳቸውን ቤት ጨምሮ የሌሎችም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤት ያለበትን ቦታ ድርጅቱ ይገባኛል በማለት ከወረሰው በኋላ ግን ቤታቸው ስለፈረሰ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት የነበረው የጠላ ሥራም ቀርቷል፡፡
..አሁን ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ ለአንዲት ክፍል ቤት 30 ብር እየከፈልኩ አራት ልጆችን ይዤ እኖራለሁ፡፡ በኪራይ ቤት እንደፈለግሽ ምግብና ጠላ መሸጥ አትችይም፡፡ ልሽጥ ብትይም የምታበስይበትና የምትሸጭበት ቦታ የለም.. ይላሉ፡፡
የጠላ ንግዳቸው ከተቋረጠ በኋላ በምን ሥራ ተሰማርተው ልጆቻቸውን እንደሚያሳድጉ ግራ የገባቸው ወ/ሮ ፅጌ በፋብሪካው ውስጥ የግንባታ ሥራ ስለሚከናወን የጉልበት ሰራተኞች እንደሚፈለጉ ሲሰሙ በደስታ መፍነክነካቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ..ለጊዜው በነበረችኝ ብር ቤት መከራየት ችለናል፡፡ እኔም ልጆቼም እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብንል ምን የሚበላ ይገኛል፡፡ በጣም ተጨንቄ ሳለሁ ይሄንን የጉልበት ሥራ አገኘሁ፡፡ በሁለት ሳምንት 112 ብር ይከፍሉኛል፡፡ ቁጭ ከማለት ይሻለኛል.. የጉልበት ሥራው አድካሚ አይደለም ወይ? ብያቸው ነበር ..አራት ልጅ የወለደ ወገብ መንቀጥቀጡ አይቀርም፡፡ ማን ይለቀዋል፤ ታጥቄ ይዤዋለሁ.. አሉኝ ፈገግ እያሉ፡፡
የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ፅጌ ላባቸውን ሲያንጠፈጥፉ ውለው የሚያገ..ትን ገንዘብ ለማብቃቃት ይጥራሉ፡፡ ጤፍና ማሽላ እየቀላቀሉ በማስፈጨት እንጀራ ይጋግራሉ፡፡ እንዲህ ከገበያው ረከስ ያለውን እህል እየገዙ የልጆቻቸውን ሆድ ሞልተው ለማደር እየጣሩ ነው፡፡ የዘንድሮውን የፋሲካ በዓልም ዶሮ አርደውና እንደ አቅማቸው ተደስተው ለመዋል እንደተዘጋጁ ነግረውኛል፡፡ ..እንደ ድሮው ጠላ መጥመቅ፣ ቅርጫ ማስገባት ባላስብም ከልጆቼ ጋር ደስ ብሎኝ ለመዋል አንድ ዶሮ ገዝቻለሁ..
ሁለተኛዋ በጉልበት ሥራ ተሰማርታ ከወንዶች መካከል ያገኘናት ደግሞ ትዕግስት ኦላና ትባላለች፡፡ እድሜዋ ከ25 እንደማይበልጥ ትገምታለች፡፡ እሷም እንደ ወ/ሮ ፅጌ ወደ መተሃራ የመጣችው እየሰራች ራሷን ለማስተዳደር ነው፡፡ እሰው ቤት ውስጥ በሰራተኝነት ተቀጥራ ብዙ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ ተቀጥራ የምትሰራባቸው ሰዎች በፋብሪካው ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ነበሩ፡፡
ከዓመት በፊት ከሰው ቤት ሰራተኝነት ወጥታ ትዳር በመመስረት የራሷን ኑሮ ጀምራለች፡፡ ባለቤቷ በፋብሪካው ውስጥ ሰራተኛ ቢሆንም የሚሰራበትን የስራ ዘርፍ በትክክል አታውቀውም፡፡ ሁለቱም የገቢ ምንጭ ኖሯቸው የወደፊት ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ እየጣሩ እንደሆነ ትናገራለች፡፡
ትዕግስት በእድሜም ወጣት እንደመሆኗ ከወ/ሮ ፅጌ በተሻለ በአካፋ አሸዋ ስትዝቅና ተሸክማ ስትመላለስ የድካም ስሜት አይነበብባትም፡፡ እስካሁን ልጅ ያልወለደች ሲሆን ለወደፊቱ ግን የመውለድ እቅድ አላት፡፡ ያኔ የጉልበት ሥራውን ልታቆም እንደምትችልና የባሏ ጥገኛ እንደምትሆን ግምቷን ገልፃልኛለች፡፡ ወይዘሮ ፅጌስ ሥራቸውን እንዲያቆሙ የሚገደዱባት አጋጣሚ ቢመጣ የማን ጥገኛ ይሆኑ ይሆን?
ትዕግስትና ባለቤቷ ሰርተው በሚያገ..ት ጥቂት ገንዘብ ፋብሪካ ግቢው ውስጥ በተሰጠቻቸው ቤት ደስተኛ ህይወት እየኖሩ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ዘንድሮ ትዳር የያዘችበት የመጀመሪያ ዓመት እንደመሆኑ የዘንድሮውን የፋሲካ በዓልም በተለየ ሁኔታ ለማክበር ተዘጋጅታለች፡፡ በሰው ቤት ሰራተኝነት እያለች በዓልን ስታከብር በዓል መሆኑን አጣጥማው እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡ ..የቤት ሰራተኛ ስትሆኚ የበዓል ቀን እንዲያውም ከሌላው ቀን በበለጠ ስራ ይበዛብሻል፡፡ ፅዳቱም፣ ምግብ መስራቱም አድካሚ ነው፡፡ ባለቤቶቹ የፀዳ ለብሰው ደስ ብሏቸው ሲያሳልፉ ታያለሽ እንጂ አንቺ በሥራ ስትጣደፊ ውለሽ ከኩሽናሽ አትወጭም፡፡ ልብሴን ቀይሬ ደስ ብሎኝ ያሳለፍኩትን በዓል አላስታውስም.. ትላለች፡፡ ዘንድሮ ግን በጉልበት ሥራ ተሰማርታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ባለቤቷም እሷም አዲስ ልብስ እንደገዙ፣ ለበዓል ዶሮ እንደሚያርዱና ጠላ እንደጠመቀች በዓሉንም የቤት ባለቤትነት ስሜት እየተሰማት እንደምታሳልፈው በደስታ ገልፃልኛለች፡፡
ከቀን ሰራተኛ ወንዶች መካከል ያገኘኋቸው ሁለቱ ሴቶች ኑሮን ለማሸነፍ ጉልበትን የሚጠይቅ ሥራ ከጎረምሶች ጋር እኩል እየሰሩ ነው፡፡ ግንባታው ተጠናቆ የቀን ሰራተኝነታቸው ሲቀር ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ ሁለቱም እርግጠኞች አይደሉም፡፡ በትዕግስት ዘሪሁን |