| ክትትል ይደረግ |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
የመጋቢት 21 ቀን 2000 ዓ.ም እና መጋቢት 28 ቀን 2000 ዓ.ም የሪፖርተር ጋዜጣ ርዕስ አንቀጾችን በደንብ ተመልክቻቸዋለሁ፡፡
"ኢሕአዴግ ራሱን ይመርምር"" እና "እርስዎ ከየትኛው ወገን ነዎት?" የሚሉትን፡፡ አዎን ኢሕአዴግ ራሱን መመርመር አለበት፡፡ በቢፒአር ሰበብ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች እንደሚወጡ ይህም የሆነው ኃላፊነት በጐደላቸው ባለሥልጣናት መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ የቢፒአር መሠረተ ሃሳብን በጣሰ መልኩ፣ የተቀመጠ ትክክለኛ መስፈርት እያለ በእነሱ በጐ ፍቃድና ፍላጐት ብቻ ሠራተኛውን እንፈለጋቸው እያደረጉት ስለሆነ መንግሥት ክትትል አድርጎ ንፁሐን ሠራተኞች ለችግር እንዳይጋለጡ መታደግ አለበት፡፡ (ከገቢዎች ሚኒስቴር ሠራተኞች አንዱ) የፖለቲካ ግሬድ በአሁኑ ጊዜ የ3ኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስሆን እኔ በምማርበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚካሄደው ፖለቲካ በትምርት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረገ ነው፡፡ በአካዳሚክ ውጤት "ኤ" ወይም "ቢ" ከማምጣት ይልቅ በፖለቲካው ተሳታፊ ሆኖ "ኤ" በማምጣት በማይመጥነው ቦታ ለመቀመጥ የሚፈልገው ተማሪ ብዙ ነው፡፡ ህዋስ የሚባሉት ተማሪዎች (የፖለቲካ አስተባባሪዎች) የፖለቲካ ግሬድ በሚሰጡበት ጊዜ "ኤ" ወይም "ቢ" የማግኘት ዕድል ያላቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው ወይም የወንዛቸው ልጆች መሆን አለባቸው፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ለዚህ አልታደልንም፡፡ ተመርቀን ስንወጣ ልንቀጠር የምንችለው በፖለቲካ ግሬድ እንጂ በትምህርት ውጤት እንዳልሆነ እናውቀዋለን፡፡ በፖለቲካ "ኤ" ወይም "ቢ" ይዞ በአካዳሚኩ 2.50 የሆነ ተማሪ ቁልፍ ቦታዎችን ሲይዝ በፖለቲካው ግሬድ ከ"ሲ" በታች በአካዳሚክ ደግሞ ከ3.00 በላይ ይዘው የወጡት ተማሪዎች ማንም ጉዳዬ አይላቸውም፡፡ ምናልባት መያድ ሊገቡ ከቻሉ ነው እንጂ፡፡ ለሀገሪቱ የሚበጀው የትኛው ነው? ቅጥር በፖለቲካ ግሬድ ከሆነ ለምን መልፋት አስፈለገ? (ኤ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ህገወጥ የመሬት ወረራ መከላከል ለምን በአዲስ አበባ ብቻ አተኮረ? በአዲስ አበባ በሕገወጥ መንገድ ማህበራትን በማደራጀት የመንግሥትና የሕዝብ መሬት ሲቸበችቡ በነበሩ ግለሰቦች ላይ መንግሥት እየወሰደው ያለው እርምጃ አስደስቶኛል፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብም የእነዚህን ህገወጥ እንቅስቃሴ ለሚመለከታቸው የፍትህ አካላት በማሳወቅ እየተወጣው ያለው የዜግነት ግዴታ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተመሳሳይ የመንግሥትና የሕዝብ መሬት ወረራ ያልቆመበትና እንዲያውም በባሰ መልኩ የተቀጠለበት አካባቢ መኖሩ ሲታይ ለምን በአዲስ አበባ ብቻ መከላከሉ እንደተመረጠ ግራ የሚያጋባ ይሆናል፡፡ በመቀሌ ከተማ በማህበራት ስም የሚሰጠው መሬት ምን ዓይነት ቅድመ መጣራት ይካሄድበታል? በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ሰዎች በከተማው ውስጥ የራሳቸው ቤት ይኑራቸው አይኑራቸው በደንብ የሚረጋገጥ አይመስለኝም፡፡ በድጋሚ ቦታ የተሰጣቸው እንዳሉ አይቻለሁ፡፡ የክልሉ የስነ ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ያለሊዝ ጨረታ በሕገወጥ መንገድ እየተካሄደ ያለውን የመንግሥትና የሕዝብ መሬት ወረራ ለማስቆምና ሙሰኞችን ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራ እስካሁን ባለመሥራቱ ችግሩ እየተባባሰ ነው፡፡ በሕገወጥ መንገድ ቦታ የወሰዱት ሳይውል ሳያድር ተጣርቶ ለሕግ መቅረብ አለባቸው፡፡ (ኮከበ ፅባህ፣ ከመቀሌ) የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ባለፈው ረቡዕ በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ ከቅንጅት ፓርቲ መታገዴን አንብቤያለሁ፡፡ የፓርቲው ሊመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ ከወ/ት ብርቱካን እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር በመሆን አፍራሽ እንቅስቃሴ አድርገሀል በማለት በተደጋጋሚ ወንጅለውኛል፡፡ ለዚህም ከወ/ት ብርቱካን ጋር ፎቶ ተነስተሀል ተብያለሁ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ደካማ አመራር መኖሩን ጠቅሼ በመተቸቴ ውንጀላ ተመስርቶብኛል፡፡ አቶ አየለ ጫሚሶ በፓርቲው ውስጥ የአካባቢያቸውን ተወላጆች በማብዛት ሌላውን የማግለል እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ ስለፓርቲው እንዲሁም ስለ ፓርቲው ሊቀመንበር የውሸት ፕሮፖጋንዳ እንድናገር የታዘዝኩትን ባለመፈፀሜ፣ ከፓርቲው አመራር አካላት ጋር ቅራኔ ፈጥሬአለሁ፡፡ በአጠቃላይ በፓርቲው ውስጥ ባለው አሰራር የማላምን በመሆኔ ራሴን ከፓርቲው ማግለሌን በቃል ለፓርቲው አመራር አካላት አስታውቄያለሁ፡፡ ይህንን ተከትሎ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተመስርቶብኛል፡፡ (አቶ ተስፋዬ አድማሴ፣ የሰሜን ሸዋ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ተወካይ) የትራንስፖርት እጥረትን ማቃለል ወይስ ማባባስ? በአዲስ አበባ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓታት ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት መኖሩ ግልፅ ነው፡፡ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ የሚካድ ባይሆንም ችግሩን ግን በሚፈለገው ፍጥነትና ደረጃ አልተቃለለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ ከሚያዚያ 16 ቀን 2000 ዓ.ም ጀምሮ የክልል ሰሌዳ ያላቸው ሚኒባሶች እንዳይሠሩ በመከልከላቸው በመጠኑም ቢሆን እየተቃለለ የነበረው የትራንስፖርት ችግር ተመልሶ ተባብሷል፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይህን እርምጃ እንዴት ሊወስድ እንደቻለ ግራ አጋብቶኛል፡፡ ሕዝቡ ማማረር ጀምሯል፡፡ በሕዝብ ችግር የሚደሰቱ ኃላፊዎች ካሉ ወደ ሕሊናቸው እንዲመለሱ አሳስባለሁ፡፡ (ሹምዬ መልአኩ፣ ከአዲስ አበባ በስልክ የተሰጠ አስተያየት) ከአፍራሽ ድርጊታቸው ይቆጠቡ እሁድ ሚያዚያ 5 በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ አርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማህበር ተከራይን በሚመለከት የወጣው ጽሑፍ ትክክል አይደለም፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ኩባንያው ምቹ የሥራ አካባቢን የመፍጠር፣ የማኔጅመንት አቅም ችግር የነበሩበት ሲሆን ለመዘጋትም ተቃርቦ ነበር፡፡ ብቃት ያላቸው ሠራተኞች፣ የሰው ኃይልና የማኅበራዊ ዋስትና ችግሮች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን፣ የንግድ አጋሮችና አበዳሪዎች ያልተከፈሉ እዳዎች ነበሩበት፡፡ ከሁሉም በላይ ከጥቅም ውጭ በሆኑ ማሽኖች ሠራተኞች ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡ ነገር ግን ከአዋሳ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማኅበር ጋር በመሆን በጋራ መሥራት ከጀመረ በኋላ ጥሩ የምርት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተወዳዳሪ ለመሆን ችሏል፡፡ በዚህ ሂደት የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ የዳይሬክተሮች ቦርድ እርዳታ ያደረገ ሲሆን ለዚህም በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ሽልማቶችን ለማግኘት ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኩባንያው በወጪ ንግድና እዳን በመክፈል መልካም ገጽታን ያተረፈ ሲሆን ሽያጩም ጨምሯል፣ ደመወዝ በጊዜው ይከፍላል፣ የሠራተኛ ማሕበሩና ማኔጅመንቱ ከተስማሙበት በበለጠ ለሠራተኞች ዓመታዊ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ በእፎይታ ጊዜውም የባንክ ብድርን ጨምሮ 18 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር እዳ ከፍሏል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች አንዳንድ ግለሰቦች ባይረኩም የእኛ ትኩረት አጠቃላይ ሠራተኛው፣ ማኔጅመንቱና ተገልጋዮች እንዲሁም የምርት አጋሮቻችን ላይ ነው፡፡ ከሥራ የታገዱ ሠራተኞች የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማደፍረስና የኩባንያውን ገጽታ ለማበላሸት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ እናሳስባለን፡፡ (ሐቢብ ናሪን፣ የአርባ ምንጭ ጨርቃጨርቅ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ) |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |