| ፌዴራሊዝም ፈልገነው ወይስ አስፈልጎን? |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
በየማነ ናግሽ
የተለያዩ አገሮች እንደየራሳቸው ታሪክ፣ አፈጣጠርና የውስጣቸው ፖለቲካዊና መልክዐ ምድራዊ ሁኔታ የሚጣጣም ሥርዓት ይከተላሉ፡፡ አገራችን ላለፉት 17 ዓመታት የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ስትከተል የቆየች ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በፅንሰ ሃሳቡ ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝተው፣ ተወያይተውበት ጥቅሙንና ጉዳቱን ለይተው እንደ አማራጭ ተቀብለውት ተስማምተውበት የጋራ መግባባት የፈጠሩበት አይደለም፡፡ በመሆኑም በተለይ "ምርጫ" በመጣ ቁጥር የክርክርና የጭቅጭቅ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሁለት ጽንፍ አመለካከቶች ይስተዋላሉ፡፡ በአንድ በኩል ሥርዓቱ ፀረ አንድነትና አገር የሚበትን "የጎሰኝነት" አስተሳሰብ የሚያስፋፋ ተደርጎ አሉታዊ ቀለም ይቀባል፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ አንድነትና ህልውና ለማስጠበቅ አማራጭ የሌለውን ብቸኛው መንገድ ተደርጎ ይመጣል፡፡ ፌዴራሊዝም ፈልገነው ወይስ አስፈልጎን ነው? ከአንድ ፓርቲ ስልጣን ላይ መቆየት የሚያያዝ ጉዳይ ወይስ ከፓርቲ አቋምና አመለካከት ነፃ ሆኖ በፖለቲካ ማዕበል የማይለወጥና የማይይነቃነቅ ቀጣይነት ያለው ነቢብ ሆኖ መቆየት አለበት? ፌዴራሊዝም የሚፈጥራቸው ችግሮች አሉ ወይስ የችግር መፍትሄ ብቻ ነው? በያዝነው ወር መጀመሪያ (ሚያዝያ 1 እና 2) የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲቨሎፕመንት ፕሮግራም ጋር በመተባበር "ፌዴራሊዝም፣ ዴሞክራሲና ህገመንግሥታዊነት በኢትዮጵያ" በሚል ርእሰ ጉዳይ ለሁለት ቀናት ውይይት አዘጋጅተዋል፡፡ የተለያዩ የሲቪል ማህበራት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራንና የሚመለከታቸው የመንግስትን የግል ተቋማት ተወካዮችና ተጋባዦች የተገኙበት መድረክ ነበር፡፡ በርእሰ ጉዳዮች ላይ ለውይይትና ክርክር መነሻ የሆኑት አራት የጽሁፍ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ደግፌ ቡላ፣ በመድረኩ የተገኙት ተወያዮች በርእሰ ጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውን በግልፅና በነፃነት እንዲያቀርቡ በመጋበዝ መድረኩን ከፍተዋል፡፡ የፎረም ፎር ዲሞክራሲ (FFD) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳ ገ/ሕይወት በበኩላቸው የመድረኩን አስፈላጊነት አስመልክተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በፌዴራል የሥርዓት አወቃቀር ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝተው መግባባት እንዲፈጥሩና የጋራ የፖለቲካ አቋም ለመያዝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከቀረቡት የጥናት ጽሁፎች በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የፌዴራሊዝም ተቋም ምክትል ዳይሬክተር በሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ንጉስ "ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ፌዴራሊዝምን በማጎልበት ረገድ ያላቸው ሚና" በሚል ርእስ የቀረበ ነው፡፡ ስልጣናቸው በህገመንግሥቱ የተወሰነ ሁለት መንግሥታት መኖራቸው፣ በፌዴራል መንግሥት ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕገ መንግሥታዊ ስልጣንና ኃላፊነት፣ በሶስቱም የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ መካከል ያለው የስልጣን ክፍፍልና ሚዛናዊነት ሌሎች የመንግሥት ተቋማትም እርስ በርሳቸው መካከል ያለውን ግንኙነት፣ እንዲሁም በፓርላመንታዊና ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓቶች በፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ያለውን ልዩነትና ተመሳሳይነት አስመልክቶ በአገራችን ውስጥ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በማዛመድ ጽሁፋቸውን አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ሰለሞን የፌዴራል ተቋማት ነፃነት፣ ሚዛናዊነት በተለይ ደግሞ በክልልና በፌዴራል መንግሥት ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት በእኩልነትና ተቋማዊ በሆነ መንገድ የተመሰረተ መሆኑ፣ በአንድ ፓርቲና በመድብለ ፓርቲ የሚተዳደሩ አገሮች በፌዴራል አወቃቀር ሥርዓት ሊኖረው የሚችል ተፅዕኖና ሌሎች ጥያቄዎች አንስተው ለውይይት የመነሻ ሃሳብ እንዲሆኑ ክፍት አድርገዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ፍትህ ቢሮ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት የሚገኙና የህግ ባለሞያ የሆኑት አቶ ደዋኖ ከድር "ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊነት፣ አተገባበርና ፈተናዎቹ" በሚል ነበር ፅሁፋቸውን ያቀረቡት፡፡ እሳቸውም በአሁኑ ወቅት የምንተዳደርበት በፌዴራላዊ አወቃቀር ሥርዓት የተቀረፀው ሕገ መንግሥት መቅረፅ ለምን እንደ አስፈለገ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግሮች/ጥያቄዎች ምን እንደነበሩና እንዴት ለመፍታት እንደተሞከረ፣ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ምን ተጨባጭ ጥቅም እንዳስገኘ፣ ሕገ መንግሥታዊነት ምን ማለት እንደሆነ በአጭሩ ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ ለውይይቱ መነሻ ይሆናሉ ያሏቸው ሃሳቦችና የተለያዩ አመለካከቶች ግልፅ አድርገዋል፡፡ የፌዴራል ስርዓት አወቃቀር በኢትዮጵያ የብሄር ግጭት ፈትተዋል ወይስ አባብሰዋል? የፌዴራል ሥርዓቱ የሁሉም ወገኖችና ቡድኖች ፍላጎት ያማከለ ነው አይደል? (በክልል ደረጃ፣ የብዝሃ ብሄረሰቦች ፍላጎት፣ የልሂቃን የፖለቲካ አመለካከት"፣ ሕገመንግሥቱ ምን ያህል ተግባራዊ እየሆነ ነው? ወደ አንድነት ወይስ ወደ ልዩነት እያመራን ነው? ወዘተ የሚሉ አንኳር ጥያቄዎች ለተወያዩ አንስተዋል፡፡ አቶ ደዋኖ የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር ፈተናዎች፣ የስልጣን ፉክክር ማዕከልነት፣ የመድበለ ፓርቲ ጥያቄና ታማኝ ተቃዋሚዎች መኖር፣ በፌዴራል ሥርዓቱ የሃብት ክፍፍልና የታክስ መሰብሰብ ጥያቄ፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች መካከል ያለው ልዩነትና የመሳሰሉ ሰፋፊ ጉዳዮች በማንሳትም አስተያየታቸውን አካፍለዋል፡፡ በተለይ ለፌዴራል ሥርዓቱ ተግባራዊነት ጋሬጣ ሆነዋል ያሉዋቸውን ችግሮች ዘርዝረዋል፡፡ የጥገኝነት አመለካከት፣ ድህነት፣ ተቋማዊ የማስፈፀም አቅም፣ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት በመርህ የተመሰረተ አለመሆን፣ የሃብት መሰብሰብ ስልጣን/ ፊስካል ፌዴራሊዝም/ 70 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት መስጠቱ ወዘተ የሥርዓቱ ዋነኛ ፈተናዎች መሆናቸው በማስረዳት እነዚህ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ጥናትና ውይይት እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል፡፡ በቀረቡ ሁለት የመወያያ ርዕሶች ላይ ለውይይትና ለክርክር መድረኩ ክፍት የተደረገ ሲሆን ከተወያዮች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ሰፊ አስተያየት ከሰጡ ተወያዮች መካከል ሕብረትን ወክለው የመጡ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም ይገኙባቸዋል፡፡ በሕገመንግሥትና ሕገመንግሥታዊነት የሚያተኩር አስተያየታቸውናና ጥያቄቸውን ሰንዝረዋል፡፡ "ችግራችን ሕገ መንግሥት አይደለም፡፡ ጥያቄው ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ እናድርጋለን ወይ? ሕገመንግሥታዊነት ማለት ምን ማለት ነው? ተቀባይነት ያለው መንግሥት መኖር፣ ሕጋዊና የተረጋጋ የስልጣን ሽግግር መፍጠር፣ የሕዝብ ፍላጎት ማክበር፣ እነዚህ በተግባር እየተዳሰሱ ነው? በእርግጥ ይሄ የሶስተኛ ዓለም ጥያቄ ነው፡፡ የሒደት ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ቆመን መጠበቅ አለብን ወይስ እንጀምረው? የሆነ ቦታ ላይ መጀመር አለበት፡፡ መሰረት መጣል አለብን ይሄ በአገራችን ተጀምሯል?" አቶ ገብሩ አስተያየታቸው በመቀጠል "በብሄር የተመሰረተ ፌዴራሊዝም የት ዓለም አለ?" በማለት በሶቪየት ህብረት መጀመሩና አገሪቱ መበታተኗን አስታውሰው የአገራችን የፌዴራል ሥርዓት ቅርፅ ተችተዋል፡፡ "የአገራችን ችግሮች የብሄር ጥያቄ ብቻ ነው? የዴሞክራሲ ጥያቄስ ከብሄር ጥያቄ ተነጥሎ ማየት ይቻላል?" በማለት በጥያቄ መልክ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በማከልም "ኩዌክ ከካናዳ የራስ ገዝ አስተዳደሯን የተጎናፀፈችው በአንቀፅ 39 አይደለም፣ በዴሞክራሲያዊ አግባብ እንጂ፡፡ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርዓት ካሰማ ነው የሚሄደው? ሌሎች ግዛቶች ይቀላቀላሉ እንጂ" በማለት የሕገመንግሥቱ አንቀፅ 39 "". እስከመገንጠል" አላስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ ሌላው ተሳታፊ በአሁኑ ወቅት ያለው የፌዴራል ሥርዓት "ወደ ውስጥ የሚያይ ሳይሆን ወደ ውጭ፣ እየሰበሰበን ሳይሆን እየተበታተነ፣ አቅጣጨው ወደ አንድነት ሳይሆን ወደ መለያየት የሚያይ፣ የጋራ እሴቶቻችን እያጠፋ የሚያድር ነው" በማለት በብሄር የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ብቸና አማራጭ አድርጎ ማየትን ኮንነዋል፡፡ ተናጋሪው መልክዐ ምድራዊ የፌዴራል ሥርዓት እንደ መፍትሄ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በተመሳሳይ አንድ ተወያይ ችግሩ የፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ አለመሆኑ በማስረዳት የሥርዓቱ አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖችን ባለመረዳት የመነጨ መሆኑን በማስረዳት፣ "ፌዴራሊዝም ፈልገነው ሳይሆን አስፈልጎን ነው" በማለት አማራጭ የሌለው ሥርዓት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም አስተያየት ሰጪው ልዩነታችን በማክበርና አንድነታችንም እንዲጠናከር ቀጣይ ጥረትና ትኩረት የሚሻ መሆኑን ሳይገልፁ አላለፈም፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ችግር እየፈጠረ ያለው የሥርዓቱ ክፋት ሳይሆን አተገባበር ላይ የአቅምና የብቃት ማነስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የእርስ በርስ ክርክሩና መደማመጡ የቀጠለ ሲሆን አንዱ ተከራካሪ፣ "በኢትዮጵያ የቆየው ችግር ምንድን ነበር? የብሄር ጭቆና ነበር ብለን የምናምን ከሆነ ይሄ ችግር እንዴት መልክዐ ምድራዊ ፌዴራሊዝም ይፈታዋል ብለን እናምናለን?" በማለት ቅርፁ በመልክዐ ምድራዊ ብቻ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ምናልባት በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት መካከል ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ይረዳ እንደሆነ እንጂ የማንነትን ጥያቄና የራስ በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንዴት ሊመልስ ይችላል?" በማለት ቀደም ብለው አስተያየት ለሰጡ ተወይይ የአጸፋ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተወክለው የመጡ አቶ ባዩህ ንጋቱ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ አስተያየትና ጥያቄ ሰጥተዋል፡፡ ፌዴራሊዝም ሆነ አሃዳዊ መንግሥት የሚያራምዱ መንግሥታት ዓላማቸው የአገር አንድነት እንዲጠበቅና የተፋጠነ ልማት ለማምጣት እንዲሁም ፍትሀዊ የሆነ የሃብትና የስልጣን ክፍፍል ለማረጋገጥ እንደሆነ ጠቁመው፣ የአገራችን የፌዴራል ሥርዓት አስፈላጊነት እንዲህ በማለት ለማስረዳት ሞክረዋል፡- "ባለፈው ታሪካችን ሲጨቋቆኑ ሲረጋገጡ የነበሩ አካላት ከሚለያዩ ያለፈውን ታሪክ ትተው ይቅር ተባብለው ሁለቱ አንድ ላይ ሕይወታቸውን ወደፊት ሊያራምዱ ይችላሉ በሚል እሳቤ፣ ብሄር ብሄረሰቦች የመገነጣጠልና የመጫጫን ስሜት አስወግደው ለሁሉም በእኩልነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያ ለመመስረት የሚያስችል መንገድና ሥርዓትን ከማስቀመጥ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ እንደ አቶ ባዩህ አባባል ሁሉም ሥርዓቶች በአገራችን ተሞክረዋል፡፡ "በንጉሱ ሥርዓት አንድ አገር ለመፍጠር ሙከራ ነበር፣ አልተሳካም፡፡ ስሜት በተጨቋኙና በተገዢው መደብ ያሳደረው ስሜትና ተፅዕኖ ማንም እንዲያስረዳን አንጠብቅም፡፡ በሕይወታችን ተሞክሮ የምናውቀውና ስናወግዘው የነበረ በመሆኑ ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡ በዝባዥና ተበዝባዥ፣ ገዥና ተገዢ የበላይና የበታች አድርጎ የሚያስተዳድር ሥርዓት እንደነበረ ለሁሉም ግልፅ ነው" ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ከተወገደ በኋላ "ሳንለያይ አብረን መቀጠል እንችላለን" የሚሉት የሚጠይቁ ተወያዩ አቶ ባዩህ፣ "ፍላጎቴን አስከብረህ፣ ማንነቴን ተቀብለህ ባለሁበት ሁኔታ እኔን ተቀብለህ የምትሄድ ከሆነ ከቻልን ተስማምተን ለመቆየት ካልተቻለ ደግሞ መንገዱ ክፍት ሆኖ በሚሄድበት ሁኔታ ሥርዓት መዘርጋቱ ግድ ብሎ በአንድ ህገ መንግሥት ጥላ ሥር ለመተዳደር ገባን፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ባይደረስ ኖሮ ኢትዮጵያ በአንድነት ለመቀጠል የምትችልበት ሌላ መንገድ አልነበረም" በማለት ሕገ መንግሥቱ የተቀረፀበትን ማዕቀፍ አመላክተዋል፡፡ አቶ ባዩህ ሰፊ የክርክር ሃሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ አንድ ሁለት ጥያቄዎችም ለተወያዮቹ አንስተዋል፡፡ "አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ስልጣኑ ከሱ ከወጣና ሌላ አካል እጅ ከገባ የዚች አገር ዕድል ምን ይሆናል?" የሚል ጥያቄ ሰንዝረው፣ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጥር አሳስበው ሥርዓቱ ከፖለቲካ ፓርቲ መለዋወጥ ነፃ ወጥቶ የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ ምንም እየተደረገ እንዳልሆነ ወቅሰዋል፡፡ "ፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲን ነጣጥሎ ማየት አይቻልም" የሚሉት አቶ ባዩህ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራት መሆን የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር አሳስበው፣ "ፓርቲዎች ታማኝ መሆን ያለባቸው ለማን ነው?" የሚል ጥያቄም አንስተዋል፡፡ አገሪቷ ከፌዴራሊዝም ውጭ ሌላ ሥርዓት ሊኖራት እንደማይችል የገለፁት አቶ ባዬህ፣ "ተቃዋሚዎች ይህንን አውቀውና አክብረው ዴሞክራትና ታማኝ ሆነው ለመቀጠል ምን መደረግ አለበት?" በማለት ጥያቄያቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት "ታማኝ ተቃዋሚ ማለት ምንድነው?" ብሎ የጀመረ ተወያይ ተቃዋሚዎች ታማኝ መሆን ያለባቸው ለገዢው ፓርቲ ሳይሆን ለሕገመንግሥቱ መሆኑን ጠቅሶ ሕገ መንግሥታዊነት ደግሞ በመጀመሪያ ሊከበር የሚገባው በራሱ በገዢው ፓርቲ መሆኑን የሚተነትን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ክርክሩን ቀጥለዋል፡፡ የመድረኩ አወያይ የነበሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕ/ር መሐመድ ሐቢብ "የአመለካከት ልዩነት ይዞ አብሮ መነጋገርና መደማመጥ ይቻላል" በማለት የመድረኩ ተወያዮች ስነ ምግባርና መደማመጥ በአገራችን መለመድ ያለበት ባህል ነው ሲሉ የመድረኩን መንፈስ አድንቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |