| ተመድ ወደ ሶማሊያ የሰላም አስከባሪ... |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
ተመድ ወደ ሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲልክ ብሪታንያ ጠየቀች
በጋዜጣው ሪፖርተር የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው ብሪታንያ የመንግሥታቱ ድርጅት በሶማሊያ ብርቱ ሚና መጫወት፣ ሚናው መጠንከር እንዲችል እንዲሁም የድርጅቱ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በሶማሊያ እንዲሰማሩ ማድረግ የሚያስችል ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ያሰራጨች መሆኑ ታወቀ፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ ሶማሊያ እንዲልክና አገሪቷን እንዲያረጋጋ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ሲጎተጉት ቆይቷል፡፡ አስራ አምስቱ የፀጥታው ም/ቤት አባላት የሶማሊያ ሁኔታ የከፋ መሆኑን የሚስማሙበት ቢሆንም የጦር አበጋዞች እስላማዊ አማጮች እና በኢትዮጵያ የሚደገፈው የሶማሊያ መንግሥት ወደ ሚዋጉበት ሶማሊያ የመንግሥታቱን ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ ጉዳይ ላይ ግን ብዙዎቹ አባል መንግሥታት ሲያንገራግሩ ቆይተዋል፡፡ ሮይተርስ (ረቡዕ ዕለት) ያገኘው የብሪታንያ መንግሥት እንደመከረበትና ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው ያሰራጨው ረቂቅ ውሳኔ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን አሚሶም የሚባለውን የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል የሚተካ የተመድ ሀይል መዘጋጀት ያለበት መሆኑን አስመልክተው ያቀረቡትን ሪፖርት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲቀበለው ይጠይቃል፡፡ ረቂቅ ውሳኔው የተመድ ጽህፈት ቤት የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሶማሊያ ስለሚሰማራበት ሁኔታ፣ ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከቁጥር አስገብቶ ኃይሉ በቁጥር (ብዛት) በአደረጃጀት፣ በኃላፊነት (ሥልጣንና ተግባሩ) እንዲሁም የሚስማራበትን አካባቢና ቦታ በተመለከተ የጀመረውን እቅድ የማውጣት ሥራ እንዲቀጥልበት ይጠይቃል፡፡ ባለፈው የካቲት ወር የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ልዑክ በሶማሊያ የሚኖረውን ቆይታ በስድስት ወር እንዲራዘም የመንግሥታቱን ድርጅት ወረቀት ወይም ፈቃድ አጽድቋል፡፡ በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል 1600 ወታደሮች ያሏቸው ሁለት የኡጋንዳ ሻለቃዎች እና 192 ወታደሮች የያዘ የብሩንዲ ሰራዊት ያካተተ ነው፡፡ ብሪታንያ ያቀረበችው ረቂቅ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ሶማሊያ ውስጥ ስላለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እና "እየከፋ የመጣው ሰብአዊነት/ ሂውማኒቴሪያን ሁኔታ" የሚያሳስበው መሆኑን ሶማሊያም በአካባቢው የአለም አቀፋዊ ሰላምና ደህንነት ስጋት መሆን መቀጠሏን ይገልፃል፡፡ አባል አገራት አሚሶምን በገንዘብ፣ በሰው ሃይል፣ በመሳሪያና በአገልግሎት እንዲያጠናክሩም አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት የምዕራባውያን ዲፕሎማት እንደሚሉት ብሪታንያ የም/ቤቱ አባላት በሚያቀርቡት አስተያየት መሰረት ረቂቁ ውሳኔ ተሻሽሎ በሚቀጥለው ሳምንት ለድምፀ ውሳኔ ይቀርባል፡፡ ብሪታንያ ያቀረበችው ረቂቅ ውሳኔ ሶማሊያ ውስጥ የሚደረገውን ሰላማዊ ፖለቲካዊ ሂደቱን ለማሰናከል ለማከላከል ወይም የሰላም አስከባሪዎችን የሚያስፈራሩትን ወይም የሶማሊያ ወይም የአካባቢውን መረጋጋት የሚያበላሽ ተግባር የሚፈፅሙትን በተመለከተ ቅጣት/ እቀባ የሚጣልባቸው መሆኑን ያስጠነቅቃል፡፡ ረቂቁ ውሳኔ በፀደቀ በ60 ቀን ውስጥ ለፀጥታው ምክር ቤት የሚቀርብ ውሳኔው የሚያካትተውና የሚያስፈፅመው ቅጣት ዒላማ የሚሆኑ "ግለሰቦችና ተቋማት" እንደሚኖሩም ረቂቁ ውሳኔ ይወስናል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |