|
Saturday, 26 April 2008 |
|
በኢየሩሳሌም መብራት የማውጣት ቅድምናችን መቼ ይመለሳል?
የትንሣኤ (ፋሲካ) በዓል በምሥራቃውያን ዘንድ ኢትዮጵያን አካትቶ ዛሬ በእሥራኤልዋ መዲና በኢየሩሳሌም በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡
ኢትዮጵያውያን ምእምናንና ካህናት በስፍራው ባለው ሀገረ ስብከታቸው አማካይነት በይዞታቸው በዴር ሱልጣን ገዳም ያከብሩታል፡፡ የኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናት ባለቤትነት ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ ቢሆንም፣ በአዲሱ ዘመን በተለያየ ጊዜ ይዞታዋ የቀናነሰበት ሁኔታ አጋጥሟታል፡፡ ከሚከበሩት በዓላት መካከል ትንሣኤ ዋናው ሆኖ የፋሲካን መብራት ለሁሉም ምሥራቃውያን የማብራት፣ የማውጣት ተግባር ከጥንት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያውያን ካህናት ድርሻ ነበር፡፡
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በሆነውና በነበረው የዴር ሱልጣን ገዳም (አንዳንድ ይዞታዎች በግሪክና አርመን ተነጥቀዋል) የምሥራቅ አገራት አብያተ ክርስቲያናት በተገኙበት የትንሣኤውን መብራት በቀዳሚነት ለሁሉም የሚለኩሰው ኢትዮጵያዊው ነበር፡፡ አሁን ግን ቅድምናውን በድፍረት ሌሎች ወስደውታል፡፡ በአሁኑ ዘመን የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ከአርመንና ሶሪያ ኦርቶዶክስ ማኅበረሰብ ጳጳሳት ጋር በመሆን ወደ ቅዱስ መቃብሩ ይገባሉ፡፡ የትንሣኤውን መብራት (ቅዱስ እሳት) ያወጣሉ፡፡ ምዕመናኑም በየሻማቸው ይለኩሳሉ፡፡ የብርሃኑ ትእምርት የክርስቶስን ትንሣኤ ያሳያል፡፡
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ "ገበታዋሪያ" በተሰኘው መጽሐፋቸው ዝርዝር ታሪኩን ጽፈውታል፡፡ በቀድሞ ዘመን በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝበ ክርስቲያን ይልቅ እጅግ ታላቅ ክብር ነበራቸው፡፡ ምክንያቱም ቅድስቲቱ ቦታ በጃቸው ስለሆነች፡፡ . . . ኢየሱስ ሕማም ሞት የተቀበለበት ደብረ ቀራንዮ ነው፡፡ እጅግ የተጌጠች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሮም የምትባለው ግሪክና አርመን በኢየሩሳሌም ያለ የሐበሾችን ይዞታ ለመቀማት ይሟገቱ ነበርና ቦታቸውን ሁሉ ከጃቸው ወሰዱባቸው፡፡
የፋሲካ ሌሊት ብርሃን ከሚወጣበት ቦታ መጀመሪያ የሚገባው የኢትዮጵያ ራኢስ (መምህር) ነው፤ ከርሱም በኋላ የሮም (ግሪክ ማለት ነው) በትረክ (ፓትርያርክ) ነው፡፡ ሦስተኛው የአርመን ራኢስ፣ አራተኛው የኩርጅ ራኢስ፣ 5ኛው የሶሪያ ራኢስ፣ ስድስተኛው የግብጽ ራኢስ ነው፡፡ ይህም የጥንት ሥርዓታቸውን ነው፡፡ ዳግምም ብርሃን በሚወጣበት ቅዳሜ ከሚሰበሰቡት ዋነኛው የኢትዮጵያ ቄስ እንደሆነ ይገለጣል፡፡
ኡጂን ሩጂ በሚባል በሁለተኛው መጽሐፍም የኢትዮጵያን ቅድምና ያሳያል፡፡ በትረኩና (ፓትርያርክ) ጳጳሳቱ ቀሳውስቱና መነኮሳቱ አንድነት ተሰብስበው ልብሰ በዓላቸውን ይለብሳሉ፤ ተመልሰው ወደ መቃብሩ ሲሄዱ አንድ ቄስ ከፊት ከፊታቸው ይሄዳል፡፡ እሱም ለዚሁ ዓመት በዓል ሥራ ብቻ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና ከዮሐንስ ቀሲስ የሚላክ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ቄሱ ነጭ ልብስ ይለብስና ዘይት የመላበት ያልተቃጠለ ፈትል ያለበት የብርጭቆ ቀንዲል በእጁ ይዞ ወደ መቃብሩ ሲደርስ እስላሞች ይከፍቱለትና ወደ ውስጥ ይገባል፡፡ ገብቶም ደጃፉን ይዘጋል፡፡ (ከ800 ዓመታት በፊት ኢየሩሳሌም በሙስሊሞች እጅ ስትወድቅ የቅዱስ መቃብር ቤተክርስቲያን ቁልፍ በኢየሩሳሌም ሙስሊም ቤተሰብ እጅ ነበር፡፡) የሮም (ግሪክ) በትረክና የቀሩት ቀሳውስት ግን ከሕዝባቸው ጋር በየጃቸው ጧፍ ይዘው ከውጪ ቁመው ይጠብቁታል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄስ ብርሃን ከወጣለት በኋላ የመቃብሩን ደጃፍ ይመታዋል፤ የሚጠብቁት ሰዎች ለመሳለም ይገቡ ዘንድ፡፡ የሮም በትረክና የቀሩት ሙጥራኖች በየጃቸው የያዙትን ጧፍ ከኢትዮጵያዊው ቄስ ቀንዲል አቃጥለው ወዲያው ፈጥነው ከመቃብሩ ይወጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች ብርሃን እያወጡ ርስታቸውን በጃቸው እንደያዙ እስከ 1694 ዓመት ድረስ ነበሩ፡፡
አለቃ ደስታ በ1928 ዓ.ም እንደገለጹት በ1920ዎቹ ዕርቅ አድርገው የሮም (ግሪክ) በትረክና የአርመን ጳጳስ ከኢትዮጵያ ቄስ ካንዱ ወይም ከሁለቱ ጋር ሁነው በዓላቸውን ያከብሩ ነበር፡፡ ሮምና አርመን ከሐበሻ ጋር ከመቃብሩ ውስጥ ገብተው እንደ ጥንተ ሥርዓታቸው ደጃፉን ዘግተው ብርሃን ያወጣሉ፡፡ በ1899 ዓ.ም የቅዳሜ ሹር ዕለት ሮምና አርመን ብርሃን ስለማውጣት በቅድምና ነገር ተጣልተው በቱርክ ዳኝነት ሲሟገቱ መዝገብ ይታይልን አሉና መዝገቡ ቢታይ ቅድምናው የሐበሾች ሁኖ በመገኘቱ ዳኛውም ቅድምናው የሐበሾች ከሆነ እነሱ ይፈልጉት እንጂ እናንተ በሰው ገንዘብ ምን ያጣላችኋል? ይልቅስ ሂዱ እንደ ጥንታችሁ ብሎ ሁለቱንም ማሳፈሩ በታሪክ ተጽፏል፡፡
ኢትዮጵያ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ በኢየሩሳሌም የነበራትንና ያላትን ይዞታ በየጊዜው የተቀናነሰባትንም ጭምር ማስከበር የቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን የግሪክ፣ አርመንና ግብጽ መንግሥታት እንደሚያደርጉት ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥትም እንደ ቀድሞው ሁሉ ጉዳዬ ብሎት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገርና ማስፈጸም ይጠበቅበታል፡፡
በዘመነ ሐዲስ ወደ ሦስተኛው ሺህ በምናመራበት 2001 ዓ.ም በኢየሩሳሌም የነበረንን ቅድምናና ክብር አጠናክረንና በዕውቀት ላይ ተመሥርተን የምንዘልቅበት እንዲሆን መጣርና መትጋትም አለብን፡፡ በሔኖክ ያሬድ |