| የኤች አር 2003 አርቃቂ ዶናልድ ፔይን... |
|
|
| Thursday, 10 January 2008 | |
|
የኤች አር 2003 አርቃቂ ዶናልድ ፔይን በአስመራ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መከሩ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑትና አወዛጋቢው ኤች አር 2003ን ረቂቅ እንዲፀድቅ በማስተባበር የሚታወቁት ዶናልድ ፔይን ባለፈው ሐሙስ ወደ አስመራ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የኤርትራ ሻዕባይት ዶት ኮም /ሻህቤይት.ኮም/ ኦፊሻላዊ ድረገፅ ዘገበ፡፡ ሁለቱም ወገኖች ተገናኝተው ከመከሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ የኤርትራና የአሜሪካ ግንኙነት፣ የቀጠናው አጠቃላይ ሁኔታ፣ እንዲሁም የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ይገኙባቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የድንበር ውዝግቡን አስመልክተው የድንበር ኮሚሽኑ ህጋዊና ይግባኝ የሌለው የመጨረሻ ውሳኔ አስቀምጦ ማለፉን አመላክተዋል፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ካርታ ለድንበሩ መካለል ይረዳሉ የተባሉት ትላልቅ ምልክቶች ማስቀመጡንና ለሁለቱም ወገኖችና ለተመድ እንደተሰጠ በማስመልከት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሉዓላዊነት ግዛቶች በግልፅ ለይቶ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ አገላለፅ የቀረው ነገር ..ወራሪ.. የሚሉትን የኢትዮጵያ ኃይል ከኤርትራ ግዛት ለቆ መውጣት ነው፡፡ ለዚህም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር ጠይቀዋል፡፡ በቅርቡ በሁለቱም አገሮች መካከል ተፈጥረዋል የተባለው የተኩስ ልውውጥና ውጥረት የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ማህበረሰብን ትኩረት ከዋናውን ጉዳይ ለማስቀየስ የፈጠረው ስልት መሆኑን አክለው አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የአጭር ጊዜ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን አስመልክቶ ተመድ ሁለቱም አገሮች ከጦርነት እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡ የኮንግረሱ አባል ዶናልድ ፖይን በበኩላቸው በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ በተመከተ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ የመጨረሻና ይግባኝ የሌለው እንዲሆን የዘወትር አቋማቸውንና እምነታቸው እንደሆነና አሁንም ውሳኔው ተፈፃሚ እንዲሆን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድትፈጥር የቻሉትን ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ሶማሊያን በተመለከተ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያና የአሜሪካ በሶማሊያ የተከተሉትን ፖሊሲና የወሰዱትን እርምጃ ውጤት አላመጣም፤ ብቻ ሳይሆን ለሶማሊያ፣ ለኢትዮጵያ፣ ለቀጠናው እንዲሁም ለአሜሪካም ምንም ያስገኘው ጥቅም እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ሶማሊያውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ የሚያስችል ሁኔታ እንዲመቻችና ለዚህም አሜሪካ የራስዋን ሚና እንድትጫወት ጠይቀዋል፡፡ ይህንን በተመለከተም አቋማቸውን ግልፅ ያደረጉት ዶናልድ ፔይን፣ እስከ አሁን በሶማሊያ የነበረው ፖሊሲ ፍሬ እንዳላስገኘና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአካባቢው መውጣት አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ..ለሶማሊየ ቀውስ መፍትሄ የሆነውን መንገድ ለመከተል ብቸኛ አማራጭ የኢትዮጵያ ወታደሮች መውጣት ነው.. ብለዋል፡፡ በኤርትራና በአሜሪካ ግንኙነት አስመልክተው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር የላትን ግንኙነት ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም ከቡሽ አስተዳደር ተመሳሳይ ፍላጎት ባለመኖሩ የጥረታቸው ውጤት ከንቱ አንደሆነ የገለፁ ሲሆን ለወደፊቱ ግን የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ይሻሻላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ባለፈው መስከረም ወር የሁለቱም አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መቋረጡን የሚታወስ ሲሆን እንደ ሚስስ ጀንዳይ ፍሬዘር የመሳሰሉት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ኤርትራ በአሸባሪ አገሮች ተርታ ለማስመዝገብ በቂ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከአሜሪካ ማናቸውም ባለስልጣናት ለማነጋገር ፍቃደኛ ያልነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከኮንግረሱ አባል ዶናልድ ፐይን ጋር ያደረጉት ንግግር ያልተለመደና እንደ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች አባባል ከአሜሪካ ጋር የተፈጠረው ውጥረት የማብረድ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ ዶናልድ ፔይን ማን ናቸው? እኚህ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል በኢትዮጵያ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የሚያተኩር ኤች አር 2003 የተባለውን ረቂቅ ህግ ያረቀቁና በአገሪቱ ኮንግረስ እንዲፀድቅ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ከፍተኛ ቅስቀሳ ..ሎቢ.. ያደረጉ ናቸው፡፡ ይህ ረቂቅ እንደየአገሪቱ ህግ መሠረት ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ በሴኔቱ እንዲሁም በመጨረሻ በፕሬዚዳንቱ ተቀባይነት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ ውጭ ያሉት የኢትዮጵያ ኃይሎች ረቂቁን እንዲፀድቅ ሲጎተጉቱ የቆዩ ሲሆን በአገር ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ ተቃዋሚ ኃይሎችም በይፋ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ አጨቃጫቂና አወዛጋቢ አድርጎት ቆይቷል፡፡ ለኢትዮጵያ መንግሥት ቅርበት ያላቸው ከረቂቁ በስተጀርባ ያሉት ግለሰቦች ከኤርትራና ሌሎች ጠላት አገሮች፣ አንዲሁም ከኦነግና ኦብነግ ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካ ከፕሬዚዳንቱ ቀጥለው ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ባለስልጣን ኮንደሌዛ ራይስ፣ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ባደረጉት ያልተለመደ ጉብኝት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ከመከሩባቸው ትላልቅ አጀንዳዎች አንዱ ይሄ ሲሆን ባለስልጣንዋ አስተዳደሩ ረቂቁን እንደማይደግፈው ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ዶናልድ ፔይን ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ግለሰቡ ከአገሪቱ ባለስልጣናት ያላቸውን ግንኙነትና ትስስር ገሀድ ያወጣ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊትም በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ወቅት ኢትዮጵያን እንደሚቃወሙ የሚታወቁት እኚህ የኮንግረስ አባል፣ አሁን ያረቀቁትን ኤች አር 2003 መርህን መሠረት ያደረገ፣ ከሁለቱም አገሮች መልካም ግንኙነት መፍጠርና በኢትዮጵያ ላይ አወንታዊ ለውጥ ከማምጣት ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን የተለየ ተልዕኮና አጀንዳ የነበረው መሆኑን የአሁን የአስመራ ጉብኝታቸው ጥርጣሬውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ዶናልድ ፔይን የአሜሪካ ምክር ቤት አባልነት ሲመረጡ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያገኙት ከኤርትራውያን ሲሆን በተለይም ንብረት ተወርሶብናል የሚሉት እንደ ኤሊያስ ፖፖሲኖስ አረቄ ፋብሪካ ያሉት ባለሃብት ኤርትራውያን የገንዘብ መዋጮ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለሮናልድ ፔን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉላቸው እነዚህ ሰዎች ንብረታችሁ እንዲመለስላችሁ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እማፀናለሁ ብለው ቃል በመግባት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ስላልፈፀሙላቸው ያገኙት የነበረው የኤርትራውያን ድጋፍ እንዳይቆም በኤርትራውያኖች ግፊት ኤች አር 2003ን ወደ ማርቀቅ መግባታቸውን ተጨባጭ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ ይህንን ዓይነት ውሳኔ ያረቀቁት እኚሁ ሰው አስመራ ሄደው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መምከራቸው ከተለያዩ ኤርትራውያን ጭምር ተቃውሞ እያሰነዘረ ነው፡፡ በየማነ ናግሽ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |