| የመንገዶች ሥራ እየተስተጓጎለበት... |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
የመንገዶች ሥራ እየተስተጓጎለበት መሆኑን ባለሥልጣኑ አስታወቀ
የኮንክሪት ታይልስና ቱቦ ማምረቻዎች ሥራ አቁመዋል በዳዊት ታዬ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በራሱ ሃይል እየተሰሩ ያሉ መንገዶችን በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ እየሆነበት መሆኑን ገለፀ፡፡ የኮንክሪት የታይልስና የቱቦ ማምረቻዎቹም በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት ሥራ አቁመዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ፍቃዱ ኃይሌ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ አሁን እየተገነቡ ያሉ መንገዶችን ለማጠናቀቅ አስቸጋሪ እየሆነ የመጣው በአሁኑ ወቅት የተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረት መሆኑንና ይህም እጥረት ካልተቃለለ በራስ ሃይል የሚሠሩ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሊቆሙ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡ በበጀት አመቱ ባለሥልጣኑ በራስ ሃይልና በኮንትራት ለተሰጡ የመንገድ ሥራዎች ከ6.7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሲሚንቶ የሚያስፈልገው ሲሆን ይህንን ሲሚንቶ ለማግኘት ለሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ጥያቄ ቢያቀርብም በተፈለገው ፍጥነትና መጠን ሲሚንቶ ማግኘት ችግር ውስጥ እንደገባም ጠቁመዋል፡፡ የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በተወሰኑ ሳምንታት ልዩነት የሚለቅልን ሲሚንቶ መጠን በጣም ትንሽ ነው፡፡ በአንዴ የሚለቅልን ከ300-350 ኩንታል አይበልጥም፡፡ ይህ ደግሞ በእቅድ የያዝነውን ሥራ ሊያሰራን አይችልም፡፡ አንዳንዴም በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ አንድም ኩንታል የማይገኝበት ጊዜ በመኖሩ ሥራ ከሚሰራበት የማይሰራበት ጊዜ እንደሚበልጥ አስረድተዋል፡፡ በመንገድ ሥራ ቅድሚያ የሚሰጣቸውና በሲሚንቶ የሚሰሩ ኮንክሪቶች፣ የፍሳሽ ቱቦዎችንና የመሣሠሉትን መስራት ሲሆን ይህ ሥራ መሠራት ካልተቻለ ዋናውን የመንገድ ሥራ መስራት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ባለሥልጣኑ በራስ ሃይል የሚሰራቸውም ሆነ ለኮንትራክተሮች ሰጥቶ የሚያሰራቸው መንገዶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳይጠናቅቁ ያደርጋል፡፡ ባለሥልጣኑ በ2000 የበጀት ዓመት ለሚያከናውናቸው ስራዎች በጠቅላላ ከሚያስፈልገው 6.7 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆነው በራስ ሃይል ለሚያሰራው መንገድና የመንገድ ግብዓት ለሆኑ ምርቶች ማምረቻነት ሊጠቀምበት ያቀደው እንደነበርም ታውቋል፡፡ በዚህ ምክንያት የመንገድ ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ ባለሥልጣኑ የሚጠቀምባቸው እንደ ቱቦ፣ ኮንክሪትና የታይልስ ማምረቻ ማዕከላቱ ዋነኛ ግብዓታቸው ሲሚንቶ በመሆኑ ማምረት ማቆማቸውን ገልፀዋል፡፡ የሲሚንቶ እጥረቱ ከበጀት አመቱ መግቢያ ጀምሮ የተፈጠረ እጥረት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱንና በእጥረቱ ሳቢያ በአግባቡ ሥራን መስራት ባለመቻሉ የባለሥልጣኑ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ከአምናው ያነሰና መስራት ከሚገባው በታች እንዲሰራ አድርጎታል፡፡ ችግሩ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት መሰራት የነበረባቸው የጥገናና የእድሳት ስራዎች በተገቢው መንገድ ሊሰሩ እንደማይችሉ የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ በክረምቱ ወቅት የፍሳሽ ቱቦዎች ሊተከልላቸው የታቀዱ መንገዶች አለመሰራታቸው ደግሞ መንገዶቹን ለብልሽት ከማጋለጡም በላይ በክረምቱ ወቅት የትራንስፖርት ዝውውር ላይ ችግር ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ የአዲስ አበባ ባላደራ አስተዳደር እንዲያውቀውና ችግሩ የሚቃለልበትን መንገድ እንዲፈልግ በማሳወቃቸው ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአስተዳደሩ ጋር በችግሩ ዙሪያ ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |