| ታክስ የተነሣለት ዱቄት ዋጋ ጨመረ |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
በቤዛዊት ሥዩምየተጨማሪ እሴትና የተርን ኦቨር ታክስ ከተነሳ በኋላ ትናሽ አሳይቶ የነበረው ዱቄት በስንዴ አቅርቦት እጥረት ጨመረ፡፡ የምሥራቅ ዱቄትና ዳቦ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ዱቄት አምራቾች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፀሐፊ አቶ ጣሰው ኃይሌ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት በስንዴ አቅርቦት እጥረት ምክንያት የዱቄት ዋጋ ጨምሯል፡፡ የተጨማሪ እሴትና የተርን ኦቨር ታክስ ሳይነሳ አንድ ኩንታል ስንዴ እስከ 370 ብር ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ገበያ አንድ ኩንታል ስንዴ በ410 ብር ለመግዛት ባወጡት ጨረታ ተሳታፊ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የዱቄት ዋጋን ለማስተካከል የስንዴ አቅርቦትን ማሳደግና ፍትሃዊ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የጠቆሙትት አቶ ጣሰው፣ የታክሶቹ መነሳት የዱቄት ዋጋ ለአጭር ጊዜ እንዲቀንስ ቢያደርግም የፋብሪካዎቹ ትልቅ ችግር የሆነው የስንዴ እጥረት ባለመፈታቱ በድጋሚ ዋጋ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ በስንዴ አቅርቦትና በዱቄት ፍላጎት መካከል ሰፊ ልዩነት ስላለ የሚመረተው ስንዴ ከሕዝብ ፍላጎትና እድገት ጋር አለመጣጣሙን ተናግረዋል፡፡ ከታክሶቹ መነሳት በኋላ የአንድ ኩንታል ዱቄት ከ50 እስከ 60 ብር ቅናሽ ታይቶ እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት ግን የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ ከ600 ብር በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዱቄት አምራቾች ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያለባቸውን የስንዴ ችግር በማስረዳት ከመንግሥት እህል መጠባበቂያ ድርጅትና ከእርሻ ሰብል ስንዴ የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጥያቄ አቅርበው ድርጅቶችን በተወሰነ ዋጋ ሽጡ ብሎ ማስገደድ የነፃ ገበያ ፖሊሲም ሆነ ሕግ አይፈቅድም በሚል ተቀባይነት ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ሶስት ዓመታት በዱቄት ዋጋ ላይ እስከ 70 በመቶ የሚደርስ ጭማሪ መከሰቱን የገለፁት አቶ ጣሰው የስንዴ ዋጋ በኩንታል በ1998 ከ180 እስከ 210፣ በ1999 ዓ.ም ከ280 እስከ 300 ብር ይገዛ የነበረው ተቀይሮ አሁን ከ600 ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡ የስንዴ ዋጋ በመጨመሩም አምራቾች በበቂ መጠን ገዝተው መጠባበቂያ እንዳይዙ ስላደረጋቸው በስንዴ እጥረት ምክንያት የዱቄት ፋብሪካዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ60 በላይ ፋብሪካዎች በስንዴ እጥረት የተዘጉ ሲሆን አብዛኛው ፋብሪካዎች ደግሞ ከአቅማቸው በታች በማምረት ላይ ናቸው" በዱቄት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ዱቄትን በግብአትነት በሚጠቀሙ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊፈጥር እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ በአለም ላይ ካለው የስንዴ ዋጋ ንረት አንፃር አምራቾች በመደራጀት ስንዴን ከውጪ ማስገባት የሚያበረታታ እንዳልሆነና አሁን ባለው ዋጋ አንድ ኩንታል ስንዴ ከውጪ ለማስገባት ከ600 ብር በላይ እንደሚፈጅ አስረድተዋል፡፡ የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት የስንዴ አምራቾች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የመንግስትና የግል ባለሐብቶች ከፋብሪካዎች ጋር በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |