Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
Jul 06th
Home arrow Sections arrow በመግለጫ ብቻ የቀሩ መፍትሔዎች
በመግለጫ ብቻ የቀሩ መፍትሔዎች Print E-mail
Saturday, 26 April 2008
አሁን የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት መፍትሔ ይሆናሉ ተብለው የተወሰዱ እርምጃዎች ጥያቄ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ፡፡ በተለይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ተጥሎባቸው የነበሩ ምግብ ነክ ምርቶች ታክሱ ከተነሣላቸው በኋላ መሠረታዊ የሆነ የዋጋ ለውጥ ሳያመጡ ቆይተው አሁን ጭራሽ ጨምረው እየሸጡ ነው፡፡

በምሣሌነት ዱቄትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሰሞኑ ገበያ አንድ ኪሎ ዱቄት ሰባት ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ዋጋው ይቀንሣል፣ አንዱ ሊትር ዘይት እስከ 14 ብር ይሆናል ተብሎ ቢገለፅም ባለሶስት ሊትር የታሸገ ዘይት 62 ብር እየተሸጠ መሆኑን ስንመለከት መፍትሄ ይሆናሉ ተብለው የተወሰዱት እርምጃዎች ውጤት እያመጡ እንዳልሆነ እንገነዘባለን፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ የተነሳላቸው ምርቶችም እንደዚሁ የሚሸጡበት ዋጋ እንደ ቀድሞው መሆኑ ለውጡ ምኑ ላይ ነው? እንድንል አድርጎናል፡፡

የፋሲካ አውደ ዓመት ገበያም ሸማቹን የሚፈታተን ሆኗል፡፡ አንድ ኪሎ ቅቤ እስከ 90 ብር ደርሷል፡፡

ጤፍ ሰሞኑ አንደኛ ደረጃ የሚባለው ከ650 እስከ 700 እየተሸጠ ነበር፡፡ አንድ ሰሞን በየመንገዱ አንድ ኪሎው በአንድ ብር ሲሸጥ የነበረው ሽንኩርት ሳይቀር ከእጥፍ በላይ አድጎ ከሁለት ብር በላይ ዋጋ ማውጣቱ የአገራችን የኑሮ ውድነት ልጓም የጠፋለት መሆኑን ያሳያል፡፡

ስኳር ከሰባት ብር ባልበለጠ እንዲሸጥ ይደረጋል ተብሎ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ከተነገረ በኋላ ያሉት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ ስምንት ብርና ዘጠኝ ብር እየገባ ነው፡፡

በመንግሥት በተወሰዱ እርምጃዎች ዋጋቸው ይቀንሳል ተብለው ይጠበቁ የነበሩ እንደ ዘይት ያሉ ምርቶችን በጅንአድ በኩል የማከፋፈሉ ሥራም ብዙ ርቀት አልተጓዘም፡፡

ጅንአድ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት መደብሮቹ ጥቂት ናቸው፡፡ ለዚህ ቅርንጫፎቹን ሳያበራክት አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሸማቾች እዚህ ቦታ መጥታችሁ ግዙ ስለማይል የተባሉትን ምርቶች እንዴት እንደሚያገኙ ግራ የሚያጋባ ይሆናል፡፡ ብዙዎች ተስፋ ጥለውበት የነበረው ዘይትም ሆነ ሳሙና በተገቢው መንገድ ምላሽ አላገኙም፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከተነሳ ዱቄት ይቀንሣል ብለው የነበሩ የዱቄት አምራቾች መልሶ ዋጋው ለምን እንደቀጠለ አሳማኝ ምክንያት ሊሰጡን ይገባል፡፡

በቅናሽ ዋጋ ለተወሰነው ህብረተሰብ ይዳረሳሉ የተባሉ ምርቶች እንደተባለው ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ይህ እድል ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉ ከተሞችም ይዳረሳል ተብሎ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በይፋ መግለጫ የተሰጠባቸው ምርቶች ያልተዳረሱበት፣ ዋጋቸው ያልቀነሰበት ምክንያት በትክክል መገለፅ ይኖርበታል፡፡

ከሰሞኑ ከዋጋ ማሻቀብ ጋር በተያያዘ ሌላው ሊነሳ የሚገባው ሲሚንቶ ነው፡፡ ሲሚንቶ አንዱ ኩንታል 300 ብር መግባቱ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሸማቹን ግራ አጋብቷል፡፡ በአገር ውስጥ እየተመረተ ያለው ሲሚንቶ አቅርቦትና ፍላጎት አልተመጣጠነም፡፡ እጥረቱ ብዙውን የህብረተሰብ ክፍል እንደሚነካ ታውቆ ገበያውን ለማረጋጋተ ከውጭ ሲሚንቶ በፍራንኮ ቫሉታ ተፈቅዶ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ተከልክሏል፡፡ መከልከሉ ተገቢ ነው ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡

ሌላም በሸማቹ ላይ የተከሰተ ጫና ማንሳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ቃል የገባውን ለመፈፀም ባለመቻሉ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ደንበኞች ላይ ቅሬታን አሳድሯል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሃይል እጥረት ስለመኖሩ በይፋ ካስታወቀ በኋላ ፕሮግራም አውጥቻለሁ ብሏል፡፡ በዚሁ ፕሮግራም መሰረት እኛም አሠራራችን ብናስተካክልም አሁንም ከፕሮግራም ውጪ መብራት እያጠፋ በፕሮግራም እንዳንሰራ አድርጎናል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ያወጣውን ፕሮግራም በትክክል እንዲተገብር መለመን ሊኖርብን ነው፡፡

ከመንግሥት አካላት የሚሰጡ መግለጫዎች፣ የሚወሰዱ እርምጃዎች በትክክል ካልታሰበባቸው፣ የተጠኑ ካልሆኑ አፍራሽነታቸው ይበዛል፡፡ ሸማቾችን ክፉኛ እያስመረረ ያለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቀነስ ከታክሲ በተጨማሪ መለስተኛ አውቶቡሶችና ኮድ ሦስት ሚኒባሶች ተመድበው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ችግሩ የተቃለለ ይመስል አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል፡፡ ይህም በመሆኑ የትራንስፖርቱ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል፡፡  

ለማን አቤት እንደሚባል፣ ማን ሊፈታው እንደሚችል አልታወቀም፡፡ ይህ ድርጊት አለመተማመንን ሊፈጥር ስለሚችል ሊታሰብበት ይገባል፡፡
 
< Prev   Next >