|
Saturday, 26 April 2008 |
|
በዳርፉር ግጭት ከ3ዐዐ ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ
በሱዳን ዳርፉር ለአምስት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ከሦስት መቶ ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ተጠሪ ጆን ሆልምስ አስታወቁ ሲል ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ጆን ሆልምስ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2000 በቀረበው ጥናት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሁለት መቶ ሺ እንደሆነ መገለፁን ጠቅሰው የተከለሰውንና ትክክለኛውን ሪፖርት ለፀጥታው ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን መንግሥት በበኩሉ በአካባቢ በተከሰተው ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር መጋነኑን ገልጿል፡፡ ጆን ሆልምስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሟቾቹ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2ዐዐ6 የተጠናውን ጥናት መነሻ በማድረግ የተሰላ መሆኑንና ሳይንሳዊ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ በማያያዝም በዳርፉር ያለው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል የዳርፉርን ግጭት አስመልክቶ "ኤ ሎንግ ዴይስ ዳይንግ" የሚል መፅሀፍ የፃፉት አሜሪካዊው ኤርክ ሪቪል "ጆን ሆልምስ የገለፁት ቁጥር ትክክለኛ አይደለም ምክንያቱም ቁጥሩን አሳንሰው ነው ያቀረቡት" ብለዋል፡፡ በማያያዝም የተለያየ መረጃን በመጥቀስ የሟቾች ቁጥር ከአምስት መቶ ሺህ በላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
* * *
አሜሪካዊው ወታደራዊ ሚስጢር ለእስራኤል በመስጠቱ ተከሰሰ
አሜሪካዊው የወታደራዊ ተቋም ኢንጂነር ቤን አሚ ካዳሽ ለእስራኤል የአሜሪካንን ወታደራዊ መረጃ የሚስጢር ሰጥቷል በሚል ክስ ተመስርቶበት ፍርዱ ቤት መቅረቡን የአሶሽየትድ ኘሬስ ዘገባ አመለከተ፡፡
በዘገባው መሠረት ካዲሽ የአሜሪካንን የኒውክሊየር መሳሪያ፣ የጦር ጄቶችና የሚሳኤሎች መረጃ እ.ኤ.አ በ198ዐዎቹ ጊዜያት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ካዲሽ አራት የስለላ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡
የሰማንያ አራት ዓመት የዕድሜ ባለፀጋው ካዲሽ ስለሁኔታው ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ "በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጥም" በማለት መልሷል፡፡ ካዲሽ ለእስራኤል የደህንነትና የመረጀ አማካሪ የአሜሪካንን የጦር መሳሪያ መረጃ በሚስጢር ሊሰጥ ሲሞክር መያዙን ዘገባው አትቷል፡፡
ካዲሽ በስለላ ተግባር በሺዎች የሚቆጠሩ መረጃዎችን ለእስራኤል መስጠቱ ታውቋል፡፡ በዚህም በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ያለፈው ሮብ ፍርድ ቤት ቀርቦ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
የእስራኤል መንግሥት ካዲሽ ላደረገው ውለታ የእስራኤል ዜግነትን እንደሰጠው ታውቋል፡፡ ካዲሽ በአሜሪካ በኒው ጀርሲ በሚገኘው የጦር ኃይል የጥናት፣ የልማትና የኢንጂነሪንግ ተቋም ውስጥ እ.ኤ.አ ከ1979 እስከ 1985 ድረስ በኢንጅነርነት ሙያ አገልግሏል፡፡
* * *
የአሜሪካንን ጥሪ ህንድ ውድቅ አደረገች
የአሜሪካ መንግሥት ኢራን የምታካሂደውን የዩራንየም ማበልፀግ ተግባር እንድታስቆም ለህንድ ያቀረበችውን ጥሪ የህንድ መንግሥት ውድቅ ማድረጉን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመለከተ፡፡
በዘገባው መሠረት የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጥሪውን ውድቅ አድርጓል፡፡ የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ህንድም ሆነች ኢራን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸን በተመለከተ የውጭ ምክር አያስፈልጋቸውም" በማለት ገልጿል፡፡
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን በቅርቡ የህንድ ባለሥልጣናት የኢራኑን ኘሬዚዳንት መሀመድ አህመዲ ነጃድን የኒውክሊየር ግንባታቸውን እንዲቆሙ የሚያግባቡ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
የኢራኑ ኘሬዚዳንት በሚቀጠለው ሳምንት በህንድ ይፋዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ዘገባው አትቷል፡፡ |