| "የዓለም የንግድ ድርጅት አባል... |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
"የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን በራሱ ግብ ነው ብዬ አልገምትም"ዶ/ር ፍቅረማርቆስ መርሶ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ ዲን ዶክተር ፍቅረማርቆስ መርሶ ጐጃም ነው ተወልደው ያደጉት፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትም የተከታተሉት እዚያው ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ ለአምስት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1986 ዓ.ም በሕግ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን (LLB) አገኙ፡፡ በመቀጠልም በሕግ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን (LLM) ከደቡብ አፍሪካ አግኝተዋል፡፡ በመጨረሻም በጃፓንና በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምር ፕሮግራም በሕግ የፒ.ኤች.ዲ ድግሪያቸውን (PHD) በዓለም ንግድ ዙሪያ አጠናቀዋል፡፡ በ1997 ዓ.ም "Ethiopia's WTO Accession: A Strenuous Step for a Poor Nation Seeking Economic Prosperity" የተሰኘ መፅሀፍ ፅፈዋል፡፡ በሥራውም ዓለም በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ ረዳት ፕሮፌሰርና ዲን በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሰለሞን ጐሹ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ባለው ጥረትና እንቅስቃሴ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የዓለም ንግድ ድርጅትስ እንዴት ተመሰረተ? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- 1939 የተቋቋመው የዓለም አቀፍ ጠቅላላ ንግድና ታሪፍ ስምምነት (GATT) ለውጦችን መቋቋም እያቃተው ነበር፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ በዓለም ደረጃ በርካታ ለውጦች ተከናውነዋል፡፡ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ታይቷል፡፡ የመረጃ ቴክኖሎጂው በጣም ማደግ የጀመረበት ጊዜ ነበር፡፡ ለንግድ የሚውሉት እቃዎች ብቻ መሆናቸው ቀርቶ አገልግሎቶችም ትልቅ የዓለም አቀፍ የንግድ አካል መሆን ጀመሩ፡፡ ቴክኖሎጂ የሚፈጥሩ ሃገራት ቴክኖሎጂዎቻችንን በተለያዩ ሃገራት ያለምንም ገደብ እየተቀዱ ነው በሚል ሃሳብ የአእምሯዊ ንብረት ጥያቄም ከንግድ ጋር የተገናኘ ነው በሚል ወደ ዓለም ስርዓቱ እንዲገባ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1986 - 1994በተደረገው የመጨረሻው የ"ማማ የንግድ ድርድር ዙር (Uruguay Round) የዓለም ንግድ ድርጅት ሊመሠረት በቅቷል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት በጣም ሰፊ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን በዋናነት የእቃ፣ የአገልግሎትና የአእምሯዊ ንብረት ስምምነቶችን ያቀፈና ዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓትን የሚመራ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶተ ጋር ሲነፃፀር ጠንካራ የአለመግባባቶች መፍቻ ሥርዓት ያለው ተቋም ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ጠቅላላ የንግድና ታሪፍ ስምምነት አሁን የዓለም የንግድ ድርጅት አንድ ዋነኛ አካል ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የዓለም የንግድ ድርጅት ባለፉት 14 ዓመት በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ምን ዓይነት ጉልህ ሚና ተጫውቷል? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- የዓለም የንግድ ድርጅት የኢኮኖሚክ ግሎባላይዜሽንን በመምራት በአሁኑ ሰዓት 152 አባላት ያቀፈ በጣም ግዙፍ የሆነ ተቋም ሆኗል፡፡ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ 95 ከመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ የዓለምን ንግድ የተረጋጋ እንዲሆን እና ንግድም እንዲጨምርና ተገማች (Predictable) እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ሪፖርተር፡- የዓለም አቀፍ ጠቅላላ የንግድና የታሪፍ ስምምነት (GATT) አባል የነበሩ ሀገራት በቀጥታ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን ችለው ነበር፡፡ በዚህ አብዛኛዎቹ ታዳጊ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ገዥዎቻቸው አማካኝነት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የሌሎች በድርድር የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የሆኑ ታዳጊ አገራት ልምድ ምን ይመስላል? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- በመጀመሪያ አብዛኞቹ ሃገራት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ታዳጊ ሃገራትም የድርጅቱ አባል ናቸው፡፡ አባልነታቸው በታሪክ አጋጣሚ ነው፡፡ ታዳጊ ሃገራቱ በብዛት በቅኝ ግዛት ስር ነበሩ፡፡ ከቅኝ ግዛት ሲወጡ GATT ቀለል ያለ የአባልነት ድንጋጌ ስለነበረው ካለምንም ከፍተኛ ውጣ ውረድ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሊሆኑ ችለዋል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት ሥራ ከጀመረበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የድርጅቱ አባል የሆኑ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሀገራት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ካምቦዲያና ኔፓል፡፡ በቅርቡ ሁሉንም ነገር ጨርሳ የሃገሪቱ ፓርላማ ስምምነቱን እስኪያፀድቀው የምትጠብቀው ኬፕ ቨርዴ ሶስተኛዋና ብቸኛዋ የአፍሪካ ሃገር ሳትሆን አትቀርም፡፡ እ.ኤ.አ እስከ ጁን 30" 2008 ድረስ ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ውጭ እስከ አሁን ድረስ በድርድር ድርጅቱን የተቀላቀለ የአፍሪካ ሃገር የለም፡፡ ሪፖርተር፡- በድርድር ላይ ያሉ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገራትስ? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- በድርድር ሂደት ላይ ያሉ በርካታ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገራት አሉ፡፡ በዓለም ላይ በአሁኑ ወቅት 27 ሃገራት በድርድር ላይ ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 10ሩ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገራት ናቸው፡፡ ለምሳሌ አልጀሪያ፣ በድርድር ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ አሳልፋለች፡፡ ሱዳንም በድርድሩ አስራ አራት ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ ለነገሩ የድርጅቱ አባል ያልሆኑት የአፍሪካ ሃገራት ራሱ ጥቂት ናቸው፡፡ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ይጠቀሳሉ፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት ስርዓት በአሁኑ ጊዜ በጣም ውስብስብ እንደመሆኑ ለእነዚህ ሃገራት ፈታኝ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረበች አምስት ዓመት ሞላት፡፡ የድርድር ሂደቱ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1997 ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ በታዛቢነት ቆይታለች፡፡ በይፋ አባል ለመሆን ጥያቄ ያቀረበችው ግን እ.ኤ.አ በ2003 ጥር ላይ ነው፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ የአባልነቱን ጉዳይ የሚከታተል የሥራ ቡድን (Working Party) ተቋቁሟል፡፡ በአንዳንድ ወገኖች በኩል ድርድሩን በአጭር ጊዜ እንጨርሳለን የሚል አመለካከት ነበር፡፡ ነገር ግን በተግባር አሁን እንደምናየው የሃገሪቱን የውጭ ንግድ ሥርዓት የሚያሳየውን ሰነድ (Memorandum on Foreign Trade Regime) ለማስረከብ እንኳን በርካታ ዓመታት ወስዶባታል፡፡ ይህንን ሰነድ ያስረከበችው እ.ኤ.አ በታህሳስ 2006 ነው፡፡ በእነዚህ ሰነዶች መሠረት ከአሜሪካና ከካናዳ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አሜሪካ ዘርዘር ያሉ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርባለች፡፡ መልስ ለመስጠትም የተወሰነ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ መልሶቹ ተጠቃለው የተሰጡት እ.ኤ.አ በሚያዚያ 2008 ነው፡፡ ጉዳዩን ለመመልከት እስከ አሁን ድረስ የሥራ ቡድኑ አልተሰበሰበም፡፡ በቅርብ ወራት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል፡፡ የሥራ ቡድኑ አባላት የአገሪቱን የውጭ ንግድ ስርዓት የሚመለከቱ ድንጋጌዎችንና ህጎች ምን እንደሆኑ በአጠቃላይ ማወቅ ስለሚፈልጉ ያን የሚመለከቱ በጣም ሰፊና ዝርዝር የውጭ ንግድ ሥርዓት ሰነድ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ከዚያ በኋላ ያልገባቸውንና ግልፅ ያልሆነላቸውን ነገሮች ወይም ደግሞ ከንግድ ድርጅቱ ስምምነቶች ጋር አይጣጣምም የሚሏቸውን ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ የመመለስ ግዴታም አለብን፡፡ መረጃ ከተለዋወጠን በኋላ የድርድሩ ሥርዓት ይጀመራል፡፡ ድርድሩ በሁለትዮሽና በጋርዮሽ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ሪፖርተር፡- የሁለትዮሽና የጋርዮሸ ድርድር መሠረታዊ አንድነትና ልዩነት ምንድን ነው? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- በመርሕ ደረጃ እያንዳንዱ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር ይችላል፡፡ ሃገራቱ በተለይ ኢትዮጵያ እቃዎችንና አገልግሎቶችን በተመለከተ ገበያዋን ክፍት ስለምታደርግበት ሁኔታ የሚደራደሩበት ነው፡፡ "የአባልነት ጥያቄሽን እንድንቀበል ምን ታደርጊልናለሽ?" የሚል ዓይነት ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ድርድር መነሻ ሃሳቡን መስጠት የሚጠበቅባት ራሷ ኢትዮጵያ ስትሆን ይህ ካልሆነ ግን አባላቱም መነሻ ሃሳቡን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በተለይም ከቀረጥና አገልግሎት ጋር በተገናኘ ብዙ ጥያቄዎች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ለአእምሯዊ ንብረት ስለሚደረገውም ጥበቃ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ምንም እንኳን በመርህ ደረጃ እያንዳንዱ አባል ለኢትዮጵያ ጥያቄ ማቅረብና መደራደር ቢችልም በተግባር ግን ጥያቄ የሚያቀርቡት አባላት ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ንግድ ግንኙነት ያላቸውና ጥቅማችን ይነካል ብለው የሚያስቡ አባላት ናቸው፡፡ የጋርዮሽ ድርድሩ ደግሞ የሥራ ቡድኑ አባላት የሚያቀርቡት ጥያቄን ይመለከታል፡፡ ይሄ በአብዛኛው የሚያተኩረው የዓለም የንግድ ስርዓት ድንጋጌዎችንና ውሎችን በማክበርና ባለማክበር ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ህጎቹ መጣጣምና አለመጣጣማቸውን ያልተጣጣሙ ከሆነስ በምን ጊዜ ነው ለማጣጣም ቃል የምትገባው? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ ይሄ በተግባር ብዙ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ለምሳሌ የሚጠይቁት ጥያቄ በኢትዮጵያ በቀጥታ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ይሄ ካለቀ የአባልነት ጉዳዩ አለቀ ማለት ይቻላል፡፡ በመጨረሻ በእቃ፣ አገልግሎትና አእምሯዊ ንብረት ስምምነት ዙሪያ የሥራ ቡድኑ ሰነድ አዘጋጅቶ ያቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ ሰነዱን ከተቀበለችውና በዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስተሮች ኮንፈረንስ ቀርቦ ከፀደቀ አባል ትሆናለች ማለት ነው፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት ስምምነት እንደመሆኑ በሀገሪቱ ህግ መሠረት የማፅደቅ ሥራ ይሰራል፡፡ ሪፖርተር፡- ከሦስት ዓመት በፊት በፃፉት ጉዳዩን የሚመለከት መፅሃፍ ላይ አንዳንድ ባለስልጣናት በ2 ዓመት አባል ለመሆን ማቀዳቸው እንደገረመዎት ገልፀው ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያዩት ምን ያህል ይቀረናል? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- ሂደቱን ራሱን ስናየው በሁለት ዓመት ይጨረሳል የሚባል አይደለም፡፡ በተግባር እንዳየነው እስከ አሁን ወደ አምስት ዓመት ወስዶብናል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ያለው ሥርዓት ስለሆነ እጅግ እየከበደ የሚመጣው በጣም በአጭር ጊዜ በሁለት ዓመት ውስጥ ያልቃል የሚለው ሃሳብ መጀመሪያውኑም የዚህን አባል የመሆን ስርዓት በአግባቡ ካለመረዳት ይመስለኛል፡፡ የሌሎችንም ሃገራት ልምድ ስንመለከት በጣም የተለያዩ ናቸው፡፡ በአብዛኛው በአማካይ ከ9 - 10 ዓመታት ይወስዳል፡፡ ካምቦዲያ ለምሳሌ 9 ዓመት ኔፓል 14 ዓመት ወስዶባቸዋል፡፡ ኬፕቨርዴ 8 ዓመት ወስዶባታል፡፡ በአጭር ጊዜ አባል የሆኑም አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አባል የነበሩት ሃገራት ሕብረቱ ሲፈራርስ ከነበራቸው የምዕራቡን ዓለም የመቀላቀል ፍላጎት አንፃር አብዛኛውን የቀረበላቸውን ጥያቄዎች በመቀበል አባል የሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ክብረ ወሰኑን የያዘችው ኪርጊዝ ሪፐብሊክ የድሮው ሶቭዬት ሕብረት ሀገር ስትሆን አባል ለመሆን የፈጀባት ከ3 ዓመት በታች ነው፡፡ በተመሳሳይ ጆርጂያ 4 ኢስቶኒያ 5 ዓመት ብቻ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ አባልነቱን ለማጠናቀቅ ከ8 - 10 ዓመት ሊወስድባት እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ሳትሆን አባልነቱ የሚሰጣትን ጥቅም እያገኘች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሕግ የተሰጣት መብት ባይኖርም ጥቅሞቹ እስካልጠፋ ድረስ አባል ለመሆን ጊዜው አሁን አይደለም የሚሉ ምሁራን አሉ፡፡ እርስዎ ምን ሃሳብ አለዎት? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- በተለምዶ አንድ ሃገር የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስብባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ በሁለት መንገድ ልናየው እንችላለን፡፡ አንደኛው ፖለቲካዊ ሊሆን ይችላል፡፡ በርካታ ሃገራትን በአባልነት ያቀፈ ተቋምን መቀላቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብርና እውቅና ይጨምርልኛል ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡ ሁለተኛ የሃገራችንን የኢኮኖሚ እድገት ከማሳደግ አኳያ አባልነቱ ሊያመጣው የሚችል ጥቅም ሊኖር ይችላል፡፡ በተለምዶ ሊገኙ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ጥቅሞች አንደኛ ገበያ ማግኘት ነው፤ ሁለተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብና ሦስተኛ የንግድ አሠራርን ግልፅና የሚተነበይ መሆኑ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የሆኑ ከቀረጥና ከኮታ ነፃ የሆነ የገበያ እድል ተሰጥቷታል፡፡ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሃገራት ይህንን እድል ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ችግር ገበያ የማግኘት ነው ወይስ የተሰጣትን እድል በአግባቡ መጠቀም ነው የሚለው ጥያቄ ተገቢ ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ እኔም ስመለከተው ዋነኛው ገበያ በአለው ችግር በበቂ ሁኔታ አምርቶ ወደ ውጭ መላክ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሃገሮች የሚሰጡት የተለየ የገበያ እድል በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛ የታሰረ (Bound) አይደለም፡፡ በራሳቸው በጎ ፈቃድ ብቻ የሚሰጥ ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል፡፡ በቅድመ ሁኔታዎች የተሞላ ነው፡፡ የአሜሪካ የተለየ የገበያ እድል ለምሳሌ በበርካታ ቅድመ ሁኔታዎች የተሞላ ነው፡፡ ለማሟላት ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ልንመካበት አንችልም፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ከሆንን ግን በቀላሉ ሊያነሱት አይችሉም፡፡ ገበያውን ዛሬ ይሰጡናል ወይስ ይነፍጉናል የሚል ሳይሆን እንደ መብት የገበያ እድል የምናገኝበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይችላል፡፡ እያደግን ስንመጣና ወደ ውጭ የምንልከው ምርት እየጨመረ ሲሄድ ይሄ ጉዳይ በጣም ጠቃሚ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በሌላ በኩል በርካታ ጥናቶች የሚያሳዩት ኢንቨስትመንት በመጨመርና የድርጅቱ አባል በመሆን መካከል ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት የለም፡፡ ኢንቨስትመንት የሚጨምረው የድርጅት አባል ከመሆንም ውጭ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት፣ የሃይል አቅርቦት፣ የተማረ የሰው ኃይል መኖሩ፣ አቅርቦት መኖሩ፣ ማትጊያ መኖሩ". ወዘተ ግምት ውስጥ በኢንቨስተሮች ሲገቡ ነው፡፡ ለዚህም ነው የድርጅቱ አባል ከሆኑ የቆዩ የአፍሪካ ሃገራት ያን ያህል ኢንቨስትመንት ሲስቡ የማናየው፡፡ ነገር ግን የድርጅቱ አባል ስንሆን የምናወጣቸው ሕጎችና የምንወስዳቸው እርምጃዎችና አሰራራችንን በሙሉ ግልፅና የሚተነበይ መሆን አለበት፡፡ ወደ ኋላ የሚመለሱ ስላልሆኑ ይታሰራሉ፡፡ በዚህም የተረጋጋ የንግድ አሰራር ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ ከንግድ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አስተዳደራዊ ስርዓቶችና የፍርድ ተቋማትም ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ውጤታማ እንዲሆኑ ስለሚጠይቅ ከዚህ ከዚህ አንፃርም የተለያዩ ማሻሻያዎችን በሃገር ውስጥ እንዲደረጉ ተጨማሪ ጫና ስለሚፈጥር እንደ አንድ ጥቅም ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህም ለኢንቨስተሮች በከፍተኛ ሁኔታ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ ሪፖርተር፡- ስለዚህ አባል ለመሆን ጊዜው አሁን ነው? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- የጊዜው ጉዳይ አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ በኋላ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ስትወስድ ቆይታለች፡፡ ማሻሻያው የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በረጅም ጊዜ ከዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ጋር ማዋሃድንም ዓላማ ያደረገ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ GATT በነበረበት ጊዜ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ኑሮ የተሻለ ይሆን ነበር ብየ እገምታለሁ፡፡ አሁን ትልቅ ዋጋ ትከፍላለች፡፡ ያኔ ተፈላጊው መስፈርት ቀላል ነበር፡፡ ያ አምልጧታል፡፡ አሁን የድርጅቱ አባል መሆን ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ነው፡፡ ከዚህም በኋላ የዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት የበለጠ ውስብስብ እየሆነ ነው የሚሄደው፡፡ በመካሄድ ላይ ያለው የዶሀ የእድገት አጀንዳ (Doha Development Agenda) አሁን ካለው በተጨማሪ በርካታ ጉዳዮችን የሚያካትት ነው፡፡ ስለዚህ የንግድ ሥርዓቱን ወደፊት ስንመለከተው የበለጠ ውስብስብ እየሆነ የሚሄድ ስለሆነና የድርጅት አባል የሚሆኑ ሃገራት የሚከፍሉት ዋጋም እየጨመረና ውስብስብ እየሆነ ነው የሚመጣው፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ላለመሆን ምክንያት የላትም፡፡ ጊዜው በፊት ካልነበረ አሁን ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ አባል መሆን አለመሆን ሳይሆን ኢትዮጵያ እድገቱን በሚመጥን ሁኔታና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቿን በሚጠብቅ ሁኔታ እንዴት አባል ትሆናለች እንዴትስ ተጠቃሚ ትሆናለች የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ አባል አትሁን የሚለው ክርክር አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡ ሪፖርተር፡- የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ተወዳዳሪና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት አለብን፡፡ አጠቃላይ የሕግ ሥርዓቱም ከዓለም አቀፉ ንግድ ጋር እንዲስማማ አዳዲስ ሕግ ማውጣትና የነበሩትን መከለስ አለብን፡፡ ተቋሞቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የማይችሉ ደካማ ናቸው፡፡ ከአእምሯዊ ንብረት ጋር የተገናኙ ሕጎች በባለሙያው የተረቀቁና ደረጃቸውን የጠበቁ ሲሆኑ ከሕዝብ መገናኛ እና ንግድና ገንዘብ ጋር የተያያዙ ሕጎች ግን ባለሙያ ያልነኳቸውና ደካማ እንደሆኑ ይተቻል፡፡ ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- የዓለም የንግድ ድርጅት አንድ ሃገር ምን ዓይነት ሕግ ያውጣ በምን ዓይነት መልኩ ሕግ ያውጣ የሚል ነገር በቀጥታ አይደነግግም ወይም አይገዛም፡፡ ነገር ግን የሚለው አንደኛ ከንግድ ሕጉ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ስምምነቶችን በተመለከተ እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ እርምጃው አስተዳደራዊ አልያም ሕግ ማውጣት ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛ ሕጉ ከስምምነቶቹ ጋር መስማማት መቻል አለበት፡፡ በተጨማሪም የሚወጡ ሕጎች፣ ውሳኔዎችና አሰራሮች ግልፅና ተገማች እንዲሆኑ ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት ሕጎቹ ለሁሉም ተደራሽ የሆኑ እንዲሆኑ ያዛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢትዮጵያ በርካታ ሕጎችን ማውጣት ይኖርባታል፡፡ አንዳንድ ልዩ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ድርጅቱ በማደግ ላይ ላሉና በእድገት ወደ ኋላ ለቀሩ ሃገራት የተሰጠውን መብት ተጠቃሚ ልትሆን ትችላለች፡፡ የድርድሩ ውጤት ገና ያልታወቀ ቢሆንም፡፡ አባል ብትሆንም ተከታታይ ክትትል አለባት፡፡ ክትትሉ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ድርጅቱ የሚወስደው እርምጃ ይኖራል፡፡ ተፅዕኖው ቀጥተኛ ሳይሆን ተዘዋዋሪ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ግን ህጎች ሲወጡ በተቻለ መጠን ባለሙያዎችን እና የተለያዩ የሕብረተሰብ አካላትና ባለድርሻዎችን በስፋት የሚያሳትፍ መሆን ይኖርበታል ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ያደጉት ሃገራት በማደግ ላይ ላሉትና በልማት ወደኋላ ለቀሩት ሃገራት ድጋፍ መስጠት እንዳለባቸውና በልዩ ሁኔታ ሊያዩዋቸው እንደሚገባ ተገል"ል፡፡ ነገር ግን ድንጋጌው አስገዳጅነት የሌለውና በሃገራቱ በጎ ፈቃድ የሚፈፀም ከመሆኑ አንፃር የእስከ አሁኑ ተግባራዊ ልምድ ምን ይመስላል? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- እነዚህ ሃገራት ካላቸው የኢኮኖሚ አቅም በመነሳት በተለየ ሁኔታ መታየት እንዳለባቸው የሚደነግጉ በርካታ ሕጎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች የግብርና ስምምነት ከሚጥላቸው ዋና ዋና ግዴታዎች ሙሉ በሙሉ ነፃ ናቸው፡፡ በርካታ ስምምነቶችን ለመፈፀም የሽግግር ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ ያደጉ ሃገራት ድጋፍ ለመስጠት የሚችሉበትም ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አባል የምትሆነው በድርድር በመሆኑ ስምምነቱ ላይ የተቀመጡት መብቶችና ጥቅሞች ለኢትዮጵያ ይሰጣታል ወይም አይሰጣትም የሚለውን መወሰን ያስቸግራል፡፡ በርግጥ የዶሀ የልማት አጀንዳ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች በተፋጠነ ስርዓት ድርጅቱን የሚቀላቀሉበትንና የሚጠየቁት የአባልነት ግዴታም ከኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ይደነግጋል፡፡ የንግድ ድርጅቱ ጠቅላላ ምክር ቤትም ይህንኑ መሠረት በማድረግ እነዚህ ሃገሮች በተፋጠነ ስርዓት የድርጅቱ አባል ስለሚሆኑበት ስርዓት መመሪያዎችን አውጥቷል፡፡ ከልምድ እንደምናየው ከሆነ ግን በድርድር የሚገቡ ሃገሮች ስምምነቶቹ ከሚጠይቁት ግዴታዎች በላይ (WTO+ obligations) ይጠየቃሉ፡፡ ይህ ካምቦዲያ፣ ኔፓልና ኬፕቪርዴን አጋጥሟል፡፡ ለምሳሌ ያህል በግብርናው ስምምነት ድንጋጌ መሠረት የውጭ ንግድ ድጎማን እነዚህ ሃገራት እንዲያስቀሩ አይጠየቁም፡፡ ድርድሩ ግን ሦስቱንም ሃገራት የውጭ ንግድ ድጎማቸውን 0 እንዲያደርጉ ነው ያደረጋቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያም ሁኔታ በድርድር የሚወሰን ነው፡፡ የሽግግር ጊዜውንም ቢሆን እንደመብት መጠየቅ አትችልም፡፡ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮች ቢያንስ ቢያንስ አስቀድመው አባል ከሆኑና በተመሳሳይ የኢኮኖሚ አቅም ላይ ከሚገኙ በልማት ወደ ኋላ ከቀሩ ሃገራት በላይ ግዴታ ልንሸከም አይገባንም የሚል ሮሮ በተደጋጋሚ ያሰማሉ፡፡ ስለዚህ እስከ አሁን ተግባራዊ አፈፃፀሙ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያም የተለዬ ነገር ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ በሌላ በኩል ሁሉንም አባል ሃገራት በተመሳሳይ መልኩ ማየት (MFN) መርህ እያደጉ ያሉና በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሃገሮችን ለመርዳት ከሆነ በልዩ ሁኔታ ይታያል፡፡ መስጠት አለባችሁ ሳይሆን ያደጉ ሃገሮች ልዩ እርዳታ መስጠት ከፈለጉ ይችላሉ ነው የሚለው፡፡ ሲሰጡም ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውንም ግምት ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ፡፡ በመካሄድ ላይ ባለው የዶሀ የልማት አጀንዳ ድርድር ውስጥ በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ ሃገራት የሚሰጠው ልዩ እገዛ ወይም ጥቅም ህጋዊ መሠረት እንዲኖረውና አስገዳጅ እንዲሆን ጥያቄ ቀርቧል፡፡ የዚህ ውጤት ምን እንደሚሆን መተንበይ ያስቸግራል፡፡ ሪፖርተር፡- በርካታ ሃገራት በሁለትዮሽ ድርድሩ ብዙ ጊዜ የሚወስድባቸው ከአሜሪካ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ ወዳጅ ሃገራት ናቸው፡፡ በቴክኒኩም ሆነ በገንዘብ አሜሪካ የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ሂደት ለማገዝ ቃል ገብታለች፡፡ ነገር ግን ይህን የምታደርገው ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የአሁኑ የአሜሪካ መንግሥት ፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስለሆነች ነው የሚሉ አሉ፡፡ በመጭው ምርጫ የመንግሥት ስርዓት ቢደረግ በግንኙነታቸው ዙሪያ ለውጥ ይኖራል? እስከ አሁንስ ከአሜሪካ በጉዳዩ ላይ ምን ተጠቀምን? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- አሜሪካ ካላት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አቅም አንፃር በዓለም የንግድ ድርጅት ሥርዓት ውስጥ ተፅዕኖ እንዳላት የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ አንድ ሃገር የራሱን ጥቅም ለማስከበር ጥረት ማድረጉ አይቀርም፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቱ አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረበችበት ጊዜ ጀምሮ በግልፅ ድጋፍ ሰጥታለች፡፡ የተለያዩ እርዳታዎችን ለማድረግም ቃል ገብታለች፡፡ የአባልነት ሂደቱ እንዲፋጠን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ፕሮጀክት ነድፋ እያስተባበረች ነው፡፡ ዩ ኤስ ኤ አይዲ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር "ዶሀ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ፕሮጀክት" በሚል ፕሮጀክት ከፍቶ ወጭ ሸፍኖ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሜሪካ ተጨባጭ እርዳታ እያደረገች ነው ያለችው፡፡ ወደፊት የሚወጣውን መተንበይ አይቻልም፡፡ አሜሪካ ኢትዮጵያን የምትደግፈው ከሽብርተኝነት ጋር በተገናኝ መንገድ ነው ወይስ አይደለም ለሚለው ግልፅ የሆነ መልስ ለመስጠት ያስቸግረኝ ይሆናል፡፡ ግን ሲባል እሰማለሁ፡፡ ከ1993 ዓ.ም በኋላ የአሜሪካ ፖሊሲ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ለነገሩ አሜሪካ አግዋንና ሌሎች የተለያዩ የንግድ ግንኙነቶችን ለማድረግ ሽብርተኝነትን መዋጋት እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ነው የምታየው፡፡ የአሜሪካ ምርጫ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይቀይራል አይቀይርም የሚለው አከራካሪ ቢሆንም ማንም ቢያሸንፍ መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ ያስከትላል ብዬ አልገምትም፡፡ ሪፖርተር፡- የአባላት ሒደቱ ላይ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ባለድርሻዎች ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- መንግሥት የራሱን እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ የውጭ ንግድ ሥርዓት ዶክመንት አቅርቧል፡፡ በንግዱ ሚኒስትሩ የሚመራ "ስቲሪንግ" ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴም አቋቁሞ ምሁራንን፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትንና ሌሎችንም አቅፏል፡፡ ነገር ግን ተጨማሪ የባለድርሻዎች ተሳትፎ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበረሰቡ ሚድያውና ምሁራን ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት ምንድን ነው? አባልነቱ የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው? ዝግጅት ያስፈልገናል ወይ? ብለን ልንወያይ ይገባናል፡፡ አሁን ግን ሁሉም ዝም እንዳለ ነው፡፡ ቢሳተፉ ለመንግሥት ብዙ ያልታዩ ቀዳዳዎችን ማሳየት ይችሉ ነበር፡፡ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ትልቅ ክንውን ሲሆን ሁሉንም ዜጎች ይነካካል፡፡ ውጤቱ ሁሉንም ይመለከታል፡፡ ሪፖርተር፡- በመፅሃፍዎ ላይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን ደካማ ተሳትፎ ተችተው ነበር፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፎ ጨምሯል? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- የአዲስ አበባ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የንግዱ ማህበረሰብን የሚያንቀሳቅሰው አካል ነው፡፡ ዝም ማለቱ አስገርሞኝ ነበር፡፡ አሁንም እንደ ትልቅ አጀንዳ አድርጎት አላየሁም፡፡ ከመንግሥት ጋር በካምቦዲያና ኔፓል አብሮ የሠራ የተንቀሳቀሰ አካል ነው፡፡ እስካሁን የንግድ ድርድሩ የአባላቶቹን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባታል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ አባልነት የሚያመጣው ጥቅምም ሆነ ጉዳት በመጀመሪያ ደረጃ የሚመለከተው እንደመሆኑ ትልቅ ሚና ሊኖረው ይገባል፡፡ የግሉ ሴክተር በተወሰኑ ደረጃዎች ተሳትፎ አለው፡፡ መንግሥት የግል ተቋሙን የግድ ማሳተፍ አለበት፡፡ በግድም አብሮ ሊሰራ ይገባል፡፡ ምክር ቤቱ ግፊት በማድረግና ተፅዕኖ በማሳረፍ ጥቅሙን ማስጠበቅ አለበት፡፡ በራሳቸው መንገድ ሥርዓቱ ውስጥ በድርድሩ አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የድርድር ሂደት ውስጥ በጣም አወዛጋቢ ሊሆን የሚችለው ጉዳይ ምን ይመስልዎታል? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- መንግሥት የአገልግሎት ሴክተሩ በተለይም ደግሞ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የመብራት፣ የገንዘብ ተቋማት". ወዘተ ለልማት አቅም ማስፈፀሚያ ቁልፍ መሳሪያ ናቸው የሚል ሃሳብ አለው፡፡ በመሆኑም የተወሰኑ ቁልፍ የአገልግሎት ሴክተሮችን ለውጭ ውድድር ክፍት ለማድረግ/ከእጁ ለማውጣት/ ቢያንስ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡ በሌላ መንገድ የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የሚደግፉ ሃገራት ቁልፍ የሆኑ የአገልግሎት ሴክተሮች ለውጭ ድርድር ክፍት እንዲሆኑ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ በልማት ወደ ኋላ የቀሩት በቅርቡ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የሆኑ ሃገራት እነዚህን የአገልግሎት ዘርፎች በተለያዩ ሁኔታና ቅድመ ሁኔታ ለውጭ ውድድር ክፍት አድርገዋል፡፡ ልብ ሊባል የሚገባው ክፍት ይሁኑ ሲባል ሙሉ በሙሉ አይደለም፡፡ GATS (የአገልግሎት ዘርፍ ስምምነት) ለአባላት በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡ ልዩ መብትና ክፍት የማይሆኑበትን ገደብ ያስቀምጣል፡፡ ምን ያህል ድርሻ የውጭ ኩባንያዎች ይይዛሉ? የት ነው ቅርንጫፍ መክፈት የሚችሉት?". ወዘተ. ገደብ ሊደረግባቸው ይችላል፡፡ የትኞቹ አገልግሎቶች ክፍት ይሁኑ የሚለውን የመወሰን ስልጣን የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ የፖሊሲ ገዳይ በመሆኑ የፖሊሲ አውጭዎች ጉዳይ ነው፡፡ ክፍት የሚሆኑ ከሆነ ግን በምን ዓይነት ሁኔታ፣ የሀገሪቱን ፖሊሲና ዓላማ በማይነካ ሁኔታ ተጠቃሚዎችን በማይጎዳ ሁኔታ መፈፀም አለበት የሚለው ነገር አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ሪፖርተር፡- በመጨረሻ ማለት የሚፈልጉት ነገር ካለ? ዶ/ር ፍቅረማርቆስ፡- ኢትዮጵያ በድርድሩ ሂደት ላይ ናት፡፡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡ ውጤታማ የጋራ ሥራ ያስፈልጋለ፡፡ ሁሉንም ሴክተር የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነቱ ይመለከታል፡፡ የማስተባበር ሥራ መሰራት አለበት፡፡ የቴክኒክ ብቃትን ማሳደግም ያስፈልጋል፡፡ በጣም ውስብስብ የሆነውን የዓለም ንግድ ስርዓት ለመገንዘብና የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ይጠቅማል፡ አባል መሆን በራሱ ግብ ነው ብዬ አልገምትም፡፡ እንዴት አድርጋ ነው በዚህ የንግድ ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚ የምትሆነው የሚለው በጣም ጠቃሚ ነጥብ ነው፡፡ እድገቱን የሚያፋጥን ከእኛ የእድገት ፖሊሲዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ማረጋገጥም አስፈላጊ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |