Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 25th
Home arrow Sections arrow ሕብረተሰቡ በዳልጋ ከብቶች...
ሕብረተሰቡ በዳልጋ ከብቶች... Print E-mail
Saturday, 26 April 2008
ሕብረተሰቡ በዳልጋ ከብቶች ግዢ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ንቁ ያልሆኑ፣ ጆሯቸውን የጣሉ፣ የቆዳቸው ፀጉር የሳሳና ወዛማ ያልሆነ፣ በአፋቸውና በአፍንጫቸው አካባቢ ለየት ያለ ፈሳሽና በተለይም አፍንጫቸው አካባቢ የመድረቅ ሁኔታ የሚታይባቸው ዳልጋ ከብቶች የተለያዩ አይነት በሽታዎች ያደረባቸው ስለሆኑ ሕብረተሰቡ ፈጽሞ እንዳይገዛ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የትራንስፖርት፣ ስጋ ስርጭትና በረዶ ቤት ዋና ክፍል ኃላፊ አስታወቁ፡፡

 

ሕብረተሰቡ ለትንሳኤ በዓል የሚያርዳቸውን ከብቶች ጤንነት አስመልክቶ ኃላፊው ዶክተር ቢተው ጌታሁን ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት፣ በዝርዝር ከተጠቀሱት የበሽታ ምልክቶች መካከል የአፍንጫ አካባቢ መድረቅ ኃይለኛ ትኩሳትን ያስከትላል፡፡

ከዚህም ሌላ ከብቶቹ በሚታረዱበት ጊዜ ጤናማ ከሆኑ ደማቸው በትክክል ሊረጋ እንደሚችል፣ ደማቸው ካልረጋና ከጠቆረም አባሰንጋ የተባለው በሽታ የያዛቸው መሆኑን የሚያመለክት ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግና ወደ ውስጥ ገብቶ ለመሰንጠቅ ከመሞከር መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በአካባቢው ከሚገኙ የእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎች ጋር ተመካክሮ ሊገዛና ሊያርድ የሚችልበትን ስልት እንዲያመቻች፣ ነጋዴዎች በቅርጫ የሚያከፋፍሉትን ስጋ ከመግዛትም እንዲቆጠብ፣ ንጽህናው በተጠበቀ ቦታ ላይ እንዲያርድ፣ ደሙን፣ ፈርሱንና ሌላውንም ተረፈ ስጋ ጉድጓድ ውስጥ እንዲቀብር አሳስበዋል፡፡ ለእርድ አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎች ንጽህና በሚገባ መጠበቅም በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ይህንን የሚያከናውነው በበዓላት ቀን ብቻ እንጂ በባዘቦቱ ግን ወደ ድርጅቱ ዘንድ አቅርቦ እያሳረደ መጠቀም እንደሚገባው ኃላፊው አመልክተው በበዓላት ቀን ቅርጫ የመከፋፈሉን ባህል ማስቀረት የሚቻለው በሂደት መሆኑንና ለዚህም እውን መሆን ሰፊ የቅስቀሳ ሥራና የግንዛቤ ማጎልበቻ ትምህርት የሚያስፈልገው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለትንሳኤ በዓል ከ2ሺህ 700 በላይ የዳልጋ ከብቶች፣ ከ500 በላይ በግና ፍየሎች ይታረዳሉ ተብሎ እንደሚገመት፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ ከ1ሺህ 200 በላይ ዳልጋ ከብቶችና ከ850 የሚበልጡ በጎችና ፍየሎች እንደታረዱ አስታውቀዋል፡፡

እርዱም የሚከናወነው ቅዳሜ ሚያዚያ 18 ቀን 2000 ከንጋቱ 11 ሰአት ላይ ሲሆን ስጋውንም ለደምበኞች የሚያጓጉዙ 16 ተሽከርካሪዎች መመደባቸውን፣ ድርጅቱ የእርድ አገልግሎት የሚሰጠው ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ላላቸው ባለልኳንዳ ቤቶች መሆኑን ዶክተር ቢተው ገልጸዋል፡፡

 
< Prev   Next >