| መረጃ ለዲያስፖራው |
|
|
| Saturday, 26 April 2008 | |
|
በጋዜጣው ሪፖርተር
ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ውስጥ ወደ ውጭ ለትምህርት፣ ለስራ እንዲሁም በስደት ከኢትዮጵያ የወጡ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ከፍተኛና ከጊዜ ወደ ጊዜም እየጨመረ የመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ምክንያቶች ወጥተው በአፍሪካ በእስያ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ቢሆንም በተለይ በሰሜን አሜሪካ በምዕራብ አውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በምሥራቅ አፍሪካና በደቡብ አፍሪካ በብዛት ተሰራጭተው ይገኛሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ከ2 ሚሊዮን በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዲያስፖራ ቢኖርም ሁሉም አቅም ኖሮት አገሩን ለማልማት ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ባይደረስም በጊዜ ሂደት ግን አቅሙን ያጎለበተ፣ ክሂሉን እያሳደገና ከሚኖርበት አገር ባህል ተጣጥሞ እየኖረ ያለው ጥቂት አይደለም፡፡ አብዛኛው ዲያስፖራ አገሩ ገብቶ በልማቱ ለመሳተፍ አይቻል እንጂ አገር ቤት ያሉትን ቤተሰቦቹንና ወዳጅ ዘመዱን ይደጉማል፡፡ አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት በ2005 ባወጣው ሪፖርቱ፣ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የላኩት ገንዘብ 800 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነበር፡፡ ይህ በህጋዊ መንገድ የተላከ ሲሆን በፖስታና በሰዎች የተላከው ቢሰላ ቁጥሩን እጥፍ ሊያደርገው እንደሚችል ገልጿል፡፡ ዲያስፖራው ቤተሰቡን በገንዘብ ከመደጎም ባሻገር አገሩን በዘላቂ ልማት ሊረዳ የሚችልበት የኢንቨስትመንት አማራጭ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ ቀደም በተሻለ መልኩም አገሩ ገብቶ በልማቱ መሳተፍ ይችላል፡፡ አብዛኛው ዲያስፖራ አገሩ ገብቶ ለመስራት ፍላጎቱ ቢኖረውም ይሳካልኝ ይሆን ወይ የሚለው ጥርጣሬ ወደ አገሩ እንዳይመጣ ማነቆ ሆኖበታል፡፡ ዲያስፖራው ለቤተሰቡ የሚልከው ገንዘብ ከእለት ተዕለት ጉርስ አልፎ በጥቃቅንና በአነስተኛ ንግድም ሊያሰማራ የሚችል ነው፡፡ ይህም ዲያስፖራው አገሩን በልማት ለማሳደግ ያለው አቅም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ዲያስፖራው በገንዘብ አቅም ብቻ ሳይሆን የሰለጠነ የሰው ኃይል በመሆኑም እንደ አንድ ካፒታል ሊታይ ይገባል፡፡ የአለማቀፉ ስደተኞች ድርጅት ሪፖርት እንደሚያሳየው ከ1980 እስከ 1991 ባለው ጊዜ ብቻ ኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚሆነውን የሰው ካፒታሏን አጥታለች፡፡ በንግድ አስተዳደርና በሌሎች ክህሎችም የሰለጠኑ ባለሙያዎች በብዛት ተሰደዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው ዲያስፖራ አገሩ ገብቶ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው በተለያየ መንገድ እየገለፀ ቢሆንም በሌላ በኩል ያለውን ገንዘብ እንዴትና ለምን አይነት ሥራ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለበት አያውቅም፡፡ ለዚህም አንደኛው ከአገሩ ርቆ ብዙ አመት በመቆየቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እዚህ ያለው የመረጃ ፍሰት ደካማ በመሆኑ ነው፡፡ አገራቸው ተመልሰው በልማት የተሰማሩትም ሆኑ ሁኔታዎች ሳይመቻችላቸው ቀርቶ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የሚያነሱት በመንግሥት በኩል የተሟላ መረጃ የማግኘት ችግርና የተቀላጠፈ አሰራር አለመኖርን ነው፡፡ በየትኛው ዘርፍ መሰማራት እንደሚችሉ፣ የትኛው ቦታ ለምን ሥራ አመቺ እንደሆነ፣ ማንን ማመን እንዳለባቸው እንዴት መሄድና መስራት እንደሚገባቸው በቂ መረጃ የሚያገኙበት ቦታ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎቱ ቢኖርም ከመጡ በኋላ ተስፋ በመቁረጥ የሚመለሱ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ዲያስፖራዎች እንደሚሉት አሰልቺ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓትና ደካማ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት መኖሩ ሃሳባቸውን አስቀይሯቸዋል፡፡ ለአገራቸው ያሰቡትንም ልማት ወደ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ይዘው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል፡፡ አንዱ የኢትዮጵያ ችግር ዲያስፖራውን በተቀናጀ መልኩ አደራጅቶ በአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ተሳታፊ ያለማድረግ ነው፡፡ በአሁኑ ዲያስፖራው በአገሩ ያለው ተሳትፎ ሊያደርግ ከሚችለው በጣም ያነሰ ነው፡፡ ዲያስፖራው ለወገኑ ከሚልከው ገንዘብ፣ በልማቱ ከሚሳተፈውና ሊፈጥር ከሚችለው የወጪ ንግድ አንፃር እያደረገ ያለው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ዲያስፖራው ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ቢሆንም ይህንን አስፈላጊ ኃይል ወደ ጥቅም ማዋሉ ዋናው ፈተና ነው፡፡ በአገሪቱ ያሉ የአሰራር መጓተቶችና የቁጥጥር ግልጽነት ማጣት በአጭር ጊዜ እልባት የሚያገኙ ባይሆኑም የአለም ባንክ የኢንቨስትመንት ዳሰሳ ሁኔታዎቹ ከቀድሞ በተሻለ መልኩ እየተለወጡ መሆኑን አስፍሯል፡፡ አፋጣኝ የሆኑ ክፍተቶችን የመሙላት ሥራ አገሪቱን ተጠቃሚ ሊያደርጋት እንደሚችልም ሳይጠቁም አላለፈም፡፡ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚባለውን ዲያስፖራ በፖሊሲዎች ላይ ማወያየትና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር በማገናኘቱ ረገድ መንግሥት ሊሰራበት ይገባል፡፡ በዳይሬክት ኢንቨስትመንትና በንግድ ልማት ብሔራዊና የእርዳታ ሰጪ ፖሊሲ አውጪዎች አቅሙ ያለው ዲያስፖራ የሚኖውን የልማት አጋርነት ከግምት ማስገባት አለባቸው፡፡ የዲያስፖራው የኢኮኖሚ አጋርነት ከግምት ገብቶ በሚሰማሩበት ዘርፍም ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በመንግሥትና በዲያስፖራው መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ልትደርስ የምትችለው መንግሥትም ሆነ ዲያስፖራው በመካከላቸው ያለውን የፖለቲካ ልዩነትን ወደ ጎን ብለው ለልማቱ ትኩረት የሰጡ እንደሆነ ነው፡፡ መንግሥት የዲያስፖራውን ፖለቲካዊ አመለካከት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚው ዘርፍ ሊያደርግ የሚችለውን አስተዋጽኦ ቅድሚያ በመስጠት ሊያሳትፍ የሚችልበትን አዋጭና ቀጣይነት ያለው መንገድ መቀየስ እንዲሁም ዲያስፖራው በወሬ ብቻ ከሚሰማው የፖለቲካና የርስበርስ ሽኩቻ ራሱን ነፃ በማድረግ አገሩ ገብቶ በልማት የሚሳተፍበትን አጋጣሚ መፍጠር ይኖርበታል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |