|
Saturday, 26 April 2008 |
|
ነዋሪዎች "ጉድጓዶች ተቆፍረው ሥራ ሲጀምሩ ችግሩ ይቃለላል" የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን
በጋዜጣው ሪፖርተር ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 01/05 ዘነበ ወርቅ አደባባይ አካባቢ ነው፡፡ የቀበሌ 01/05 አስተዳደር ጽ/ቤትን ይዘው ወደ ላይ ሲያቀኑ ጂቲ ዜድ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በየቤቱ የተሰቀሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ከርቀት ያያሉ፡፡
ግቢያቸው ሲገቡ ደግሞ በትዕዛዝ የተሰሩ ይመስል የውሃው መውረጃ ቧንቧና የውሃው ቆጣሪ በእኩል ተከርክመውና በእኩል ቁመት ተመጥነው ያገኙዋቸዋል፡፡
በማጠራቀሚያዎቹ ውሃ ከገባ ግን ከ8 ወር በላይ አስቆጥሮ ነበር፡፡ እንደ እድል ሆኖ በሳምንትም ይሁን በሁለት ሳምንት አንዴ በሌሊት ከመጣ ያጋጠማቸው ይቀዳሉ፡፡ ያጡት ደግሞ እንደ ልማዳቸው ቁልቁል በመውረድ ቀበሌ 01/05 አስተዳደር ጽ/ቤት ፊት ለፊት ካለው ከሶስት ከማያንሱ የውሃ መሸጫ ቤቶች ከአንዳቸው ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡
በስምንት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዚያ 4 ቀን 2000 ዓ.ም ለዚያውም በቀን ውሃ ማግኘታቸውን የገለፁልኝ የአካባቢው ነዋሪ የውሃ ማጠራቀሚያቸው እስኪሞላ ድረስም የውሃው ኃይል መኖር "አስገርሞኛል" ብለዋል፡፡ "ውሃ በዚህ ኃይል ሲፈስ ያየሁት ከ8 ወራት በፊት ነበር፡፡ ውሃ በአግባቡ ማግኘት ካቆምን ወደ ሶስት አመታትን አስቆጥረናል፡፡ ቀድሞ በየዕለቱ እናገኝ የነበረው ውሃ ቀስ በቀስ ቀርቶ በሳምንት አንዴ አርብ ለቅዳሜ ከሌሊቱ ዘጠኝ እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ነበር የምናገኘው፡፡ እሱም እየጠፋ 15 ቀናትና ከዚያ በላይ መቆየት ጀምሮ ነበር፡፡ የውሃው ግፊት ከቆጣሪው ቁመት ልክ ባለማለፉ ነበር የቧንቧችንን ቁመት በዛው ልክ ማሳጠራችን፡፡ እንዲያም ሆኖ ውሃ ሲመጣ የደቀነው እቃ እንኳ ሳይሞላ ውሃው ተመልሶ ይጠፋል" በማለት ምን ያህል የውሃ እጦት ችግር ለከፍተኛ ወጪና እንግልት እንደዳረጋቸው አያይዘው ገልፀዋል፡፡
ዛሬ ዛሬ እየገጠማቸው ያለው ችግር ውሃ መጥቶ ሊቀዱ ሲፈልጉ ውሃው በዛችው አጭር ቧንቧም ያለመውረዱ ነው፡፡ አብዛኛው የአካባቢው ነዋሪ ውሃውን በሳምንትም ሆነ በ15 ቀናት ሲያገኝ የሚቀዳው በእኩል ሰዓት አንዴ በመሆኑ በአቀማመጣቸው ከታች ሰፈር የሆኑት ቧንቧቸውን በቅድሚያ የከፈቱ ሰዎች ብቻ የእድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ከእነሱ ፍላጎት አልፎና ተርፎ ወደ ላይ ወዳሉት ውሃ የሚደርሰው ከታች ያሉት በቅቷቸው ሲዘጉ በመሆኑና ይህ የሚሆነው ደግሞ ተመጥኖ በሚሰጣቸው የሰዓት ገደብ የታችኞቹ ፍላጎት ከተሟላ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የተደቀነው እቃ ሳይሞላ ሌሊቱ ይነጋና ውሃው እንደ ወትሮው እልም ይላል፡፡
በዚህ አካባቢ ውሃ የሚሸጠው 20 ሊትር በሚይዘው ጀሪካን 50 ሳንቲም ሲሆን ማጓጓዣው ደግሞ ሁለት ከሃምሳ ገብቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ውሃ በጀሪካን ለሚያመላልሱ ሰዎች በጀሪካን የሚከፍሉት 2 ብር የነበረ ሲሆን አሁን 2 ብር ከ50 ለመክፈል ተገደዋል፡፡ በአጠቃላይ ለ20 ሊትር ውሃ ሶስት ብር መክፈል የግድ ነው፡፡ ታክሲ ከተገኘ ደግሞ አንድ ጀሪካን በ1 ብር ይጫናል፡፡ ይሁንና ካለው የትራንስፖርት ችግር አንፃር ተጠቃሚው በጀሪካን 3 ብር ማውጣቱ የግድ ይሆናል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ ከሆነ ለዚህ ሁሉ ችግር ውሃና ፍሳሽ እንዳለው ከዝናብ ጋር የተያያዘ የውሃ አቅርቦት ችግር ኖሮ ሳይሆን "ውሃውን በአግባቡ ያለማከፋፈል ነው፡፡"
አየር ጤና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03/05 አካባቢም ተመሣሣይ የውሃ ችግር አለባቸው፡፡ የእነሱን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ውሃ ለመቅዳት ከአየር ጤና ዘነበ ወርቅ አደባባይ ድረስ ካለው የውሃ መሸጫ ስፍራ መመላለሳቸው ነው፡፡
ለአካባቢው ነዋሪዎች የውሃ እጥረት ችግር መከሰት የጀመረው ከሶስት ዓመታት በፊት ጀምሮ ሲሆን የ1999 እና የ2000ው ደግሞ የከፋ ነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ባሉ ጊዜያት ውሃ ሳይቋረጥ በየእለቱ ያገኙ ነበር፡፡
"ውሃና ፍሳሽ ውሃ የምታገኙት በፈረቃ ነው ሳይል፣ ሳያሳውቀንና መቼና መቼ ውሃ እንደምናገኝ ሳይገልጽልን ውሃን ያህል ነገር ሲያቋርጥብን ምን እንደሚሰማው አላውቅም" ሲሉ የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ ምንም መረጃ ስለሌላቸው በየቀኑና በየሌሊቱ ውሃ መጥቶ ይሆን በማለት መፈተሽ ልምድ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ለአካባቢው ነዋሪዎች ውሃ በቀን ማግኘት የህልም እንጀራ ነው፡፡ በሌሊት በሳምንት ወይም በ15 ቀን አንዴ ለሚመጣውም ሳይቀዱ የሚያልፋቸው ጊዜ ይበልጣል፡፡ እንደ ማንኛውም የውሃ ችግር ባለበት አካባቢ እነሱም ጋር የሃይል እጥረት በመኖሩ ውሃውን በአግባቡ ሳያገኙ ውሃ መጥቶ የሚሄድበት ጊዜ ይደርሳል፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ባሉት ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ በመጠጥ ውሃ እጥረት የተነሳ መቸገራቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ ከተማ፣ በአራዳና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ባሉት ቀበሌዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ እንዳመለከቱት ውሃዋ ቀን፣ ቀን ፈጽሞ እንደማትመጣ ነገር ግን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ድረስ ጭልጭል ትልና ተመልሳ እንደምትሄድ ነው፡፡
ከእነዚህም መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 04/05 ነዋሪ የሆኑ አቶ ተክለወልድ ገላን እንዳብራሩት ችግሩ የውሃ እጥረት ብቻ ሳይሆን ታሪፍ መጨመሩም ነው፡፡
"በጠብታ መልክ እየወረደ ለተጠቀምነው ውሃ ፍጆታ የምንከፍለው ታሪፍ ከሦስት ወራት በፊት በሰፊው ተጠቅመን ስንከፍለው ከነበረው ታሪፍ በእጅጉ የበለጠ ነው" ብለዋል፡፡
ወጣት ሚሚ ጌድዮን የተባለችው የዚሁ ቀበሌ ሌላዋ ነዋሪ በበኩሏ በአንድ አጥር ግቢ ውስጥ አምስት አባወራዎች እንደሚገኙና እያንዳንዱም አባውራ የውሃ ቧንቧ እንዳለው አስረድታለች፡፡ ከእነዚህም መካከል የሦስት አባወራዎች ውሀ ሌሊት ላይ ብቻ ስትመጣ የሁለቱ ግን ቀኑን ሙሉ አንዳለ ወጣቷ አመልክታ ብቅ ጥልቅ እያለች ሌሊት ላይ የምትመጣውን ውሃ ለመቅዳት ሲባል መኝታ እንደሌለ አስታውቃለች፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወንድሙ ከበደ "ውሃ የምትገኘው ሌሊት ላይ ብቻ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ቀን ሥራ ላይ ስለምንውል ሌሊት ተነስተን ለመቅዳት ይደክመናል፡፡ ጠዋት እንቀዳለን ስንል ትጠፋለች" ብሏል፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ነዋሪዎች ውሃ ፍለጋ ጀሪካንና ባሊ እያንጠለጠሉ ሩቅ መንገድ ሲጓዙ እንደሚስተዋሉ አስረድቷል፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከበልግ ዝናብ ጋር በተያያዘ የውሃ እጥረት አይገጥመኝም ብሏል፡፡ በሳሪስ ሼል አካባቢ፣ በቅሎ ቤት እስከ አርብ ባለው ጊዜ ለ3 ተከታታይ ቀናት ውሃ አላገኙም ነበር፡፡
በኮተቤ፣ በሽሮሜዳ፣ በፈረንሳይ አለም ባንክ፣ ካራ ቆሬና በከተማዋ መሃል አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች የውሃ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን እየገለፁ ነው፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የማስታወቂያና ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌትነት ገሰሰ እንደገለፁልን ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ጂ.ቲ.ዜድ በሚባለው አካባቢ ያለውን የውሃ እጥረት ለማቃለል ካባ ግቢ ውስጥ ጥልቅ ጉድጓድ እየተቆፈረ ነው፡፡ ጉድጓዱ ተጠናቅቆና አስፈላጊው መሳሪያ ተገጥሞ ውሃ የመስጠት አገልግሎት ሲጀምር ከለገዳዲ ከሚያገኙት በተጨማሪ ውሃ ይኖራቸዋል፡፡ ይህም የአካባቢውን የውሃ እጥረት ያቃልላል፡፡
በሌላ በኩል ከ15 ቀናት በፊት ኃይለኛ ግፊት ያለው ውሃ ሊያገኙ የቻሉት ከዚህ ቀደም ውሃው እያለ ሳይለቀቅላቸው ቀርቶ ሳይሆን ተርሚናል ጋር መብራት በመጥፋቱና ውሃ በፓምፕ የሚያገኙ አካባቢዎች ውሃ ባለማግኘታቸው የተነሳ ነው፡፡
በጂ.ቲ.ዜድ አካባቢ ያሉት ደግሞ ውሃ በግፊት የሚያገኙ በመሆናቸው ኃይል ያለው ውሃ ሊያገኙ ችለዋል፡፡
አቶ አሰፋ ጸጌ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የመካኒሳ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው በአየር ጤና አካባቢ ማኅበራትን ጨምሮ ለረዥም ጊዜ የነበሩ ችግሮችን መፍታታቸውን ነው የገለፁት፡፡ "ከውሃ እጥረት ጋር ተያይዞ ውሃ በሶስት ቀንም ሆነ በሳምንት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ በግለሰብም ሆነ በማኅበራት ደረጃ ያለባቸውን ችግር ሪፖርት ካደረጉ ችግሩን እንፈታለን" ብለዋል፡፡
የውሃ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ትክክለኛ ቦታቸውን ጠቅሰው ለቅርንጫፉ ሪፖርት ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ሥራ አስኪያጁ አሳውቀዋል፡፡
"አካባቢያዊ ችግር ካላቸው ይንገሩን እንፈታለን፡፡ አለም ባንክና ካራ ቆሬ አካባቢ ያለውንም ችግር ለመፍታት እየሰራን ነው" ሲሉ ገልፀዋል፡፡ |