| በደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይግባኝ... |
|
|
| Wednesday, 30 April 2008 | |
|
በደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይግባኝ ላይ ፍ/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ሊሰጥ ነው
በጋዜጣው ሪፖርተር የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከስሰው ከአንድ ዓመት በፊት እስከ እድሜ ልክ እሥራት ፍርድ ያገኙ ባለሥልጣናትን አስመልክቶ በቀረበው ሁለት የይግባኝ መዝገቦች ላይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሚያዚያ 29 ቀን 2000 ዓ.ም የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮቻችን ጠቆሙ፡፡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት በጥር ወር 1999 ዓ.ም በዘር ማጥፋት ወንጀል በተጠረጠሩ የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የዕድሜ ልክ እሥራትን ጨምሮ በየደረጃው የቅጣት ውሣኔ ካሳለፈ በኋላ በተከሳሾቹ በኩል በተናጠል "ነፃ ልንባል ይገባል፣ ጥፋተኛ ከተባልንም ቅጣቱ በዝቷል፣ ይቀነስልን" በሚል ይግባኝ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ በየግላቸው የይግባኝ አቤቱታ ያቀረቡት የደርግ ባለሥልጣናት ብዛት ምንጫችን ያመለከተው ነገር ባይኖርም በግል ይግባኝ ካቀረቡት መካከል ሌ/ኮ/ፍሰሐ ደስታ እና ሻ/ል ለገሰ አስፋው እንደሚገኙበት ጠቁሟል፡፡ ልዩ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ጨምሮ በ21 ተከሳሾች ላይ ፍ/ቤቱ የዕድሜ ልክ እሥራት ቅጣት በማሳለፉ ቅር መሰኘቱን በመግለጽ ተከሳሾቹ በሞት እንዲቀጡለት በመጠየቅ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ አቅርቧል፡፡ ፍ/ቤቱ ሁለቱንም ወገኖች በቃል ሲያከራክር ቆይቶ በመዝገቦቹ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለሚያዚያ 29 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈረደባቸው የደርግ ባለሥልጣናት ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ተይዘው ጥቅምት 15 ቀን 1987 ክስ ተመስርቶባቸው ከ16 ዓመት በኋላ በጥር ወር 1999 ዓ.ም የቅጣት ውሳኔ ማግኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |