| ኤሌክትሪክ የሚቋረጥበት ፕሮግራም... |
|
|
| Wednesday, 30 April 2008 | |
|
ኤሌክትሪክ የሚቋረጥበት ፕሮግራም በአንድ ሰዓት ከፍ አለ
በጋዜጣው ሪፖርተር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ትላንት ይፋ ባደረገው የአንድ ወር ፕሮግራም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቋረጥባቸው ቀናት ፕሮግራም በአንድ ሰዓት አራዘመ፡፡ ከፈረቃ ውጪ የሚደርስ የኃይል መቋረጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ አቶ ሰንደቁ አርአያ የኮርፖሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ የገጠመውን የኃይል እጥረት ለማስተካከል በያዝነው ወር ባወጣው የፈረቃ እደላ ፕሮግራም መሠረት እስከ ሰኔ 30/2000 መድረስ ስለማይቻል ኃይል የሚቋረጥባቸው ቀናት ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግ፤ ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የነበረውን እስከ 3 ሰዓት እንዲራዘም ወስኗል፡፡ በዚሁ መሠረት አዲሱ ፕሮግራም ከሚያዚያ 20 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2000 የሚሠራበት ይሆናል፡፡ "ከፈረቃ ውጪ በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ለምን ኃይል ይቋረጣል?" በሚል ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ችግሩን ለመቅረፍ የኮርፖሬሽኑ የቴክኒክ ቡድን እያጠና የመፍትሄ ሃሳብ እያቀረበ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከፈረቃ ውጪ የኃይል መቋረጥን መፍትሄ ለመስጠት ብርቱ ጥረት እያደረገ ነው" ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አንዳንድ የኮርፖሬሽኑ ደንበኞች በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ በይፋ በጋዜጣ ካወጣው ፕሮግራም በተጨማሪ በማንኛውም ቀንና ሰዓት የኃይል መቋረጥ በተደጋጋሚ ማጋጠሙ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግሩም ከዚህ በፊት ያልነበረ ከመሆኑ አንፃር ሲታይ ሆን ተብሎ የሚደረግ ይመስላል በማለት ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ በተያያዘም ከሚያዚያ 22 - 26 ቀን 2000 ዓ.ም ለሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሩ በሚካሄድባቸው ዋና ዋና ቦታዎች ኃይል እንደማይቋረጥ አቶ ሰንደቁ ጠቁመው ስፖርተኞች ባረፉባቸው ሆቴሎች ኃይል በሚቋረጥባቸው ቀናት ዲዝል ጄኔሬተሮች እንዲጠቀሙ የቴክኒከ እገዛ ለመስጠት የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች ተንቀሳቅሰው አጥጋቢ ውጤት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከሐራምቤ ሆቴል በስተቀር ሁሉም ሆቴሎች የጄኔሬተር ተጠቃሚ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |