Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በድክመት ተተቸ
ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በድክመት ተተቸ Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
በኃይሌ ሙሉ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአገሪቱ ካለው የገዘፈ ሙስና ጋር የማይጣጣም ሪፖርት እንደሚያቀርብ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለመክሰስ ድፍረት ማጣቱን በመግለፅ በተቃዋሚዎች ትችት ቀረበበት፡፡

ኮሚሽኑ የ2000 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ሪፖርቱን ትላንትና (ሚያዚያ 21 ቀን 2000 ዓ.ም) ባቀረበበት ወቅት አቶ ልደቱ አያሌው የኢዴአፓ መድኅን ሊቀመንበር እንደተናገሩት ኮሚሽኑ እየሠራው ያለው በአገሪቱ ከሚታየው ሙስና ጋር ሲነፃፀር ሙስና በአገሪቱ የለም እንዴ የሚያስብል፣ ሪፖርቱም አገሪቱ ያለችበት የሙስና ደረጃ ምን ላይ እንደሆነ የማያሳይ ሲሉ ተችተውታል፡፡

የባለስልጣን ሀብት መጠን መመዝገብ በብዙዎች አገር የሚሰራበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ልደቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊተገበር ያልቻለበትን ምክንያት ጠይቀዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮም ከፍተኛ የሚባሉ ባለስልጣናት ክስ ሲቀርብባቸው እንደማይታዩ ገልጸው "[ባለስልጣናት የማይከሰሱት] ንጹህ ሆነው ነው ወይስ ድፍረት ጠፍቶ ነው" ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ልደቱ ገለፃ ኮሚሽኑ በሰዎች ጥቆማ ጥገኛ ከሚሆን ይልቅ የራሱን የመረጃ ሥራ ቢያጠናክር ሙስናን ለመቆጣጠር የተሻለ አቅም ይኖረዋል፡፡

አቶ ተመስገን ዘውዴ በበኩላቸው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርት የሚገልጸው በሙስና ውስጥ ስላሉ ትናንሽ ወፎች እንጂ ስለትላልቆቹ አሞራዎች እንደማያወራ ተናግረዋል፡፡

የአምስት ሺ ብር ደመወዝ ያላቸው አንዳንድ ባለስልጣናት በሚሊዮን ብር የሚያወጣ ሁለት ቪላዎች ሰርተው 50 ሺ ብር የሚያከራዩበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙት አቶ ተመስገን የእነዚህን ባለስልጣናት ሁኔታ ሳይመረምር ፀረ ሙስና ስለጥቃቅን ሙስናዎች ብቻ ሪፖርት ማቅረቡን እንደ ድክመት ወስደውታል፡፡

የኦፌዴን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ደግሞ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ ያከናወናቸውን ሥራዎች የገመገሙ አንዳንድ ግለሰቦች የኮሚሽኑ አቅም ይህን ያህል ደካማ ነው እንዴ በማለትና እንደማይደረስባቸው በማወቅ ወደ ዝርፊያ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ቡልቻ እንደሚሉት ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደካማ በመሆኑ ሊፈርስ ይገባዋል፡፡ በኮሚሽኑ ፋንታም ቁጥጥር የሚያደርጉ የመንግሥት ተቋማትንና አቃቤ ሕግን ማጠናከር እንደሚሻል ገልጸዋል፡፡

ከፓርላማ አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነር አቶ አሊ የኮሚሽኑ የመረጃ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ቢያምኑም መሥሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ በጠቋሚዎች ጥገኛ የአለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

"ከፍተኛ ባለስልጣናት ያልተከሰሱት ንጹህ ስለሆኑ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም ረፀረ ሙስና ኮሚሽንሪ የንጽህና ሰርተፍኬት አይሰጥም" ብለዋል፡፡ የኮሚሽኑ ሥራ የሚለካውም ባለስልጣናትን በመክሰስ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የባለስልጣናትን ንብረት የማስመዝገብ በተመለከተ ግን ኮሚሽኑ አንዳንድ ደንቦችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ሰነዱም በቅርቡ ለሕዝብ ውይይት እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡ የሀብትና ንብረት ምዝገባውም በቅርቡ ይጀመራል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለው ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ተቋማት ሲቋቋሙ ተደብቀው የኖሩ ተግባራት ጐልተው እንደሚወጡ የገለጹት ኮሚሽነሩ ሕዝቡ የኮሚሽኑን አቅም ስለተመለከተ እንዝረፍ ብሎ እየዘረፈ ነው በሚለው የአቶ ቡልቻ አመለካከት እንደማይስማሙ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ በትናንትና ሪፖርቱ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና ችግር እንዳለባቸው የተረጋገጡ የመሥሪያ ቤቶችን ስም ይፋ አድርጓል፡፡

በኮሚሽኑ ጥናት መሠረት የሙስና ችግር አለበት ተብሎ የተገለጸው አንዱ መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ነው፡፡

እንደኮሚሽኑ ሪፖርት ከሆነ ባለስልጣኑ ለመንገድ ሥራ ተነሽዎች ካሳ ከፍተኛ ሀብት የሚያወጣ ቢሆንም የካሳ ክፍያን አዋጅ ቁጥር 455/97ን ለማስፈጸም የሚያገለግሉ ደንብና መመሪያዎች የሌሉት መሆኑን በዚህም የንብረቶች አገማመት ሁኔታ ተጋንኖ ወይም አንሶ ሊሰጥ የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከ1997 - 1999 ባለው በጀት ዓመት ብቻ 455 ሚሊዮን 14 ሺ 547 ብር ለካሳ ክፍያ የዋለ ቢሆንም ከግምት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል አሰራር የለም፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከዚያ ጋር በተያያዘ ችግር ምክንያት በገጠርና ከተማ ወረዳዎች በተለያዩ ቦታዎች ለተመሳሳይ ንብረቶች ወጥ የሆነ አገማመት ሊታይ አልቻለም፡፡ ለግምት የሚሰበሰቡ መረጃዎች መዛባትና ተገቢ የማረጋገጥ ሥራ አለማከናወን፣ ለምሳሌ እንደ ኑግና ሰሊጥ የመሳሰሉ ምርቶች በማይመረቱባቸው አካባቢዎች ጭምር ካሳ እንዲከፍሉ ማድረግ፣ በቦታው ላይ የማይኖሩ ግለሰቦችን እንዳሉ በማድረግ ግምት እንዲከፈል የማድረግ ሥራ እንዲከናወን ክፍተት የፈጠረ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሶ እንደዚህ ዓይነቱን የሀብት ብክነት ለመከላከል የሚያስችሉ የማሻሻያ ሀሳቦች በኮሚሽኑ መቅረቡ ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የመንገድ ፈንድ ጽ/ቤት በ2000 በጀት ዓመት የገጠርና ከተማ መንገዶች ጥገና ሥራዎች የቴክኒክ ቁጥጥር አገልግሎት የሚሰጡ አማካሪ ድርጅቶችን አወዳድሮ ለመቅጠር ያወጣው ጨረታ ሂደት የመንግሥትን ስርዓት ባልጠበቀ የመንግሥትን ጥቅም ባላስጠበቀና ሁሉንም ተወዳዳሪዎች እኩል በሆነ መልኩ እንዳላስተናገደ በመጣራቱ የብር 5 ሚሊዮን 197 ሺህ 977 ብር ግዢ እንደታገደና ተገቢው ማስተካከያ ተወስዶ በድጋሚ እንዲወጣ መደረጉ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡

በኮሚሽኑ የአሰራር ችግር አለበት ተብሎ የተገለጸው ሌላው መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ነው፡፡  ድርጅቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊጣጣም በሚችል መልኩ ተሻሽሎ የጸደቀ የቀረጥ ነፃ ሽያጭ የአፈጻጸም መመሪያ አለመኖር፣ የሚጠቀምባቸው ሰነዶች ግልጽነት የሚጐድላቸው መሆኑ፣ በሽያጭ ደረሰኞች ላይ ተገቢው ቁጥጥር አለመኖርን፣ ለተፈቀደላቸው ባለመብቶች ብቻ ሽያጭ መፈጸሙን የሚቆጣጠርበትና የሚያረጋግጥበት አሰራር ስልት ደካማ መሆን የድርጅቱ ድክመቶች ተደርገው ተወስደዋል፡፡

የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኤጀንሲ እየተከተለው ያለው የግዥ ስርዓት ከመንግሥት የግዥ ስርዓት ጋር ያልተጣጣመና ህጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑንም የኮሚሽኑ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ እንደሪፖርቱ ከሆነ ኤጀንሲው የሚከተለው አሰራር በጣም ውሱን የሆኑ ድርጅቶችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግና የተለያዩ የሙስናና ብልሹ የግዥ አሰራሮች እንዲከሰቱ የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር ጥራት ያለው አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል ነው፡፡ በተደጋጋሚ በእርዳታ እህል ስርቆት የሚጠየቁ አጓጓዦች በዋነኛነት የጨረታው ተሳታፊ እና በተደጋጋሚ አሸናፊ የሚሆኑበት ሁኔታ መታየቱም ተጠቁሟል፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን የአሰራር ችግር አለበት ብሎ የገለጸው ሌላው መሥሪያ ቤት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በድርጅቱ ላይ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ለማስታወቂያ ሽያጭ የሚውለው አየር ሰዓት አመዳደብ (ቅደም ተከተል አወጣጥ)፣ ክፍያ አፈጻጸምና በድርጅቱ ውስጥ አየር ሰዓት የሚጠቀሙ ተባባሪ ድርጅቶች (አጋር ፕሮግራም አዘጋጆች) አመራረጥና የውል አፈጻጸም፣ የዱቤ ሽያጭ በአግባቡ አለመሰብሰብን የሚመለከቱና ሌሎችም የመመሪያ፣ የክትትልና ቁጥጥር ክፍተትን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉና ለአድሎአዊ አሰራርና ለብክነት የሚጋበዙ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስትራር ጽ/ቤት የትምህርት ማስረጃ አሰጣጥን በተመለከተም የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር ጽህፈት ቤት በርካታ መረጃዎችን የሚያስተዳድርና ከዚህ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ለበርካታ ተገልጋዮች የሚሰጥ ቢሆንም አሰራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የማያመላክትና ለበርካታ ክፍተቶች የተጋለጠ መሆኑን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ ኮሚሽኑ ያካሄደውን የጥናት ውጤት ክትትል ላደረገባቸው ተቋማት ቢሰጥም ተቋማቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ምላሽ እንደማይሰጡ ተገል ል፡፡

የኮሚሽኑን ሪፖርት ተከትሎ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡

"ለቀረበላቸው ጥናት ምላሽ በማይሰጡ ተቋማት ላይ ኮሚሽኑ ለምን እርምጃ አይወሰድም?" ተብለው ለተጠየቁት አቶ አሊ ሲመልሱ "ካሮቱን እንጅ ዱላውን መጠቀም ባለመፈለጋችን ነው" ብለዋል፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ምላሽ የማይሰጡበት ሁኔታ መኖሩን የገለፁት ኮሚሽነሩ መሥሪያ ቤቶች ስህተት ቢፈጽሙም ኮሚሽኑ እርምጃ ለመውሰድ እንደማይቸኩል ከዚያ ይልቅ የአማካሪ ተባባሪ ሆኖ ለመፈጸም እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡

"አንዳንድ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሠራተኞች ሙስና ይፈጽማሉ?" በሚል ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ አሊ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሠራተኞች የተገኙት ከሕብረተሰቡ በመሆኑ በሕብረተሰበ ላይ የሚታዩ ችግሮች በእነሱ ላይ ሊታዩ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ከሙስና ጋር በተያያዘም ሁለት ሠራተኞች በሙስና ቅሌት ተጋልጠው ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን አንድ ሰው ከሥራ መባረሩንና ሌላ አንድ ሰው ደግሞ የሁለት ወር ደመወዝ እንዲቀጣ በመደረጉ አኩርፎ ከሥራ መልቀቁን ገልጸዋል፡፡
 
< Prev   Next >