Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Saturday
May 10th
Home arrow Sections arrow የቴዲ አፍሮ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆነ
የቴዲ አፍሮ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ሆነ Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
Imageበሌላኛው ክስ በነፃ ተሰናበተ

በታምሩ ጽጌ

የፌዴራል ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አመልክቶ የነበረውን የዋስትና ጥያቄ የከፍተኛው ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት  በትናንትናው ዕለት ውድቅ አደረገው፡፡ በሌላ መዝገብ ከቀረበበት ክስ በዕለቱ በነፃ ተሰናብቷል፡፡

አርቲስት ቴዎድሮስ ዐቃቤ ሕግ ባሻሻለው፣ በቸልተኛነት የሰው መግደልና በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት ወንጀል ክስ ላይ ከተከራከረ በኋላ ፍርድ ቤቱ በዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ 21 ቀን 2000 ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና የተጠቀሰበት የወንጀል አንቀፅ ዋስትናን የሚከለክል በመሆኑ ማመልከቻውን እንዳልተቀበለውና ተከሳሹ ማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከላከል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ፍ/ቤቱ የጠቀሰው አንቀፅ ዋስትናን በተመለከተ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 63(1) መሰረት "ማንኛውም የተያዘ ሰው የተከሰሰበት ወንጀል የሞት ቅጣትን ወይም 15 ዓመት ወይም በላይ የሆነ ፅኑ እስራት የማያስቀጣው ከሆነ፣ ወንጀል የተፈፀመበት ሰው በደረሰበት ጉዳት የማይሞት የሆነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ ለመልቀቅ ይችላል" ይላል፡፡

በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 575 "በአደጋ ላይ ያለ ሰውን አለመርዳት፣ ማንም ሰው በራሱ ወይም በሦስተኛ ወገኖች ላይ አደጋ በማያደርስ ሁኔታ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ሊረዳው ሲችል፣ በሕይወቱ፣ በሰውነቱ ወይም በጤንነቱ ላይ ሊደርስ በሚችል፣ አደጋ ላይ የሚገኘውን ሌላ ሰው አስቦ ሳይረዳው የቀረ እንደሆነ ከ6 ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል" ይላል፡፡

 ፍርድ ቤቱ እንደጠቀሰው በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 543(3) መሰረት ሰውን የገደለ እንደሆነ፣ ጥፋተኛው ሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎችን የገደለ ወይም ወንጀሉን የፈፀመው ግልፅ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያ ተላልፎ እንደሆነ ወይም የሚያሰክሩ ወይም የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጦችን በመውሰድ ራሱን ከኃላፊነት ነፃ የሚያወጣ ሁኔታ ውስጥ ካስገባ በኋላ ቢሆንም እንኳ ቅጣቱ ከአምስት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራትና፣ ከብር አሥር ሺ እስከ 15 ሺ ብር የሚደርስ መቀጮ ይሆናል ይላል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ የቀረቡትን ክሶች አጣምሮ ማየት እንደማይቻል፣ ወደፊት እውነታው ነጥሮ እንደሚወጣ ገልፆ፣ የዋስትና ጥያቄውን እንዳልተቀበለው ተናግሯል፡፡

ተከሳሹ (ቴዲ አፍሮ) እናቱን ከውጭ አገር በስልክ እንዲያነጋግር እንዲፈቀድለት የጠየቀውን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ፣ በራሱ ወጭ እንዲያነጋግር እንዲፈቀድለት ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ "ተከሳሹ የተመሠረተበትን ክስ ቢክድም ምስክሮቻችንን አቅርበን እንድናሰማ ይፈቀድልን" ሲል ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡

የአርቲስት ቴዎድሮስ ጠበቃ በበኩላቸው "ዐቃቤ ሕግ ምስክር አሰማለሁ ብሏል፡፡ አሁን ካሉ አሁኑኑ ይሰሙልን ወይም አጭር ቀጠሮ ይሰጠን" ብለው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹን ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ባለው መሰረት የምስክሮች የምስክርነት ቃል ለመስማት ለግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን "ሰለሜ ሰለሜ" በሚለው የሙዚቃ ስራው ውስጥ የአእምሮ የፈጠራ የሥራ ውጤቴ የሆኑ አምስት የሥዕል ሥራዎቼን ከሙዚቃው ጋር በሲዲ በማሳተም በኢኮኖሚና በሞራሌ ላይ ጉዳት አድርሶብኛል በማለት አቶ አዲስ ገብሩ በከፍተኛው ፍ/ቤት እስረኛ ወንጀል ችሎት የመሰረቱትን ክስ ፍርድ ቤቱ "ሊያስከስሰው አይችልም" በሚል ውድቅ ተደርጎለታል፡፡

በትናንትናው ዕለት ሁለቱም ክሶች አርቲስቱ በተከሰሰበት 8ኛና 10ኛ ወንጀል ችሎት መታየት ሲገባቸው ወደ ፍትህ አዳራሽ (3ኛ ወንጀል ችሎት) ተዘዋውረው በአንድነት እንዲታዩ ተደርገዋል፡፡

ችሎቱ እንዳበቃ ቴዲ አፍሮ በፖሊሶች ታጅቦ በጓሮ በር ሲወጣ፣ በችሎቱ ታድሞ የነበረው አድናቂና ደጋፊ ጩኸትና ፉጨት በማሰማቱ ፖሊሶች ሁሉንም እንዲቀመጡ ካደረጉ በኋላ አግባብ እንዳልሆነ ተናግረው ቀድመው ጩኸትና ፉጨት እንዲሁም አንዳንድ ነገሮችን ተናግረዋል በሚል በደህንነቶች ጥቆማ የተደረገባቸውን ታዳሚዎች ፖሊስ ወደ ኋላ በማስቀረት ሌላው በሰልፍ እንዲወጣ አድርጓል፡፡
 
< Prev   Next >