Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ለአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ34.5...
ለአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ34.5... Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
Imageለአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ34.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል

ኢቴቪ 12 ካሜራዎችን ተከራይቷል


በጋዜጣው ሪፖርተር

ኢትዮጵያ ዛሬ በይፋ የሚጀመረውን የ16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ዝግጅቷን የተሳካ ለማድረግ በድምሩ ከ34.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጓ ተጠቆመ፡፡

ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ጋዜጣ እንዳረጋገጡት ለ16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ዝግጅት ፌዴሬሽኑ ለአጠቃላይ አቅም ግንባታ 10 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ከመንግሥት አምስት ሚለዮን ብር፣ ከስፖንሰርሺፕ ሦስት ሚሊዮን ብር ተገኝቷል፡፡

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን (IAAF) 150 ሺ ዶላር ግምት ያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ትንሿ ሜዳ ማሟሟቂያ ትራክ በዕርዳታ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ስታዲየም አትሌቶች ሲሮጡ የሚያሳይ ስክሪን ኪራይ ወጪ መሸፈኑን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮግራሙን ለመቅረፅ ከሚያስፈልገው 16 ያህል ካሜራዎች ውስጥ 12 ያህል ካሜራዎችን የኪራይ ወጪ መሸፈኑን፣ የዚህም ግምት ከ100 ሺ ዶላር በላይ መሆኑን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይኸንኑ ሻምፒዮና ውድድር ከግምት ውስጥ በማስገባት በ14 ሚሊዮን ብር ወጪ በሲኤምሲ አካባቢ ባለሰባት ፎቅ ሕንፃ መገንባቱን ምንጮቹ አስታውሰዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ጊዜ ውስጥ ያስገነባው ይኸው ሕንፃ ባለፈው ሰኞ የመረቁት በወቅቱ ለሕንፃው ግንባታ ቦታ እንዲገኝ ጥረት አድርገዋል የተባሉት አፈ ጉባዔ ተሾመ ቶጋ እና በወቅቱ ቦታውን ፈቅደዋል የተባሉት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ አርከበ ዕቁባይ ናቸው፡፡ በምረቃ ሥነሥርዓቱም ላይ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበራት ፌዴሬሽን እና የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች ተገኝተዋል፡፡

ሕንፃው ከአራተኛ ፎቅ ጀምሮ ለቢሮ አገልግሎት የሚውል ሲሆን ከዚያ በታች ለሱፐር ማርኬት፣ ለፊልም ማሳያ፣ ለቤተመፃሕፍት አገልግሎት፣ ለአትሌቶች ሳውና ባዝና የመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚሰጥበት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

ሕንፃውን የገነባው ኮንትራክተር ካቡ ኮንስትራክሽን ሲሆን የሕንፃውን ዲዛይን የሠራውና አማካሪ በመሆን 500 ሺ ብር የሚገመት ነፃ አገልግሎት የሰጠው አቶ በእግዚአብሄር አለበል መሆናቸው ከፌዴሬሽኑ የተገኘ መረጃ አመልክቷል፡፡

ከሚያዚያ 22 - 26 ቀን 2000 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ከ43 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡና 1000 የሚደርሱ ስፖርተኞች እንዲሁም 200 ያህል ጋዜጠኞች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
 
< Prev   Next >