Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የፕሬስ ነፃነት ማለት
የፕሬስ ነፃነት ማለት Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
ከየትኛውም አቅጣጫ፣ ከማንኛውም አካል፣ ከማንኛውም ወገን ተፅዕኖ ነፃ መሆን ማለት ነው

በአለም አቀፍ ደረጃ የፕሬስ ነፃነት ቀን በየዓመቱ እ.ኤ.አ ሜይ 3፣ ዘንድሮ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜ ይከበራል፡፡

በአገራችን የፕሬስ ነፃነት እንዲጎለበትና እንዲያብብ የአገራችን ፕሬስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ብሎ መገምገምና መወያየት፣ ከዚያ ተነስቶ ደካማ ጎንን አስወግዶ ጠንካራ ጎንን ማጠናከር ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡

የፕሬስ ነፃነት በአንድ አገር አለ ወይስ የለም ብሎ ለመለየት ከሁሉም በፊት መታየት ያለበት የአገሪቱ ሕግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በማያወላውል ደረጃ ግልፅ የሆነ የፕሬስ ነፃነትን የሚያስከብር ሕገ መንግሥት አላት፡፡ ምንም እንከንና ጉድለት የሌለው አንቀፅ 29 ሙሉ በሙሉ የፕሬስ ነፃነትን ያስከብራል፣ ያረጋግጣል፡፡

ጣጣ የሚፈጠረው ግን በፕሬስ ሕጉ ላይ ነው፡፡ የፕሬስ ሕጉን አሻሽላለሁ ብሎ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥረቶችን እያካሄደ ነው፡፡ ተደጋጋሚ ረቂቆችም አውጥቷል፡፡ በዚህ ወርም አዲስ ረቂቅ አውጥቶ አወያይቷል፡፡ ረቂቁ ግን አሁንም ሕገ መንግሥቱ ያሰፈረውን አንቀፅ 29 የሚያንፀባርቅና የሚያስተገብር ሳይሆን የሚያዳክምና የሚፃረር ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት ሳይቸኩልና የአንድ ወገንን አስተያየት ብቻ ተቀብሎ ወደ ማፅደቁ መሄድ የለበትም፡፡

በረቂቁ የሰፈረውን የኢንፎርሜሽን ሕግና የፕሬስ ሕግ የተደባለቀ ስለሆነ መለየት ይገባዋል፡፡ ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተለያይቶ እንደሚቀርብ የገቡትን ቃል ማክበር ያስፈልጋል፡፡

የፕሬስ ሕግ የሚመለከቱ በርካታ ሕጎች በየነጋሪት ጋዜጣው ተበትነው ስለሚገኙ አንድን ሕግ ብቻ በማየት በኢትዮጵያ የፕሬስ ሕግ ይህን ይመስላል ለማለት አስቸጋሪ በመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ውስጥ ያለው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ ያለው፣ በብሮድካስቲንግ ሕግ ውስጥ ያለው፣ በንግድ ሕግ ውስጥ ያለው ወዘተ. ተሰባስቦና ተዛምዶ አንድ ላይ እንዲጤንና ውይይት እንዲደረግበት ያስፈልጋል፡፡

አቀራረቡም፣ የአረቃቁ ሂደትም ተገቢው የሕግ አወጣጥ ደንብና ሥርዓት እንዲከተል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ይዘቱም፣ አቀራረፁም፣ አቀራረቡም፣ አረቃቀቁም፣ የውይይት አቀራረቡም ተገቢ ደረጃውን ያልጠበቀ ስለሆነ መንግሥት እንዳያፀድቀውና በጥሞና አይቶ እንደገና የሚረቅበትን መንገድ ለማፈላለግ ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡

ጠንካራ ሕገ መንግሥት አውጥቶ፣ ይህን የመሰለ አሳሪ የፕሬስ ሕግ ማውጣት የራስን ልጅ እንደ መግደል፣ የራስን እምነት እንደ ማሰናከል፣ የራስን ፅዳት በራስ እንደማቆሸሽ የሚቆጠር ነው፡፡ ለሕዝብም፣ ለአገርም፣ ለፕሬስም፣ ለኢሕአዴግም አይጠቅምም፡፡

ይህ በመንግሥት በኩል ያለ ችግር ሲሆን የፕሬስ ነፃነትን የሚፈታተኑ ችግሮች የሚመጡት ግን ከመንግሥት ብቻ ነው ማለት የዋህነት ነው፡፡ ከማንኛውም አቅጣጫ፣ ከማንኛውም አካልና ከማንኛውም ወገን የፕሬስ ነፃነትን የሚጎዳና የሚጨፈልቅ ተፅዕኖ ሊመጣ ይችላል፡፡

በአገራችንም በተጨባጭ ይህ ታይቷል፡፡ እየታየም ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ እንዳይጠናከር እንቅፋት ሆነዋል፡፡ የእኛን አመለካከት ካልደገፋችሁ፣ ካላስተጋባችሁ ከተቃወማችሁ ወዮላችሁ ባይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡

ይህ ዛቻና ፉከራ፣ በራሱ በፕሬስ ነፃነት ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በሰበካና በድለላ ፕሬሶች የተቃዋሚ ፖርቲዎች መሣሪያ እንዲሆኑ ያደረጉ በርካታ ተቃዋሚዎችም አሉ፡፡ እንደተራ ተላላኪ እገሌን ስደብልን፣ እከሌን አዋርድልን ሲባሉና ጉርሻ ሲሰጣቸው ሌላውን መንከስና መዝለፍ ሥራችን ብለው የተያያዙት ፕሬሶች፣ ጥቂቶች እንዳልሆኑ በተግባር አይተናል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋቁመዋቸው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መመሪያ ሰጥተዋቸው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲጣሉ አብረው የተጣሉ፣ ሲከፋፈሉ አብረው የተከፋፈሉ ፕሬሶች እንዳሉም አይዘነጋም፡፡ የፕሬስ ነፃነት ስንል ከእንደዚህ ዓይነት ጫናና ሎሌነት ነፃ መሆን ማለትም ነው፡፡

በፕሬስ ነፃነት ላይ ጫናና አደጋ የሚያደርሱ ግን መንግሥት፣ ገዢ ፓርቲ ወይም ተቃዋሚ ፓርቲና ግለሰቦች ብቻ አይደሉም፡፡ ከፖለቲካ ውጭ የሆኑ ታዋቂና ባለሃብት ነን የሚሉ አንዳንድ ግለሰቦችም በፕሬስ ነፃነት ላይ ጫና ያደርጋሉ፡፡

አሸባሪዎችም የራሳቸው ጫና ያደርጋሉ፡፡ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎችም ለምን ታጋልጣላችሁ እያሉ በፕሬስ ላይ ይዘምታሉ፡፡ ግድያ ይፈፅማሉ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በላቲን አሜሪካ በእነዚህ ዓይነት ወገኖች በፕሬስ ነፃነት ላይ የደረሰው አደጋ ይህ ነው አይባልም፡፡ በእነዚህ ቡድኖች የደረሰው አደጋ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ከደረሰው አደጋ በላይ ነው፡፡

ሽብርና አደንዛዥ ዕፅ ውስጥ ባይኖሩበትም፣ ባለሃብት በመሆናቸው ብቻ ተወቀስን ብለው "ቡራ ከረዩ" የሚሉም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ባለሃብቶቹ ምንም ሳይናገሩና ሳያስፈራሩ ቅርበት አለን የሚሉና "እንድንቆጣ ውክልና ተሰጥቶናል" የሚሉ ሰዎች ለምን እንዲህ ይባላል እያሉ መብት ሲጥሱና የአካኪ ዘራፍ ማስፈራሪያቸውን ሲያዥጎደጉዱት እናያለን፡፡ በእኛ በራሳችንም ሰሞኑን በብዛት እየደረሰብን ነው፡፡

ይህም ቢሆን ከመንግሥትና ከተቃዋሚ አልመጣም ግን ከግለሰቦች የመጣ ነው፡፡ ቁምነገሩ እኛ የማንወደውን ነገር አትፃፉ፣ አትናገሩ፣ አታጋልጡ ነው፡፡ ይኼ ፀረፕሬስ ነፃነት ነው፡፡

ስለፕሬስ ነፃነት ስናስብ ከየትኛውም አቅጣጫ ይምጣ፣ በማንኛውም አካል ይፈፀም፣ በማንኛውም ወገን ይፈፀም፤ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትና ፀረ ሕገ መንግሥት ከሆነ፣ ፀረ የፕሬስ ነፃነት ነው፡፡ ያንዱ ሎሌ ሆኖ ሌላውን መቃወም፣ ለፕሬስ ነፃነት መቆምን አያሳይም፡፡ ለፕሬስ ነፃነት የቆመ ወገን ሁሉ ማንኛውንም ጫና ይታገል፡፡  
 
< Prev   Next >