| ለኢንቨስትመንት የቀረቡት ፕሮጀክቶች... |
|
| Thursday, 10 January 2008 | |
|
ለኢንቨስትመንት የቀረቡት ፕሮጀክቶች ሥራ ሲጀምሩ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሥራ ያገኛሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ እስከ ህዳር 2000 ዓ.ም ድረስ በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ፈቃድ ያገኙ ባለሀብቶች ካፒታል 331 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገለፀ፡፡ ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ እድል ያገኛሉ፡፡ ፈቃድ ከተሰጣቸው ውስጥ ወደ ተግባር ከገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል አግኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ አቢ ወልደመስቀል ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከሐምሌ 1984 ዓ.ም እስከ ህዳር 2000 ዓ.ም ድረስ ለ28..230 የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱንና 331 ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል መገኘቱን አሳውቀዋል፡፡ ፈቃድ ከተሰጣቸው ውስጥ አስራ አራት በመቶው የውጭ ባለሀብቶች ሲሆኑ ሰማንያ ስድስት በመቶው ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ዳይሬክተሩ ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ ወደ ግንባታ እንዲሁም ማምረትና አገልግሎት የመስጠት እንቅስቃሴ የጀመሩ ባለሀብቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቶ አቢ ወልደመስቀል ፈቃድ ወስደው በተግባር ላይ በሚገኙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ300..000 በላይ ለሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠራቸውንና ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሀብቶች በሙሉ ወደተግባር ሲሸጋገሩ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ኤጀንሲው በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከማበረታታት አኳያ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ያስረዱት አቶ አቢ በዚህም መሠረት ከአምስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ኩባንያ ለመመስረት በአማካይ 258 ቀናት ይፈጅ እንደነበር አሁን ግን ወደ አራት ሰዓት ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአምስት ዓመት በፊት ለውጭ ተቀጣሪዎች በአማካይ ሀምሳ ስምንት ቀናት ይፈጅ እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት በአንድ ሰዓት ፈቃድ እየተሰጠ መሆኑን፤ ከሁለት ወር በላይ በአማካይ ይፈጅ የነበረው የኢንቨስትመንት ፈቃድም ከአራት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ አሳውቀዋል፡፡ መንግሥት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ከማበረታታት አኳያ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አቶ አቢ ወልደመስቀል ገልፀው፤ በመሬት አሰጣጥ፣ በኤሌክትሪክ፣ በውሃና በቴሌኮሙኒኬሽን አቅርቦት ዙሪያ ከፍተኛ መሻሻል እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ አቶ አቢ ወልደመስቀል የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት አኳያ በተግባር ላይ ያሉት የውጭና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑንና ከውጭ የሚመጣውን ምርት በመተካት የሀገሪቷን ኢኮኖሚ እያሳደጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተሾመ ንቁ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |