Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow ጉዲፈቻ
ጉዲፈቻ Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008

Image
ዳንኤል ደሬሳ
በምሕረት ሞገስ

ጉዲፈቻ መቼና እንዴት ተጀመረ ለሚለው ግልጽ ማስረጃ ባይኖርም በኢትዮጵያ፣ በግሪክ፣ በሮም፣ በሩሲያ፣ በጃፓንና በመሳሰሉት አገሮች ጉዲፈቻ ሲሰራበት የነበረ ባህል እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የጉዲፈቻ አጀማመር ከቤተሰብ መፍለስ፣ ከግል ይዞታ እንዲሁም ሃይማኖትና ማኅበራዊ ተቋማት ከመመስረታቸው ጋር የመጣ ሲሆን በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል፡፡

ጉዲፈቻ በአለም ላይ ያስፈለገው የአንድን ጎሳ ትውልድ ለማሻገር፣ ወራሽ፣ ጧሪና ደጋፊ እንዲሁም በአምልኮት ውስጥ የሞተን ሰው መንፈስ ተክቶ የሚሰራ ሰው ለማግኘት ነው፡፡

የፈጠራ ዝምድና (ጉዲፈቻ) በሰው ልጅ ታሪክና በስልጣኔ ውስጥ አንድ ርምጃ ወደፊት ቀድሞ የነበረ የዝምድና መመስረቻ ዘዴ ነው፡፡ ጉዲፈቻ መብት ለሌላቸው መብት የሚያጎናጽፍ ማንነታቸውን ለማያውቁ ማንነት የሚሰጥ ባህል ነው፡፡ እንዲሁም ጉዲፈቻ የወንድ የዘር ሐረግ እንዲቀጥል ለማድረግ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ 

አቶ ዳንኤል ደሬሳ በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ኤክስፖርትና ባህል ነክ ጉዳዮች አጥኚ እንደገለፁልን በኦሮሞ የጉዲፈቻን ስርዓት የተለየ የሚያደርገው በተለይ በቦረና እና በአርሲ ኦሮሞ ያልሆነን ብሄረሰብ ሁሉ በጉዲፈቻ ዘመድ የሚያደርጉበት ባህል ስላለ ነው፡፡ ሌሎች ህዝቦችን በጉዲፈቻ ወደ ራስ ማቀላቀል ትልቅ ሥፍራ አለው፡፡

 ሌሎችን ወደ ራስ ማቀላቀል በጥንታዊው ዘዴ ኦሮሞዎች ያልሆኑትን ወደ ኦሮሞ ለመቀላቀልም ተችሏል፡፡ የጉጂ ኦሮሞዎች የጦር ምርኮኞችን በጉዲፈቻ ወደ ራሳቸው ሲቀላቅሉ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በኦሮሞ ባህል ጉዲፈቻ በሶስት አይነት ይመደባል፡፡ ኢልማ ጉዲፈቻ ማለትም በጣም ከቅርብ ዘመድ ወንድ ልጅን በማደጎነት መቀበል፣ ገላ ጉዲፈቻ ማለትም ለእረኝነት፣ ለሥራ ተብሎ ከሴትም ከወንድም ኦሮሞ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል በጉዲፈቻነት መቀበል እንዲሁም ኮርፖራል አዶፕሽን ኦሮሞ ያልሆነን ብሔረሰብ በጉዲፈቻ መቀበልና መቀላቀል ነው፡፡

ኢልማ ጉዲፈቻ (የቅርብ ከሆነ ዘመድ ወንድ ልጅን በጉዲፈቻ መቀበል) በአብዛኛው ወንድ ልጅ የሌለው ሰው የሚጠቀምበት ነው፡፡ "አነሳሱም ሴት ልጅ አግብታ ስትሄድ የባሏ ናት፡፡ ወንድ ልጅ የቤተሰቡን የዘር ሐረግ የሚያስተላልፍ ነው ተብሎ በመታሰቡ ነው፡፡"

አቶ ዳንኤል እንደሚሉት በኢልማ ጉዲፈቻ የጾታ ጉዳይ የሚነሳ ቢሆንም ሴት ልጅን በጉዲፈቻ የማሳደግ ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም ከወንድ ጋር ልዩነት አለው፡፡ በጣም ቅርብ ከሆነ የሥጋ ዘመድ ሴት ልጅን በጉዲፈቻ የሚወስዱ ከሆነ የአቀባበል ባህላዊ ስነስርዓቱ ከወንድ ጋር እኩል ነው፡፡ ሆኖም እንደ ወንድ ልጅ በውርስ ብዙ የምታገኘው ሃብት አይኖርም፡፡ የአባት እቃዎችን ሁሉ ለመውረስ አትችልም፡፡ በመሆኑም በኢልማ ጉዲፈቻ በአብዛኛው የሚወሰዱት ወንዶች ናቸው፡፡ 

"ወንድ ልጅ የሌለው ከቤተሰቡ እሳት ማለትም የዘር ሃረጉ እንደጠፋ፣ ወንድ ልጅ የሌለው ሰው ሲሞት ለሙቱ መንፈስ (ኤክራ) እንደየ ባህሉ ሁኔታ የሚዘከረውን ዝክር የሚያቀርብ ሰው ስለሌለ የሙት መንፈሱ ደረቅ ድንጋይ ትልሳለችና ወንድ ልጅ የግድ መኖር አለበት" የሚል አመለካት በመኖሩ ወንድ ልጅ የሌላቸው ወንዶችን በጉዲፈቻ መውሰድ በእጅጉ የሚፈለግ ነው፡፡

ኢልሜ ገሉ በአብዛኛው ችግር ያለባቸውን ሰዎች ልጅ ወስዶ ማሳደጉ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ለከብት እረኝነትና ለስራ እንዲያግዙ ታስቦ የሚወሰዱ ልጆች ናቸው፡፡ ኢልማ ጉዲፈቻም ሆነ ኢልማ ገሉ በቤተሰብ፣ በአካባቢ ሰዎችና በግለሰብ ደረጃ የሚከናወኑ የጉዲፈቻ አይነቶች ናቸው፡፡

ኮርፖራል አዶፕሽን በጎሳ የሚደረግና በገዳ ሥርዓት የሚከናወን ነው፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ ኦሮሞ ያልሆነን ብሔር ወደ ኦሮሞ የመቀላቀል ስርዓት ነውና፡፡

የጉዲፈቻ አቀባበልና አጠያየቅ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢ አንድ አይነት አይደለም፡፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሆድ ውስጥ ተፀንሶ ያለውን ልጅ "ወንድ ልጅ ከሆነ ጉዲፈቻ ትሰጠኛለህ" ብሎ የመጠየቅ ሁኔታ አለ፡፡ ይህ አይነቱ አጠያየቅ በቦረና አካባቢ የተለመደ ነው፡፡

አንድ ልጅ ከተወለደ በኋላ ስም ሳይወጣለት በፊት የመጠየቅ አካሄድም አለ፡፡ ይህን ለማድረግ ልጅ የሌላቸው ባልና ሚስት፣ የጎሳው ሽማግሌዎች እና በጣም ቅርብ የሆኑ የስጋ ዘመዶች በአንድ ላይ በመሆን ነው የሚጠይቁት፡፡ ለጥያቄው ከመሄዳቸው በፊትም የፀነሰችው ሴት የኋላ ታሪክና የምትወልድ መሆኗ ተጠንቶ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉት በጉዲፈቻ የተቀበሉት ልጅ እንዲወልድላቸው፣ እንዲከብድላቸውና እንዲበረክትላቸው ከማሰብና ከመጓጓት ነው፡፡

በጉጂ ኦሮሞ ውስጥ የጉዲፈቻ ሰጪውም ሆነ ተቀባዩ መጀመሪያ መደራደርና መግባባት አለባቸው፡፡ እናቲቱ "ወላድ ናት" የሚለውን ካጠኑና ከተግባቡ በኋላ ሕፃኑ ገና ሳይወለድ ጨርቅ (ኤርቤ"፣ እትብት የሚቆረጥበት (ቀረባ"፣ የሚተኛበት ቆዳ (ኢቲሊ"፣ ውሃ የሚቀዳበት ቅል (መሳቁል) ለፀነሰችው ሴት ይወስዳሉ፡፡ ልጁ ሲወለድ ቀድሞ ከሰጡት እጅ መንሻ በተጨማሪ የወተት ከብትና፣ የእርድ በሬ በባህላዊ የአሰጣጥ ስነስርዓት ያስረክባሉ፡፡ ልጁ ሲወለድም ወላጅ እናት ወልዳ እንደምትታረስ ሁሉ በጉዲፈቻ ከሚቀበሉት ባልና ሚስት ሚስቲቱ ልክ እንደወለደች ኡልማ ትገባለች (ትተኛለች፣ ትታረሳለች"፡፡

በሜጫና ቱለማ ኦሮሞ ውስጥ በጽንስ ደረጃም ሆነ ከተወለደ በኋላ ጉዲፈቻ ይጠየቃል፡፡ መካን ቤተሰቦች፣ ከጎሳ ታላላቅ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ጉዲፈቻ ወደ ሚጠይቁበት ቤት ይሄዳሉ፡፡ በሚሄዱበት ጊዜ በራስ ላይ የሚደረግ (ከሌቻ"፣ ጫጩ (ከጨሌ የሚሰራ ጌጥ"፣ ሲቄ (የሴት ዘንግ"፣ ጨርቆሳ (እርጥብ ሳር) እንዲሁም ቡና ይይዛሉ፡፡ ጉዲፈቻ በሚጠይቁበት ቤት ሲደርሱም በሆዳቸው መሬት ላይ ተኝተው የህፃኑን ወላጆች "ወራሽ ልጅ ስጡን" ብለው ይለምናሉ፡፡ መካኖቹ መጀመሪያ "ወራሽ ስጡን" ብለው ሲወድቁ እነሱን አጅበው የመጡት የጎሳ ሽማግሌዎች "ወራሽ ስጧቸው" ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ወላጆች ከተስማሙ "ተነሱ እንሰጣችኋለን" ይላሉ፡፡

ከሌቻ በኦሮም ባህል የአምላክ ኃይል ያለበት ነው ተብሎ ስለሚታመን ሰዎች ይፈራሉ፡፡ ይህን ይዘው የሚሄዱት የወላጆቹን (ሰጪዎቹን) ልቦና ለመስበር ነው፡፡ ከሌቻ ይዘው መሄዳቸውም "የምናሳድገው ልጅ የቤታችን መሪ (አባወራ) ይሆናል" የሚለውን ለማሳየት ነው፡፡ ከሌቻውን የሚይዘውም ወንድየው ነው፡፡

ጫጩ (በጨሌ የሚሰራ ጌጥ) ይዛ የምትሄደው ሴት ስትሆን አሳዳጊዋ ሴት ስለሆነች ጫጩ የሴቷን የወላጅነት ስሜት ማረጋገጫ ነው፡፡ በጫጩ ላይ የሚያማምሩ ጌጦች የሚደረጉ ሲሆን ይህም የመዋለድን ሂደት ለማሳየት ነው፡፡

ጨርቆሳ (እርጥብ ሳር) ይዘው የሚሄዱት የሰላምና የወላድነት ምልክት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ቡና የሚገልፀው "ብዙ" መሆንን ነው፡፡ መዋለድንና መብዛትን ለማመላከት፡፡

ሲቄ (ሴት ልጅ ትዳር ይዛ ስትወጣ እናቷ የምታወርሳት ዘንግ) ስትሆን ይህን ይዘው የሚሄዱትም ሲቄ የያዘች ሴት ክብር ያላትና ቃሏም የተከበረ ስለሆነ ነው፡፡

ይህን ሁሉ ይዘውም ሰውየው "ልጄን አልሰጥም" ካለ በርጩማ (መቀመጫ) ገልብጠው ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ "በርጩማ ጎንብሱ" የሚባል ሲሆን መልዕክቱም "ዘርህ ይቁም" ነው፡፡ ከሌቻውንም ወደ መሬት ይዘቀዝቁታል፡፡ በመሆኑም ወላጆች ወደዱም ጠሉም ማኅበራዊ እሴት ነውና ጥያቄውን ይቀበሉታል፡፡

በዚህ ሁኔታ ልጁን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ስም የሚያወጡትም ጉዲፈቻ የወሰዱ ናቸው፡፡ ያደገና ስም የወጣለት ልጅ ከሆነ ደግሞ ስሙ ይለወጣል ሆኖም ሳይወለድ ወይም ተወልዶ ስም ካልወጣለት ሕፃን እኩል ባህላዊ አከባበሩ አይከናወንለትም፡፡ ቢከናወነለትም ቀለል ያለና የተለየ ነው፡፡

ለጉዲፈቻ የተጠየቁት እናትና አባት መኝታ ክፍል (ዲንቃ) በር ላይ ይቀመጣሉ፡፡ የወላጅ አባት ልጁን ወስዶ ታፋው ላይ ያስቀምጣል፡፡ ከዛም አንስቶ ከአብራኬ የወጣውን አንቺ ወለድሽው ብሎ ለሚስቱ ይሰጣታል፡፡ የዚህ ትርጉም ከአብራካችን የወጣውን ልጅ ለእናንተ ሰጥተናል ነው፡፡

ልጁ ሕፃን በመሆኑና የእናቱን ጡት መጥባት ስላለበት ስነስርዓቱ ከተከናወነ በኋላ ወላጅ እናቱ እንድታጠባው ትተው ይሄዳሉ፡፡ የወተት ከብትም ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ጨክነው ሕፃናኑን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ደረቅ ጡታቸውን እያጠቡና የከብት ወተት እየሰጡ ያሳድጋሉ፡፡ "ደረቅ ጡት ጠብቶ አደገ" የሚባለውም በዚህ መልክ በጉዲፈቻ ለተወሰደ ሰው ነው፡፡

የተወሰደው ሕፃን ሶስት ዓመት ሲሞላው ስም የመስጠት ስነስርዓት፣ (ሞጋሳ) ይከናወንለታል፡፡ የሞጋሳውን ባህላዊ ስነስርዓት የሚያከናውኑትም ህፃኑን የወሰዱትና እናትና አባት የሆኑት ቤተሰቦች ናቸው፡፡ ለሕፃኑ ስም ሲሰጠው ከአባቱ ጋር ሰባት ሆነው የአባቱ (በጉዲፈቻ የወሰደው) የቅርብ የስጋ ዘመዶች ሳይተኙ ያድራሉ፣ ድግስ ይዘጋጃል፣ የሥጋ ዘመድና ጎሳዎች ይመጣሉ፡፡ ልጁንም አባቱ እንደተቀበለው ሁሉ ጎሳው ይቀበለዋል፡፡ የጎሳው አባልም ይሆናል፡፡ ይዘፈናል፤ ስነስርዓቱም ይከናወናል፡፡

የሞጋሳ ስነስርዓቱ ሲከናወን ባህላዊ እቃዎችን ይዘውም ይሄዳሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ሲቄ (የሴት ዘንግ"፣ ሀቦቦ (የወንድ ዘንግ"፣ ሊጬ (አለንጋ"ና የመሣሠሉት ይገኙበታል፡፡ አለንጋ ይዘው የሚሄዱት አለንጋው የህግ ስነስርዓትን ማስከበሪያ ተምሳሌት ስለሆነ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት በልጁ ላይ አንድ ጉዳት ቢደርስ አሳዳጊው እንደሚቀጣ ለማሳየትም ነው፡፡ አሳዳጊ ቃል ይገባል፡፡ የልጁም ህጋዊነት ይረጋገጣል፡፡ ጎሳው ልጁ በስነስርዓት ማደጉን ይከታተላል፡፡ ልጁ ላይ ጉዳት ከታየ የጎሳው መሪዎች ጣልቃ ይገባሉ፡፡ የከፋ ችግር ካለ እንኳን በተቻለ መጠን እንዳይለያዩ ያደርጋሉ፡፡ ችግሩ ገፍቶ መለያየት ካለባቸው ልጁ መውረስ የሚገባውን ሁሉ አግኝቶ ይሄዳል፡፡

በገላ ጉዲፈቻ ግን ልጆች አይወርሱም፡፡ ምክንያቱም በገላ ጉዲፈቻ የመጣ ልጅ ሲፈልግም ወደ ወገኖቹ ስለሚሄድ ነው፡፡ መሃን ያልሆኑ ወላጆች ልጅ እያላቸው በጉዲፈቻ ሌላ ተጨማሪ ልጅ ቢያመጡም እንደ በኩር ልጅ ነው የሚታየው፡፡ ውርስም ያገኛል፡፡

በኮርፖራል አዶፕሽን ውስጥ በጉዲፈቻ የሚገቡ ሰዎች በቡድን፣ በጎሳ ወይም በግለሰብ ደረጃ ሊሆን ይችላል፡፡

ባህላዊ የአቀባበል ስነስርዓቱ የሚከናወነው እርድን ጨምሮ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው "ደምህ ከደማችን ተቀላቅሏል፡፡ ጎሳችን ነህ" ለማለት ነው፡፡ 

 

 
< Prev   Next >