| የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጣምራዊነት |
|
|
| Wednesday, 30 April 2008 | |
|
በሰለሞን ጎሹ
"ዜጎች በፖለቲካ ውስጥ እንዲሳተፉ አይገደዱም፣ ባለመሳተፋቸውም ተቃውሟቸውን የመግለጽ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ሆኖም ከዜጎች የተሟላ ተሳትፎ ካልተሰጠው ዴሞክራሲ መዳከም ይጀምራል" ይላል "ዴሞክራሲ ምን ማለት ነው?" የሚለው በአሜሪካ የማስታወቂያ አገልግሎት ተዘጋጅቶ በአቶ ሽፈራው ተፈሪ የተተረጎመው መፅሐፍ፡፡ በቅርቡ ቅዝቅዝ ብሎ የተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ዜጎች በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎአቸው በአስፈሪ ሁኔታ መቀነሱን የሃገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደትም መዳከሙን በግልፅ ያሳያል፡፡ በ1997 ዓ.ም ተደርጎ በነበረው ሶስተኛው ብሄራዊ ምርጫ ቅንጅት 109፣ ሕብረት 52 እንዲሁም ኦፌዴን 11 የፓርላማ መቀመጫዎችን በማሸነፍ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን ወደ አንድ ደረጃ ወስደውት ነበር፡፡ ዜጎች በሃላፊነት ስሜት የሚሳተፉበት ከባቢ አየር አሁን በአንፃራዊነት ቀንሷል፡፡ የሚገርመው በዚህ ጊዜ በተመሳሳይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ይበልጥ ግራ የተጋባበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የሃብት ክፍፍል ልዩነት መስፋት፣ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ አልቀመስ ማለት፣ በኢኮኖሚው እድገት ላይ ብሄራዊ ስምምነት መጥፋቱ፣ የገንዘባችን የመግዛት አቅም መዳከሙ". ወዘተ ዜጎችን ከማማረር አልፎ በአግራሞት ዝም እያሰኘ ነው፡፡ መንግሥት በፖሊሲና በስትራቴጂው አማካኝነት የኢኮኖሚውን አቅጣጫ የመቅረፅና የማስተባበር ሃላፊነትና ግዴታን በዋነኛነት ይሸከም እንጂ ኢኮኖሚው ችግር ቢከሰትበት ብቸኛ ተጠያቂ አይሆንም፡፡ የሌሎች ባለድርሻዎች ተሳትፎም የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ እነሱን በሃላፊነት ለማሳወቅ ግን በቅድሚያ ሙሉ ተሳትፎአቸውን ማረጋገጥ ግድ ይላል፡፡ "ዴሞክራሲ በሰፈነበት አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ያለምንም ፍርሃት በፈለጉት የግል ድርጅት፣ ማህበርና የፈቃደኞች ቡድን ውስጥ አባል የመሆን ዕድልና አማራጭ አላቸው፡፡ አብዛኛዎቹ እነዚህ ድርጅቶች በመንግሥት ፖሊሲ ነክ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ይሁኑ እንጂ በመንግሥት ቁጥጥር ሥራ የሚንቀሳቀሱት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ግለሰቦች በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ እንደፈለጉ የመደራጀትና የመሳተፍ ነፃነት ሲኖራቸው ለዴሞክራሲ መሰረት ይሆናል፡፡ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በአንድ ድርጅት ውስጥ ተሰሚነታቸው ይጨምራል" ይላል ከላይ የተገለፀው መፅሀፍ፡፡ ዜጎች የፈለጉትን ድርጅት፣ ማህበርና ቡድን የመቀላቀል ሙሉ ነፃነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖሩ ጥርጣሬ ያላቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ በእኛ ተጨባጭ ሁኔታም አባል የሆኑት ሰዎች ተመሳሳይ ፍላጎት ሲያንፀባርቁ አይታዩም፡፡ ሀገራችን ከመንግሥት ቅርብ ክትትል ሥር የወደቀ ነፃ ገበያን ታራምዳለች፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት ብቻ ኢኮኖሚውን ይምሩት ብንል ብልጣ ብልጦች በብዙሃኑ ሕዝብ መከራ ስቃይና ድህነት ላይ እንዲደልቡ ማመቻቸት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ቁጥጥር ማድረጋቸው የሕዝብ ጥቅምን ለመጠበቅ እስከሆነ ድረስ በራሱ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ገዢው ፓርቲን ከመንግሥት ለመለየት በተቸገርንበት ወቅት ላይ ንግዱና ኢኮኖሚው የሚንቀሳቀሰው በፖለቲካው አየር ከሆነ ወደማንወጣው አዘቅት ማምራታችን አይቀርም፡፡ አንድ ቡድን ብቻውን ሀገር የሚመራበት ሁኔታ ያረጀ ያፈጀ ተረት ሆኗል፡፡ የመንግሥት ብቃት ዛሬ የሚለካው የተለያየ ፍላጎትና ስሜት እንዲሁም አመለካከት ያላቸውን የተለያዩ ቡድኖች በማስተባበርና በማቀናጀት እንዲሰሩ በማስቻልና ባለማስቻል ነው፡፡ መንግሥት የቡድኖቹ እንቅስቃሴ ላይ ሊያስርፍ የሚችለውን ተፅዕኖ ያህል ቡድኖቹም በመንግሥት ላይ ግፊት ሊያደርጉ የሚችሉበት ሰፊ እድል አለ፡፡ የአቶ ሽፈራው ተፈሪ ትርጉም "በዴሞክራሲያዊ ሕብረተሰብ ውስጥ የሚገኙት ብዙ ቁጥር ያላቸው ቡድኖች በተለያየ ዓላማ ተደራጅተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የተወሰኑ ጉዳዮችን ለማስፈፀም በመንግሥት ላይ ግፊት በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ሃሳብ አስፈፃሚ ወይም ተደራዳሪ ቡድኖች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ለምሳሌ የንግድ ምክር ቤቶች፣ የባለሙያ ማህበራት ወይም የሰራተኛ ማህበራት በሚያራምዱት የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ የኢኮኖሚውንም ጥያቄ አብሮ የሚያካትት ቢሆንም ከሙያቸውም ውጭ ወጣ እያሉ የሕብረትሰቡን ፍላጎት የሚያንፀባርቁ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ" ይላል፡፡ በእኛ ሀገር ልምድ የንግድ ምክር ቤቱ፣ የባለሙያ ማህበራት እና የሰራተኛ ማህበራት የፖለቲካ አመለካከት ለማራመድና መንግሥት ላይ ተፅዕኖና ግፊት ለማድረግ በሞከሩበት ሁኔታ "የሕገ ወጥ ኃይሎች መሳሪያ" ተብለው በአዲስ መልክ እንዲደራጁ ተገደዋል፡፡ አስተያዬት ሰጪዎች አሁን ያሉት ቡድኖች አብዛኛዎቹ አመራሮች ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው እንደሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚቀርፅላት አካል እንዲጠፉ አድርጓል፡፡ መንግሥት ከየትኛውም አቅጣጫ የሚወረወርበትን ተቃውሞና ትችት በበጎ ጎኑ ወስዶ ከራሱ ጋር አነፃፅሮ የሚጠቅመውን ወስዶ ያላመነበትን መተው እንዲያም ካለ የእሱ መንገዶች ለምን የተሻሉ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ማስረዳትና ማሳመን ይጠበቅበታል፡፡ የአሁኑ አያያዝ ግን ሁሉንም አካል በእኔ ቡራኬ መንገድን ቀጥል ካልተመቸህ ግን ጥፋ ይመስላል፡፡ ማህበሮቹ፣ ቡድኖቹና ድርጅቶቹ አንድ የተለየ ግብና አላማ ያላቸው ሲሆን የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን ለማስከበር የፖለቲካ አካሄድ ላይ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የህብረተሰብ ደህንነትና ፍላጎት ለዘላቂ ጥቅማቸው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ "እነዚህ ቡድኖች የሚያራምዱት አስተሳሰብ ለሕዝብ የጋራ ግልጋሎት በሚሰጡት ዘርፎች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በነዚህ ቡድኖች መካከል የግል ፍላጎቶች በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ናቸው" ይላል የአቶ ሽፈራው ተፈሪ ትርጉም፡፡ በቅርቡ የእንግሊዙ ሞርጋን ባንክ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌርን አማካሪው አድርጎ ሲቀጥር ብሌር ስለሚኖራቸው ሚና ሲናገሩ "በአሁኑ ጊዜ ፖለቲካንና ኢኮኖሚን ለያይቶ ማስኬድ አይቻልም" ነበር ያሉት፡፡ ፖለቲከኞች በደካማ ኢኮኖሚ መኖርን አይመኙም፡፡ የአሜሪካን ሪፐብሊክ እጩ ተወዳዳሪ ጆን ማኬይን ከወራት በፊት "ኢኮኖሚክስ አይገባኝም" ማለታቸው ለሚዲያው ሲሳይ ከሆነ በኋላ በአንፃራዊነት በጉዳዩ ላይ ጥሩ ግንዛቤ ያላቸው ባራክ አባማና ሂላሪ ክሊንተን የተሻለ የማሸነፍ እድል አላቸው የተባለውን ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ "ቡድኖች ግዙፍና የማይደረስበት የሆነውን መንግሥትንና ራሱን አግልሎ የሚኖረውን ግለሰብ በማቀራረብ እንደ አንድ አስታራቂ ኃይል በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በእነርሱም እንቅስቃሴ ማለትም ክርክር፣ ግጭት፣ መቻቻልና ስምምነት አማካኝነት ነው ሕብረተሰቡ የአባላቱን ደህንነትና እድገት ማስከበር የሚችለው" የሚለው የአቶ ሽፈራው ተፈሪ ትርጉም መፅሀፍ ነው፡፡ የመብቶች መከበር፣ የሕግ የበላይነት፣ ምርጫ፣ የዴሞክራሲ ባህልና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ያሉት አንድ ሀገር ተራ ዜጎች በመሪዎቻቸው ላይ በአንፃራዊነት ትልቅ ደረጃ የሚሰጠው ቁጥጥር እንዲያደርጉ ይፈቅዳል፡፡ ዜጎች ሁሌም ንቃተ ህሊናቸው የዳበረ መብትና ግዴታዎቻቸውን ተረድተው የሚፈፅሙና የሚጠይቁ ብሎም የሚያስፋፉ ይሆናሉ፡፡ ይህ ተግባራዊ ከሆነ ደግሞ ዴሞክራሲ ህዝቦች ሊያገኙት የሚጓጉለትና የሚጥሩለት ነገር ይሆናል፡፡ ዴሞክራሲ ራሱን በአዲስ መልክ መቅረጽ አልያም አካሄዱ ላይ ማሻሻያ ማድረግ መለያዎቹ ናቸው፡፡ ፖለቲካው ጤነኛ በሆነባቸው አገራት ኢኮኖሚው ለማደግ ጊዜ ሲፈጅበት አልታየም፡፡ በአህጉራችን አፍሪካ ጥሩ ምሳሌ የምትሆነው ሀገር ቦትስዋና ስትሆን የፖለቲካ ተቋሞችን በመገንባትና በማሳደግ አስደናቂ ለውጥ አምጥታለች፡፡ ነፃ የዴሞክራሲያዊ ከባቢያዊ አየር በመፍጠር፣ የምርጫ ማጭበርበርን በማስቀረት፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ በማካሄድ፣ ነፃ የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም፣ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በማሳደግና ለሕግ የበላይነት መተርጎም ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድረጓ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በአስገራሚ ፍጥነት እያደገ ነው፡፡ ቦትስዋና እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ደካማ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ደካማ ሲቪክ ማህበረሰቦች፣ ሀላፊነት የማይሰማው ነፃ ፕሬስ፣ እንዲሁም የአናሳዎች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ያጋጥማት ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቿ ልክ እንደ እኛዎቹ በቀላሉ ይሰነጣጠቁ ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ችግር የነበረባቸው ሲሆን የምርጫ ኮሚሽኑ ለመንግሥት የወገነ ተብሎም ይተች ነበር፡፡ ቦትስዋና ይህን ሁሉ ችግሯን የፈታችው በቅድሚያ በችግሮቹ መኖር በማመን "እንዴት ችግሮቹን እንፍታ?" ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ድርጅቶቹን፣ ቡድኖችን፣ ማህበሮችንና በአጠቃላይ ዜጎችን ስላሳተፈች ነው፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎችም የመጫዎቻ ሜዳውን እኩል ተደራሽ አድርጋ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ቅንጅት ደግሞ መልካም አስተዳደርን ፈጥሯል፡፡ በዚህ ተጠቃሚ የሆኑ የኢኮኖሚውን አቅጣጫ በመወሰን ሚና ያላቸው አካሎች በሙሉ ውጤታማና ጥራት ያለው ስራ እንዲሰሩ ሁሉም ተመቻችቷል፡፡ በሥርዓቱ ላይ እምነት ያሳደሩት ዲያስፖራዎችም ወደቦትስዋና በመምጣት የራሳቸውን ድርሻ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፓርላማ መቀመጫ ስላላቸው ውሳኔ አሰጣጡ በሕዝቡ ቁጥጥር ስር ነው፡፡ የፖለቲካ ተቋሞችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉና እየተስፋፉ መሆናቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በሌላው አለም እንደታየው ሁሉ ቦስትዋናም ቀስ በቀስ ዴሞክራሲን ገንብታ ኢኮኖሚዋን ጠግናለች፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሻሻል ለሚደረገው ጥረት ፖለቲካዊ አመራሩ ወሳኝ ነው፡፡ አመራርን የሚተገብረው ዜጋ ከሌለ ምርታማነት አይኖርም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለኢኮኖሚው ስጋት እየሆነ የመጣው የዋጋ ግሽበት ከኢኮኖሚ እድገታችን ጋር አልጣጣም ብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ በልማት ግሽበቱን ለመቀነስ ብሄራዊ መግባባት ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ የማይፈልገንን መግዛት እንጅ መምራት አንችልም፡፡ ኢሕአዴግ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አዳዲስ ሕጎችን ማውጣት ያሉትንና ጉድለት የተከሰተባቸውን መከለስ የሚኖርበት የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ህልውናና ብልፅግና ሲልም መሆን አለበት፡፡ በመላ ምት የሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚክስ አይደለም ለዳር ተመልካች ለጉዳዩ ባለቤቶችም ግራ የሚያጋባና ከሚጠበቀው በታች ወይም በላይ ሲሆን ልዩነቱም የማይገመት ይሆናል፡፡ ከምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር በተጨማሪ የአለም የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ባመጣው ሰበብ በርካታ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋቸው ጨምሯል፡፡ መንግሥት ይህን ችግር ለመቅረፍ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ አውጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የህገ ወጥ ነጋዴዎችን ተግባር ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ስራ ጀምሯል፡፡ የረጅም ጊዜ ዘላቂ ልማት ግንባታው ሂደት በነበረበት ፍጥነት እንኳን እንዳይቀጥል የመብራት፣ የውሃና የስልክ አገልግሎት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሪፖርት ተከትለው ሃገሪቱን እያመሱ ነው፡፡ የችግሮቹን መንስኤ በአንክሮ ላየው ተለዋጭ እቅዶች አለመኖራቸው፣ ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው የመንግሥት ባለሥልጣኖች በተጠያቂነትና በግልፅነት መርህ ስለማይመሩ ነው፡፡ ከወራት በፊት ኢሕአዴግ አባላቱን 4 ሚሊዮን ማድረሱን ሲነግረን በርካታ ባለሥልጣናትና ዳኞች ከሙስና ጋር የተገናኙበትን መንገድ በግልፅ እንዴት ጉዳዩ እንደተከሰተ በአጥጋቢ ሁኔታ አልነገረንም፡፡ ሙስናው በተከበሩ የመንግሥት ተቋማት ባንክ፣ ፍርድ ቤትና መብራት ሀይል መፈፀሙ ለሁልጊዜም ቢሆን የሕዝብ እምነት የሚሸረሽርና በመንግሥትና በዜጎች መካከል የጥርጣሬ መንፈስ የሚያሳድር ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡ ይህ ሁሉ የፖለቲካ ተፅዕኖ የሚከተለው ግን በበርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚገመተውን ገንዘብ ኪሳራና የኢኮኖሚ ውድቀት ሳዘነጋ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከምዕራባዊያንና ከአሜሪካ ጋር ከተወዳጀባቸው አበይት ምክንያቶች አንዱ የኢኮኖሚክ ፖሊሲው ዋነኛው ነው፡፡ ፖሊሲው በራሱ ችግር አለበት ለማለት አይቻልም፡፡ ፖሊሲው ወደ ተግባር ሲለወጥ የመጡት ለውጦችም ቀላል አይደሉም፡፡ ከአንድ ዩኒቨርስቲ ወደ 20 በላይ ዩኒቨርስቲዎች፣ የመብራት፣ የውሃና የስልክ ሰፊ ሽፋን፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት አመርቂ ሽፋን፣ በርካታ የመንገድ ሥራዎችና ማስፋፊያዎች፣ የአገልግሎት፣ የማምረቻና የእርሻ ስራዎች፣ የአስተዳደር መዋቅር ስራዎች". ብዙ ብዙ ለውጦች ተከስተዋል፡፡ ይህ አንድ ሰነፍና ራስ ወዳድ መንግሥት የሚያመጣው ለውጥ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለውጡ የፈጠነ ራዕይና ተስፋችንን ያቀረበ እንዲሆን መንግሥት አሁንም ሆደ ሰፊ በመሆን በጥንቃቄና በገለልተኛነት ምርቱን ከእንክርዳዱ እየለየ በርካታ ዜጎችን ያሳተፈ ለውጥ ይሁን ነው የምንለው፡፡ ይህ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማህበራት፣ የሰራተኛ ማህበራትና የንግዱ ማህበረሰብ በራሳቸው መንገድ በነፃ እንዲንቀሳቀሱ አሁንም እድሉን አይዝጋባቸው፡፡ እንደውም የሚዘጋ ካለ እነሱን መጠበቅና መንከባከብ ዋነኛ የመንግሥት ስራ ነው፡፡ ይህን ያደረጉት እነ ቦትስዋና የደረሱበትን በማስታወስ የመጨረሻ ግባችንን "ከድህነት ተላቃ በመካባበርና ለመፈቃቀድ የተመሰረተች ኢትዮጵያን ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሃገሮች ተርታ መመደብን" ለመምታት መጣር ይኖርብናል፡፡ መንግሥት ጣምራ የሆኑትን ኢኮኖሚንና ፖለቲካን ለማስታረቅ ጊዜ ባይወስድ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ "የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል" ተረት ወደ ተግባር ለመቀየር ክፍተት ማግኘቱ አይቀርም፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |