| የአዋሽ ባንክ የብድር መጠኑን... |
|
|
| Wednesday, 30 April 2008 | |
![]() የአዋሽ ባንክ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ በከፊል በዳዊት ታዬ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ 126.6 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንና ሊሰጥ ይገባ የነበረው የብድር አገልግሎት መጠን ተገቢ እድገት ማስመገብ አለመቻሉን አስታወቀ፡፡ ትናንት በሒልተን ሆቴል በተካሄደው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በባንኩ ዳይሬክተሮች የቀረበው 2ዐዐ7 ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው ባንኩ ከመቼም ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ ማግኘቱን ይገልፃል፡፡ በ2ዐዐ7 የበጀት ዓመት ባንኩ ያገኘው ጠቅላላ ትርፍም 2ዐዐ6 ከተገኘው ትርፍ በ33 በመቶ ብልጫ እንዳለው የጠቆመው ይኸው ሪፖርት በ2006 ባንኩ አግኝቶት የነበረው የተጣራ ትርፍ 95 ሚሊዮን ብር እንደነበርም ያስረዳል፡፡ ለአጠራጣሪና የተበላሹ ብድሮች (Non Performing Loans) የተያዘውን ገንዘብ ጨምሮ የባንኩ ጠቅላላ የብድር አገልግሎት መጠን በ2ዐዐ7 መጨረሻ 2.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም በ2ዐዐ6 የበጀት ዓመት ከተመዘገበው ተመሳሳይ አገልግሎት ጋር ሲነፃፀር በሦስት በመቶ ብቻ መጨመሩን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ግን በየአመቱ የሚሰጣቸው የብድር መጠኖች ከፍተኛ ልዩነት ያሳዩ ነበር፡፡ ይህም ልዩነት ከ15 በመቶ በላይ ብልጫ አላቸው፡፡ በሌላ በኩልም በ2007 የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን የጨመረ ቢሆንም የብድር አገልግሎቱ መጠን ተገቢውን እድገት ማስመዝገብ አለመቻሉን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ የብድር መጠኑ በተፈለገው መጠን ሊያድግ ስላለመቻሉ ሁለት ምክንያቶች የተቀመጡ ሲሆን አንደኛው ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች መጠባበቂያ ገንዘብ መጠን ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑና የባንኩ ትርፍ ተቀማጭ ገንዘብ (Excess liquidity) መጠን ማነስ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በባንኩ የብድር አገልግሎትን በተመለከተና እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከፍተኛ የሚባለው ብድር የተሰጠው ለአገር ውስጥ ንግድ አገልግሎት ሲሆን ይህም ከጠቅላላ ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ የ33 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ ደግሞ 10.4 በመቶ ድርሻ በመያዝ በሁለተኛ ደረጃ ይዟል፡፡ ኮንስትራክሽን የማምረቻ ዘርፍ፣ የእርሻና የወጪ ንግድ ተከላካይ ደረጃዎችን እንደያዙም በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል፡፡ ለአገር ውስጥ የንግድ አገልግሎት የሰጠው ብድር በ2ዐዐ7 የበጀት ዓመት ከተሰጡት ብድሮች ሁሉ ከፍተኛውን እጅ ቢይዝም በ2ዐዐ6 በዚህ ዘርፍ ከሰጠው ብድር ጋር ሲነፃፀር ብድሩ ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ለዚህ ዘርፍ በ2ዐዐ6 የተሰጠው ብድር 866.01 ሚሊዮን ብር ሲሆን በ2007 ግን 826.57 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ከአርባ ሚሊዮን ብር ልዩነት እንዳለው ያሳያል፡፡ በዚሁ በብድር አሰጣጥ ዙሪያ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ባንኩ ለማምረቻዎች የሰጠው ብድር ካለፈው የ2ዐዐ6 ብድር ጋር ሲነፃፀር ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያንስም ያመለክታል፡፡ የብድር መጠኑ ያደገው ዘርፍ ደግሞ በህንፃና ለኮንስትራክሽን እንዲሁም ለትራንስፖርትና ለላኪዎች የተሰጠው ብድር ሲሆን በተለይ ለላኪዎች በ2ዐዐ7 258.5 ሚሊዮን ብር ብድር የተሰጠ ሲሆን በ2006 ተሰጥቶ የነበረው ግን 224.6 በመሆኑ በዚህ ዘርፍ የሚሰጠው ብድር አድጓል፡፡ ይህም ልዩነት ከ38 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡ የብድር አመላላሽን በተመለከተም በሪፖርቱ ላይ እንደተገለፀው "ባንኩ ከብድር በፊትና ከብድር አሰጣጥ በኋላ የሚያደርጋቸው ቁጥጥሮችንና ክትትሎችን በማጠናከሩ የባንኩ የተበላሸ ብድር ወደነጠላ አሃዝ መውረድ መቻሉንም አመልክቷል፡፡ ትናንት በተካሄደው በዚሁ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ በተያዘው አጀንዳ መሠረት የባንኩን ካፒታል ወደ 550 ሚሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ መስማማቱንና የ2007 የትርፍ ክፍያ ላይም ውሳኔ ተላልፏል፡፡ በባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ችግር ውስጥ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁንም ሁለት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ያልተሟሉለት መሆኑ ታውቋል፡፡ የባንኩ የቀድሞው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አሁን በቦርድ አባልነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ 46 የሚሆኑ ቅርንጫፎችን ከፍቶ በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆን የሠራተኞቹንም ቁጥር ወደ 1698 አሳድጓል፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |