Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow "የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ አለን ካልን...
"የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ አለን ካልን... Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
Image"የአሥራ ሦስት ወር ፀጋ አለን ካልን አሥራ ሦስቱንም ወራት መሸጥ አለብን"
አቶ ፋንቱ ጐላ፣ የሰሜን ሎጂ ባለቤት

አቶ ፋንቱ ጐላ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት በቱሪዝም ኢኮኖሚክስ ነው፡፡ በአብዛኛው ህይወታቸውን ያሳለፉትም በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ነው፡፡ ቀድሞ የብሔራዊ ሆቴሎች ኮርፖሬሽን በሚባለው መሥሪያ ቤት ለ18 ዓመታት ያህል ሠርተዋል፡፡ በዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች ዋና ሥራ አስኪያጅነትም አገልግለዋል፡፡ ኒክ ክሬን ከተባሉ አንድ እንግሊዛዊ ጋር በቅርቡ በሰሜን ፓርክ ስለገነቡት የሰሜን ሎጂ ኃይሌ ሙሉ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የሰሜን ሎጂን ለመገንባት ምን አነሳሳችሁ?

አቶ ፋንቱ፡-
የሰሜን ፓርክ በዓለም ብርቅዬ ተብለው በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ቅርሶች አንዱ ነው፡፡ ብሔራዊ ፓርኩ ከተፈጥሮ መስህቡ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ የዱር እንስሳት ዋልያ አይቤክስ፣ ቀይ ቀበሮ እና ጭላዳ ይገኙበታል፡፡ ብሔራዊ ፓርኩን ለመጐብኘት ቱሪስቶች ሲመጡ በአካባቢው የሚያርፉበት ቦታ አልነበረም፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከብሔራዊ ፓርኩ አጠገብ በሚገኘው ደባርቅ ከተማ ለሁለት ዓመት ያህል የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ተከታትያለሁ፡፡ እዚያ በነበርኩበት ሰዓት ቱሪስቶች ድንኳን ይዘው ወደ ብሔራዊ ፓርኩ ይሄዱ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከፓርኩ ለመድረስና በኢትዮጵያ በከፍታ አንደኛ የሆነውን ራስ ዳሸን ተራራን ለመውጣት እስከ ሰባት ቀን ያህል ይወስድባቸው ነበር፡፡ ቱሪስቶቹ ረጅም ጉዞ ተጉዘው ወደ ፓርኩ ሲደርሱ ማረፊያ አልነበራቸውም፡፡

ማረፊያ በሌለባቸው ቦታዎች ላይ ማረፊያ ቦታ ቢሰራ የሚል ጉጉት ነበረኝ፡፡ የራሴን የአማካሪ ኩባንያ ካቋቋምኩ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከውጭ አገርና ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በመሆን በጋራ እንሰራለን፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኒክ ክሬን የተባለ አንድ እንግሊዛዊ ለሌላ ሥራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ የሰውየው አመጣጥ ኋላ ቀር ለሆኑ የገጠር ትምህርት ቤቶች የትምህርት መሳሪያ ለመርዳት ነበር፡፡ እርዳታ ያበረከተላቸው ትምህርት ቤቶች ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለመከታተል በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አገሪቱን እየወደዳት መጣ፡፡ እኔም መሠራት ስለሚቻሉ ልማቶች አወራው ነበር፡፡ እርሱም ይህ ዓይነቱ ፍላጐት ካለህ ለምን በጋራ አንሰራም አለኝ፡፡ ስምምነት ላይ ደረስን፡፡ አራት የቱሪዝም አካባቢዎችን ለምርጫ አቅርበን በመጨረሻ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክን መረጥን፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሜን ብሔራዊ ፓርክን ለምን መረጣችሁት?    

አቶ ፋንቱ፡-
ሰሜን ብሔራዊ ፓርክን ስንመርጥ በጣም ከባድ ውሳኔ እንዳስተላለፍን እናውቅ ነበር፡፡ በአካባቢው ከአንድ መንገድ በስተቀር መብራትና ውሀ አልነበሩም፡፡ ቴሌፎን የለም፡፡ ከተማው ውስጥ የሚገኙ መሠረተ ልማት በሙሉ በፓርኩ አካባቢ የሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ሰሜን ብሔራዊ ፓርክን አሰባችሁ የሚሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ውሀ በአካባቢው አይገኝም፡፡ ተራራው ላይ ወጥተህ የምታገኛቸው የተወሰኑ ምንጮችን ነው፡፡ እነዚህን ምንጮች በሰው ኃይል በማጐልበት ለግንባታ እንዲውሉ አደረግን፡፡ በፓርኩ አካባቢ የቴሌፎን አገልግሎት ስላልነበር 21 ኪሎ ሜትር ተጉዘን ነበር ስልክ የምናኘው፡፡ ለግንባታ የሚውል አሸዋ የምናመጣው 7ዐ ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘን ነበር፡፡ በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ የሚገኝ ድንጋይ ማንሳት አይቻልም፡፡ እንደህግ ሆኖ የተቀመጠ ጉዳይ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ኘሮጀክቱ ከፍተኛ ገንዘብ አስወጥቶናል፡፡ ኘሮጀክቱን ያከናወንነው በራሳችን መሀንዲሶች ባይሆን ኖሮ ከዚህ በባሰ መልኩ ለከፍተኛ ወጪ እንዳረግ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ የህንፃውን ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቀቅን፡፡ የግንባታ ሥራውን ከጨረስን በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ ጥያቄዎች መጡ፡፡ የኃይል ጥያቄውን ለመፍታት በአካባቢው ጀኔሬተር መትከል እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን እዚያ ያለንበት አካባቢ እንዲጐዳ አልፈለግንም፡፡ ሁለታችንም ለአካባቢ ትልቅ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ብቻ አይደለም የምንሯሯጠው፡፡ ብሔራዊ ፓርኩ ያለው የአየር ንብረት በምንም መልኩ እንዲነካ አንፈልግም፡፡ ያለውን ነገር ጠብቀን መጓዝ ነው የእኛ ፍላጐት፡፡ እኛ የምናራምደው የኢኮ ቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢኮ ቱሪዝም ምንድነው?

አቶ ፋንቱ፡-
ኢኮ ቱሪዝም ሦስት ባለድርሻ አካላት አሉት፡፡ አንደኛው ራሱ ኢንቫይሮመንቱ ነው፤ ሁለተኛው ማህበረሰቡ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ እኛ ባለሀብቶቹ  ነን፡፡ ሦስታችንም ተጠባብቀን መሄድ አለብን፡፡ በዚህም መሰረት ከቁፋሮ ጀምሮ እስከሎጂው የፍፃሜ ሥራ ማህበረሰቡ እንዲሳተፍ ተደርጓል፡፡ በተቻለ መጠን የዚያ አካባቢ ኢንቫይሮመንት እንዳይነካ፣ ዛፎች እንዳይቆረጡ፣ ድንጋዮች እንዳይፈነቀሉ ጥረት አድርገናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደ 1ዐ ሺህ የሚጠጉ አገር በቀል ዛፎች በአካባቢው ተክለናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአካባቢው ላከናወናችሁት ኢንቨስትመንት ምን ያህል ወጪ አውጥታችኋል?

አቶ ፋንቱ፡-
በአጠቃላይ ወደ 7.2 ሚሊዮን ብር አውጥተናል፡፡ ለግንባታ የዋለው ውሀ የወሰድነው 2ዐዐ ሜትር የኢሊቬሽን ከፍታ ካለው ምንጭ ወደ ታች ወርደን ነው፡፡ ውኃውን ከታች ወደ ላይ የወሰድነው በሦስት ፓምኘ አቀባብለን ነው፡፡ ሥራው ምን ያህል ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስወጣ ከዚህ መገመት ትችላለህ፡፡ ለፓርኩ የሚውል የኃይል አቅርቦት ያስመጣነው 21 ኪሎ ሜትር ከሚርቀው የደባርቅ ከተማ ነው፡፡ የመብራት አገልግሎት ወደ ፓርኩ እንዲላክልን ጠይቀን ነበር፤ ነገር ግን አልተረዱንም፡፡ ምንም አማራጭ ስላልነበረን ከመብራት ኃይል ጋር በግል ተፈራርመን 850 ሺህ ብር በመክፈል ከደባርቅ ከተማ ወደ ፓርኩ የኤሌክትሪክ መስመር እንዲዘረጋ አደረግን፡፡

ትብብርም ተደርጎልናል፡፡ የኤሌክትሪክ መስመሩን ስናስዘረጋ ከ850 ሺህ ብሩ ውስጥ ቀድመን እንድንከፍል የተደረገው አስር በመቶ ብቻ ነው፡፡ ሌላውን በየወሩ እየከፈልን ነው፡፡ ከመብራት ኃይል ጋር በተደጋጋሚ በመሄድ ለመደራደር ብንሞክርም ከዚህ በላይ ሊረዱን አልቻሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው ውጭ ያከናወናችሁት ምንድነው?

አቶ ፋንቱ፡
- ከኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታው በተጨማሪ ሶላር ኢነርጂ ጥቅም ላይ አውለናል፡፡ ሶላር ኢነርጂን የምንጠቀመው የሻወር ውሀ ለማሞቅ ብቻ ሳይሆን የሎጂውን የመሬት ስር እንዲያሞቅ ጭምር ነው፡፡ ሎጂው የተሰራበት ቦታ ቀዝቃዛ በመሆኑ በተቻለ መጠን በተለይ መኝታ ክፍሎቹ ሙቅ እንዲሆኑ ጥረት አድርገናል፡፡ ውሃውን በሶላር እናሞቅና በእያንዳንዱ መኝታ ክፍሎች የመሬት ስር በተዘረጉ ቱቦዎች ሙቅ ውሃ እንዲገባና ቀዝቃዛው እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡ አልጋውና የመፀዳጃ ቤቱ ያረፈበት ቦታ ሙቀት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአልጋው አካባቢ የማሞቂያ ፋይበር እንዲለጠፍበት ተደርጓል፡፡ ጣሪያው በሙሉ ተመሳሳይ ኢንሱሌሽን ማቴሪያል ተለጥፎበታል፡፡ እያንዳንዱ የእንግዳ ማረፊያ የተዘጋጀው በዚህ መልኩ ነው፡፡ አልጋዎችንና ፍራሾቻችን ያስመጣነው ከውጭ ነው፡፡ ነገር ግን ከውጭ የምታየው ነገር በሙሉ የአገር ውስጥ ምርት ነው የሚመስልህ፡፡ ሎቢያችን በጣም ሰፊ ነው፡፡ ራሱን የቻለ ኪችን አለ፡፡ የሠራተኞች መታጠቢያ ሻወር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ኘሮጀክት ለአካባቢው ህብረተሰብ ያስገኘው ጥቅም ምንድነው?

አቶ ፋንቱ፡-
በግንባታው ወቅት ገበሬውን ቀጥረን አሰርተናል፡፡ ኘሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 7.2 ሚሊዮን ብር ወጪ የወጣባቸው 26 ክፍሎች፣ ትልልቅ ሬስቶራንትና ባር ያለው የተሟላ ሎጂ ከፍተንበታል፡፡ 3ዐ የሚሆኑ ቋሚ ሰራተኞች ቀጥረናል፣ 140 የሚሆኑ ሰራተኞች በየቀኑ ለሁለት ዓመት ያህል በግንባታው ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ የጉልበት ሰራተኞች የወጡ ብዙ አናጢዎች፣ ግንበኞችና ኤሌክትሪሺያኖች አፍርተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሠራተኞች መኖሪያ ተጨማሪ ቤቶችን እየሰራን እንገኛለን፡፡ የእነዚህን ግንባታ እያከናወኑ ያሉት ኘሮጀክቱ ሲጀመር የቁፋሮ ሰራተኞች የነበሩ ናቸው፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የዚህ ኘሮጀክት ትልቁ ስኬት የአካባቢውን ሰዎች የሙያ ባለቤት ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሎጅውን ከገነባችሁ በኋላ እያከናወናችሁ ያለው ሥራ ምንድነው?

አቶ ፋንቱ፡-
በኢኮ ቱሪዝም ፅንሰ ሀሳብ መሰረት ኢኮሎጂውን እየጠበቅን ነው፡፡ ከክልሉ የፓርክ ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን በአካባቢው ዛፎችን እንተክላለን፣ እንከባከባለን፣ እንጠብቃለን፡፡ ሁለተኛ ማህበረሰቡን በተመለከተ ለሎጂው አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ጥሬ እቃዎችን የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲያመርት እያደረግን ነው፡፡ ቆስጣ፣ ሰላጣ፣ ድንች የመሳሰሉትን ምርቶች የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲያመርት እናበረታታለን፡፡

በርካታ ገበሬዎች የፖም ምርት እያቀረቡልን ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጐበኘ የፖም እርሻ አለ፡፡ በተቻለ መጠን ገበሬው ከእኛ ጋር አብሮ እንዲሰራ እያደረግን ነው፡፡ አንድ የቅርሳ ቅርስ ሱቅ ከፍተን ለአካባቢው ህብረተሰብ ሰጥተናል፡፡ ሱቁን የሚሰሩበትና የሚቆጣጠሩት ራሳቸው ገበሬዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ገበሬዎቹ ራሳቸውን በማደራጀት ፈረስና በቅሎ በማቅረብ ለቱሪስቶች በማከራየት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡ የአካባቢው ወጣቶችም ከዚህ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እየተፈለገ ነው፡፡ በአካባቢው የሚገኙ  ትምህርት ቤቶችን በመርዳት በኩልም ከፍተኛ ሥራ እየሰራን ነው፡፡ አውሮፓ ውስጥ ከሚገኝ አንድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በጭስ ምክንያት አይኖቻቸውን የሚታመሙትን የአካባቢውን ሴቶች ችግር ለመቅረፍ ጭስ አልባ ምድጃ ተሰርቶ በነፃ እየተሰጠ ነው፡፡ ወደ 3ዐዐ የሚጠጉ ባለትዳር ሴቶች የምድጃው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህ ተግባር ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የተለያዩ ቁሳቁሶች በማቅረብ እንረዳለን፡፡ ቱሪስቶች ለጉብኝት ሲመጡ ለአካባቢው ነዋሪ አምስትና አስር ሳንቲም ከሚሰጡ ይልቅ በሆቴሉ ውስጥ ባስቀመጥነው የአግዳሚ ወንበር ናሙና መሰረት አንድ ወይም ሁለት ወንበር ገዝተው ለትምህርት ቤቶች እንዲያበረክቱ እናደርጋለን፡፡ አላማችን በእንደዚህ ዓይነት እርዳታ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡ ሎጂው በሰፊው የማህበረሰብ ኘሮግራሞች ላይ አብሮ ለመስራት የራሱን ኘሮግራሞችን እየዘረጋ ነው፡፡     ገቢያችን እየተሻሻለ ከመጣ ለማህበረሰቡ የሚውሉ አገልግሎቶችን እንሰራለን፡፡

ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረትና ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ለማድረግም ከፋውንዴሽኖች ጋር ተፃፅፈን የሚያበረታታ ምላሽ አግኝተናል፡፡ በሙከራ ኘሮጀክት ለአስር ወጣቶች ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርታቸውን እስከሚጨርሱ ድረስ የስፖርት ትጥቅ እየተሰጣቸው በአትሌቲክስ ስፖርት እንዲሳተፉ፣ ለአሰልጣኞችም የተወሰነ አበል እየተከፈላቸው ተማሪዎችን እንዲያሰለጥኑ ይደረጋል፡፡ ይህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ወደፊት ከዚህ በተሻለ ብዙ ሥራዎችን እንሠራለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የሰሜን ተራራ አትሌቶችን ከሚያፈራው ከበቆጂ አካባቢ ጋር ይመሳሰላል፡፡ አንጋፋ አትሌቶቻችን ወደ እዚያ በመሄድ ቢሰለጥኑ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ አካባቢው ለሯጮች ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቢያስብበትና ከዚያ አካባቢ ለሚመጡ አትሌቶች ትኩረት ቢሰጥ ጥሩ ነው፡፡ ከአካባቢው ከፍታ በተጨማሪ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አስርና አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ተጉዘው በመሆኑ የተፈጥሮ ጥንካሬ ይሰጣቸዋል፡፡ የአሜሪካ ፋውንዴሽን በሰጠን ትንሽ ድጋፍ የተወሰኑ ተማሪዎችን መልምለን እየረዳን ነው፡፡ የአገራችን ታዋቂ አትሌቶች ደግሞ ወደ ስፍራው ተጉዘው ቢታዩ እና ሁለት ወይም ሦስት ሰው ስፖንሰር ቢያደርጉ ብዙ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሎጂው ከተሰራ በኋላ በጐብኝዎች ቁጥር ላይ ለውጥ ታይቷል?

አቶ ፋንቱ፡-
በአካባቢው ምንም ዓይነት ማረፊያ ባልነበረበት ጊዜ ከሰባት እስከ ስምንት ሺህ የሚደርሱ ቱሪስቶች አካባቢውን ይጐበኙ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ብሔራዊ ፓርኩ በሄድንበት ወቅት በአካባቢው የነበረው 15 ክፍል ያለው አንድ ሆቴል ብቻ ነበር፡፡ ቱሪስቶቹ የጋራ መፀዳጃ ቤትና የጋራ ሻወር እንዲጠቀሙ ይገደዱ ነበር፡፡ የእኛ ሎጂ ከተከፈተ በኋላ ግን ሦስትና አራት ፎቅ ያላቸው ሌሎች ሰባት ትልልቅ ሆቴሎች በደባርቅ ከተማ እየተገነቡ ነው፡፡ ሁለቱ አገልግሎት ለመስጠት ተቃርበዋል፡፡ ከተማዋ እየተቀየረች መጥታለች፡፡ ከተማዋ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለች ብዙ ለውጥ ይታይባታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኛ ጀማሪዎች በመሆናችን ህዝቡ እንደጀግና ነው የሚያየን፡፡ ይህ በጣም የሚያበረታታ ነው፡፡ እንግዶቻችን የሚያገኙት ሰርቪስ አዲስ አበባ ከሚገኙ ትልልቅ ሆቴሎች የሚያንስ አይደለም፡፡ ጐብኝዎች የሚፈልጉትን ዓለም አቀፍ ምግብ ያገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቱሪዝም ችግር ምንድነው?

አቶ ፋንቱ፡-
የአገራችን ቱሪዝም አንዱ ደካማ ጐኑ ወቅታዊ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ችግር መቀየር አለብን፡፡ የአስራ ሦስት ወር ፀጋ አለን ካልን አስራ ሦስቱንም ወራት መሸጥ አለብን፡፡ በአውሮፓ ስድስቱ ወደ ቀዝቃዛ፣ ሦስቱ ወራት ስኘሪንግ ቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ በጣም በረሃማ ናቸው፡፡ አውሮፓ ውስጥ በሙቀት ጊዜ በካናቴራ ነው የምትሄደው፡፡ ኢትዮጵያ ግን እንደዚህ ዓይነት ችግር ያለባት አይደለችም፡፡ ነሐሴ ላይ በሸሚዝ መሄድ ትችላለህ፡፡ አንዱ ጋር ሲዘንብ አንዱ ጋ ፀሐይ ይሆናል፡፡ በክረምት ወራት ሰሜን ተራራ ተፈላጊ ቦታ ነው፡፡ የአውሮፓን ሀሩር የማይወዱና ቅዝቃዜን የሚመርጡ ሰዎች ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ቢመጡ ይመቻቸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግም የኘሮሞሽን ስትራቴጂያችንን መቀየር አለብን፡፡ በአረብ አገራትም ማስታወቂያ መስራት አለብን፡፡ አብዛኛዎቹ የአረብ አገራት በቱሪስትነት የሚጓዙት ወደ ስዊትዘርላንድ፣ ኖርዌይና ዴንማርክ ነው፡፡ እኛ ወደመካከለኛው ምሥራቅ ሄደን ኘሮሞሽን ብንሰራ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ኢትዮጵያ ለመካከለኛው ምሥራቅ ቅርብ በመሆኗ ለጉብኝት ተመራጭ ልትሆን ትችላለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ገንዘቡ ያለው መካከለኛ ምሥራቅ ውስጥ ነው፡፡ እዚያ ያለውን ገበያ ልንስብ የማንችልበት መንገድ የለም፡፡ ሸቀጣ ሸቀጥ ብቻ ማምጣት ሳይሆን ቱሪስትንም ለማምጣት በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዘመቻ ቢካሄድ ጥሩ ውጤት ያስገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሰሜን ሎጂን ጐብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅት ምን ተነጋገራችሁ?

አቶ ፋንቱ፡-
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ያልጠበቅነውና ድንገተኛ ነበር፡፡ በመምጣታቸው በጣም ተደስተናል፡፡ አንድ የአገር መሪ መጥቶ ድርጅትህን ሲጐበኝልህ በጣም ያስደስትሃል፡፡ ሎጂውን ተዘዋውረው በመጐብኘት አበረታተውናል፡፡ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለውናል፡፡ ባዩት ነገር የተደሰቱ ይመስለኛል፡፡ እርሳቸው ለጉብኝት በመጡበት ጊዜ በጣም ብዙ ቱሪስቶች ነበሩ፡፡ አየሩም በጣም ጥሩ ነበር፡፡ የእርሳቸው ጉብኝት ለእኛ ትልቅ ሞራል ነው፡፡ አንድ የአገር መሪ ሁለት መቶ ኪሎ ሜትር በመኪና ተጉዞ ድርጅትህን ሲጐበኝልህ ደስታህ ወሰን አይኖረውም፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ተነጋገራችሁ?

አቶ ፋንቱ፡
- ስለ አጠቃላይ ስለ ሰሜን ተራራ ተፈጥሮ ተወያይተናል፡፡ ስለ ሶላር ኢነርጂ አጠቃቀም ተነጋግረናል፤ ስለቱሪስቶችም አንስተናል፡ በአካባቢው የአውሮኘላን ማረፊያ የለም፡፡ ስለዚያም ጉዳይ ተነጋግረናል፡፡ በአጠቃላይ ያደረግነው ውይይት አስደሳች ነበር፡፡
 
< Prev   Next >