Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Aug 08th
Home arrow Sections arrow ክቡር ሚኒስትር
ክቡር ሚኒስትር Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
(የፋሲካ እለት ነው፡፡ እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ቤተሰቦች መጥተዋል፡፡ በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የምትማረውና የመመረቂያ ጽሁፍ ለማዘጋጀት የመጣችው ልጃቸውም አብራ ተቀምጣለች፡፡ ወሬው ተሟሙቋል)

- ደስ የሚል በዓል ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በተለይ ለእናንተ ለፆማችሁ ይበልጥ ደስ ይላል፡፡ እኔ እንኳ አልፆምኩም፡፡
- ለመሆኑ የሚፆም ባለሥልጣን፣ የሚፆም ኢሕአዴግ አለ?
- አይጠፋም፡፡ ለመፅደቅ ተብሎ ባይሆንም ከቤተሰብ ጋር አብሮ ለመሆን የሚፆም ይኖራል፡፡ የማይፆም ከሆነም በሃይማኖት ላለማመን አይደለም፡፡
- አሁንማ በማርክሲስትነት አትታሙም፡፡
- የሚያማማ አይጠፋም፡፡ ይህን የማይፈቅዱት ማርክሲስቶች ስለሆኑ ነው፤ የሚሉ አሉ አይደል?
- አንዳንዱ ነው እንጂ አንዳንዱ ባለሥልጣን ለንብረትና ለገንዘብ የሚያደርገው ሩጫ እንኳን ማርክሲስት ሊሆን ተወልዶ ያደገው "ዎልስትሪት" ውስጥ ይመስላል፡፡
- በሉ፣ በሉ በአውደ ዓመት ስለ ፖለቲካ አናውራ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ እናውራ እንጂ፡፡ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባም በማሟያ ምርጫውም አሸንፏል ደስ ብሎናል፡፡ እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንኳን አብሮ ደስ አለን፡፡ ተቃዋሚዎች ጠንከር ብለው ቢወዳደሩ ኖሮ ይበልጥ ደስ ይል ነበር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ አብዳችኋል? እንዴት ብለው ነው ጠንከር ብለው የሚወዳደሩት? የሌላቸውን፡፡
- አንዳንዶቹ ጥሩዎች ናቸው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንዳሉት አንዳንዶቹ ጥሩዎች ናቸው፡፡ በተለይም ወጣቶቹ ይሻላሉ፡፡ እነ ልደቱ ይጠሉ የነበሩት አሁን የተሻሉ መሆናቸው ሕዝቡ እየገባው ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ ግን ያሳፍራሉ፡፡ ጉደኞች ናቸው፡፡ በተለይ ከምርጫው ወጥተናል ማለታቸው ያስቃል፡፡
- በጣም ያስቃል፡፡
- የዝንጀሮዋ ዓይነት እኮ ነው፤ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የዝንጀሮዋ ምን?
- ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር፣ ዝንጀሮዋ ፍሬ ለመብላት ፈልጋ ፍሬው ጋ ለመድረስ ትዘላለች፡፡ መድረስ ያቅታታል፡፡ ትዘላለች፡፡ መድረስ ያቅታታል፡፡ መጨረሻ ተስፋ ቆርጣ ትተወዋለች፡፡ ግን መድረስ ስላቃተኝ ትቸዋለሁ አላለችም፡፡ ሌላ ምክንያት ነበር የሰጠችው፣ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አለች?
- "ድሮውንም ፍሬው አልበሰለም" አለች፡፡
- ድሮውንም ምርጫው ፍትሐዊ አይደለም፤ እንዳሉት ዓይነት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ ዛሬ ጧት ልጄ ከኢንተርኔት ያገኘሁት ነው ብሎ አንድ የሰጠኝ ጽሁፍ ብቻዬን አሳቀኝ፡፡
- ስለምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር፣ ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ጽጌ የትጥቅ ትግል እንጀምራለን አሉ፡፡
- ውይ ያውም እነ ብርሃኑ ነጋ፡፡ አይ የቅንጅት ነገር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ ከቅንጅትም ወጥተናል አሉ፡፡ ሰላማዊ ትግል ከሚያምኑት ተለይተናል ብለዋል፡፡ መታጠቃቸው እኮ አይገርምም፡፡ "መለኪያ ቢታጠቁ" አይገርመንም፡፡
- "ኦዲተሮች" እንዳይደርሱባቸው ቢታጠቁምኮ አይገርምም፡፡
- ሃ! ሃ! ሃ! ይህች ቆንጆ የአውድ ዓመት ቀልድ ናት፡፡ የፋሲካ ቀልድ ናት፡፡ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለነገሩማ ክቡር ሚኒስትር እንደ ነፃ አውጪ መታጠቃቸው እንጂ እንደ ቴክሳስ ካውቦይ ቢታጠቁ ምን ይገርማል?
- ለመሆኑ ሁለቱ ብቻ ናቸው፡፡
- ሌሎችም አሉ፡፡
- የሴትየዋስ?
- ማን ነች ሴትዮ ክቡር ሚኒስትር?
- ያቺ አዲስ አበባ እንገናኛለን፤ ብላ ለቅንጅት ቃል የገባችው፡፡
- አና ጎሜዝ እስካሁን ስሟ የለም፡፡
- ቢያንስ ቢያንስ እሷ የኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል ይገባት ይሆናል፡፡ በሉ በሉ ምሳ ቀርቧል ወንበር ላይ እንቀመጥ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር፣ አንዱ ጋዜጣ ምን ብሎ እንደፃፈ ያውቃሉ፡፡ ስጋውና እንቁላሉ ውድ ስለሆነ እስኪረክስ ድረስ "ፆሙ ይራዘምልን፣ ፋሲካ ይተላለፍልን" አለ፡፡
- ዋጋ እስኪረክስ ከተጠበቀማ ምን ጊዜም ላይከበር ይችላል፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር እናንተም እንደዚያ ትላላችሁ እንዴ?
- ምን ማለት ነበረብን?
- ይረክሳል፤ አይዟችሁ ነው ልትሉን የሚገባው፡፡
- ለምን እንደዛ እንላለን፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እንደዚያ ታደርጋላችሁ ብለን ነውኮ የመረጥናችሁ፡፡
- የምግብ ችግር የዓለም ችግር ነው፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ የዓለም ችግር የሆነውን የዓለም ችግር ነው ብለን እንቀበለዋለን፣ የራሳችን ችግር ደግሞ እንፍታው፡፡
- የራሳችን የሆነ ችግር አለ ብላችሁ ነው?
- ተው ተው ኢሕአዴጎች ሰው የሚላችሁን አዳምጡ፣ ከዚህ ያለማዳመጥ በሽታ ተገላገሉ" ተፈወሱ"
- ምነው? መቸ አናዳምጥም አልን፡፡
- ይኸው እያላችሁ አይደል፡፡ የምግብ እጥረትን በሚመለከት ምን እናድርግ ብላችሁ ፖሊሲያችሁን ከመፈተሽና ከማስተካከል ይልቅ የዓለም ችግር ነው ማለት ጀመራችሁ፡፡
- እስቲ አሁን ፖለቲካውን እንተውና እንፈስክ፡፡
- የተባረከ የተቀደሰ".

(ምሳ ተበላ፣ ተጠጣ፣ ተሳቀ፣ ተፈሰከ፡፡ እንግዶቹ ሄዱ፡፡ መሸት ሲል ክቡር ሚኒስትር ቡና እንጠጣ ተባብለው ከልጃቸው ጋር ወጡ)

- ይህ ሃርቫርድና አሜሪካ ከባህላችን እያራቀሽ ነው ወይስ የዓመት በዓል ባህላችን እየወደድሽው ነው?
- እኔም እንደነሱ ክቡር ሚኒስትር ልበልና".  የእኛ አገር ባህልኮ የትም አይገኝም፡፡ እኔ በባህሌ በጣም ነው የምኮራው፡፡ መቀራረብ፣ ፍቅርና መተሳሰብ ያለበት ነው፡፡ አርብ ዕለት እንዴት ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ብዙ ፎቶ አንስቻለሁ፡፡
- ምን ነበር አርብ ዕለት?
- በአንድ በኩል የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ሰግደው ከመስጊድ ወደ ቤታቸው በብዛት ይጎርፋሉ፡፡ በሌላ በኩል የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ለመስገድ ወደ ቤተክርስቲያን ይጎርፋሉ፡፡ አብዛኛው ነጭ ለብሷል፡፡ አብዛኛው ፈገግታና ደስታ አለው፡፡ ሁለቱም ሃይማኖት ተባብሮና ተጠናክሮ ጎን ሊጎን ሲሄድ ማየት እንዴት ደስ ይላል፡፡
- እንዴት አስተዋይ ልጅ ወጥቶሻል እባክሽ፡፡
- እውነት እውነት፣ ልዩ ደስታን የሚፈጥር ነበር፡፡ ዓለም እርስ በርስ ሲባላ እኛ አገር ልዩነታችንን ይዘን አንድ መሆናችን የሚያኮራን ነው፡፡
- ጎሽ አንቺም የምታኮሪ ልጅ ሆነሻል፡፡ ፖለቲካውስ ጠለቅ ብለሽ እያጠናሽው ነው? እዚያ ያለው የተሳሳተ ዲያስፖራ እንደሚያወራው አይደለም፡፡
- እነሱን ተዋቸው፡፡ እንኳን ለአገር ለራሳቸውም አልተጠቀሙም፡፡ ነገር ግን፡፡
- ነገር ግን ምን?
- ኢሕአዴግ ቢሆን ራሱን መመርመር አለበት፡፡
- ምን ችግር አለውና፡፡ ኢሕአዴግ ድሮም አሁንም ትክክል ነው፡፡
- አሁንም ጥሩ እየሰራ ነው፡፡ ይህ ሃቅ አይካድም፡፡ አስገራሚ የትጥቅ ትግል አካሂዳችኋል፡፡ ብሄር ብሄረሰብ በቋንቋውና በባህሉ እንዲኮራ አድርጋችኋል፡፡ ምርጫ፣ ፕሬስ የመሳሉትን ጀምራችኋል፣ በርካታ የልማት ስራዎችን ሰርታችኋል፡፡
- ታዲያ ይሄ የሚደንቅ እንጅ ተራ ስራ ነው እንዴ?
- አዲስ አበባን እንደገና እየሰራችሁ ነው፡፡ ልዩ ከተማ ሆናለች፡፡
- ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ፈልገሽ ነው ወይስ አንቺም ምሁራዊ አቃቂር ጀመርሽ?
- አይደለም፣ አይደለም አዳምጠኝ፡፡
- አዳምጨሻለሁኮ፡፡ ራሳችሁን መርምሩ አልሽ፡፡ ማንም ሳይነግረን ራሳችን የመረመርን ድርጅት ነን፡፡ የሃርቫርድ ሰብስክሪፕሽን አያስፈልገንም፡፡
- የኢሕአዴግ ችግር ይኸው ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ራሱን ብቻ የማዳመጥ በሽታ፡፡
- አሁን እኔ አላዳመጥኩሽም?
- መች አዳመጥከኝ? አላናግር አልከኝ እኮ፡፡
- እስቲ የፈለግሽውን ተናገሪና አዲስ ነገር ካለሽ እንይ፡፡
- አመሰግናለሁ አባት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በይ ቀጥይ አትቀልጅ፡፡
- ኢሕአዴግ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ አለበት፡፡
- እስካሁን አልሰራም?
- ሰርቷል፡፡ ነገር ግን የተለመደው ታሪክ ማለት አይደለም፡፡
- እንዴት የተለመደው ታሪክ?
- አፄ ቴዎድሮስ እጄን አልሰጥም ብለው ራሳቸውን ገድለዋል፡፡ እንግሊዞች ሊማርኩዋቸው አልቻሉም፡፡ ቆራጥ መሪ ነበሩ፡፡ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ታሪክ ነው፡፡
- እናስ?
- አፄ ዮሐንስ ዶግአሊ ላይ አሸነፉ፡፡ ደርቡሾችን ተዋጉ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ታሪክ ነው፡፡
- እህ፡፡
- አፄ ምኒሊክ የአድዋ ድልን አረጋገጡ፡፡ አኩሪ ታሪክ፣ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ታሪክ፡፡
- አፄ ኃይለሥላሴ ጣሊያን ሲወር አገራቸውን ወክለው በሌግ ኦፍ ኔሽንስ አቤት አሉ፡፡ ከእንግሊዞች ጋር ሆነው ጣሊያንን አባረሩ፡፡ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ታሪክ፡፡
- ከጦርነት ጋር የተያያዘ ታሪክ ኢሕአዴግም አለው፡፡ ደርግን አባሯል፡፡ ሻዕቢያን ከባድመ ጠራርጓል፡፡ አሸባሪዎችን ከሞቃዳሾ አስለቅቋል፡፡ የጦርነት ታሪክ፡፡
- ስሚ አፄ ቴዎድሮስም ጋፋትን የመሰለ የቴክኒክ ትምህርት ቤት ከፍተው በአገር ውስጥ ባለሙያ ያሰሩና የጀመሩ ናቸው፡፡ ጦርነት ብቻ አይደለም፡፡ አፄ ዮሐንስም አገርን የጠበቁ ያኮሩ ናቸው፡፡ አፄ ምኒሊክም ምድር ባቡር ሰርተዋል፤ ትምህርት ጀምረዋል፡፡ ዘመናዊ ስልጣኔን አስገብተዋል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴም ሕገ መንግሥት አውጥተዋል፤ የተጀመረውን ስልጣኔ አስፋፍተዋል፡፡ መቼ የጦርነት ታሪክ ብቻ ሆነና፡፡
- ዳዲ ሚኒስትር ሆይ፡፡ ያልከው ትክክል ነው፡፡ ጎልቶ የሚወጣውና የሚነገረው የሚዘከረው ግን የጦርነትና የጀግንነት ታሪክ ነው፡፡
- አንቺ ነሽኮ ያጎላሽው፡፡ የኢሕአዴግ ታሪክ የልማት ታሪክ ነው፡፡
- አድምጠኝ የሕግ ተማሪ ነኝ፡፡ ለመመረቂያ ፁሁፌ ሕግ ነክ ነገሮች እያጠናሁ ነው፡፡ ሳነብ አእምሮዬ ውስጥ የሚመጣው ለምን ኢሕአዴግ ታሪክ ሰርቶ አያልፍም የሚል ነው፡፡
- ለምሳሌ ምን?
- እኔ ያንተ የኢሕአዴግ ልጅ ነኝ፡፡ እከራከራለሁ፡፡ በውጭ አገርም ፀረ ኢሕአዴግ ከሆኑ ሃይሎች ጋር እከራከራለሁ፣ በተለይ በተለይ የሚያኮራ ሕገ መንግሥት አስገኝታችኋል፡፡ የራሳችሁን ሕገ መንግሥት ግን ራሳችሁ ታበላሻላችሁ፡፡
- ውሸት!
- በሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 29 የሰፈረውን የፕሬስ ነፃነት የሚያረጋግጥ አንቀፅ በእጅጉ የሚያኮራ ነው፡፡ የፕሬስ ሕግ ብላችሁ የምታወሩት ያለው ግን አንቀፅ 29ን የሚፃረር ነው፡፡
- ለዚህ ነውኮ ያለውን የፕሬስ ሕግ ለማሻሻል አዲስ ረቂቅ ያወጣነው፡፡
- ይኸውልህ ረቂቁ ቢቀርና ያለው ቢቀጥል ይሻላል፡፡ ረቂቁ  ነው ሕገመንግሥቱን የተፃረረው፡፡ የብሮድካስቲንግ ሕጉ ተውተፍትፏል፡፡ ሥራ ላይ ማዋልም አልተቻለም፣ የፕሬስ ሕጉና የኢንፎርሜሽን ሕጉ ተደባላልቋል፡፡ አንቀፅ 29ን ያፀደቀ መንግሥት፣ የፕሬስ ሕግ ብሎ እያልፈሰፈሰው ይገኛል፡፡ ለምን ኢሕአዴግ ጥሩ የፕሬስ መሠረትን በመተው ታሪክ ሰርቶ አያልፍም?
- ስንት ሌባና አጭበርባሪ ፕሬስ እንዳለ አንቺ አታውቂም፡፡
- ጥሩ የፕሬስ ሕግም አጭበርባሪ ፕሬስ ይኑር አይልም፡፡
- ሃሳብ እንዲጨመር ውይይት ተደርጎበታል፡፡
- ነበር እዚያ ውይይት ላይ አስፈቅጄ ገብቼ ነበር፡፡
- እናስ?
- እናማ፣ የኪንግጋርተን ጥያቄና መልስ ነው የሚመስለው፡፡ ዋናዎቹ ተከራካሪዎች የሉም፡፡ ጠይቀን እንመልሳለን ነው፡፡ ሕግ እንደዚህ አያወጣም፡፡
- እና አይፅደቅ ነው የምትይው?
- አዎን አይፅደቅ፡፡ አለመፅደቁ ከማንም በላይ ለኢሕአዴግ ይጠቅመዋል፡፡
- እንዴት ነው የሚጠቅመው?
- በዓለም ፊት ለሂስና ለወቀሳ የሚዳርገውን አስተያየት ይዞ አይቀርብም፡፡
- ህምም...
- አየህ አባባ፡፡ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፣ በኢሕአዴግ ስም የሚደረጉ ክርክሮችና የሚወጡ ሕጎች በጥንቃቄ ልታዩዋቸው ይገባል፡፡ እኔ የኢሕአዴግ ቤተሰብ ልጅ ሆኜ ነው የምነግርህ፡፡ የፕሬስ ረቂቅ፣ የኤን.ጂ.ኦ ሕግ፣ የብሮድካስት ረቂቅ ሕግ እያሉ ማውጣት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለኢሕአዴግ አይጠቅመውም፡፡
- ሕግ አያስፈልገንም እያልሽ ነው?
- አያስፈልግም አላልኩም፡፡ ለአገር፣ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት በሚጠቅም መልኩ ማርቀቅና ማፅደቅ እየተቻለ አታጠማዙት ነው ያልኩት፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የማይስማማ አታርቅቁ፣ አታፅድቁ ነው የምለው፡፡
- እና አንቺ በምትይው ታሪክ ይሰራል፡፡
- እንዴታ" ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ሕጎችና ዴሞክራሲያዊ ተቋሞችን የመሰረተ፣ ልማትን ያረጋገጠ የፍትሕ የዴሞክራሲና የልማት መንግሥት መሪ ተብሎ በታሪክ ይፃፍለታል፡፡
- ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡
- ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርስልኝ፡፡
- ራስሽ ጽፈሽ ላኪላቸው፡፡
- አንተ ትልክልኛለህ?
- እኔማ አልክም፡፡ በፅሕፈት ቤታቸው በኩል ላኪው፡፡
- እዚያ ፅሕፈት ቤት ያሉት ሰዎች ነገሩን ይረዱታል ብለህ ነው?
- ደመወዝ የሚከፈላቸውኮ ነገሩን ይረዳሉ ያቀርባሉ ተብሎ ነው፡፡
-  ይቅርታ አድርግልኝ፣ አንዳንዱ ተፃራሪውን ይመስላል፡፡
- አልገባኝም፡፡ ከዚህ ውጭ ለምን ይከፈላቸዋል፡፡ መርሁ ምን ይመስልሻል?
- "ስለማይረዱ ይከፈላቸው!"
 
< Prev   Next >