Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Friday
Jul 04th
Home arrow Sections arrow የበግ ደላላው
የበግ ደላላው Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
Imageበምሕረት አስቻለው

ወደ ሾላ የበግ ተራ ገበያ በመግባት ላይ ሳለን ገበያው መግቢያ አካባቢ ከአንድ ሱቅ ደጃፍ ላይ ቁጭ ብሎ "ፍሬንድ ጠቦት ላማርጥ?" ብሎ ጠየቀን፡፡ እኛም ጠጋ ብለን አነጋገርነው፡፡ ተከስተ ብርሀን አበበ ተወልዶ ያደገው እዚያው ሾለ በግ ተራ አካባቢ እንደሆነ ገለፀልን፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ የበግ ተራ አካባቢን ያዘወትር እንደነበረም አልደበቀም፡፡ ተከስተ ብርሀን አሁንም ከሳምንት እስከ ሳምንት ጊዜውን በግ ለመግዛት ወደ ገበያው የሚሄዱ ገዢዎችን ጠቦት በማጋዛት ያሳልፋል፡፡ "ተወልጄ ያደግኩት እዚሁ አካባቢ በመሆኑ ገበያው ውስጥ ስለሚሸጡ በጐች አይነትና የዋጋ ሁኔታ አውቃለሁ፡፡ በግ ማጋዛትን ሥራዬ ብዬ ከጀመርኩ ስድስት ዓመት ይሆነኛል" ብሏል፡፡

በገበያ ውስጥ ዘወትር በበዓልም ሆነ በአዘቦት ቀን በግ የሚያጋዙ ሃያ የሚሆኑ የበግ ደላሎች ሲኖሩ በበዓል ወቅት ቁጥራቸው ሰማንያ የሚደርስበት አጋጣሚ አለ፡፡ እኛም በግ የማጋዛት ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን ለመመልከት ይዘነው ወደ መሀል ገበያው አመራን፡፡ በርካታ የበግ ነጋዴዎች፣ የበግ ደላሎችና አንዳንድ ገበያተኞች እየደጋገሙ ይጠሩታል፡፡ እዚህ ገበያ ወስጥ ካሉ የበግ ደላሎች ረዥም ጊዜ በሥራው የቆየኸው አንተ ነህ? ስንል ጠየቅነው "አይደለሁም፤ ሀያና ሰላሳ ዓመት የሠሩ የበግ ደላሎች አሉ፡፡ በዚሁ ሥራ ሀብት ያፈሩና ትዳር የመሰረቱም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አሁንም ሥራውን ዘወትር አይስሩ እንጂ በዓመት በዓል ሰሞን ከገበያው አይጠፉም፡፡ ጠቦት ያጋዛሉ" በማለት መልሶልናል፡፡

ተከስተ ብርሀን እንደገለፀው ለበግ ማማረጥ ይህ ነው ተብሎ የተቀመጠ ክፍያ ባለመኖሩ እያንዳንዱ ገበያተኛ ደስ ያለውን ብር በግ ላጋዛው ፣የበግ ደላላ፣ ይሰጣል፡፡ አንዳንዱ በገዛው ጠቦት በመደሰት መቶም ሀምሳም ብር ይሰጣል፡፡ ሁለትና አንድ ብር የሚሰጥም አይጠፋም፡፡ አብዛኛው ሰው የሚሰጠው ግን አስር ወይም አሥራ አምስት ብር ነው፡፡ በግ ለመግዛት ከሚመጣው አብዛኛው የበግ ደላሎችን እርዳታ የማይፈልግ ሲሆን እሱም ጠቦት ለማማረጥ የሚያግባባው ወጣቶችን ነው፡፡

ወደ ገበያው የሄድነው ከበዓል ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ስለነበር አብዛኞቹ የበግ ደላሎች አንድ ግንብ ሥር ሰብሰብ ብለው ተቀምጠው ገበያተኛ ሲጠባበቁ አየን፡፡ ሰዎች በርቀት ወደ ገበያው ሲመጡ በመመልከት የገበያተኛውን የሰውነት ወይም የአለባበስ ሁኔታ በመግለፅ ያ ሰው መያዙን አንዱ የበግ ደላላ ለሌሎቹ ያሳውቅና ሰውዬው ፍቃደኛ ከሆነ ወደ ገበያው ይዞት ይገባል፡፡ ይህን የሚያደርጉት እርስ በርስ ላለመጋጨትና በዚህ ምክንያት ገበያ ላለማጣትም እንደሆነ አስረድቶናል፡፡

ምንም እንኳ የከተማ ልጅ ቢሆንም ተወልዶ ያደገው ሾላ በግ ተራ አካባቢ በመሆኑ የጠቦት አይነቶችን በሚገባ እንደሚያውቅ የሚናገረው ተከስተ ብርሀን አንድ ገበያተኛን ጠቦት ለማማረጥ ከሰላሳ ደቂቃ በላይ እንደማጠፋ ገልጿል፡፡ የአንዳንዱ ገዢ የሚፈልገው ጠቦት ከመግዛት አቅሙ ጋር ያልተገናዘበ መሆንና የአንዳንድ ገዢዎች ምርጫቸውን ወዲያው ወዲያው መቀያየር ደግሞ ከገዢዎቹ ጋር ጠቦት በማማረጥ የሚያጠፋውን ጊዜ ለመወሰን አስገድዶታል፡፡

ቅዳሜ ቅዳሜ ጥሩ ገበያ ያለ ሲሆን በጾም ወቅት፣ የእለት ምግቡን ጨምሮ ሌሎች የእለት ወጪዎችን በመሸፈን ቤቱ በቀን አሥር ብር ይዞ እንደሚገባና በተለያዩ በዓላት ወቅት ደግሞ በቀን እስከ መቶ ብር እንደሚያገኝ ተናግሯል፡፡ በደላላ ሲገዛ የበግ ዋጋ ይጨምራል? "ይህ ስህተት ነው፡፡ እኛ ገዢዎችን ጠቦት ስናማርጥ የተወሰኑ የበግ ነጋዴዎች ጋር ብቻ አይደለም ይዘናቸው የምንሄደው፡፡ በእለቱ ያለውን የጠቦት ገበያ ሁኔታ እንገልፅላቸዋለን፤ ያሉትን የበግ አይነቶችና የዋጋውን ሁኔታም እንነግራቸዋለን፡፡ ከዚያ የእነሱን ፍላጐት እንጠይቃለን፡፡ በዚህ መልኩ ነው ወደ ገበያ ውስጥ ይዘናቸው የምንሄደው፡፡ በተለያየ ወቅት በግ ለመነገድ ወደ ገበያው የሚመጡት ነጋዴዎችም በርካታ በመሆናቸው ከማናቸውም ጋር ያለን ቀረቤታ ተመሳሳይ ነው"

የአካባቢው ኗሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ስላለው የበግ ገበያ ሁኔታ ስለሚያውቁ የበግ ደላሎችን እንደማይጠቀሙ በመጠቆም የሚያውቃቸውን ወይም ዘመዶቹን ጠቦት ቢያጋዛም ክፍያ እንደማይቀበል ይናገራል፡፡ ይህን ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በማንኛውም አጋጣሚ በግ የሚያጋዛውና ሦስት ዓመት ያስቆጠረ ደንበኛ አለው፡፡ ስልክ በመደወል፣ የሚፈልጉትን የበግ ዓይነትና ዋጋ በመግለፅ ብር ልከው በግ የሚያስገዙ ደንበኞች መኖራቸውን ከተከስተ ብርሀን ንግግር ለመረዳት ችለናል፡፡

የአሁኑን የፋሲካ በዓል እንዲሁም በዚህ ዓመት በተከበሩ ሌሎች በዓላት የታየውን የበግ ገበያ ሁኔታ በማስመልከት፣ አዲስ ዓመት ላይ የነበረው የበግ ገበያ የተረጋጋ፣ የገና በዓል ገበያም ደህና እንደነበረ የአሁኑ የፋሲካ በዓል ገበያ ግን ቀዝቃዛ እንደነበር ተናግሯል፡፡ ባለፉት በዓላት አራት መቶ ብር ይሸጥ የነበረ በግ ስምንት መቶ ብር የገባበት ሁኔታ መኖሩንም አልደበቀም፡፡

በግ ካጋዙ በኋላ ተሸክማችሁ ታክሲ ተራ አድርሱ መባል፣ ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ከተዞረ በኋላ ደንበኞች ገንዘብ ሊከፍሉ ወደ ኪሳቸው ሲገቡ የገንዘብ መሰረቅ ወይም ቤት ረስቶ መምጣት የበግ ደላሎች የእለት ከእለት ገጠመኝ ነው፡፡ እሱን ስላጋጠሙት ሁኔታዎች እየነገረን ሳለ አንድ ደንበኛውን ወደ ገበያው ሲገባ ተመለከተውና ይቅርታ ጠይቆን በጥድፊያ ወደ ሰውዬው ሄደ፡፡
 
< Prev   Next >