Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Thursday
Aug 07th
Home arrow Sections arrow ወጣቱ የአምሳለ ፍርድ ቤት ቡድን መሪ
ወጣቱ የአምሳለ ፍርድ ቤት ቡድን መሪ Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
Image
ምትኩ መኮንን
በሰለሞን ጎሹ

ወጣት ምትኩ መኮንን ከሳምንት በፊት ነው ከአሜሪካን ዋሽንግተን የተመለሰው፡፡ በዘንድሮው በፊሊፕ ዓለም አቀፍ የአምሳለ ፍርድ ቤት (moot court) ውድድር ለመሳተፍ ወደ ቦታው ያቀናውን የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፋኩልቲ ልዑክ በመምራት ነው የሄደው፡፡

ምትኩ በመጀመሪያው ብሔራዊ የአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር የፅሁፍ ዘርፍ አሸናፊ ቡድን አባል ነበር፡፡ በሁለተኛው ብሔራዊ ውድድር ደግሞ በፅሁፍም ሆነ በቃል ክርክሩ አሸናፊ የነበረው ቡድን አባል ነው፡፡ በሦስተኛው ብሔራዊ ውድድር ደግሞ ዘንድሮ ሁለተኛ የሆነውን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቡድን አሰልጣኝ ሲሆን አዘጋጅም በመሆን ፕሮግራሙን አስተባብሯል፡፡

"ጊዜው ይሮጣል፡፡ ወጣትነትም እንደዚያው ነው፡፡ ሀገራችን በርካታ ወጣት ሃይል አላት፡፡ በወጣቱ ላይ እምነት መጣል ከጀመረች ቅርብ ጊዜዋ ነው፡፡ የእድሜ እኩዮቼ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው" ብሏል፡፡

በዚህ ዓለም አቀፍ የአምሳለ ፍርድ ቤት ውድድር እስከ አሁን ድረስ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (የአሁኑ አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ በስተቀር ሌላ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተሳታፊ አልነበረም፡፡ ዘንድሮ ግን አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ባህር ዳርና ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አምርተዋል፡፡

እድሉን እንዴት አገኙት? "የውድድሩ አስተባባሪዎች ድረ ገፅ አለ፡፡ በዚያ በኩል ማመልከቻ ትሞላለህ፡፡ ለማመልከቻው ትከፍላለህ፡፡ ለታዳጊ ሀገሮች ዋጋው ይቀንሳል፡፡ ምን ያህል ዩኒቨርሲቲዎች አንድን ሀገር ይወክሉ የሚለውን ለመወሰን የተለያዩ ዓይነት ምዘናዎች ያደርጋሉ፡፡ የእኛ አራት ዩኒቨርሲቲዎች በጠቅላላ ወደ ዋሽንግተን እንዲሄዱ የተደረገው ከዚህ በፊት ብዙ ቡድን ልከን ስለማናውቅና የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ እንዲኖረንና ወደፊት ደረጃውን የጠበቀ ብሔራዊ ውድድር ለማዘጋጀት ትምህርት እንቀስምበታለን ብለን በጠየቅናቸው መሠረት ነው" በማለት ወጣት ምትኩ ይመልሳል፡፡

በውድድሩ ላይ ሀገራት በአንድ እንደ ሁኔታውም ከአንድ በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ይወክሏቸዋል፡፡ የቀሩት በዋሽንግተን ብሔራዊ ውድድር የሚያደርጉትና የሚሸነፉት ቡድኖች ተመልካች ሆነው ውድድሩን ይከታተላሉ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በብሔራዊ ውድድር አሸንፎ ኢትዮጵያን የወከለ ሲሆን ጅማ ሁለተኛ ወጥቷል፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ የላቀ ታሪክ ያለው ሲሆን በተለይም እ.ኤ.አ በ1972 እና በ1974 የውጤት ዓመታት ናቸው፡፡ በፕሮፌሰር ጎሹ ወልዴ የተመራው ቡድን በ1972 በቃል ክርክሩ ሁለተኛ በፅሁፍ ደግሞ አሸናፊ ነበር፡፡ በ1974 ግን በፅሁፍም ሆነ በቃል ክርክሩ አሸናፊ በመሆን አኩሪ ታሪክ ፅፏል፡፡

ከዚህ ልምድ ጥቅም አግኝቷል? ወጣት ምትኩ "ልምድ ጠቃሚ ነው፡፡ ዋነኛው ነገር ግን ዝግጅትህ ነው፡፡ ሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ውድድሩ እንደሚሄዱም እርግጠኞች አልነበሩም፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ችግር ነበረብን፡፡ አዲስ አበባ ከመነሻው ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ በተደረገው ብሔራዊ ውድድርም ሌሎቹ ቡድኖች ተቀራራቢ ፉክክር አድርገዋል" ይላል፡፡

በውድድሩ ላይ ያደገና እያደገ ያለ የሕግ ስርዓት ያላቸው፣ የሲቪል ሕግና የኮመን ሎው የሚከተሉ ሀገራት ተሳትፈዋል፡፡ ለልምድ ልውውጥም ውድድሩ ጠቃሚ ነው፡፡ የፍርድ አጠቃቀስ፣ የዓለም አቀፍ ሕግ አተገባበር፣ ወዘተ. ላይ በርካታ ልምድ መቅሰም እንደሚቻል ወጣት ምትኩ አስረድቷል፡፡ "ዳኞቹ ራሱ ከዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመጡ በመሆናቸው የሚጠይቁት ጥያቄና በኋላም የሚሰጡት ማብራሪያ የስልጠና ያህል ዋጋ ነበረው" ሲልም ያክላል፡፡

በአምናው ውድድር አውስትራሊያና አሜሪካ ለፍፃሜ ደርሰው አውስትራሊያ ያሸነፈች ስትሆን ዘንድሮም ሁለቱ ዩኒቨርሰቲዎች ለፍፃሜ ደርሰው አሜሪካ ልታሸንፍ ችላለች፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ፉክክር ምትኩ ተመልካቹ ሲከታተልና ሲደግፍ ነበር፡፡ በእለቱ የአሜሪካ ጠበቆች ማኅበር ስብሰባውን ስለሚያደርግ ብዙ ዝነኛ ጠበቆች እንደነበሩና ብዙዎቹ ተሳታፊ ዩኒቨርሲቲዎች ከሁለቱ በመማር በቀጣይ ውድድሮች ለፍፃሜ ለመድረስ እንዳቀዱ ወጣት ምትኩ አመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሕግ ስርዓቱን እያሻሻለች ትገኛለች፡፡ ተወዳዳሪዎቹ፣ ተሳታፊ ተማሪዎችና አሰልጣኞች ከዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ ለስርዓቱ መዳበር አስተዋፆ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

"በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አምሳለ ፍርድ ቤት ራሱን የቻለ የትምህርት ዓይነት ሆኗል፡፡ክህሎትና ተግባራዊ ልምድ ማግኛ ነው፡፡ ሥርዓታችን ከዓለም ያደገ የሥነ ሥርዓት ያላቸው ሀገሮች ጋር እንዲቀራረብ፣ ሀገራችን የምታፈራቸው ተማሪዎች ከሌላ ሀገር ተማሪዎች ጋር ያላቸውን ልዩነት ማየት አለባቸው፡፡ እኛ ጋ የሌሉ ብዙ በጎ ነገሮች አሉ፡፡ በቀጥታ ኮርጀን ወይም ገልብጠን ባናመጣም ከእኛ ልማድ፣ ባህልና ሕግ እንዲሁም ተግባራዊ ተሞክሮ ጋር የሚሄዱ ደንብ፣ ሕግና መርሆችን በማምጣት የሥርዓታችን አካል እንዲሆኑ መጣራችን አይቀርም" ሲል ወጣት ምትኩ ሊኖራቸው የሚችለውን አስተዋፅኦ ገልጿል፡፡

ለሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወዳዳሪ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሆነበትን ምክንያት የጅማ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ተማሪ ተኮር በመሆኑና ያለ ብዙ ቢሮክራሲ ስለሚተባበር ነው፡፡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ስፖንሰር ሲያገኙ ጅማን ዋሽንግተን እንዲሄድ ስፖንሰር ያደረገው የለም፡፡ ትራንስፖርትና የኪስ ወጭ የቻለው የግቢው አስተዳደር ስለሆነ ምሥጋና እንደሚገባው ወጣት ምትኩ አሳስቧል፡፡
 
< Prev   Next >