Lost Password? No account yet? Register
  • Increase font size
  • Decrease font size
  • Default font size
  • default color
  • red color
  • green color

Reporter - Amharic Version     

Sunday
May 18th
Home arrow Sections arrow የኬንያ ፓርቲዎች ለመራጮች...
የኬንያ ፓርቲዎች ለመራጮች... Print E-mail
Wednesday, 30 April 2008
የኬንያ ፓርቲዎች ለመራጮች ጉቦ መስጠታቸው ታወቀ

በቅርቡ በኬንያ በተካሄደው የኘሬዚደንታዊ ምርጫ ውድድር ወቅት የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመራጮች ጉቦ ይሰጡ እንደነበረ በኬንያ የተደረገ ጥናት አመለከተ፡፡

የፓርቲዎች የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ጥናት ያደረገው በኬንያ የሚገኝ "ኳሊሽን ፎር አካውንቴብል ፓርቲ ፋይናንስ" የተባለው ተቋም በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት በኬንያ የሚገኙ ፓርቲዎች አርባ ሚሊዮን ዶላር ገደማ ለመራጮች ጉቦ ሰጥተዋል፡፡

በጥናቱ መሠረት የኘሬዚዳንት ሞዋይ ኪባኪ "ናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ" እና የራይላ ኦዲንጋ "ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ሙቭመንት ፓርቲ" የግቦ መስጠት ተግባር ተዋናይ ነበሩ፡፡ የኪባኪ ፓርቲ ከመንግሥት ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱንና ገንዘቡንም ለመራጮች በግቦ መልክ ማከፋፈሉን ጥናቱ አስታውቋል፡፡

የጥናት ተቋሙ ሊቀመንበር ቻርለስ ኦቲኖ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጫቸውን እንዲሁም የገንዘብ ወጪያቸውን እንዲያሳውቁ የሚያደርግ ህግ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ ለዚህም የኘሬዚዳንቱ ፓርቲ ከሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱን በዋቢነት በመጥቀስ፤ "የፓርቲዎች የገንዘብ ምንጭና ወጪ በግልፅ መታወቅ አለበት" ብለዋል፡፡

በጥናቱ መሠረት የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋም ከደንበኞቹ የሰበሰበውን ስምንት ሚሊየን ዶላር ለኘሬዚዳንቱ ፓርቲ በድጋፍ መልክ አስረክቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ተቋማት ከተገልጋዮች ከተመን በላይ ክፍያ በመሰብሰብ ለምርጫ ቅስቀሳ አውለዋል፡፡

ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር ይመች ዘንድ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጫቸውንና ገቢያቸውን እንዲያሳውቁ፣ የፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎችም እንዲሁ የሀብት መጠናቸውን እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ህግ እንዲወጣ ተጠይቋል፡፡

በኬንያ በተካሄደው የኘሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር አንድ ሺ አምስት መቶ ሰዎች ሲገደሉ ከስድስት መቶ ሺ በላይ ዜጐች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡

የተመድ ወታደሮች ለኮንጐ አማፅያን የጦር መሳሪያ ሰጡ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ዴሞክራቲክ ኮንጐ አማፅያን የጦር መሳሪያ በመስጠት ወርቅና የዝሆን ጥርስ ይቀበሉ ነበር ሲል የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ፡፡

በዘገባው መሰረት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ የተሰማራው የተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል አባላት በአካባቢው ከሚገኙ የአማፂ ወታደሮች ጋር ህገወጥ የመሳሪያ ልውውጥ እያደረጉ እንደነበረ ተጠቁሟል፡፡

በዘገባው የህንድና የፓኪስታን የድርጅቱ ወታደሮች ከአማፅያኑ ወርቅና የዝሆን ጥርስ በመቀበል የጦር መሳሪያ ያስታጥቁ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የድርጅቱ የከፍተኛ አመራር አካላት የማጣራት ተግባር መጀመራቸው ታውቋል፡፡

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐ የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል በቁጥር በከፍተኛነቱ ተጠቃሽ ሲሆን አስራ ሰባት ሺ ወታደሮች እንዳሉት ተገልጿል፡፡

የሙጋቤ ፓርቲ ለፓርላማ አባላት ውድድር መሸነፉ ተገለፀ

በዚምባቡዌው የኘሬዚደንት የሮበርት ሙጋቤ ፓርቲ ለፓርላማ አባላት በተካሄደው ውድድር መሸነፉን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡

በዘገባው መሰረት ከአንድ ወር በፊት በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ ስርዓት ውጤት የገዢው ፓርቲ መሸነፉ የታወቀ ሲሆን ፓርቲው ውጤቱን አለመቀበሉ ታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት የድምፅ ቆጠራው ለሁለተኛ ጊዜ ተካሄዶ የሙጋቤ ፓርቲ መሸነፉ ተገልጿል፡፡

የዳግም ቆጠራው በተካሄደባቸው ሀያ ሦስት የፓርላማ መቀመጫ የውድድር ቦታዎች በአሥራ ስምንቱ ውጤቱ አለመቀየሩ ታውቋል፡፡ የኘሬዚዳንት መጋቤ "ዛኑ -ፒኤፍ" ፓርቲ በፓርላማው የበላይነት ለማግኘት ከዘጠኝ በላይ ተጨማሪ መቀመጫ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡ ፓርቲው ይህንን ውጤት አለማግኘቱን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በዘገባው መሠረት የኘሬዚዳንት መጋቤ ፓርቲ እ.ኤ.አ ከ198ዐ ጀምሮ በፓርላማው ውስጥ የነበረውን የበላይነት አጥቷል፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑ የዳግም ቆጠራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ውጤቱ እንደሚገለፅ አስታውቋል፡፡
 
< Prev   Next >