| ኩማ ወደ ማዘጋጃ ቤቱ እያቀኑ ነው |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
ኢሕአዴግ ከሳምንታት በፊት የተደረገውን የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ማሸነፉን ገልጿል፡፡ ይህም ያልተጠበቀ ውጤት አልነበረም፡፡ በ1997 ከተደረገው ምርጫ፣ “የሰማይና የመሬት ያህል” የተሳትፎው ቅዝቃዜ ልዩነት ባሳየበት ሁኔታ ኢህአዴግ ብቻውን ሮጦ ብቻውን ማሸነፉ በማንም ዘንድ በእርግጠኛነት ያልተገመተ አልነበረም፡፡ለምርጫ ቀርበዋል የተባሉት ተወዳዳሪዎች በሙሉ፣ ካላቸው ሕዝባዊ ተቀባይነትና ዕውቅና አኳያ “ኢሕአዴግ ብቻውን ሮጧል” ከመባል የሚያስቀሩት ባለመሆናቸው ውጤቱ ውድድሩን ቀድሞት እንደነበር አያከራክርም፡፡ ከጋዜጣው ሪፖርተር ከዚያ ይልቅ በ1997 ምርጫ ኢሕአዴግ በተለይ ሙሉ በሙሉ በተሸነፈበትና አሁን ደግሞ በዚያው መጠን ባሸነፈበት አዲስ አበባ ለከንቲባነት ማንን ያወጣል የሚለው ጥያቄ ይብዛም ይነስ የተለያየ ግምት ሊያሳድር ስለሚችል ያከራክር ይሆናል፡፡ አዲስ አበባ በቻርተርድ ከተማነቷና ከርዕሰ ከተማነቷ አኳያ ብቻ ሳይሆን በገቢዋና በሥሩዋ ከምታስተዳድረው ሃብት አንፃር እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ይዛለች፡፡ በዚህ አኳያ ለአዲስ አበባ ከፍተኛ የአስተዳደር ቦታ የሚመረጠው ሰው ማንነት በግምት፣ ወይም ኢሕአዴግ እንደቀድሞው እንደሚያደርገው የብሔረሰብ ውክልናን ብቻ ተመርኩዞ የሚሰጥ ምደባ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ መለኪያ የግድ ያስፈልጋል፤ ከተባለም በተጨማሪ ከተማን የማስተዳደር አቅም ያካበተ ያለው ከንቲባ እንዲሆን የሕዝቡ ፍላጎት ነው፡፡ የኢሕአዴግን ፖሊሲ ከማስፈፀም ተግባር ባሻገር ሁኔታዎችን የመገንዘብ አቅምና የግሉ እንቅስቃሴ ከነዋሪው ጋር ያለው መቀራረብ አዲስ አበባን ለማስተዳደር የሚመረጥ ሰው መለኪያ እንዲሆን እንመኛለን፡፡ በአሁኑ የምርጫ ውጤት ኢሕአዴግ የአዲስ አበባን አስተዳደር ይረከባል፡፡ በዚያው መጠን ከፍተኛ ካድሬዎችን በምርጫው ያስገባው ኢሕአዴግ አቶ ኩማ ደመቅሳን ወደ ከንቲባነት እንደሚያመጣቸው ይገመታል፡፡ የአቶ ኩማን ሹመት ለመገመት የሚያስችሉት ምክንያቶች በኢሕአዴግም ሆነ በኦሕዴድ ውስጥ ከፍተኛው የፓርቲ ሰው መሆናቸው፣ አብረዋቸው ወደ ምርጫው ከገቡት ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የፓርቲ ሰዎች በፓርቲው አመራርና በሚኒስትርነት የቢሮ ሥራ ነባር በመሆናቸው ነው፡፡ አቶ ኩማ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ከጥቂት ቀናት በስተቀር በከፍተኛ ስልጣን ላይ ቆይተዋል፡፡ በአገር አስተዳደር ሚኒስትርነት በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትነት ሰርተዋል፡፡ በ1993 የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴን መሰንጠቅ ተከትሎ፣ አቶ ኩማ የያዙት መስመር “አንጃ” ተብሎ ከሚጠራው ጋር ስለመሰለፋቸው ከኦሕዴድ ሊቀመንበርነት ወርደው ተራ አባል፣ ከፕሬዚዳንትነታቸው ወርደው በስደተኛ የመምሪያ ሰራተኛ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ርሳቸው “ፕሬዚዳንትም ሆንኩ ዘበኛ ምንም ማለት አይደለም፡፡ የድርጅትን አላማ ከሥልጣን ደረጃ ጋር አላያይዝም” እንዳሉት በተመደቡበት ቦታ ሥራቸውን እየሰሩ ወደ አቅም ግንባታ ሚኒስትር ዴኤታነት አሁንም በመከላከያ ሚኒስትርነት ሹመት ለመያዝ በቅተዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚም ሆነዋል፡፡ አቶ ኩማ ይህን ሁሉ ልምድ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የድርጅታቸውን ፖሊሲ ከማስፈፀም አኳያ ብቻ ሳይሆን የግላቸው ስብዕናና አቅም ከሚፈተንበት ወንበር ላይ ሊቀመጡ ነው፡፡ በሙያ የሥራ መደቦች ጭምር በብሔር ተዋጽኦ ምደባ የሚያምነውና የሚያስደስተው፣ የሥራ ድልድሉንም በዚህ ረገድ በማድረግ የሚታወቀው ኢሕአዴግ፣ እስካሁን ከብአዴን፣ ከሕወሓትና ከኢሕዴድ ሥራ አስፈፃሚዎች ተመርጠው አዲስ አበባን በከንቲባነት እንዲመሩ አደርጓል፡፡ አቶ ኩማ ወደ ከንቲባነት ቢሮ ከዘለቁ ኦሕዴድ ለሁለተኛ ጊዜ አዲስ አበባን ሲያስተዳድር የኢሕአዴግ አንደኛው ድርጅት ደቡብ ሕዝቦች እስካሁን ተራ አልደረሰውም ማለት ነው፡፡ አቶ ኩማ በኦሮሚያ ለሚመራው ድርጅት ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሳለ የጥቅም ግንኙነት ያላትን አዲስ አበባን ቢመሩ የጥቅም ግጭት አይፈጠርምን? የሚል ጥያቄ በቅድሚያ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ወደ አዲስ አበባ መምጣት በኦሮሚያና በአዲስ አፈበባ መካከል ያለውን የመሬትና የሌሎች በውዝፍ የተቀመጡ የጥቅምና የይገባኛል ጥያቄዎች፣ ለመፍታት ይረዳ እንደሆነ ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ የሥራ አስፈፃሚ፣ ሆነው የወሰኑትን በአዲስ አበባ ከንቲባ ወንበራቸው ሲቀመጡ ሊከራከሩበትና ጥያቄ ሊያቀርቡበት ይችላሉ ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ የአዲስ አበባን ጥቅም ለማስከበር የኦሮሚያን ጥቅም ማሰብ ሊኖርባቸው ነው፡፡ ይህም አቶ ኩማን “የመንቶች እናት ተንጋላ ትሙት” እንደሚባለው ያደርጋቸዋል፡፡ የፌደራል አወቃቀርን በሚከተሉ ይልቁንም እንደኛ አገር የተጠናቀቀ የወሰን ክልል የሌላቸው ክልሎች፣ ሁሉም ጥቅሙን ለማስከበር ይመቸኛል በሚለው መንገድ የተለያዩ ጥያቄዎች፣ ውይይቶች፣ አቋሞች ይወስዳል፡፡ ለአቶ ኩማ ግን እንዲህ አይነቱ አሰራር እንደማይመቻቸው መገመት ይቻላል፡፡ ርሳቸው የኢሕአዴግ ፖሊሲ ሁሉንም ያሳምረዋል ብለው ተመችቶኛል ቢሉ እንኳ፣ ከአዲስ አበባ ወይም ከኦሮሚያ በአንደኛው በኩል መነቀፍና መተቸት አይቀርላቸውም፡፡ ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ በአስተዳደሩ መሬት ተሰጥቷቸው ቤት ለመገንባት የተዘጋጁትን የኦሮሚያ ክልል ክልሉ የእኔ ነው፣ ብሎ እግድ ጥሎ ግለሰቦች ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ሲዳረጉ፣ የአገር ሃብት የሆኑት ሲሚንቶን የመሳሰሉ የግንባታ እቃዎች ሲበላሹ ታይተዋል፡፡ የባለአደራ አስተዳደሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጣልቃ እንዲገቡ ከመወትወት ያለፈ ስልጣን ሳይኖረው ቆይቷል፡፡ ችግሩን አስመልክቶ የባለአደራው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ከመግለጽ በቀር ለችግሩ እልባት ለመስጠት አቅም አንሶታል፡፡ ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጭምር የሚያውቀውን የሁለቱን ክልሎች ችግር፣ አቶ ኩማ ለአዲስ አበባ ጥቅም ቆመው ለማስፈፀም የኦሕዴድ ሥራ አስፈፃሚነታቸው የሚረዳቸው አይመስልም፡፡ አቶ አሊ አብዶ፣ አዲስ አበባን በመሩበት ወቅት የመሬት ወሰን ጥያቄ ችግር ጎልቶ አለመታየቱ፣ ርሳቸው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ በመሆናቸው ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን የጥቅም ጥያቄ መፍትሄ ሰጥተውት ሳይሆን፣ በጊዜው የአዲስ አበባ የልማት እንቅስቃሴ ማገድ የኢሕአዴግ “ፖሊሲ” ስለሆነ የሚያገናኛቸው ምክንያት ባለመኖሩ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ልማት እንዲፋጠን ኢሕአዴግ እንደ አመራር የሰጠው አቅጣጫ ባለመኖሩ፣ ለጠፋው ጥፋት ሁሉ የአቶ አሊ አብዶ ድክመት እንደሆነ ሁሉ ሲወቀሱበት ቆይተዋል፡፡ የኢሕአዴግ በአዲስ አበባ የልማት አቋም ላይ የተለወጠው የሕወሓትን ማዕከላዊ ኮሚቴ መሰንጠቅ በኋላ የያዘው አቋም ነው፡፡ አቶ አርከበ እቁባይ ወደ ከንቲባነት ከመጡ በኋላ በርካታ የልማት ሥራዎች ተጀመሩ፡፡ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ተዘረጉ፣ አሁን የሚታዩት የመንገዶችና የመኖሪያ ቤቶች መስፋፋት በዚያን ጊዜ የተጀመረ ነው ቢባል ስህተት አይመስልም፡፡ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ ላይ ያለው አዝጋሚ የልማት አቋም፣ በድንገት መለወጥ አቶ መለስ ዜናዊ የመንግሥቱን አመራር በሙሉ ኃላፊነትና ሥልጣን መምራት ከጀመሩ በኋላ በመሆኑ አቶ ኩማም ከከንቲባነት ከተመደቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከታተሉት የልማት እንቅስቃሴ አስፈፃሚ መሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳ የአቶ መለስ ክትትል ቢኖርበትም የአቶ ኩማ በግል ችግሮችን የመፍታትና ከሕዝብ ጋር የመቀላቀል አቅም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ አቶ ኩማ ወደ አዲስ አበባ ከንቲባነት ሲመጡ ቀድመው የነበሩትና በውዝፍ የተላለፉ በርካታ ችግሮችም እንደሚቆዩዋቸው የታወቀ ነው፡፡ በአቶ ተፈራ ዋልዋና በአቶ አሊ አብዶ ከንቲባነት ወቅት የነበረው የዘገምተኛ አስተዳደር ውጤት፣ በአቶ አርከበ ወቅት የታየው መሬትን እንደፈለጉና የሊዝ ኮሚቴ ሳያውቀው ጭምር በአንድና በሁለት ሰዎች ፊርማ ለሚቀርቧቸው ሰዎች የመስጠት አሰራር የፈጠረው ጥርጣሬና ጥላቻ በራስ ፈቃድ አንድን ቦታ ለሁለት ሰዎች በመስጠት እስከማጋደል የተደረሰበት አሰራር የሚያቆየው የሕዝብ ስጋት ይጠብቃቸዋል፡፡ በተጨማሪ በአቶ አርከበ የሚታመን ምክንያት ሳይኖር፣ ፍትሕ በጎደለውና በጥላቻ ስሜት የተከናወነው የሰራተኛ ቅነሳ በአስተዳደሩ የፈጠረው የባለሙያ እጥረት፣ በባለአደራው ዘመን የተንሰራፋው ገደብ ያጣው የሙስና አሰራር ከመጀመሪያው እለት ጀምሮ የሚፈታተኑዋቸው ችግሮች እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ እነዚህ የጠቃቀስናቸው እንደማሳያ እንዲሆኑ እንጂ አዲስ አበባ በአሁኑ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ልማትና በተወሳሰበ ችግር ውስጥ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ሁሉም ነገር በኢሕአዴግ አመራር፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እይታና አመራር ዙሪያ ቢሆንም የአቶ ኩማን የማስፈፀም ችግሮች የሚያቃልሉበት መንገድ ርግማን ወይም ምስጋና ያተርፍላቸዋል፡፡ አቶ ኩማ በአዲስ አበባ በማስተዳደር የሙስናን ዘርማንዘር የሆኑትን አድልዎን፣ በጥቅም መደለልን ወገንተኝነትን ለመዋጋት የቱን ያህል እንደተዘጋጁ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም አዋጪው መንገድ እነዚህን ለመዋጋት ቆራጥና ዝግጁ መሆን ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ አደጋው ይተርፋቸዋል፡፡ የሕዝብ እንባ እርሳቸው ላይ ይፈሳል፡፡ የሚፋረዳቸውም በሩቅ ርቀት ያሉ ዞንና ወረዳዎች ሳይሆኑ ከጉርብትና ጀምሮ ዙሪያ ገባቸውን የከበባቸውና ቅርባቸው ያለው የአዲስ አበባ ነዋሪ በመሆኑ የሚሰሙት የዋለ ያደረ ቅሬታ አይሆንም፡፡ እንደ ዋና ጉዳይ ሊጠቀስ የሚገባው ከሕዝቡ ጋር ያላቸው ቅርበትና የሚገናኙበትን መንገድ ማጠናከር እንዳለባቸው ከልብ የሚያምኑበት ጉዳይ መሆኑ ላይ ነው፡፡ እንደ አቶ ተፈራና አሊ አብዶ በራቸውን ለሕዝብና ለመረጃ የሚቀረቅሩ ሳይሆኑ እንደ አቶ አርከበም ግማሽ ድረስ ሰርተውበት በኋላ እንደተዉት (ተገምግመውበት መሆኑን እናውቃለን) ዓይነት ሳይሆን፣ እንደ ከንቲባ ብርሃነ በራቸውን ለጋዜጠኞች ክፍት አድርገው ሕዝቡን በቀጥታ የማነጋገር ልማድ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ወይስ የፈለጉትን ለመናገር፣ የሚፈልጉት ከንቲባ እንዲናገሩ ፈቃድ ይፈልጋሉ? ይህ ብቻ አይደለም፤ በተለያዩ መድረኮች ሕዝቡን ማግኘት፣ ችግሩን አቤት ሊላቸው ሲፈልግ በአጃቢዎች ከማስገፋት ይልቅ ማቅረብ፣ በባለመደገፊያ ምቹ ወንበራቸው ሆነው መረጃዎችን ከመጠበቅ ይልቅ በስራቸው የሚገኙትን ቢሮዎችና ክፍለ ከተሞች በአካል እየሄዱ መቆጣጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አለበለዚያ አቶ ኩማ በዚህ ዘመን ከንቲባ ሆኖ በዚህ ዘመን ተሻረ የሚል ስም ብቻ ይዘው ይቀራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ወደፊት በሚመጡት ተወላጆቻቸው ጭምር የሚያስተቻቸው ይሆናል፡፡ አቶ ኩማ የከንቲባነቱን ወንበር መያዛቸው ከታወቀ በኋላ በርካታ ደጅ ጥናቶች በርካታ ስልኮች (ከሚኒስትሮች ጭምር) በርካታ ባለሃብቶች ፋታ አይሰጧቸውም፡፡ በአገራችን የሹመት ልማድም እነዚህ ሁሉ እንደሚከተሉ ተሿሚውም ያውቃል፡፡ በዚያ ልክ በርካታ ድሆች፣ ለፍቶ አዳሪዎች፣ ፍትሕ እንዲሰጡዋቸው መልካም አስተዳደር እንዲያሰፍኑላቸው አይናቸውን ይሰኩባቸዋል፡፡ በሙስና እንዳይጎዱ በከተማቸው ሰርተው የመኖር መብታቸው እንዳይገፉ ይጠብቋቸው ዘንድ ተስፋ ያደርጉባቸዋል፡፡ እነዚህን ፈተናዎች እንዴት እንደሚወጡት እንቅልፍ የሚነሳ ጭንቀት ውስጥ ሊጥላቸው ይገባል፡፡ - በረሃ እያለን የምንኖረው ከአርሶ አደሩ ጋር ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከገባን በኋላ ከብዙ ሰዎች ጋር አንገናኝም፡፡ በተለይም ስልጣን ላይ ከወጣሁ በኋላ ከሰዎች ጋር አልገናኝም፡፡ ግን እምነቴና አመለካከቴ ሆኖ አይደለም፡፡ ኃላፊነቱና ሥልጣኑ በጥበቃም አንፃር ነፃ ሆኖ እንደ ልብ ከሰው ጋር ለመገናኘት ጫና ያደርጋል፡፡ በግሌ እንዲህ ያለው ነገር ጥሩ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም ለሪፖርተር ጋዜጣ ቃለ ምልልስሩ ስልጣን ላይ ሲኮን ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ ብዙ አብሮ የሚጨፍር ኃይል ይበዛል፡፡ ከሥልጣን የመውረድ ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ይርቃል፡፡ ይህ መስተካከል ያለበት የተዛባ አመለካከት ይመስለኛል፡፡ ሰው እንደ ሰውነቱ መመዘን አለበት፡፡ ሁሌ ስልጣን ላለው መስገድ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በፕሬዚዳንትነት ዘመኔ ይቀርቡኝ የነበሩ እርቀውኝ ነበር፡፡ ማሰብ የሚችሉ ያልሸሸጉም አስተዋይ ሰዎች አይቻለሁ፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |