| “ሐብሊ በጥገኛ አመራርና ባለሃብቶች... |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
|
“ሐብሊ በጥገኛ አመራርና ባለሃብቶች የተተበተበ በመሆኑ ለውጥ አያመጣም”
አቶ አብዲ ሰብሪ የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ሃዲድ) ሊቀመንበር አቶ አብዲ ሰብሪ በሃረር ሚለንየም የስፖርት በዓል በአዲስ አበባ የሐረርን ክልል ተጠሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ሃዲድ) ሊቀመንበር ናቸው፡፡ አቶ አብዲ አዲሱ ፓርቲያቸው በተቃዋሚነት ያለውን እንቅስቃሴና በሃረሪ ክልል ባለው አጠቃላይ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሁኔታ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- ከሐረር ብሔራዊ ሊግ (ሃብሊ) ወጥታችሁ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆናችሁ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተስማምታችኋል የሚባል ነገር አለ፣ እውነት ነው? አቶ አብዲ፡- በፍፁም፡፡ ከእውነት የራቀና መሰረት የሌለው አሉባልታ ነው፡፡ እስከ አሁን ፓርቲያችን እውቅና ካገኘ ጊዜ ጀምሮ ከሃብሊ ጋር ምንም ዓይነት ድርድር አላደረገም፡፡ ሃብሊ ከአሁኑ ቀደም በራሱ በነበረበት ችግር አንዱ በሌላው የሚኮነንበት ጊዜ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ያሉትን አባላቶች ጥገኛ ባለሃብቶች እያለ ሐረሪ ያለው ደግሞ ለገዢው ፓርቲ ኪራይ ሰብሳቢ እያለ የሚኮንንበት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ በዛ ዙሪያ ላይ የራሳቸውን ችግር የፈቱበት ሁኔታ ነው እንጂ ከእኛ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ሃዲድ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ አባሎች ሓብሊን እየሸሹ ወደ እኛ እየመጡ ነው፡፡ ከእነሱ ጋር ተስማምተናል በማለት የሚነዙት ኘሮፖጋንዳ ይህንን ህዝብ ለማቆም ነው፡፡ የእኛን ሥራ ሆን ብለው ለማበላሸት ነው፡፡ ህዝባችንን ከእኛ ጋር ለማጋጨት ነው፡፡ ህዝቡ እየጠየቀን ያለውም ይሄንን ነው፡፡ እንታገላለን ብላችሁ ከእናንተ ጋር ትግል ውስጥ ገብተናል፡፡ እናንተ ግን ከእኛ ጋር ሳትወያዩ ተስማምታችኋል እያለን ነው፡፡ እኛ ደግሞ ህዝባችንና አባሎቻችን ሳናማክር የምናደርገው ነገር አይኖርም፡፡ ሪፖርተር፡- አብራችሁ ብትሰሩ ችግሩ ምንድነው? የተለየ ነገር አላችሁ? ለምሳሌ ከነሱ ኘሮግራም የሚቃረንና የማያስማማ ነገር አላችሁ፤ አቶ አብዲ፡- እኛ የራሳችን የሆነ ኘሮግራምና አላማ አለን፡፡ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ከነሱ የተለየ የምንለው እኛ ልማታዊ አስተሳሰብና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተከትለን ህዝቦች በመልካም አስተዳደር፣ በፍትህ ዙሪያ እንዲሁም በልማት ፍትሃዊ ክፍፍል እንዲኖር ኘሮግራሞች ቀርፀን ስትራቴጂ አስቀምጠን እየሰራን መሆናችን ነው፡፡ እውቅና ካገኘን ጊዜ ጀምሮ ጠቅላላ ጉባዔ ለመሰብሰብ የፍፃሜ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ በሐረሪ፣ በአዲስ አበባ እንዲሁም በድሬዳዋ ቅርንጫፎችን ከፍተን ያለንን ኘሮግራም በማስተዋወቅ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሪፖርተር፡- አብዮታዊ ዲሞክራሲ የምትከተሉ ከሆነ ከገዢው ፓርቲ ምን የተለየ ዓላማ አላችሁ? አቶ አብዲ፡- እኛ ከእነሱ የምንለየው በህዝብ ላይ ባለን አመለካከት ነው፡፡ እነሱ ህዝብ ሲሉ በአካባቢው ያሉት የተወሰኑ የሥራ አስፈፃሚዎች አባላትና ደጋፊዎቻቸው ማለት ነው፡፡ እኛ ህዝብ ስንል የተጨቆነውን የሃረሪ ህዝብ ነው፣ ምንም ዓይነት መከፋፈል ሳይኖር፣ በአሁኑ ጊዜ በሦስት/አራት ቦታ ተከፍለዋል፡፡ ስለዚህ እኛ አንድነት ይኑር ነው የምንለው፡፡ አንድነት የምናመጣው ግን ሁሉንም ህዝብ አንድ አድርገን ማንቀሳቀስ ስንችል ነው፡፡ ጠ/ሚ መለስ “ሃረሪ ላይ ጭላንጭል እንጂ ብርሃን አይታይም” ብለዋል፡፡ ያንን ብርሃን እንዲታይ ከህዝቡ ጋር እንሰራለን፡፡ ሪፖርተር፡- ሃረር በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ክልል ነች፡፡ ፓርቲያችሁ ከሐረሪ (አደሬ) ውጭ ያሉት ብሔር ብሔረሰቦችን ያስተናግዳል? አቶ አብዲ፡- ዲሞክራሲያዊና ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው የማንኛውም ብሔረሰብ አባል ከእኛ ጋር በአባልነትም በከፍተኛ አመራር ደረጃም ፎርማሊቲውን ካሟላና መተዳደሪያ ደንባችን ከተቀበለ ከእኛ ጋር መሥራት ይችላል፡፡ እውቅና ለመውሰድ በክልሉ የጀመርነው እንቅስቃሴ ፊርማ በምናሰባስብበት ጊዜ ኦሮሞው፣ ሱማሌው፣ ጉራጌው፣ ሃረሪው ፈርሞልናል፡፡ ስለዚህ ለድርጅቱ መቆም ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ሪፖርተር፡- ከሃብሊ ጋር አብራችሁ የማትሰሩበት ምክንያት ምንድነው? የኘሮግራም ልዩነት አላችሁ? አቶ አብዲ፡- ከኃብሊ ጋር መሥራት ያልቻልንበት ጠላቶች ሆነን አይደለንም፡፡ ኃብሊ ዴሞክራት ከሆነ በማንኛውም ሰዓት በጋራ መሥራት እንችላለን፡፡ የኃብሊ ትልቁ ችግሩ ግን ድርጅቱ ለውጥ ቢያደርግም ጥገናዊ ለውጥ እንጂ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ አልቻለም፡፡ ዋና መሰረታዊ ልዩነታችንም የድርጅቱ ኘሮግራም ወረቀት ላይ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ተግባር ሲገባ ነው፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችም ቢሆኑ ከድርጅቱ ዓላማ ውጭ እየሰሩ ነው፡፡ የሁላችንም ኘሮግራም አብዮታዊ ዲሞክራሲን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ልዩነታችን አመሰራረታችን ነው፡፡ የእኛ ዓላማን መሰረት ያደረገና ትክክለኛ አቅጣጫን የተከተለ ነው፡፡ የሃብሊን አመሰራረት ስንወስድ፣ ኢህአዴግ በገባ በመጀመሪያ ወቅት ከየዕድሮቹ ሁለት ሁለት ተወክለው ነው የተመሰረተው፡፡ በዓላማ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ሪፖርተር፡- የአፈፃፀም ልዩነት ብቻ ከሆነ ችግሮቻችሁ በድርጅቱ ውስጥ ገብታችሁ ማስተካከል አትችሉም? አቶ አብዲ፡- እኛ ድርጅቱ ውስጥ የነበርን ሰዎች ነን፡፡ አላፈናፍን ብሎን ነው ጥለን የወጣነው፡፡ ኃብሊ ከጥገኛ አመራርና ከጥገኛ ባለሃብቶች የተያያዘ በመሆኑ ምንም ለውጥ ማምጣት አይችልም፡፡ ድርጅቱ በአጠቃላይ ከጥገኝነት ያልተላቀቀ፣ ጥቂት ባለሃብቶች የሚመሩትና ከፍተኛ አመራሮችም ከእነዚህ ባለሃብቶች ጋር ግላዊ ጥቅማቸውን አረጋግጠው የሚገኙበት ነው፡፡ እነሱ በሄዱበት መንገድ እስካልሄድን ድረስ ለውጥ እናመጣለን፡፡ በመጨረሻ የወሰነው እኛ ማስተካከል ያለብን ኃብሊን ነው ወይስ የሃረሪ ህዝብ ነው? ብለን የሃረሪ መሆኑን አምነን ነው፡፡ በድርጅቱ ውስጥ በዝምድናና በቡድን ነው የተሰገሰጉት፡፡ አንድ ሰው ፎርማሊቲውን አሟልቶ አባል መሆኑ ሳይታወቅ በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ተቀምጦ ታገኘዋለህ፡፡ ስለዚህ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተገን አድርገው ነገር ግን የስርዓቱ ግልባጭ ነው የሚሰሩት፡፡ የሥራ ዕድገት፣ የውጭ ዕድልና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ተጠቃሚ የሚሆኑ ከአመራሮቹ ጋር ከፍተኛ ግንኙነት ያላቸው ብቻ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የሃረሪ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቱ ተጠቃሚ እንደሆነ በተለያዩ የመንግሥት ሚዲያዎች እንሰማለን፣ ውሸት ነው ማለት ነው? አቶ አብዲ፡- ደርግ ከወደቀበት ጀምሮ ከኦህዴድ/ኢህአዴግ ጋር አጋር በመሆን መንግሥት መስርተን ክልሉ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ አለ፡፡ በህገ መንግሥቱ በተሰጠው መብት ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻለም፡፡ ለምሳሌ በቋንቋችን ተጠቃሚ አልሆንም፡፡ ኦፌስላዊ ሥራ አሁን የሚሰራው በፌዴራል መንግሥት (አማርኛ) ቋንቋ ነው፡፡ በህገ መንግሥቱ ግን የክልሉ ቋንቋ ሃረሪና ኦሮምኛ ተብሎ ተቀምጧል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ እንዲሁም የሃረሪ ብሄራዊ ጉባዔ ለሃረሪ ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ ባህሉን፣ ቅርሱንና ቋንቋውን እንዲያስጠብቅ የተቋቋመ ጉባዔ ነው፡፡ እስከ አሁን ግን የሰራው ሥራ የለም፡፡ ቋንቋው ለምሳሌ በጥቂት ትምህርት ቤቶች ብቻ ነው እየተሰጠ ያለው፡፡ ሪፖርተር፡- ይሁን እንጂ እናንተም ራሳችሁ በድርጅቱ (ሃብሊ) ውስጥ ነበራችሁ፡፡ የክልሉ ችግር ግን ሥር የሰደደ ነው፡፡ እናንተም ተጠያቂዎች ናችሁ፤ አቶ አብዲ፡- በድርጅቱ ውስጥ አማራጭ በማጣት ከውጭም ከውስጥም ስንታገል የነበርን ሰዎች ነን፡፡ አሥራ ስድስት ዓመት ሙሉ ጥረት ስናደርግ የነበረው ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡ ትክክለኛ መስመርና ልማታዊ የሆነ አቅጣጫ እንዲከተል ሞክረናል፡፡ ነገር ግን አልቻልንም፡፡ እስከ አሁን ህዝቡ የተሰጠው መብት ሳይጠቀም የቆየበት ምክንያት ይሄው ነው፡፡ የራሳችን አማራጭ ስናፈላልግ ቆይተን በመጨረሻ በሚሌንየሙ ምክንያት ከዓለም ሁሉ የተሰባሰቡ የክልሉ ተወላጆች (የሚባለውንና በክልሉ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አይተው) ከእኛ ጋር ተመሳሳይ አቋም የያዙ በርካቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ለዚህ ውሳኔ ደርሰናል፡፡ ሪፖርተር፡- ሚሌኒየሙ በሃረር ሲከበር አብዛኛዎቹ የክልሉ ተወላጅ ዲያስፖራዎች መጥተው በዓሉን ተካፍለዋል፡፡ ጥሪ ያደረገላቸው ደግሞ ገዢው ፓርቲ ነው፤ አቶ አብዲ፡- ለሚሌኒየሙ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራዎች መጥተው ነበር፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት የአገር ፍቅራቸው በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡ መጥተው ግን አመላለሳቸው በጣም ነው የሚያስዝነው፡፡ አብዛኛዎቹ ተከፍተው ነው የሄዱት፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ባለሙያዎች በአገራቸው ለመሥራት መጥተው ሳይሆንላቸው ተመልሰዋል፡፡ ማንም ሰው ዘወር ብሎ ያያቸውና ያነጋገራቸው አካል የለም፡፡ አሰባሰቡ ጥሩ ነበር፣ አጨራረሱ ግን ጥሩ አልነበረም፡፡ ወደ አገራቸው ሲመጡ የገመቱትና መጥተው በተግባር ያዩት የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- አንዳንዶቹ ግን በሚድያ ሲናገሩ ደስ እንዳላቸውና በአካባቢው ጥሩ ለውጥ እንዳለ ሰምተናል፣ እርስዎ ደግሞ ተከፍተው እንደሄዱ እየነገሩኝ ነው? አቶ አብዲ፡- ከ3ዐ ዓመት በኋላ አገርህ ስትመጣና መሬቱን ስታይ ራሱ ደስ ይልሃል፡፡ “አገሬ ገብቻለሁ፣ የአገሬ ህዝብ ማግኘቴ ደስ ብሎኛል” ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ የእያንዳንዱ የነዋሪው የኑሮ ደረጃ ከ3ዐ ዓመት በፊት የነበረው ሲታይና አሁን ዝቅ ያለ ሆኖ ስታገኘው ትበሳጫለህ፡፡ በእርግጥ ራስ በራስህ አስተዳደር ውስጥ ሆነህ በነፃነት ስትንቀሳቀስ ትደሰታለህ፡፡ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ስታይ ግን ለውጥ የለም፡፡ በነገራችን ላይ ሰው ወደ አገሩ መጥቶ በሚዲያ ሲጠየቅ ደስ ብሎኛል ነው የሚልህ፡፡ አንፃራዋ የሆነ ለውጥ አለ፡፡ ሃረር ዕድሜዋ አንድ ሺህ ነው፣ እንደ እድሜዋ ግን አላደገችም፡፡ ይሄ መንግሥት ከመጣ 17 ዓመቱ ነው፡፡ በ17 ዓመታት ውስጥ ሁል ጊዜ ስለ ውሃ እጥረት ማውራት ምን ማለት ነው? የመንግሥት በጀት በመጠባበቅ ብቻ ሳይሆን የክልሉ ተወላጅ ባለሃብቶች አስተባብሮ ልማት የሚሰራ አካል የለም፡፡ አጠቃላይ መሰራት ያለበት ያህል አልተሰራም፡፡ የሚወራው ሌላ፣ የተሰራው ሌላ ነው፡፡ የሃረር ህዝብ ራሱ በራሱ ማስተዳደር ሲጀምር ብዙ ነገር መሥራት ይገባው ነበር፡፡ ሃረር ላይ እዚህ ግባ የሚባል የተሰራ ነገር የለም፡፡ ህዝቡ ተሰቃይቶ ነው ያለው፡፡ ችግሩን የሚሰማው ሦስተኛ አካልም የለም፡፡ ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ በክልሉ ያለው ችግር በደፈናው ሳይሆን በምሳሌ ሊያስረዱኝ ይችላሉ? አቶ አብዲ፡- የተለያዩ ሹማምንቶች የተቀያየሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል አልነበረም፡፡ አሁን ደግሞ ከ1986 ዓ.ም. ጀምረው ፍቃድ ወስደው በኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ አካላት በካሬ ሜትር 6ዐዐ ብር እንዲከፍሉ በሚል ማስታወቂያ አውጥተዋል፡፡ ካልከፈላችሁ ግን የቀድሞ ካርዳችሁ ይቆማል ተብለዋል፡፡ በልማት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ዜጎች ይህንን መክፈል አንችልም በማለት እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የአገሪቱን ፖሊሲ መከተል አለበት፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አካባቢውና እንደየክልሉ እየታየ ነው ተግባራዊ የሚሆነው፡፡ ይሄ ግን በሃረር አይሰራም፡፡ ሰዎቹ የትም ቦታ የሌለ በእኛ ላይ ተጭኖብናል እያሉ ነው፡፡ ህጋዊ ሰውነት ስላላችሁ ይህንን ድርጊት ለሚመለከተው አካል አሳውቁልን ብለዋል፡፡ የክልሉ ወጣቶችም ከፍተኛ ችግር ላይ ነው ያሉት፡፡ አሁን ያሉት የወጣት ማህበራት የወጣቶቹን ችግር ማዕከል አድርገው መፍታት የቻሉ አይደሉም፡፡ መንግሥት ለወጣቶች ትኩረት አልሰጠም፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ፓኬጆች ተጠቃሚዎችም ለገዢው ፓርቲ ቀረቤታ ያላቸው፣ አባላትና ዘመዶች ብቻ ናቸው፡፡ ሪፖርተር፡- እናንተ ብትሆኑ ግን ለአባላችሁና ከእናንተ ጋር ቅርበት ላለው አካል አታደሉም? አቶ አብዲ፡- ይሄን ድርጅት እየመሰረትን ያለነው የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ነው፡፡ ህዝብ ሲባል የአንድ ቤተሰብ ስብስብ አይደለም፡፡ አንድ ሰው የአገርና የህዝብ ሹም ሲሆን ከራሱ ዘመድ ወጥተዋል ማለት ነው፡፡ ማየት ያለበት ሰፊውን ህዝብ በእኩል ነው፡፡ ለዚህ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ግዴታንና መብትን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለምትሰራው ሥራ ሁሉ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ልትወስድ ይገባል፡፡ ሪፖርተር፡- ኃብሊ ረዥም ዕድሜ ያለው ድርጅት ነው፡፡ ይሄ ድርጅት ሊያስወግዳቸው ያልቻለ መሰረታዊ ችግሮች አሉ፡፡ እናንተ ገና አዲስ ፓርቲ ናችሁና ምን ያህል አቅምና ዝግጅት አላችሁ? አቶ አብዲ፡- በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ልምድ አካብተናል፡፡ ድርጅቱ እየሄደበት ያለውን ሁኔታ በግልፅ እናውቀዋለን፡፡ ችግሩ ምን ጋር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ብንናገር ሰሚ አጥተን ነው፡፡ ምክንያቱም ራሱ ድርጅቱ ለለውጥ ያዘጋጀ አይደለምና፡፡ መልካም አስተዳደርና ልማት ከማስፈን አንፃር እያደረገው ያለው ነገር ከማንም አካል በላይ እናውቀዋለን፡፡ የህዝቡን ቅሬታና ችግር መገንዘብ እንችላለን፡፡ ከፍተኛ የአስተሳሰብ ለውጥ አድርገን ለለውጥ ራሳችንን ያዘጋጀን አካላት ነን፡፡ ክልሉን ለማልማትም በየአካባቢው ያለው የክልሉ ተወላጅ እንዴት ማስተባበር እንዳለብን እናውቃለን፡፡ ከአገር ውጭ ያለው የክልሉ ተወላጅ እያበረታታንና ድጋፍ እየሰጠን ነው፡፡ ህዝቡን ይዘን ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚና የዲሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት የሚያቅተን አይሆንም፡፡ በኃብሊ የውስጥ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ፣ የመገማገምና የመወያየት ባህል የለም፡፡ እኛ እንዲህ ዓይነት አካሄድ አስወግደን ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ ድርጅቱ መኖሩ የሚታወቀው በምርጫ ወቅት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ የዕለት ተዕለት ሥራ ሳይሰራ ህልውናውም አጠራጣሪ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ትልቅ ችግር የአመራር ብቃት ማነስ ነው፤ ማስተባበር አለመቻል ነው፡፡ |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |