| ሻዕቢያ |
|
|
| Sunday, 04 May 2008 | |
እሱም “ይረፍ” እኛም እንረፍ!!ቢመከርም ቢዘከርም ሁከትና ረብሻ ከመፍጠር ወደኋላ የማይል ሰው፣ ጎረቤትም ሆነ የሰፈር ሰው ዕድሜና ጤና አይመኙለትም፡፡ በሕይወት እያለ “በሞተና ባረፍን” ይባልለታል፡፡ ሲሞትም “ጥሩ፣ ትሁት፣ ሰው አክባሪ ነበሩ” ብሎ የሚያነብለት አይገኝም፡፡ "እሱም አረፈ፣ እኛም አረፍን” ተብሎ ነው የሱ ነገር የሚደመደመው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ሆነ እንጂ፣ ሻዕቢያም ከእንደዚሁ ዓይነት ሰውዬ የተለየ ምኞትና አባባል ሊሰጠው አይችልም፡፡ የራሱን ቤትና ሰፈር እያመሰ፣ የአፍሪካ ቀንድንም እያወከ ያለ ድርጅትም፣ መንግሥትም ሆኗል፡፡ ሱዳንን፣ የመንንና ኢትዮጵያን ሲተነኩስና ሲጎነታትል የከመረውና ውጤት አልባ ሆኖ የቀረው ሻዕቢያ፣ ሰሞኑን ደግሞ “ወር ተረኛ” ያደረገው ጅቡቲን ነው፡፡ ከሕጋዊ መንገድ ውጭ ወታደሮቹን ወደ ጅቡቲ ክልል አስገብቷል፡፡ በዚህም ሻዕቢያ፣ ተንኳሽነቱንና ጠብ ጫሪነቱን እንደገና አረጋግጧል፡፡ ሻዕቢያ ፀረ ሰላምም፣ ፀረ- ልማትም፣ የአካባቢ እንቅፋትም፣ ከሆነ ሰነበተ፡፡ ፀረ ሰላም ስንል ካለ ጦርነትና ግጭት መኖር ስለማይችል ነው፡፡ ፀረ ልማት የምንለውም ሌሎች አገሮች በልማት ላይ እንዳያተኩሩ ጊዜያቸውን፣ የሰው ሃይላቸውንና ገንዘባቸውን እሱን ለመከላከል እንዲያውሉት ስለሚገደዱ ነው፡፡ የሻዕቢያ ጦረኝነት እንደ እብደት የሚታይ እንጅ “ለኤርትራ ጥቅምና ክብር ብዬ የማደርገው ነው” የሚል ሽፋን ሊሰጥበትም የማይቻል ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ የኤርትራ ሕዝብ በታሪኩ አጋጥሞት የማያውቅ ከምንም ጊዜውም በከፋ የችግር አረንቋ ውስጥ ተዘፍቋል፡፡ እንዲህም የሆነው በሻዕቢያ ምክንያት ነው፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ዴሞክራሲና ፍትሕ እያገኘ ነው እንዳይባል፣ ወይም ደግሞ ዛሬ ባያገኘውም ነገ ያገኘዋል፤ ተብሎ ተስፋ እንዳይደረግ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ ህዝብ ዴሞክራሲ አይፈልግም፤ አያስፈልገውምም፤ ብለው ዘግተዋል፡፡ እንዲያውም ዴሞክራሲ የአሜሪካ ስለሆነ አንፈልገውም፤ ብለዋል፡፡ የኤርትራ ሕዝብ፣ ሻዕቢያ ስላላት ምርጫም አያስፈልገውም፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ሃሳቡንና የልቡን የሚገልፅለት ሻዕቢያ ስላለ ነፃ ፕሬስ አይፈልግም፤ ከሻዕቢያ በላይ የኤርትራ ሕዝብ የሚፈልገው ስለሌለ መድብለ ፓርቲ አይፈልግም ብለው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ያለቀለት አቋም ገልፀዋል፡፡ በዚህ አምባገነናዊና አረመኔያዊ አመራር ምክንያት የኤርትራ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ የዴሞክራሲ ሽታ የሚባልም በሩቁ ማየት አልቻለም፡፡ እንኳን እሱ ተናግሮና ውጭ ያለ ዘመድህ ተቃውሟል፤ ተብሎ አገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ቀም ስቅሉን የሚያይበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በልማት በኩልም ስራ ወዳዱ የኤርትራ ሕዝብ፣ የሚያሰራው አጥቶ ተመፅዋችና ከውጭ ገንዘብ የሚጠብቅ ሆኗል፡፡ ውጭ ያለው ኤርትራዊ እንደድሮው መኪና፣ ፍሪጅ፣ ቴሌቪዥን፣ ኮምፒዩተርና ሌሎች ዕቃዎችም ገንዘብ ወደ አገር ቤት መላክ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግሥት ስለሚቀማውና ስለሚሰርቀው ነው፡፡ ከዚያ በላይም ዋናው ችግር የምግብ ችግር እየሆነ በመምጣቱ ነው፡፡ ስለዚህም ፓስታ፣ ሞኮሮኒ፣ ዱቄት ብቻ እንዲልክ የተገደደ ዲያስፖራ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኤርትራ ሕዝብ ወደ ሱዳን፣ ወደ ኢትዮጵያ፣ ወደ ግብፅ እየተሰደደና ባሕር ውስጥ እየቀረ ነው፡፡ ይህ ሁሉ አሳዛኝ ድርጊት የደረሰበት በሻዕቢያ ምክንያት ነው፡፡ በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ሻዕቢያ የኤርትራ ሕዝብ ጠላት ነው፡፡ ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ጠላት ነው፣ ሻዕቢያ የሱዳን ሕዝብ ጠላት ነው፣ ሻዕቢያ የጅቡቲ ሕዝብ ጠላት ነው፣ ሻዕቢያ የየመን ሕዝብ ጠላት ነው፣ ሻዕቢያ የሶማሊያ ሕዝብ ጠላት ነው፡፡ በፕሮፖጋንዳ ጠላት ባይመስልም በተጨባጭ አቋምና ተግባር ግን የአካባቢውና የአገሩ ሕዝብ ጠላት ሆኗል፡፡ የኤርትራ ሕዝብና የአካባቢ አገሮች ሕዝቦች፣ የኤርትራ መንግሥትን ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ አጣጧል፡፡ አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ ሻዕቢያም የሚያርፉበት የአካባቢው ሕዝብም የሚያርፍበት ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ፣ ሻዕቢያ ከጥፋት ተቆጥቦ እጆቹን ሰብስቦ “ማረፉን” ከመረጠ መልካም ነው፡፡ አለበለዚያ ደግሞ አካባቢውን እየበጠበጠ መኖር እንደማይችል ቀጥተኛና አፋጣኝ መልዕክት ሊተላለፍለት ይገባል፡፡ በሰላማዊ መንገድ “ማረፉን” ካልመረጠ በሃይል “የሚያርፍበት” ሁኔታ መፍጠር የግድ ይሆናል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የኤርትራ ሕዝብና የአካባቢ አገሮች ሕዝብ ሊተባበሩ ይገባል፡፡ የኤርትራ ሕዝብም በአጉል “ወዲ አፎምንት” ተወጥሮ፣ ከአካባቢው ሕዝብ ተነጥሎ የአምባገነኖች መጫዎች ሆኖ መኖር የለበትም፡፡ በቃኝ እምቢ ሊል ይገባል፡፡ የአካባቢው መንግሥታትና ሕዝብም ሻዕቢያን መጥላትና ከኤርትራ ሕዝብ መጥላት ጋር እንዳይቀላቀሉ ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ሊረዳና ሊደግፍ የሚገባው ሕዝብ እንጅ ጠላት አይደለም፡፡ ስለሆነም ጥረታቸውና እርምጃቸው በሻዕቢያ ላይ ያነጣጠረ እንጅ በኤርትራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሻዕቢያ መንግሥት ጊዜ ቢሰጠው “ወደ ልቡ ይመለሳል” የሚባል ቡድን አይደለም፡፡ “ትዕግስት መራራ ናት፤ ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ነው” እየተባለ ወሰን የሌለው ትዕግሥት ቢሰጠውም ሊገባው አይችልም፡፡ አምባገነኖች ጊዜ ባገኙ ቁጥር ጥፋታቸው እየከፋ መሄዱ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ አስፈላጊ እርምጃ ተወስዶ እንዲህ ዓይነቱን አባባል የምንሰማበት ጊዜ ሩቅ አይሁን፡፡ “እሱም አረፈ - እኛም አረፍን!!” |
| < Prev | Next > |
|---|
| Home |
| Sections |
| Forums |
| Reporter - English Ver. |
| Register |
| Contact Us |